የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስለኢትዮጵያ መድረክ በአፋር ብሔራዊ ክልል ባዘጋጀበት ወቅት፤ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሃጂ አወል አርባ አፋር ላይ መገናኘት ማለት በሉሲ ምድር መገናኛት ነው። በተለይም ደግሞ ስለሰላም ፣ አንድነት እና ልዕልና ለመወያየት በሉሲ መንደር መገናኘት ልዩ ነገር ነው በማለት ነው ሀሳብ መስጠት የጀመሩት።
ሀጂ አወል አርባ እንዳሉት ፤ በዚህ ምድር ላይ ትልቁ ባንክ የሃሳብ ባንክ ነው። በመድረኩ የተነሱ ስለሰላም፣ አንድነት እና ልዕልና በሁሉም የኢትዮጵያ ቤተሰብ ጆሮ መድረስ ይገባዋል። አሁን ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የናፈቀው ሰላም እና ሰላም ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሁን ላይ የራሱን ስራ በሚያከናውንበት ወቅት አፋር ሰመራ ላይ ስለሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላም እድገት፣ አንድነት እና ልዕልና ውይይቶች እየተካሄዱ ናቸው። ውይይቶች በቀላሉ ችግሮችን መቅረፍ ስለሚያስችሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደዚህ አይነት ልምዶችን ሊለማማድ ይገባል።
ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ያካተተ ሰላም፣ አንድነት እና ልዕልና ላይ ያተኮረ ውይይት እንደቀላል የሚታይ አይደለም። ለአስተሳሰብ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት አለበት የሚሉት ሃጂ አወል ፤ ሀገር የምትፈርሰው አስተሳሰብ ሲፈርስ ነው። በሌላ አነጋገር ሀገር የምትገነባው አውንታዊ የለውጥ አስተሳሰብ ሲኖር ነው። ሀገር የምትገነባው አስተሳሰባችንን በአውንታዊ መልኩ ስንገነባ እና መቀየር ሲቻል ብቻ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ትልቁ ነገር ሰላም ነው። ይህንን ካልን የሰላም ምንጩ የሚገኘው ከየት ነው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። የምንጠብቀው ከማንስ ነው? በሚሉት ነጥቦች ላይ መግባባት ያስፈልጋል ይላሉ። ከፈጣሪ ምርጥ ስሞች ውስጥ አንዱ ሰላም ነው። ፈጣሪ ራሱን ሲያስተዋውቅ «ሰላም ነኝ» ብሏል። ጀነትም ደግሞ የተሰየመችው በሰላም ነው። ፈጣሪም «ቀጣዩ ጀነት የሰላም ምድር ነው » ብሏል።
እንደ ሃጂ አወል አርባ ገለጻ፤ ሀገርን ከአንድ ቤተሰብ ጋር አመሳስሎ መመልከት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሀገር ማለት ሰው ነው። ሰው የሌለበት መሬት ትርጉም የለውም። የሰው መሰረት ደግሞ ቤተሰብ ነው። መጀመሪያ ሰላም የሚገኘው ለራስ በሰጠው ልክ ነው። ሰላም ለሌሎች ለመስጠት መጀመሪያ ለራስ ሰላም መሆን ተገቢ ነው። ውስጣዊ ሰላም ሊኖር ይገባል። ከዚያ ቀጥሎ ለሌሎች ሰዎች ሰላምን መስጠት ይቻላል። መጀመሪያ ለማን ? ከተባለ መልሱ ለቤተሰብ ይሆናል።
አንዳንድ ሰዎች ቤተሰባቸውን መምራት አቅቷቸው እንዲሁ በስሜት ከባድ ሃላፊነት የሚጠይቀውን ሀገር የመምራት ኃላፊነት ካልሰጣችሁኝ ሲሉ ይስተዋላሉ። ይህ ልክ አይደለም። ቤተሰቡን መምራት ያልቻለ እንዴት ሀገሩን ሊመራ ይችላል? ሀገር ለመምራት መጀመሪያ ራስን የመግዛት ፈተናን ማለፍ ያስፈልጋል። ራሱን የገዛ ሰው ቀጥሎ ቤተሰብ መምራት የሚባለውን ፈተና ተፈትኖ በማለፍ ለቤተሰቡ እንከን የማይወጣለት ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ወይም ንጉስ ሆኖ ማሳየት አለበት። ምክንያቱም ትዳር ከባድ ኃላፊነት ነው። ቤተሰብ ሰላም ከሆነ ሀገርም ሰላም ይሆናል። ኢትዮጵያ ሰላም የምታድርው መቼ ነው ? ተብሎ ከተጠየቀ መልሱ ሁሉም ቤተሰብ ሰላም ያደረ ዕለት ነው በማለት ሰላምን ከየት ማግኘት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
እንደሀጂ አወል ገለጻ፤ የሀገረ መንግስት ግንባታ በጽኑ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ እና በዘላቂነት ሰላምን ለማምጣት የሀገር አንድነት አስፈላጊ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ነገር ግን የሀገርን አንድነት ለማምጣት ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለህዝብ አንድነት ነው። ምክንያቱም ሀገር አንድ መሆን የሚችለው ህዝቡ አንድ ሲሆን ብቻ ነው።
በቅርቡ ተከስቶ የነበረውን የሰላም ዕጦት ብንመለከት ለተፈጠረው ችግር ዋነኛው ምክንያት የሀገር አንድነት አለመኖሩ ሳይሆን የህዝብ አንድነት ስላልነበረ ነው። በእርግጠኝት መናገር የሚቻለው የህዝብ አንድነት የሌለው ሀገር የሀገር አንድነት ቢኖረውም ከመፍረስ አይድንም። በእነዚህ አራት ዓመታት በሀገራችን ተከስቶ ለነበረው ችግር ሌላው ምክንያት የመመራት ልምድ አለመኖር ነው። ይህም ሰላማችንን አናግቶ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎናል። ስለሆነም በአንድ ሀገር ሰላም ማምጣት ከተፈለገ ማንኛውም ሰው መመራትንም አብሮ መልመድ ያስፈልጋል።
መመራት ምንም ማለት አይደለም። መምራትም በቋሚነት የሚወሰድ አይደለም። በጥሩ ሁኔታ ህዝብን ካገለገልኩ እና ከመራሁ መሪ ሆኜ ልቀጥል እችላለሁ። ካልሆነ ግን ቦታውን ለመልቀቅ እገደዳለሁ። ምክንያቱም ሀገር የጋራ ሃብት ነው። በአጠቃላይ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እኛ ኢትዮጵያዊን እንደ ሀገር መልመድ ያለብን ነገር መመራትን ነው።
ሌላው ሰላምን ለማምጣት ከሚረዱ አብይ ጉዳዮች መካከል መናበብ፣ መከባበር ነው። ቤተሰብ ቤተሰብ የሚሆነው ሲከባበር እና መናበብ ሲችል ነው። መናብበ እና መከባበር ካልተቻለ ግን በቤተሰብ ውስጥ ሰላምን ማምጣት አይቻልም። በሀገር ደረጃም ተመሳሳይ ነው። ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ከተፈለገ እርስ በርስ መናበብ እና መከባበር ያስፈልጋል።
ሀገር ማለት በአንድ በታሪክ አጋጣሚ በሃይል ወይም በምርጫ ያሸነፈ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ሀብት ንብረት ማለት አይደለም። ሀገር ማለት የጋራ እና የሁሉም ዜጋ ነው። በአጋጣሚ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ ጊዜ ፤ በአንድ ሰዓት በአንድ ምርጫ ሊያሸንፉ አይችሉም። አንድ ፓርቲ ወይም አካል ብቻ ያሸንፋል። አንድ ፓርቲ ወይም አካል አሸነፈ ማለት፤ ሀገር የእርሱ ብቻ ናት ማለት አይደለም። ስለሆነም በአንድ ሀገር ዘላቂ ሰላም ማምጣት ከተፈለገ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ ፓርቲዎች በመደማመጥ እና በመከባባር ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ግድ ነው።
እንደ ሀጂ አወል አርባ ገለጻ፤ ለሰላማችን እንቅፋት የሆኑ የእርስ በርስ ግጭት፣ አለመደማመጥ፣ መሳሳብ፣ የተለጠጡ ሃሳቦችን የመያዝ እንደዚህ አይነት ነገሮችን በውይይት እና በመግባባት ማለፍ ያስፈልጋል። ሀገር ለመገንባት ሀሳብ ማዋጣት ያስፈልጋል። ሃሳባችንን እያዋጣን ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ አለብን። የሃሳብ ውድድር ላይ ብቻ ጊዜ መግደል ሳይሆን የተወዳደርንበትን ሃሳብ ወደ ተግባር መቀየር ያስፈልጋል።
እንደ ሀገር ሰላም ለማምጣት በህዝብ አንድነት ላይ ትልቅ ስራ መሰራት አለበት። የሀገር አንድነትን አስጠብቀን የሰላም ዘብ መሆን ካልቻልን ህልውናችንን የማናጠናክርበት አንዳችም ምክንያት የለም። ባለፈው ዓመት በሀገራችን ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ ታሪካዊ ጠላቶቻችን አሁን አበቃላቸው፤ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች እያሉ ተዘባብተውብን ነበር። በወቅቱ ከበርካታ ዲፕሎማቶች ጋር ተገናኝቶ የማውራት እድልም ገጥሞኝ ነበር። ዲፐሎማቶቹ በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ የነበራቸው አመለካከት እና በጦርነቱ መጨረሻ ላይ የተመለከቷቸው ነገሮች እና አስተሳሰባቸው እጅጉን የተራራቀ ነው።
በጦርነቱ መጀመሪያ ኢትዮጵያ እንድምትፈርስ ያስቡ ነበር። አሁን ላይ ግን ሁሉም ነገር ተቀይሮ ሲመለከቱ የኢትዮጵያን ታላቅ ሀገርነት ሳይወዱ በግድ ተቀብለዋል። ጠንካራ ህዝብ እንዳላት አምነዋል። እንደውም የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲህ ነው ብሎ ፈርጆ ማስቀመጥ አይቻልም ያሉኝም አሉ። የኢትዮጵያን ህዝብ ገምግሞ እንዲህ ነው ብሎ መናገር ከባድ መሆኑን ሲናገሩ እየተደመጡ ነው። ለምን ? ኢትዮጵያዊያን በሰላም ወቅት ውስጣዊ ችግሮች ሊኖርባቸው ይችላል። ከበድ ያለ ሀገራዊ አጀንዳ ሲመጣ ደግሞ አንድም ቀን እንዳልተጋጩ ሳይሆን ወደፊትም አንድም ቀን እንደማይጋጩ ሆነው በአንድነት ጠላትን ለመፋለም ይሰለፋሉ። የሚገርመው የትናቱ አይደለም፤ ለነገም የሚጋጩ አይመስሉም ።
በአፋሮች የተለመደ አንድ አባባል አለ፤ ‹‹የራስህ ወገን ወይም ዘመድ በድንጋይ ቢመታህ የመታኝ በኩበት ነው ብለህ ዝም ብለህ እለፈው። ነገሩን አታካብደው፤ አታክረው። በቃ ! በኩበት እንጂ በድንጋይ አልመታኝም፤ ብለህ እለፈው። በአንጻሩ ደግሞ ባዕድ የሆነ አካል በኩበት ቢመታህ አልተረፍኩም! በድንጋይ ነው የመታኝ በል። ለምን ? ምክንያቱም ዛሬ ለሙከራ በኩበት ከመታህ ነገ በከባድ ድንጋይ ወይም ከድንጋይ ከበድ ባለ መሳሪያ ደብድቦ ሊገድልህ ይችላል›› በማለት ነው በአንድ አገር ህዝብ መሃል ግጭት ቢኖርም በቀላሉ መታየት እንዳለበት እና የባዕድ አገር ወረራን ግን በቀላሉ ማለፍ እንደማይገባ ያስረዱት።
ከዚህ የአፋሮች አባባል አንድ ነገር መረዳት ይቻላል። አሁን ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እርስ በርሱ መዋደድ እና ገመናውን መሸፋፈን አለበት። ራሱንም ከውጭ ወራሪ ለመከላከል አንዱ ወንድም ህዝብ በኩበት ሲመታ በድንጋይ ነው የተመታሁት ብለን ከጎኑ ልንቆም ይገባል ይላሉ።
ሰላም ማለት ሀገር ነው፤ ሰላም ማለት ፍትህ ነው። ለአንድ ሀገር መንግስት ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ፍትህን እና ሰላምን ለማስፈን እንዲሁም የሀገር እና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ ነው። መንግስትም መንግስት የሚሆነው ሰላምን፣ ፍትህን እና ደህንነትን ማረጋገጥ ሲችል ነው። ህዝብ ሰላም ከሆነ ሀገር ሰላም ይሆናል። መንግስትም ሰላም ይሆናል። ከዚህ አንጻር አስበን ከተንቀሳቀስን እና ከሰራን በሀገራችን ሰላም እና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራትም በሁለንተናዊ መልኩ መርዳት እንችላለን ይላሉ።
አሁን ላይ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ሰላማችንን እና ልማታችንን ሊያደናቅፍ የሚችል ነገርን ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያዊያን ግንባር ቀደም ዓላማ የሆነውን ልዕልና እና ብልጽግና ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። አጀንዳችን መሆን ያለበት የኢትዮጵያ ልዕልናን ለማረጋገጥ ሌሊት እና ቀን እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት እንጂ በተቃራኒ አቅጣጫ መሳሳብ መሆን የለበትም።
የበርካታ ሀገራት ታሪኮች እንደሚያመላክቱት ከአስከፊ ጦርነት ወይም ከእርስ በእርስ ግጭት በኋላ ሀገራቸውን ከፍታ ላይ ማስቀመጥ ችለዋል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ከማንም ሳይጠብቁ ከእኔ ምን ይጠበቃል? የእኔ ድርሻ ምን መሆን አለበት? ብለው መስራት ስለቻሉ ነው። ኢትዮጵያዊያንም የእነዚህን ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ኢትዮጵያ ያለእኔ ተሳትፎ ጎደሎ ናት ብሎ በማሰብ ለኢትዮጵያ እድገት እና ልዕልና ማንኛውም ዜጋ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠርኩት ለኢትዮጵያ ልዕልና የበኩሌን እንዳበረክት እንጂ ያለምክንያት አይደለም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ለዚህም ራስን ማዘጋጀት ይገባል።
በሀገራችን ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ወቅት ማንኛውም አፋር ብትጠይቁት ኢትዮጵያ ማለት እኛ አፋሮች ነን ብሎ ይመልሳል። ከዚያ ኢትዮጵያ ደግሞ ማንነቷ ተከብሮ እንድትኖር መከላከያ ያስፈልጋል በሚል እንደአፋር መግባባት ተቻለ። በዚህም መከላከያ በሁሉም ቦታ ማድረስ ስለማይችል፤ ሁሉም የአፋር ህዝብ እኔ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነኝ ብሎ ማሰብ እንዲችል ተደረገ። የአፋርን ህዝብ እያንዳንድህ ጄኔራል ነህ! ይህን ተቀበል ብለን ተማመን። በዚህም ሁሉም አፋር በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ቦታ ላይ ራሱን ቁጭ አደረገ፡፡
በዚህም መተማመን ላይ ተደረሰ። ከዚያ በኋላ ስለመከላከያ ሌላ ነገር ማውራት አቆምን። በዚህም ዋናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአፋር ሶስት ወረዳዎችን ሲሸፍን ሌላውን የቀረውን የጦር ቀጠና የተሸፈነው በአፋሮች ነበር። ምክንያቱም እኛ አፋሮች ቀድመን ራሳችን መከላከያ ነን ብለን ስለወሰን፤ በዚህም መላውን አፋርን ከችግር መከላከል ቻልን። ኢትዮጵያንም ማዳን ተቻለ።
ኢትዮጵያዊያን ሁላችንም ለጋራ ሰላም ለጋራ እድገት እና ልዕልና ከመቆም ውጭ ሌላ ምንም አማራጭ የለንም። በአንድ ወቅት ሁለት ጓደኛሞች ነበሩ። አንደኛው አውንታዊ ሃሳብ ይዞ ወደ እድገት እና ልዕልና ሊያመራው ወደሚችል ስራ ውስጥ ይገባል። ከዕለታት አንድ ቀን ይህ ማድረግ የፈለገው ሰው እጅግ አድካሚ እና ጠንካራ የፍየል በረት ይሰራል። ይህ በእንዲህ እያለ ሁለተኛው ሰው ግን አንደኛው ሰው በዚህ ልክ እየለፋ ዝም ብሎ ይመለከተው ነበር ። መጨረሻ ላይ ግን ስራ ሳያግዝ የቆየው ጓደኛ የትጉሁን ሰው ግድግዳ ተጠቅሞ ሌላ በረት ሰራ። መጀመሪያ ላይ ያለገዝከኝን መጨረሻ ላይ ግን የእኔን ግድግዳ ተጠቅመህ እንዴት በረት ትሰራለህ ? ብሎ ጠየቀው። ምንም ሳያግዝ ግድግዳ የሠራው ሁለተኛው ሰው ምን አገባህ? ሲል መለሰለት።
የመጀመሪያው ሰውዬ በሁለተኛው ሰውዬ መልስ ሳይናደድ ለመሆኑ በረቱን የሰራኸው ለምንድን ነው? ሲል ጠየቀው። ሁለተኛው ሰነፍ ሰውዬም መጀመሪያ በረቱን የሰራኸው አንተ ስለሆንክ በረቱን ለምን እንደሰራኸው ንገረኝ ይለዋል። መጀመሪያ በረት የሰራው ሰውዬም በረቱን የሰራሁት በርካታ ፍየሎችን ላረባበት ነው ብሎ ይመልሳል። ይህ ሰው በአውንታዊ አስተሳሰብ ራሱን ለእድገት እና ልዕልና እያዘጋጀ ነበር።
መጀመሪያ በረት የሰራው ሰው ሁለተኛውን በረት የሰራውን ሰው አንተስ የእኔን በረት ተጠቅመህ በረት የሰራኸው ለምንድን ነው? እቅድህ ምንድን ነው? ብሎ ይጠይቀዋል። እኔ እንደ አንተ በርካታ ፍየሎችን ማርባት አልፈልግም። እኔ በዚህ በረት ውስጥ ማርባት የምፈልገው በጣም ትላልቅ የሆኑ ወደ 30 የሚደርሱ ቀበሮዎችን ላራባበት ነው ብሎ ይመልስለታል።
ፍየል ለማርባት በጎ አስተሳሰብ ይዞ መጀመሪያ በረት የሰራው ሰውዬም ኧረ አላህን ፍራ እንዴት ፍየል ለማርባት አቅጄ ከሰራሁት በረት ጎን ቀበሮ ለማርባት ታስባለህ ? ቀበሮ እና የፍየል እርባታ በታሪክ አጋጣሚ በአንድ አካባቢ ተደርጎ አያውቅም። እባክህ ቀበሮ ማርባቱ ይቅርብህ ይለዋል። ነገር ግን አሉታዊ አስተሳሰብን በጭንቅላቱ የከተተው ግለሰብ ምን አገባህ? እኔ የተመቸኝ ቀበሮ ማርባት ነው ? ቀበሮ አረባለሁ ብሎ መለሰ።
ይህን ተከትሎ ሁለቱ ሰዎች ወደከፋ ጠብ ውስጥ ይገቡና አንገት ለአንገት ይያያዛሉ። ይህ በእንዲህ እያለ አንድ ሽማግሌ ወደቦታው ይደርሳል። ሽማግሌውም አንገት ለአንገት ተያይዘው የነበሩትን ሰዎች አላቀው የጸባቸውን መነሻ ምን እንደሆነ ሁለቱንም ይጠይቃሉ። መጀመሪያ በረት የሰራው እና አውንታዊ አስተሳሰብ ይዞ ፍየል ለማርባት የተነሳው ሰውዬ ‹‹ምን መሰልዎት አባቴ፤ እኔ አንድ ሰው ከሰራ እና ከበረታ ወደሚፈልገው ልዕልና መቀየር ይችላል ብዬ አስቤ ይህን የሚመለከቱትን በረት ከፍተኛ የገንዘብ እና የጉልበት ውጭ አድርጌ ገነባሁት። እኔ በረቱን ስሠራ ይህ ሰው መጀመሪያ በእኔ እየሳቀ እና እየቀለደ ምንም ሳያግዘኝ ተኝቶ ሲመለከተኝ ነበር፤ ብሎ ጀምሮ … የጸባቸው መነሻ የሆነውን ጉዳይ ለሽማግሌው ካስረዳ በኋላ ይህ ሰው ግመል፣ ወይ ፍየል ወይ ከብት ማርባት ይችላል ግን እንዴት ፍየል ለማርባት ከሳብኩበት ቦታ ቀበሮ አረባለሁ ይላል? ቀበሮች እና ፍየሎች ጎን ለጎን ካለ በረት ከተቀመጡ ቀበሮዎቹ በአንድ ሌሊት ፍየሎቼን ጨርሰው ይበሉብኛል፡፡›› ሲል ተናገረ።
ሽማግሌውም ቀበሮ አረባለሁ ያለውን ሰውዬ ይሄማ ልክፍት ነው? አሉት። ቀበሮ አረባለሁ ያለው ሰውዬም የምን ልክፍት ነው የሚያወሩት? ሲል ሽማግሌውን ጠየቀ። ሽማግሌውም ልጄ በሰይጣን ክፉኛ ተለክፈሃል፤ ቀበሮ የሚበላ ስጋ የለውም፤ የሚጠጣ ወተት የለውም ታዲያ ቀበሮ አረባለሁ ማለት ከሰይጣንንት ልክፍት በቀር ምን ሊባል ይችላል? ብለው ጥያቄውን በጥያቄ መለሱለት። ቀበሮ አረባለሁ ያለው ሰውዬ በቃ እኔ የተመቸኝ ቀበሮ ማርባት ነው ብሎ በአቋሙ ጸና።
ሽማግሌውም ደግመው ይህ አካሄድህ የልክፍት ነው አሉት። ታዲያ ልክፍት ከሆነ ለዚህ ልክፍት መድሃኒቱ ምንድን ነው? ሲል ቀበሮ አረባለሁ ሲል የነበረው ሰውዬ ሽማግሌውን ጠየቀ። ሽማግሌውም የልክፍቱ ፍቱን መድሃኒቱ ቁጭ ብሎ መወያየት ነው ሲሉ መለሱለት። ሽማግሌውም ቀጥለው ኑ ቁጭ በሉ እና ስለችግሩ እንወያይ ሲሉ ሁለቱን የተጣሉ ወገኖች ቁጭ እንዲሉ አደረጉ።
በውይይታቸውም ይህ ሰው ቀበሮ እንዲያረባ ያደረገው ምንድን ነው ? ብለው በጥልቀት ተነጋገሩ። ሰውዬው ለረጅም ጊዜ በጥፋት አስተሳስብ ውስጥ ከቆየ ጥፋቱን እና ክፋቱን እንደመልካም ነገር እንደሚቆጥር ተግባቡ። ቀበሮዎች ቀበሮ ሆነው የሚታዩት ለፍየል አርቢው እንጂ በክፋት ለአመታት ለኖረው ለቀበሮ አርቢው ግን ቀበሮዎችን እንደ ፍየሎች እንደሚቆጥራቸው ተገነዘቡ። ለምን የጥፋት እና የክፋት አካሄዱ ለበርካታ አመታት ስላደረገው ጥፋቱ እና ክፋቱ ተመችቶታል። ጥፋቱ ደስ ይለዋል። ሰይጣን ሸልሞታልና። በመጨረሻም ሁለቱ የተጣሉ ሰዎች ሽማግሌው ባመቻቸው የውይይት መድረክ መስማማት ላይ ደረሱ በማለት በዚህ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ምንም አይነት ችግር በውይይት መፈታት እንደሚቻል ሀጂ አወል አስተማሪ በሆነው ተረት ሃሳባቸውን ገለፁ።
ሀጂ አወል ደጋግመው እንደሚሉት ሰላም እንዲሁ አይገኝም። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በመሳሪያ አፈሙዝ ከማሸነፍ ይልቅ በውይይት አሸናፊ ሆኖ መውጣት ይመረጣል። ለምን ? በአፈ ሙዝ ማሸነፍ ዛሬ ላይ የተሸነፈው ሰው ነገ ላይ ጉልበት ባገኘ ወቅት አሸናፊውን ለመበቀል አፈሙዝ ይዞ መምጣቱ የማይቀር ነው። ስለሆነም ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ውይይት ከጠመንጃ አፈሙዝ የበለጠ ዋጋ ያለው መሆኑን ሁሉም ሰው ሊገነዘብ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የሰላምን ዋጋ ለመግለጽ ከባድ ነው። ስለሰላም ዋጋ ለመረዳት ከፈለግን በቅርቡ በሀገራችን ከተፈጠረው የሰላም እጦት ጋር ተያይዞ ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ መቀሌ የተደረገውን የአውሮፕላን በረራ ብቻ መመልከቱ በቂ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን የነበረው የሰላም መደፍረስ ተከትሎ በመቀሌ እና በአዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ግንኙነታቸው ተቋርጦ ነበር። ይሁንና አሁን ላይ የተፈጠውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ አውሮፕላን ወደ መቀሌ በረራ ባደረገ ጊዜ በአሉላ አባ ነጋ ኤርፖርት የነበረው ደስታ፣ ለቅሶ እና ሌሎች ሁነቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርን መቀሌ እንደ ጨረቃ እርቃን እንደነበር አሳይቶናል። ለሁለት ዓመታት ተለያይተው የነበሩ ሰዎች ሲገናኙ ከሞተ ሰው ጋር እንጂ በሕይወት ካለ ሰው ጋር የተገናኙ አይመስልም ነበር። ይህም ሰላም ለሰው ልጆች ያለውን ውድ ዋጋ ምን ይህል እንደሆነ ያመላክታል።
ጀግና መሪ ማለት ወደ ጦርነት ከመግባቱ በፊት ጦርነቱ ሊያስከትላቸው የሚችላቸውን ጥፋቶች ተንብዮ ሀገርንም ህዝብንም ከጥፋት የሚያድን ነው። የመጀመሪያውን የጦርነት ሁነት አይቶ በመጀመሪያው ሁነት የሚደሰት አይደለም። ጀግና ማለት የመጀመሪያውን ተመልከቶ የመጨረሻውን የሚተነብይ ነው። በአፋር ሁለት ጎሳዎች ተጣልተው ለሰላም በተቀመጡ ጊዜ የአፋር ሽማግሌዎች ሰላም የሚፈልገውን እና የማይፈልገውን ጎሳ የሚለዩበት የራሳቸው መለያ መስፈርት እንዳላቸውም ያብራራሉ።
ሰላም የሚፈልግ ጎሳ የትናንቱን በዜሮ እናባዛው እና ለነገ እናስብ፤ ለአዲስ ሕይወት እንዘጋጅ ይላል። በዚህም ከልቡ ሊታረቅ መፈለጉን ያመላክታል። ሁለተኛው መታረቅ የማይፈልግ ጎሳ ግን የወደፊቱን አጨልሞ ይመለከታል። ለመታረቅ ሽማግሌ ፊት ቆሞ ለእርቅ ከመቀመጡ በፊት የነበሩ ጥፋቶችን እና ቁስሎችን በተደጋጋሚ ያነሳል። ለነገ የሚያስብበት ጊዜ ፈጽሞ የለውም። ይህን ተከትሎ ሽማግሌዎች የትናትናውን እያነሳ የወደፊቱን መመልከት የተሳነው ጎሳ መታረቅ እንዳልፈለገ ፤ ለሰላም እጁን እንዳልዘረጋ በደንብ ይገነዘባሉ፡፡
የአፋር ሽማግሌዎችም ሰላምን ለማምጣት ከትናንትናው ይልቅ ለነገ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ትናንትን እያነሳ ለሚከራከረው ጎሳ ይመክራሉ፤ ይዘክራሉ። በዚህም ሁለቱንም ጎሳዎች ወደ ሰላም ያመጧቸዋል። እኛም እንደሀገር ሰላም መሆን ከፈለግን በፊት የነበሩ ቁስሎችን በዜሮ አባዝተን ለነገው ማሰብ ያስፈልጋል ሲሉ ቂምና ቁርሾ የነገን ሰላም እንደማያመጣ ይናገራሉ።
ሌላው በመድረኩ በሀጂ አወል የተብራራው አንድነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ነው። ስለ አንድነት ሲያስረዱ አንድ የአፋር ተረትን ተጠቅመው ነበር። በአንድ ጎጆ ውስጥ የሚኖሩ ወፎች ነበሩ። ወፎቹ ጎጇቸውን የሰሩት ዛፍ ላይ ነበር። ወፎች ዛፋ ላይ ጎጇቸውን ሰርተው እየኖሩ አንድ ቀን ጎጇቸው ውስጥ እያሉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ አውራ ግመል ወደዛፉ ተጠግቶ የጎጆዋን ሳር ለመብላት ፈልጎ ጎጆዋን ወደ አፉ አስገባ ። በጎጆዋ ውስጥ ጸብ ላይ የነበሩ ሁለቱ ወፎችም ከጎጇቸው ጋር በግመሉ ተበሉ።
ወፎቹ ሰላም ቢኖራቸው እና ቢተባበሩ ግን አይደለም በግመሉ ሊበሉ ይቅርና ጎጇቸውንም አያስደፍሩ ነበር ። እኛም ጎጇችን ውስጥ እርስ በርስ ስንበላላ እንደግመሉ ከውጭ ለመጣ ጠላት ሲሳይ እንዳንሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አንድ ስንሆን ሁሉም ያከብረናል። የምንሰራው ሥራም ውጤታማ ይሆናል። ስንበታተን ግን ማንም እየተነሳ ይጫወትብናል። ይህን ለመገንዘብ በሀገራችን ለተወሰነ ጊዜ በነበረው የሰላም እጦት ወቅት ያየናቸው ምልክቶች ከበቂ በላይ አስተማሪ ናቸው።
ሰላም ሲባል ከሁሉም በላይ ፍትህ፣ የህግ የበላይነት፤ ስርዓት ማስከበር ማለት ነው። ምክንያቱም የህግ የበላይነት እና ፍትህ በሌለበት ሰላም ከየትም አይመጣም። ጠንካራ ሀገር እንዲሁ መፍጠር አይቻልም። ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር መጀመሪያ ጠንካራ የስራ ባህል፣ አንድነት ያለው ህዝብ ያስፈልጋል። ከዚያ ቀጥሎ ጠንካራ ኢኮኖሚ ያስፈልጋል። ከጠንካራ ኢኮኖሚ ቀጥሎ ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ጠንካራ ፖሊስ፣ ጠንካራ የደህንነት ተቋም መገንባት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ ትልቅ አቅም መገንባት ያስፈልጋል። ከዚያ የሚከበር እና የሚፈራ ሀገርን መፍጠር ይቻላል።
ታላቅነት የሚረጋገጠው አንድነት ሲኖር ነው። የአንድ ወይም የሁለት ክልል ታላቅነት አንድን ሀገር ሊያሻግር አይችልም። በአፋር ክልል የአንበጣ ወረረሽኝ፣ ጎርፍ እና ሌሎች ችግሮች መከሰታቸው በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ፣ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ተማሪዎች፣ ጡረተኞች ፣ አካል ጉዳተኞች በአጠቃላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአፋር ጋር በአንድነት መቆማቸውን ያየንበት ነው። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያዊነት ኩራት መሆኑን አይተናል። የአንድነትንና የኢትዮጵያዊነትን ልክ አይተናል።
አፋር ጀግና እየተባለ ሲወደስ ይሰማል። አፋርን ጀግና ያደረገው ኢትዮጵያዊን በአንድነት ከጎኑ ስለቆሙ ነው። አሁንም ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል በደንብ መሰራት አለበት። ልዕልናችንም ለማስቀጥል የተጀመሩ የልማት ስራዎችን መጨረስ እና ሌሎች አዳዲስ የልማት ስራዎችን መጀመር ያስፈልጋል።
በሚቀጥለው ስለኢትዮጵያ ውይይት መቀሌ ተገናኝተን ስለሰላም ፣ አንድነት እና ልዕልና መምከር ይጠብቀብናል። ገጥሞን የነበረውን የሰላም ችግር በውይይት እየፈታን ነው። አሁንም ይህን አጠናክረን መቀጠል አለብን በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥር 8/ 2015 ዓ.ም