አዲስ አበባ፡– የስሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እሳት ቃጠሎ አንድ ሳምንት ከቆየ በኋላ አሁን በሶስት ቦታዎች ላይ ከሚታይ ጭስ በስተቀር በቁጥጥር ስር መዋሉን የስሜን ተራሮች ብሔራዊ የፓርክ የኅብረተሰብ እና ቱሪዝም ኃላፊ ገለጹ፡፡
የፓርክ የኅብረተሰብ እና ቱሪዝም ኃላፊው አቶ ታደሰ ይግዛው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የፓርኩን ቃጠሉ አስመልክቶ እንደገለጹት፤ የስሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሰደድ እሳት ቃጠሎ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ሆኖም በገደላማ ሶስት ቦታዎች ላይ ጭስ ይታያል፡፡
ሄሊኮፕተሯ ወደ ፓርኩ ከመጣች ጀምሮ እስካሁን ድረስ እሳቱን ለማጥፋት 20 ጊዜ ተመላልሳ ውሃ መርጨቷን ኃላፊው ገልጸው፤ ሰደድ እሳቱን በመቆጣጠር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ታይቷል ብለዋል፡፡
ትናንት ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ቃጠሎ አለመኖሩንም ጠቅሰው፤ በፓርኩ ዳግም ቃጠሎ እንዳይከሰት በመከላከያ፤ በክልሉ ልዩ ሀይልና በአካባቢው ሚሊሻዎች ጥብቅ ጥበቃና ቅኝት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቃጠሎው የተጎዳውን ደን መልሶ ለማልማት የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን ለማፍላት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና ከ90 በመቶ በላይ በቃጠሎው ጉዳት የደረሰበት የጓሳ ሳርም ዝናብ ሲያገኝ እንደሚያገግም ጠቁመዋል፡፡
እስከ ትናንት ከሰዓት በኋላ ድረስ ፓርኩ በተቃጠለበት አካባቢዎች አሰሳ መደረጉን ጠቅሰው ምንም አይነት የዱር እንስሳት (ዋሊያ፤ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ) አለመሞታቸውን ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ሁለት የእስራኤል እሳት አጥፊ ባለሙያዎች ከሄሎኮፕተሯ ፓይለት ጋር በሬድዮ ግንኙነት በማድረግ ርጭቱ በአግባቡ እንዲካሄድ አድርገዋል፡ ፡ የተወሰኑት ደግሞ ሄሎኮፕተሯ ነበር፡፡ በባለሙያዎቹ በሰጡት ምክረ ሀሳብ መሰረት ውሃ በቦቴ ወደ ፓርኩ በመቅረቡ ከደባርቅ አካባቢ አንድ ዙር ውሃ ለመቅዳት 30 ደቂቃ ይፈጅ የነበረውን ወደ10 ደቂቃ ዝቅ ማድረግ በመቻሉ የእሳት ቃጠሎውን በፍጥነት መቆጣጠር ተችሏል።
በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ ከ700 ሄክታር በላይ በሚገመት የፓርኩ ይዞታ ላይ ጉዳት ማድረሱ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
በጌትነት ምህረቴ