በብዙ የቀብር ስነስርአቶች ላይ ተገኝቼ አውቃለሁ። ብዙዎቹ ሟቾች በሕይወት እያሉ የማላውቀው መልካምና የሚያስቀና አዲስ ማንነት ተችሯቸው የሕይወት ታሪካቸው ሲነበብ ታዝቤያለሁ። እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ስመለከት ብዙ ጊዜ ለራሴ፤ “ለዚያች ሰዓት ብቻ ፈጣሪ የሟቹን ሕይወት መልሶለት የራሱን የሕይወት ታሪክ የመስማት እድል ቢገጥመው ‹‹እንዲህ ዓይነት ፃድቅ ነበርኩ እንዴ?›› ብሎ ግራ የሚጋባ ይመስለኛል። ያን ሁሉ ያላደረገውን መልካም ሥራና ገድል ሲዘረዘርለት ሲሰማም ‹‹ወይኔ ለካ እንዲህም ማድረግ እችል ነበር?›› በማለት የሚፀፀትም ይመስለኛል።
በቅርቡ አንድ ከልጅነቴ ጀምሮ በማውቀው ሰው የለቅሶ ስነ ስርአት ላይ ያስተዋልኩት ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለዚህ ሰው የተነበበለት የሕይወት ታሪክ እንደሌሎቹ ያለቅጥ ተጋንኖ እንኳን ያልሠራውን በችሮታ የሚለግስ የሠራውንም በቅጡ የሚገልጽ አለመሆኑን አስተውያለሁ።
ይህ ሰው በአንድ ወቅት የአካባቢው አስተዳዳሪ የነበሩ ሰው፤ እንዲያገለግላቸው ወደ ቤታቸው አምጥተው ቀጥረው ያሰሩት ነበር። እሱ ግን የቀጠሩኝ እርሳቸው ናቸው ሳይል የአካባቢውን ሰው በሙሉ በጉልበቱ ያግዝ ነበር። አብዛኛውን የህይወቱን ጊዜ ሀብታምና ድሀ ሳይል በነጻ የሚያገለግል በሱ ልክ ያገልጋይነትና የቅንነት ልብ ያለው ሌላ ሰው የሚገኝ አይመስለኝም፤ ለዛ ነው በቀብር ስፍራው ጥሩ ሰው ነበር የተባለው አጭር ታሪክ ለሱ ያንሰዋል ያልኩት።
ይህ ሰው ለስራ ወደ ቀዬው ሲመጣ ስንት ዓመቱ እንደነበር ወይም የተወለደበት ዓመተ ምህረት የሚያውቅ ሰው ባለመኖሩ የህይወት ታሪኩ ጅማሬ እኔ ሳገባ እንትናን ያክል ነበር በሚል መላምት ተደመደመ።
ሟቹ አባቴ፣ ወንድሜ አጎቴ…ብሎ የሚያለቅስለት አንድም የስጋ ዘመድ የሌለው ብቸኛ ቢሆንም የቀዬው ሰው ሁሉ ወዳጁ የነበረ ደግሰው ነበረ። ይህ ደግ ሰው አባዬ፣ አባዬ ብሎ የሚያለቅስለት አንድም የስጋ ልጅ ባይኖረውም በደግነቱ የወለዳቸው አያሌ ልጆች ነበሩት። እናም እነዚህ ልጆቹ ከልባቸው አልቅሰውለታል፣ የቀብር ስፍራው አባዬ! አባዬ! በሚል ጩኸት ተደበላልቋል። ባገሬው የለቅሶ ባህል መሰረት ትላልቅ ሰዎች ሲሞቱ እንደሚደረገው በጉራጊኛ “ወርኮተማነረ” እየተባለ በታላቅ የቀብር ሥነሥርዓት ተቀብሯል። “ወርኮ ተማነረ ዋቢ የነበረ ኧኳ ተፈተረ“ ትርጉሙም ትልቅ የነበረ ዛሬ አረፈ ደግ የነበር ዛሬ አረፈ እንደማለት ነው።
በዚህም በቀብሩ ዕለት ሴቶቹ እጆቻቸውን እንደ አሞራ ዘርግተው ካገለደሙት ነጠላ ጋር ዘለል፣ ዘለል እያሉ ልብ በሚነካ መንገድ ሙሿቸውን ያወርዳሉ። ወንዶቹም ግርማ ሞገሳም ፈረሳቸው ላይ ሆነው አንዳንዶቹ እራሳቸውን ባለንጋቸው እየገረፉ የወርኮ ተማነር ሥርዓተ ክዋኔ ያንቆሮቁሩታል። ይህ በጉራጌ ማህበረሰብ የተለመደ የለቅሶ ስነስርአት ነው። ሁኔታው እንኳን የሚያውቁት ሰው ይሁንና ማንንም ቢሆን ያስለቅሳል።
በአገሬው ባህል መሰረት ይህ የለቅሶ ስነስርአት ለተከበሩ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ነበር፣ ታዲያ ይህ ወዳጄ ሀብታም ሆኖ ወይም ጥሩ ቤተሰቦች ኖረውት አይደለም ለዚህ የታደለው፣ መንደሩ ሁሉ የእሱ ውለታ ስላለበት ደግ ሰው ስለ ነበረ ነው፣ በዚህ ጊዜ እንባ እየተናነቀኝ በለቅሶው ቦታ ላይ ቆሜ በትዝታ ወደ ኋላ ነጎድኩ። ይሄ የአካባቢያችን ዋርካ ከላይ ያደፈ ሰማያዊ ካናቴራ መልበስ ያዘወትራል። ወደ አንገቱ ከፍ ብለው ሲመለከቱት መዘዝ፣ መዘዝ ያሉት ኮሌታዎች በርከት ያሉ ካናቴራዎችን ደራርቦ መልበሱን ያሳብቁበታል። ከስር ጥቁር ሱሪ ይለብሳል። ሱሪውን በኮባ ገመድ ወገቡ ላይ ሸብ ካረገ በኋላ ለቅልጥፍና ወይም ለውበት አላውቅም እግሮቹ ጋርም ሱሪውን በዛው በኮባ ገመድ ከባቱ ጋር አዋዶ ይጠፈንጋቸዋል። ሸፈፍ ሸፈፍ ያሉት ተረከዞቹ ጫማውንም ያንሻፍፉበታል። ብዙ የመንደራችን ሰዎች የዋህነቱን እያዩ እንደ ሞኝ እየቆጠሩ ሲስቁበት ብዙ ጊዜ ተመልክቻለሁ።
ይሁን አንጂ ለቅሶ ቦታው ላይ መልካምነቱን ደግነቱን እያነሱ ሲያለቅሱ ህሊናቸው ቢያረፍድም መልካምነት የሚያስቅ ሳይሆን ትልቅ በረከት መሆኑን የተረዱ መስለዋል። ለነገሩ ልጅ ሆኜም ቢሆን ስቀው ሲያበቁ ‹‹እሱ ምን አለበት! የእግዜር ሰው›› ሲሉት ሰምቻለሁ፤ ጥያቄው በእግዜር ሰው ይሳቃል እንዴ? የሚለው ነው። ‹‹እሱ ምን አለበት የእግዜር ሰው!›› የሚሉት የዋህነቱንና ደግነቱን ለመግለጽ ነው።
ሌላው አብሮ ትዝ የሚለኝ ነገር ለልጆች የነበረው ፍቅር ነው፤ ሰውየው ጠላ እጅግ ይወድ ስለነበር ጠላ ባለበት ማህበር ሁሉ ይገኛል። ታዲያ እሱ ጠላውን ብቻ ይጠጣና የሚሰጠውን ዳቦ በኪሱ በሰፈሩ ላለነው ህጻናት ይዞልን ይመጣ ነበር። በእርግጥ ዳቦው በኪሱ ይዞ ስለሚመጣ ኪሱ ውስጥ የነበሩ ብጥቅጣቂ ነገሮች ሁሉ የሙጥኝ ይሉት ነበር፤ ያን ያዩ አዋቂዎች ዳቦውን ስንበላ ፊታቸውን ቢያጨፈግጉም እኛ ግን እጅግ የምንደሰትበት ነገር ነበር። ዛሬ ለቅሶው ላይ ብዙ ወጣቶች አባዬ እያሉ ያለቀሱት እንደዚህ ያለውን ፍቅር ስለቀረባቸው ይሆን ብዬ አስቢያለሁ።
አንዳንዴ ይህን ሰው ሳስብ በአካባቢው ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ቀድሞ የሄደ ይመስለኛል። አንዳንዴም ከማህበረሰቡ ለየት ያለ ፍልስፍና የነበራቸውን አደፍርስ እና ጉዱ ካሳን ያስታውሰኛል። በዛች በገጠር መንደር ለሴት ተብለው የተተው ስራዎችን ወደ ጓዳ እየገባ ይሰራ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ይህ በማህበረሰባችን ውስጥ ያልተለመደ ፍልስፍና ነው። ታዲያ በዚ ስራው አንዴ እንኳን ሲመሰገን ሰምቼ አላውቅም፣ ከዛ ይልቅ ወልየ (ሴታሴት) እያሉ ሲሰድቡት ሰምቻለሁ፣ ሰው በህይወት እያለ ማመስገን ነውር የሆነብን ይመስል በቀብሩ ስፍራ ላይ ብዙ ሴቶች ይህንን ደግነቱ እያነሱ ሲያመሰግኑት ነበር።
ለዚያም ይመስለኛል ምንም እንኳን ጠያቂ የስጋ ዘመድ ባይኖረውም አገሬው ተንከባክቦ የጦረው፣ ለቅሶው እንዲያ በአካባቢው ባህል ‹‹ውርኮ ተማነረ›› የቀለጠው። በትዝታ መንጎድ የጀመረው ልቤ በማንነቱ ሲሳብ ሲቀና የታወቀኝ ይሄኔ ነው::
የሰውየው እንዲያ ባመረና በታላቅ ሁኔታ ትንሽ ትልቁ አልቅሶ ቢቀብረውም በማያልቀው መልካም ሥራው ነውና ይገባዋል አልኩኝ። የእንዲህ አይነት ሰዎች የሕይወት ታሪክ ግን ከጸሐፊ ማጣት ብቻ ሳይሆን እንደ አስተማሪም ስለማይቆጠር አላውቅም በበቂ ሁኔታ ሲነገርላቸው አይሰማም። ለሰውየው የሕይወት ታሪክ ጽፎ ከማንበብም በላይ ማሕበረሰቡ በተግባር የሚገባውን ክብር ሁሉ ሰጥቶ በመቅበር ቢክሰውም የእንዲህ አይነት ሰዎች ሥራና ፍልስፍና ግን መነገር አለበት።
ይህን ገጠመኝ ወደዚህ ያመጣሁት እንዲህ አይነት ልብ የማይባሉና የአካባቢን ኋላቀር ልማድ ጥሰው አዲስ አሰራር የሚያሳዩ በጎ ሰዎችም አሉ ለማለት ነው። ብዙ ጊዜ መልካምነት የሚመሰገነው በታዋቂ ሰዎች ሲሆን ነው። ዳሩ ግን የእነዚህን ታዋቂ ሰዎች ምግባር የቀረፀው የእነዚህ ታዋቂ ያልሆኑ ሰዎች አስተወፅዖ ነው። አንድን አካባቢ እንደ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የእንዲህ አይነት ግለሰቦች ሚና ከፍተኛ ነው። ማህበረሰብ ደግሞ የእንዲህ አይነት ሰዎች ውጤት ነው። ስለዚህ አዳዲስ አተያይ ያላቸውን ሰዎች ማበረታትና ማስተዋወቅ ይገባናል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ጥር 3 /2015