ኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላትን በዓደባባይ በድምቀት ከሚያከብሩ አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። እነዚህ በዓላት በአብዛኛው ምንም እንኳን መንፈሳዊ ይዘት ቢኖራቸውም በህዝብ ውስጥ ማህበራዊ ትስስር በመፍጠር እና አንድነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው እሙን ነው። በተለይም የተለያዩ ቋንቋና ባህል ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን በማቀራረብ እና እስከ ጋብቻ በሚዘልቅ ግንኙነት በማወዳጀት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው።
በኢትዮጵያ ጊዜ ጠብቀው የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ከመንፈሳዊ ፋይዳቸው ባለፈ በውስጣቸው በያዙት መስህባዊ ገፅታ ምክንያት በርካታ የውጭ እና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ይስባሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ የጥምቀት በዓል ነው። የስነ-መለኮት ምሁራን ጥምቀት ለሚለው ቃል መነከር፣ መታጠብ፣ መረጨት እና የመሳሰሉትን ትርጓሜዎች ይሰጡታል። ጥምቀት በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባህር የተጠመቀበትን ዕለት በማሰብ የሚከበር በዓል ነው።
የጥምቀት ዋዜማ ደግሞ ከተራ ይባላል። የከተራ እለት ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚሰማው የደውል ጥሪ ታቦታቱ፤ የተለያዩ ህብረ- ቀለማት ያላቸው አልባሳት በለበሱ ህዝበ ክርስቲያን ታጅበው ጉዟቸውን ወደ ጥምቀተ ባህር ያደርጋሉ። በዕለቱ ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተሰናዳ በኋላ፤ ታቦተ ህጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ- መቅደሱ ታቦታት በወርቅ እና በብር መጎናፀፊያ እየተሸፈኑ፤ በተለያየ ህብር በተሸለሙ የክህነተ- አልባሳት በደመቁ ካህናትና መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ለመሄድ ሲነሱ መላው አብያተ- ክርስቲያናት የደውል ድምፅ ያሰማሉ። ምዕመናንም ከልጅ እስከ አዋቂ በአፀደ ቤተ ክርስቲያን እና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ።
ታቦታት ከቤተ መቅደሳቸው ወጥተው በምዕመኑ ታጅበው ማደሪያ ቦታቸው ይደርሳሉ። በዚያን ጊዜ ዳቆናትና ቀሳውስት በባህረ- ጥምቀቱ ዙሪያ ሆነው ከብር የተሰሩ መቋሚያና ፅናፅል እንዲሁም ከበሮ ይዘው በነጫጭ እና በወርቅ ቀለም ባሸበረቁ እጥፍ ድርብ አልባሳት አምረውና ተውበው፤ የኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት ታሪክ የሚያወሱ ወረብና መዝሙሮችን ጣዕም ባለው ዜማ ያቀርባሉ። ሌሊቱን ስብሀተ – እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ በመቀጠልም ስርዓተ ቅዳሴው ይፈፀማል።
የጥምቀት በዓል ለአገር አንድነትና ህዝባዊ ትስስር ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ካሉ የአደባባይ በዓላት መካከል በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው። እርግጥ የጥምቀት በዓልን እንደጀርመንና ሩሲያ የመሳሰሉ የአውሮፓ አገራት የሚያከብሩት ቢሆንም በኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት በላቀና በደመቀ ስነስርዓት ነው የሚከበረው። ጥምቀት ካለው መንፈሳዊ ፋይዳ ባሻገር የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴታቸው በማድረግ እና በመጠበቅ ከትውልድ ሲያስተላልፉት የኖሩት ትልቅ የአደባባይ በዓል ነው።
በጥምቀት የተነፋፈቀው ይገናኛል፤ የማይተዋወቁ ወዳጅ ይሆናሉ፤ የተጣሉ ባላንጣዎች እርቅ ያወርዳሉ። በተለይም የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ባህል ለሌላው ከማስተዋወቅ ባሻገር እርስ በርስ ያላቸውን መስተጋብር የሚያጠናክሩበት ልዩ ክስተት ነው፤ ጥምቀት!። ለዚህም ነው ጥምቀት ሃይማኖታዊ ቀኖናን መተግበሪያ ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ ህይወት መሰረት የሚጣልበት እንደሆነ ብዙዎች የሚያስማሙበት።
ከዋዜማው (ከተራ) ጀምሮ ታቦታት ከየአቢያተ- ክርስቲያናቱ በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ በዝማሬና በምዕመናን ታጅበው የሚሄዱበት ሃይማኖታዊ ስርዓት ልዩ ድምቀት ያለውና የእምነቱ ተከታዮችን ብቻ ሳይሆን ሌላውን ህብረተሰብ ጭምር በናፍቆት የሚጠብቁት ትዕይንት ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ይህ በዓል መሰረቱ ሃይማኖት ይሁን እንጅ ባህላዊ እሴቱ የበለጠ አጓጊ ነው። በተለያዩ ባህላዊና ደማቅ የአገር ባህል አልባሳት በለበሱ ምዕመናን የሚደምቅበት፤ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ መድረክ የሚያሳዩት የሞቀ ውዝዋዜ እና የወጣቶቹ በአርሞኒካ የታጀበ ቄንጠኛ ጭፍራ ባብዛኞቻችን እዝነ-ልቦና በደማቁ የተከተበ ልዩ በዓል ነው።
በጥቅሉ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ከባህላዊ ወግና ስርዓት ጋር አጣምሮ የያዘ ነው ማለት ይቀላል። በዚህ በዓል በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ህብረ – ቀለማዊ የሆነ ጨዋታቸውን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ያቀርባሉ። በዓሉን ለማክበር ወደ ጥምቀተ ባህር የሚሄዱ ሰዎች ከበዓሉ በፊት ተዋወቁም አልተዋወቁም በዚያን ዕለት በጋራ ሆነው ጥዑም ዜማዎችን ያንቆረቁራሉ። ይህ ዕለት ማንም ሰው ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ የውስጡን የሚገልፅበትና በጋራ የሚጫወትበት ዕለትም ጭምር ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጓደኝነት ለመተጫጨት ለሚፈልጉ ወጣቶች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል። መላው ኢትዮጵያውያን ይህንን በዓል ዘርና ቀለም ሳይለዩ በአንድነት ያከብሩታል። በመሆኑም በዓሉ ህዝብን በማቀራረብና የመረዳዳት ባህልንም በማሳደግ ረገድ የጎላ ሚና ተጫውቷል፤ በመጫወትም ላይ ይገኛል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ቱባ ባህል እና ወግ በየአካባቢው የተለያየ አይነት አለባበስ ቢኖርም ለጥምቀት ሁሉም እንደ ባህሉና ወጉ መዋቡ እና ማጌጡ ግን አይቀሬ ነው። በተለይም በገጠሪቱ የአገሪቱ አካባቢዎች ሹሩባ፣ ጋሜና ቁንጮ የሚሰሩ ልጃገረዶች እጆቻቸውን እና እግሮቻቸውን በእንሶስላ አስጊጠው አምባር እና ጠልሰም፣ አልቦና ድሪ፣ ጉትቻና ሻሽ ሸብ አድርገው የውበት ልክና ጥግ ላይ ያርፋሉ።
በጥምቀት ደስታ፣ በጥምቀት ባህል፣ በጥምቀት ትዳር እና ፍቅር ይቀነቀናሉ። በተለይም ልጃገረዶች ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ….›› በተባለለትን ልዩ የአገር ባህል ልብሳቸው ተውበው በዓሉን ይታደማሉ፤ ኮበሌዎችም አይናቸው ያረፉበትን ኮረዳ የሚያገኙትና የሚያጩበት በዚሁ ደማቅ በዓል ነው። በነገራችን ላይ የወጣቶቹ የውበት አጠባበቅ ስነ-ስርዓት ከልጃገረዶች ጋር ሲነፃፀር ያን ያክል ትኩረት የሚሰጠው ባይሆንም ለጥምቀት አዲስ መልበስ ግን ወግ ነው።
በአንዳንድ ሰሜናዊ የአገሪቱ አካባቢዎች ወጣት ወንዶች ከጭናቸው ጋር ልክ የሆነ ቁምጣ ዳሩና ኪሱ በቁልፍ አጊጦ ከግጥም ኮት ጋር መልበስ ያዘወትራሉ። እርግጥ ነው፤ በጥምቀት የሚዘወተረው አለባበስ በዚህ አካባቢ ይህን ይመስላል ለማለት የተመዘገበ ነገር ባይኖርም የተለያዩ ባህላዊ አልባሳት በድምቀትና በስፋት የሚታዩበት በመሆኑ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖት ይዘቱ ባለፈ ባህላዊ እሴቱም ከፍ ያለ እንደሆነ ግልፅ ነው።
በተለይም በገጠራማው የአገሪቱ አካባቢዎች የጥምቀት በዓል ሲደርስ ከከተሜው የተለየ ዝግጅት ይደረጋል። ወንዶች ፀጉራቸውን ያበጥራሉ። ጥሩ በትርና መልካም ቁምጣ ያዘጋጃሉ። ሴቶች ሹርባ ይሳራሉ፤ እንሶስላ ይሞቃሉ። ጥምቀት ሲዳረስ ሰው ሁሉ ባለው እና በሚችለው ይዋባል። አንዱ ከሌላው ልቆ ለመገኘት ውድድሩ ይጧጧፋል። ድባቡ አጀብ ነው የሚያሰኘው። እስክስታ የሚችሉት አንዱ ከሌላው በልጦ የታዳሚውን ቀልብ ለመሳብ እንዴት እንደሚችሉ ሲጨነቁ ይሰነብታሉ። ድምጽ ያላቸው እና ግጥም መደርደር የሚችሉትም የማህበረሰቡን በተለይ ደግሞ የተቃራኒ ፆታን ቀልብ ለመሳብ እና ለመታጨት ጉሮሯቸውን ሲጠራርጉ ይሰነብታሉ።
ይህ ኩነት ኢትዮጵያ ብሂልን ከባህል ጋር አዛምዳ ከሌላው የክርስቲያን ዓለም በተለየ አከባበር በዓሉን ማክበሯ፣ በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ አስችሏታል። በአገር ውስጥ ካለው ማኅበረሰብ በተጨማሪ በርካታ የውጭ አገር ጎብኝዎች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና መንፈሳዊ ተጓዦች የሚታደሙበት በዓል በመሆኑ እንዲሁም የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ ቀልብ እየሳበ በመምጣቱ የአከባበር ሥነ-ስርዓቱን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምሕርት፤ የሳይንስና የባሕል ድርጅት በ«UNESCO» ጥበቃ ስር በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ተርታ ለመመዝገብ ችሏል።
ይህንን ደማቅ እና የእኛነታችን ማሳያ የሆነውን የአደባባይ በዓል ለዘመናት በማክበር ሂደት የአገሪቱ ህዝቦች ዘር ቀለም ሳይለያቸው ዛሬም በአንድነትና በህብረት በማክበር ላይ ናቸው። በሌላ በኩል ግን አሁን አሁን ጥምቀትን የመሰለ የህዝብ ለህዝብ አብሮነት መገለጫ የሆኑ በዓላትን የሚበርዙ አፍራሽ ተግባራት እዚህም እዚያም ሲፈፀሙ ይስተዋላል። አንዳንድ ለራሳቸው ጥቅም ያደሩ አካላት በዓላቱ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘታቸውን ለቀው ፖለቲካዊ አንድምታ እንዲይዙ በማድረግ ለዘመናት ተከባብረውና ተቻችሎ የኖሩትን ህዝቦች ለማቃቃር ጥረት ያደርጋሉ። አልፎ አልፎም ቢሆን ብሔረሰቦች ወግና ባህላቸውን በሚያንፀባርቁበት በዚህ በዓል ጠብ አጫሪ ሃሳቦችን በማስላለፍ መንፈሳዊ አንድምታው ለቆ የአምባጓሮ አደባባይ ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎችም አሉ።
በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ የሃይማትኖና የብሔር አክራሪዎች ‹‹ከእኔ በላይ ላሳር›› በሚል አጉል እብሪት ክርስቲያን ከሙስሊሙ በመረዳዳት እና በመተጋገዝ የሚያሳልፉ ይህ የመቻቻል ተምሳሌት የሆነ በዓል ዓውድን ወደ ጦርሜዳነት ለመቀየር ደፋ ቀና የሚሉበትም ሁኔታ አጋጥሟል። በመንግስትና በእምነት መዋቅር ውስጥ የተደበቁ እነ ‹‹ጭር ሲል አልወድም›› ባዮችም ቢሆኑ የጋራ የሆነችውን አገር የአንዱን የበላይነት ለማግዘፍና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ለአገር ሰላም ስጋት የሚጡበት ሁኔታም ታይቷል። በተለይ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች መንገድ የሳቱትን የመመለስና የመገሰስ ሃላፊነታቸውን በመዘንጋት የችግሩ ተሳታፊ ሆነው የሚገኙበት ክስተት ከታሪክ ተወቃሽነት አያስመልጣቸውም።
የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት መገለጫ፤ የመልካም ገፅታዋ መስታወት፤ የቱሪዝሙ የጀርባ አጥንት የሆነውን ይህንን ልዩ በዓል ሰላማዊና የመቻቻል እሴትነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የማድረጉ ሃላፊነት የሁሉም ነው። በተለይም በመላው አገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነት እንዲሰፍን የኃይማኖት አባቶች ህብረተሰቡን የማስተማር ተግባራቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው። የሃይማኖት አባቶች ህዝብን በማስተማር ሰላምና ፍቅር እንዲጠናከር በተናጠልና በጋራ ማስተማር ቀዳሚ ተግባራቸው ለሆን ይገባል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮና ከህብረተሰቡ እሴት በሚቃረን መልኩ ህገ-ወጥ ተግባራት የሚፈፅሙ አካላትን መንግስት ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ ለህግ ማቅረብ አለባቸው ባይ ነኝ። ይህ ሲሆንም ነው ጥምቀትም ሆነ ሌሎች የአደባባይ በዓላትን የመቻቻል፤ የአንድነት እሴቶቻችን ማሳያ ሆነው ሊቀጥሉ የሚችሉት። አልፎ ተርፎም የአገሪቱን የቱሪዝም የገቢ ምንጭ ማሳደግና ምጣኔ ሃብቷን ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚቻለው። ለዚህ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደቀድሞው ሁሉ አብሮነቱን ማጠንከርና ፀረ ሠላም ሃይላትን መከላከል ይገባዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም