በዚህ ዘመን የሳተላይቶች ሚና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፤ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የአየር መንገድ እንቅስቃሴዎች፣ የአየር ጸባይ ለመረዳት የሚደረጉ ጥረቶች፣ የተለያዩ ወታደራዊና የሲቪል ስራዎች በሳተላይት የሚተላለፍ መረጃን ይፈልጋሉ። ቴሌቪዥኖችና ራዲዮኖች ሳተላይቶችን ይፈልጋሉ፤ ዛሬ አገልግሎቱ እየተስፋፋ የመጣው የጂፒኤስ ቴክኖሎጂም የሳተላይት መኖርን የግድ ይላል።
በአጠቃላይ ሳተላይቶች ለሀገሮች ምጣኔ ሀብት፣ ለወታደራዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች የተሳለጠ መሆን ያላቸው ሚና ከፍተኛ እየሆነ መምጣት፣ ሀገሮች ሳተላይቶችን ተከራይቶ ከመጠቀም ባሻገር የራሳቸውን ሳተላይት በማምጠቅ ስራ እንዲጠመዱ አድርጓቸዋል።
ሕዋ ላይ ያሉ ሳተላይቶች መረጃዎችን በመሰብሰብ ከግዙፍ ክንውኖች እስከ ጥቃቅን እንቅስቃሴዎች በመመዝገብ ይይዛሉ። ሳተላይቶቹ የመሬትና የሕዋ ሳይንስ ምልከታ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የከተማ ልማት፣ የአደጋን መከላከል ፣የካርታ ሥራ ፣ የግብርና የደን ልማት፣ የሜትሮሎጂ፣ የጂፒኤስ እና የዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሀብትን መቆጣጠር የሚያስችሉ መረጃዎችን በመስጠት ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ነው። ከዚህ ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመድረሳቸው አስቀድሞ ለመተንበይ፣ ደህንነትን ለመጠበቅ የሚረዱ መረጃዎችን ለማወቅ እንደሚውሉም መረጃዎች ያመላክታሉ።
በዓለም ላይ በፍጥነት እየዘመነ ያለውን የሕዋ ሳይንስ ዘርፍ በመጠቀም ያደጉት ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት ሳተላይቶችን ወደ ሕዋ በማምጠቅ የመሬትና የሕዋ ምርምርን በማሳደግ ከዘርፉ ብዙ ጠቀሜታ አግኝተዋል። ለዚህም ነው ያደጉት ሀገራት ዓለምን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሳተላይት በመገንባት ወደ ሕዋ በማስወንጨፍ ረገድ አንገት ለአንገት ተናንቀው እየተፎካከሩ የሚገኙት።
ኢትዮጵያም የሕዋ ሳይንስ ዘርፍን መቀላቀሏን ያበሰረችው በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባመጠቀችው Ethiopian Remote Sensing Satellite–01‹‹ETRSS-1›› የመሬት ምልክታ ሳተላይት አማካይነት ነው። ሳተላይቷ ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ሕዋ መምጠቋ ይታወሳል። ሳተላይቷ ወደ ሕዋ ከመጠቀች ሦስተኛ ዓመቷን አስቆጥራለች። ወደ ሕዋ የመጠቀችው ለሁለት ዓመት ተኩል አገልግሎት እንድትሰጥ ታስባ ቢሆንም፣ የቆይታ ጊዜዋን በስድስት ወራት አራዝማ በመቆየቷ ሦስተኛ ዓመቷ በያዘነው የፈረንጆቹ ወር ተከብሯል።
በዛሬ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን ሳተላይቷ በእነዚህ ሦስት ዓመታት በሕዋ ላይ ስላከናወነቻቸው ተግባራትና ስለበረከተችው አስተዋጽኦ ዳሰናል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ እንደሚሉት ፤ ‹‹ETRSS -1›› የመሬት ምልክታ ሳተላይት የማምጠቁ ሂደት ለሁለት ዓመት ተኩል አገልግሎት እንድትሰጥ ታስቦ የተካሄደ ቢሆንም፣ ሳተላይቷ ተጨማሪ ስድስት ወራት በመቆየት አሁንም ድረስ መረጃ የመስጠት ተልዕኮዋን በአግባቡ እየተወጣች ነው። ይቺ ሳተላይት በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ታሪክ የመጀመሪያዋ ስትሆን ወደ ሕዋ ከተላከች አንስቶም እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተች ትገኛለች።
ሳተላይቷ በኢትዮጵያ ሕዋ ሳይንስ ላይ ስለፈጠረችው መነቃቃት፤ ስለሰጠችው መረጃ፤ ሳተላይትን ዲዛይን በማድረግ፣ በመፈተሽ፣ በመቆጣጠርና በመጠገን የቴክኖሎጂ አቅም በመፍጠር ረገድ ያበረከተችው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አቶ አብዲሳ ጠቅሰው፤ ሳተላይትን ካመጠቁ አገራት ጎራ እንድንሰለፍ በማድረግ በገጽታ ግንባታ ላይ ስላደረገችው በጎ አስተዋፅኦም ተናግረዋል። በትውልዱ ላይ ስለጫረችው ተስፋና ስለፈጠረችው መነሳሳት እንዲሁም የ‹‹ETRSS-2›› የቅድመ ዝግጅት ሥራ እንዲከናወን መነሻና ብርታት መሆኗን አስታውቀዋል።
የ ‹‹ETRSS -1››በኢትዮጵያ ስፔስ ፕሮግራም ውስጥ ለትውልድ የምትጠቀስ ታሪካዊ ሳተላይት ነች ያሉት አቶ አብዲሳ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ በሕዋ ውስጥ ከፍተኛ ሙቀትን እና ቅዝቃዜን እንዲሁም ከፀሐይ የሚነሱ አደገኛ ጨረሮችን፣ አለፍ ሲልም ‹‹ETRSS -1›› እኮ ጠፍታለች የሚሉ መርዶ ነጋሪዎችን የሟርት ቃላት ተቋቁማ የታቀደላትን የሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ማጠናቀቋ ሳያንስ ከተያዘላትም ጊዜ ስድስት ወር አሳልፋ እስካሁን ድረስ አገልግሎት እየሰጠች መሆኑን ነው ያብራሩት።
በሳተላይቷ አገልግሎት እጅግ ደስተኞች ነን ያሉት አቶ አብዲሳ፤ ለዚህ ከእንጦጦ ቁርና ብርድ ጋር እየታገሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የተቋሙ ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል። ይህም ለተቋሙም ይሁን ለመላው ኢትዮጵያውያን ኩራት ያጎናጸፈ ትልቅ ገድል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሳተላይት ኦፕሬሽን ዘርፉን የሚመሩት ኢንጂነር መላኩ ሙካ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን የ‹‹ETRSS -1›› የመሬት ምልክታ ሳተላይት ወደ ሕዋ መላኳ በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ሳተላይት ወደ ሕዋ ስታወናጭፍ በወቅቱ በሕዋ ላይ ያሉ ሳተላይቶች ወደ አርባ ይጠጉ እንደነበር ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አሥረኛ ሳተላይትን አወንጫፊ አገር መሆኗ በሕዋ ዘርፍ ስሟ ከፍ እንዲል ያደረገ ተግባር መሆኑን ነው ያብራሩት።
ሳተላይቷ ከመጠቀች ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በርካታ ትሩፋቶችን እያስገኘች ነው ያሉት አቶ መላኩ፤ ይህም በዲዛይን፣ በጥገና እና በኦፕሬሽን ዘርፍ ያለውን የሰው ኃይል አቅም በመገንባት ለሌሎች የሚተርፍ ከፍተኛ አቅም መገንባት ያስቻለ አቅም መፍጠሯን እንደሚያመለክት ነው የገለጹት።
እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፤ ሳተላይቷን ከመቆጣጠር እና ተልዕኮ ከመስጠት አኳያ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። በእነዚህ ሦስት ዓመታት ከሦስት ሺ በላይ የመረጃ ቅብብሎሽ የተደረገ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከአንድ ሺ ሁለት መቶ በላይ የሚሆኑት ተልዕኮዎች ለሳተላይቷ ተሰጥተዋል። የውሃ ሀብትን አስመልክቶ መረጃ ለሚፈልጉ አካላት ተገቢው መረጃ ይሰጥ ነበር። በተለይም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የሚፈለጉ መረጃዎችን ከመስጠት አንጻር ፤ በየዓመቱ የነበሩ የውሃ ሙሌቶችንና ከዚያ ጋር ተያይዞ የተገደበው ውሃ የሚይዘውን ቦታና የሚኖረውን ቅርጽ በ ‹‹ETRSS-1›› የመሬት ምልከታ ሳተላይት መረጃ ማወቅ አስችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የደን ሽፋንን፣ ለድርቅ እና ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ የአፋርና የዳሰነች ቦታዎችን እንዲሁም የውሃ እጥረት ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች መለየት ተችሏል። ሰፋፊ የፍራፍሬ ዛፎችን እና እርሻዎችን ደህንነት ለመቆጣጠርና ለመንከባከብ ከሳተላይቷ የሚገኘው መረጃ ጥቅም ይሰጥ እንደነበር ጠቅሰው፤ በዚህም በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ስላለ የፍራፍሬ ጫካ እና በመተሃራ ሸንኮራ አገዳ ማሳ በተገኘው መረጃ ላይ ተመስርቶ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚያስችል ነው አቶ መላኩ ያብራሩት።
‹‹ኢትዮጵያ ሳተላይት ማስወንጨፏ ለአዲሱ ትውልድ መነቃቃትን ይፈጥራል፤ ይህንንም አጠናክራ መሄድ እንደምትችል ተስፋን የሚያሰንቅ ነው›› ያሉት አቶ መላኩ፤ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ላይ እምነትና ተስፋ የሚጥል ትውልድ ለመፍጠር ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል። የነገ የሀገር ተረካቢ ወጣቶችና ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከትምህርት ቤቶች እንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ የምርምር ማዕከል መቆጣጠሪያ ጣቢያው ድረስ በአካል ተገኝተው በዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች እንደሚጎበኙ ጠቅሰው፤ በጉብኝታቸውም በተመለከቱት እንደሚደነቁና በኢትዮጵያ በሕዋ ሳይንስ ዘርፍ የተጀመረው ሥራ እንዲህም ይቻላል እንዴ ብለው ነገን እንዲያስቡ፣ ተስፋ እንዲሰንቁ ያደረገ መሆኑን ነው አቶ መላኩ ያብራሩት።
ኢትዮጵያ ያስወነጨፈቻት የ«ETRSS -1» የመጀመሪያዋ ሳተላይት የመማሪያ መጻሕፍት ሽፋን እንዲሆን መደረጉንም ጠቁመዋል። በተጨማሪም የሕዋ ሳይንስ ትምህርት በአንድ ምዕራፍ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት መድረጉ በትውልዱ ላይ መነቃቃት በመፍጠር እንደሚያግዝ አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የ«ETRSS -1» ሌሎች ሳተላይቶች ዲዛይን ለማድረግ ትልቅ ራዕይ፣ ሞራልና መነቃቃት እንዲኖር ያደረገ ክስተት ነው። እንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ የምርምር ማዕከል ከተለያዩ የዓለም ሳተላይቶች መረጃን በመቀበል ከብዙኃ ሳተላይቶች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ሀገሪቷ የምትፈልገው የመረጃ ፍላጎት ተደራሽ እንዲሆን ያስቻለ አቅምን የፈጠረ ነው። ይህም የሀገሪቱ ተቋማትን ትልልቅ የመረጃ ፍላጎት ለመፍታት የ«ETRSS -1›› ቀጥሎ የተፈጠረው የብዝኃ ሳተላይቶች ዲዛይን አዲስ የፈጠራ ጥበብ የታየበት ነው። ይህ የብዝኃ ሳተላይቶች ዲዛይን በጣም ብዙ ሥራዎች የሚሰራ በዓለም ገበያ ውዱና በጣም ዘመናዊ የሚባል ሳተላይት ነው። ኢትዮጵያ እዚህ ላይ ቀድማ መድረሷ ደግሞ ትልቅ ስኬት ያስገኘ ነው።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ ዓሊ እንደተናገሩት፤ ዓለም ዛሬ የደረሰበት አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ምዕራፍ የዲጅታል ቴክኖሎጂ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የውሂብ አልተኔት ትንታኔ፣ የቁስ በይነ መረብ እና ሌሎች መጻኢ ቴክኖሎጂዎች ተዳምረው እንደኛ ሀገር በዕድገት ደረጃ ላይ ባሉ ሀገሮች ላይ ዕድልም ይዘው መጥተዋል፡፡ ፈተናም ጋርጠዋል፡፡
«አዲሱ የኢንዱስትሪ አብዮት ፈተና የሚሆንብን የኢንዱስትሪውን የለውጥ ሂደት እና አቅጣጫ በውል ሳንገነዘብ ለእሱ የሚመጥን የተግባር ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ሳናደርግ ስንቀር ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በአንጻሩ ከተጠቀምንበት ከዚህ ቀደም የነበሩት የኢንዱስትሪ አብዮቶች ከከፈቱት እድል በላይ የግዴታ ከአንድ የኢንዱስትሪ ደረጃ ጠብቀን ወደ ሌላው ረድፍ መሄድ ሳይጠበቅብን ይልቁንም በዘግይቶ ደራሽ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመን ፈጥነን መድረስ የሚያስችለን እድል የሚፈጥርልን ነው ይላሉ።
በተለይም 70 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ሕዝብ ወጣት በመሆኑ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ቱሩፋቶች ድንበር ሳይገደባቸው፤ ርቀት ሳይወስናቸው ከአንድ ዓለም ጫፍ እስከ ሌላው ዓለም ጫፍ ፈጥኖ መድረስ በሚቻልበት ዘመን አራተኛ የኢንዱስትሪ አብዮት ከፈተናዎቹ ይልቅ የመልማትና የማደግ እድል የሚፈጥሩበት አዝማሚያዎች በእጅጉ ልቀው እንደሚታይበት ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ያብራሩት።
በስፔስና የጂኦስፓሻል ዘርፍ እያስመዘገብናቸው ያሉ ውጤቶች አሁን ላይ የልማት ፕሮግራሞች ውጤታማነት ላይ የሚኖራቸው ፋይዳ እንደተጠበቀ ሆኖ የመጪው ጊዜ ተወዳዳሪነታችንን ከማጎልበት አኳያ የሚኖራቸው አብርክቶ ምትክ የለሽ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ሦስት ዓመቱ የተከበረለት የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የመሬት ምልክታ ሳተላይት የ«ETRSS -1›› አይን ገላጭ ሳተላይታችንን ከመሆኗም ባሻገር አስቀድሞ ከታሰበበት በተለይ ተጨማሪ ስድስት ወራት መቆየት መቻሏ ሁላችንን አስድስቷል ሲሉ ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም