ትላንትናን መሰረት አድርጎ ዛሬን የገነባው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ትላንት እንዴትና ምን ይመስል ነበር፣ ምን አይነት ሀገራዊ ኩነቶችና ክስተቶችንስ በማህደሩ ላይ ከትቦ አልፏል? የሚሉትን ሀሳቦች የኋልዮሽ የሚቃኝበት ‘አዲስ ዘመን ድሮ’ እንደተለመደው ዛሬም ልዩ ልዩ ዜናዎችን ቀነጫጭቦ አቅርቦላችኋል። በዛሬው አምዳችን በዋናነት የደርግ መንግስት አብዮት በተጧጧፈበት 1960ዎቹ መጨረሻ የተዘገቡ ጉዳዮችን መራርጠናል። በተደጋጋሚ ይጋጩ የነበሩት ሁለቱ ጎሳዎች እርቅ ስለመፈጸማቸው፣ በዱላ ብቻ የጦር መሳሪያ ስለማረከው ጀግና፣ የቀድሞው የቤጌምድርና ሰሜን ስም መቀየሩ፣ ስለተዘጉት ሶስቱ ፍርድ ቤቶች፣ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ወዛደሮች መታጠቃቸው እንዲሁም ኢትዮጵያን ስለጎበኙት ታላቁ የነጻነት ታጋይ ፊደል ካስትሮን የተመለከቱ ዜናዎች ተካተዋል።
ይጋጩ የነበሩት ጎሣዎች ታርቀው ሠርጎ ገቦችን ለመደምሰስ ወሰኑ
ሐረር(ኢ.ዜ.አ) ሐረርጌ ክፍለ ሀገር በደገሃቡር ወረዳ በሂግሊሴ ቀበሌ የሚኖሩት ሬር መገንፊቅ የሬር ሸርማርኬ ጎሳዎች ከሰባት አመት በላይ በመካከላቸው የነበረውን የነፍስ ግድያና የዝርፊያ ቅራኔ ሰሞኑን በእርቅ አስወገዱ።
ሁለቱም ጎሣዎች በመካከላቸው የነበረውን ቅራኔ ከማስወገዳቸውም በላይ ለመደብ ትግል ክንዳቸውን በማስተባበር ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲ ካፒታሊዝምን ለመደምሰስ ተስማምተዋል።
ከዚህም ሌላ በጎረቤት አገር በኩል ሠርገው የሚገቡትን ወንበዴዎች ለመደምሰስ ወስነዋል።
ማክሰኞ መጋቢት 26/1969ዓ.ም
ገበሬው በዱላ የጦር መሣሪያ ማረከ
በወገራ ወረዳ በልማምያ ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ሊቀ መንበር የሆነው ደበበ በላይ ሰሞኑን መሣሪያ ያነገቡ አራት የኢዲዩ ወንበዴዎች ከመኖሪያ ቤቱ ድረስ በመሄድ ሊገድሉት ሲሞክሩ በያዘው ዱላ ብቻ ተከላክሎ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስበት አንድ የጦር መሣሪያቸውን የማረከባቸው መሆኑን ተገለጠ።
ሊቀመንበሩ አደጋ ሊያደርሱበት ከቃጡት ከእነዚሁ ወንበዴዎች ተከላክሎ የማረከው የጦር መሣሪያ አንድ ዲሞፍተር ጠመንጃ መሆኑን የወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት አስታውቋል።
ሐሙስ ሚያዝያ 27/1969ዓ.ም
የቤጌምድርና ሰሜን ስም ተለወጠ
የቤጌምድርና ሰሜን ክፍለ ሀገር ይባል የነበረው ከትላንት ጀምሮ የጎንደር ክፍለ ሀገር ተብሎ እንዲጠራ የተወሰነ መሆኑን የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር ትናንት አስታወቀ።
እሑድ ታህሳስ 13/1969ዓ.ም
ባለጉዳይ በመጥፋቱ በሦስት ወረዳዎች መደበኛ ፍርድ ቤቶች ተዘጉ
አርባ ምንጭ፣(ኢ.ዜ.አ) በጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር ከንባ፣ ምዕራብ አባያ፣ ዲታ በተባሉት ወረዳዎች የነበሩት መደበኛ ፍ/ቤቶች የሚያስተናግዱት ባለጉዳይ ባለማግኘታቸው መዘጋጀታቸውን የክፍለ ሀገሩ የከፍተኛ ፍ/ቤት ሰብሳቢና ተጠሪ ዳኛ ገለጡ።
አርብ ነሐሴ 14/1969ዓ.ም
የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ወዝአደሮች ታጠቁ
ሰፊው ሕዝብ የመጣለትን አብዮት ከውስጥና ከውጭ ቀልባሽ ኃይሎች መከላከል ይችል ዘንድ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ከተሸጋገረ ወዲህ ጭቁኑን አርሶ አደርና ወዝአደር ለማስታጠቅ በገባው ቃል መሠረት ባለፈው እሑድ ከቀትር በላይ የመተሐራን ወዝአደሮች አስታጥቋል።
በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወዝአደሮች ተካፋይ በሆኑበት ሰልፍ ላይ ትጥቁን ዘጠኝ አባላት ላሉት የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ወዝአደሮች የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴ ያስረከቡት 50 አለቃ ለገሰ አስፋው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የወታደራዊ ክፍሎች የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊና የጊዜያዊ የትጥቅ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ናቸው።
ማክሰኞ ሐምሌ 16/1969ዓ.ም
ኢትዮጵያን መድፈር በእሳት መጫወት መሆኑን ሶቪየት ሕብረት ገለጠች
በኅብረተሰብአዊት ለኢትዮጵያ ላይ በሱዳን መንግሥት ባለሥልጣኖች በኢምፔሪያሊስቶችና በአድኃሪ ሀይሎች ድጋፍ ወረራ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ታስ የተባለው የሶቪየት ዜና አገልግሎት ባለፈው እሑድ ከሞስኮ አስታወቀ።
*****
በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ለመፈጸም የሚደረገውን ዝግጅት በሚመለከተው ጉዳይ ታስ ባለፈው እሑድ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው።
“በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ለመፈጸም ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን የሚያመለክቱ ዜናዎች ከጥቂት ጊዜ ወዲህ ከልዩ ልዩ ክፍሎች ይሰማሉ። በዜናዎች መሰረት መደበኛ ወታደሮች ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወሰን በመላክ ላይ ናቸው። የታጠቁ ቡድኖች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ሰርገው እየገቡ ለፀረ-አብዮተኞችና ለተገንጣይ ቡድኖች የሚሰጡት ድጋፍ እንዲያፋፍሙ እየተደረገ ነው። ሁኔታው ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ ግጭት እንዲነሳ ለማድረግና በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ተራማጅ መንግሥት ለመገልበጥ የሚቃጣ ነው። ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ የሚደረገው በሱዳን ባለስልጣኖችና እንዲሁም በኢምፔሪያሊስት አድኃሪ ኃይሎች ሙሉ ተካፋይነት መሆኑ ግልጽ ነው።
******
በኢትዮጵያና በሶቪየት ኅብረት መካከል የሚደረገውን የወዳጅነት ግንኙነትና ተራድኦ በሚመለከተው የሁለቱ አገሮች የጋራ መግለጫ መሰረት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን በማጠናከር ላይ የምትገኘው ሶቪየት ኅብረት በኢትዮጵያ አካባቢ የሚደረገውን ሁኔታ በቅርብ ትከታተለዋለች። ታስም ሶቪየት ኅብረት፣ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ተግባር ለመፈጸም በመዘጋጀት ላይ የሚገኙትና በዚሁ እቅድ እንዲቀጥሉ የሚገፏፏቸውን ክፍሎች የምታወግዝ መሆኗን እንዲገልጽ ሥልጣን ተሰጥቶታል። አድራጎቱ በእሳት እንደሚጫወት እንደሚቆጠርና ራሳቸውን በዚሁ ጉዳይ ለሚያስገቡ በአፍሪካ ሕዝቦችና በመላው ዓለም ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች በኃላፊነት ይጠየቃሉ።
እሮብ ሚያዝያ 26/1969 ዓ.ም
ጓድ ካስትሮ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት መጡ
የኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊና የሚንስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ዶክተር ፊደል ካስትሮ ሩዝ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ትላንት ከእኩለ ቀን በኋላ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ከዶክተር ፊደል ካስትሮም ጋር ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት መልዕክተኞች መካከል የኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የፖለቲካ ቢሮ አባልና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ጓድ ክርሎስ ረፍዬል ሮድርጉስ ይገኙበታል።
ማክሰኞ መጋቢት 6/1969 ዓ.ም
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2015