ግብርናው አሁንም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሰፊ ድርሻ ይዞ ይገኛል። መንግስትም ለእዚህ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። የምግብ ዋስትናን እንዲሁም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ከግብርናው ዘርፍ የወጪ ንግድ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በመንግስት፣ በግብርናው ዘርፍ አካላት፣ በአርሶ አደሩና በሌሎች የዘርፉ አካላት እየተደረገ ባለው ርብርብ ከዘርፉ የሚገኘውን ምርት ማሳደግ ተችሏል። ግብርናው በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ገቢ ያለው ድርሻም አሁንም ከፍተኛ መሆኑን ቀጥሏል።
እንዲያም ሆኖ ግን የግብርና ምርቶች የአቅርቦትና ፍላጎት ክፍተት ይስተዋላል፤ ይህን ክፍተት ለመሙላት አሁንም ርብርብ እየተካሄደ ይገኛል። በአገሪቱ በመኸርና በበጋ መስኖ እየተካሄደ ያለው የስንዴ ልማትም ከዚሁ አኳያ የሚታይ ነው። ግብርናውን ለማዘመን፣ የተሻሻለ ዝርያ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች መጠቀም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራም ነው።
በተለይ የተሻሻለ ዝርያ ከመጠቀም አኳያ ብዙ ርቀቶች ተሄደዋል። ቴክኖሎጂው በሄክታር የሚገኘውን ምርት በወሳኝ መልኩ መጨመር አስችሏል። አርሶ አደሩም የቴክኖሎጂዎቹን ፋይዳ እየተገነዘበ መምጣቱን ተከትሎ ምርትና ምርታማነቱ የዚያኑ ያህል እያደገ ነው። ይህንንም የዘርፉ ባለሙያዎች እያረጋገጡ ናቸው።
የዘርፉ ባለሙያዎች የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማምጣት የተሻሻለ ምርጥ ዘር መጠቀምን ማበረታታቸውን ቀጥለዋል። የባለሙያዎችን ምክረ ሀሳብ ተቀብለው፣ በመንግሥት ድጋፍና ክትትል የምርትና ምርታማት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂ የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ውጤታማ ስለመሆናቸው የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። የመስክ ጉብኝቶችና የተሞክሮ ልውውጦችም ይህንኑ እያረጋገጡ ናቸው። በዚህም አንዱ አርሶ አደር ከሌላው እንዲማር እየተደረገ ነው።
የተሻሻለ ዝርያ መጠቀም ባህል እያደገ የመጣው ብዙ ፈተናዎች ታልፈው ነው። በቴክኖሎጂው አጠቃቃም ላይ የአመለካከት ልዩነት ሲስተዋል ቆይተዋል። ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም አለመፍጠን ይስተዋላል። የተሻሻለ ዝርያ ከነባሩ ዝርያ ይልቅ ለበሽታ ይጋለጣል የሚል ስጋት ያላቸው አርሶ አደሮች ነበሩ፤ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎችም ከጥቅሙ ይልቅ ክፍተቱን ይዘው የሚሰጡት መረጃ በአርሶ አደሩ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፏል። በጣእም እና በንጥረ ነገር/ኦርጋኒክ መሆን አለመሆን/ላይ ልዩነት ስለመኖሩ ሊናገሩ የሚችሉት አርሶ አደሮች ሳይሆኑ እነዚህ የዘርፉ ባለሙያዎች ናቸውና።
የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ጉምቢቹ ወረዳ ነዋሪውና በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ከበደ ሸዬ፤ የተሻሻለ ዝርያ ለምርታማነት የሚመረጥ እንደሆነ ያምናሉ፤ አጠቃቀሙ ግን ነባር ዝርያን በተሻሻለ ዝርያ በመተካት ወይንም ነባር ዝርያው እንዲጠፋ በማድረግ መሆን የለበትም የሚል አቋም አላቸው።
ስጋቱም አስፈላጊነቱም ተገቢ ነው የሚሉት የግብርናው ዘርፍ ተመራማሪና አማካሪ ዶክተር አምሳሉ አያና አሁን ላይ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ብዛትና ፍላጎት ለማሟላት ምርታማነትን መጨመር የግድ እንደሆነ ነው የገለጹት። የተሻሻለ ዝርያ የተሻለ ምርት እንደሚሰጥም በመግለጽ፤ ነባር ዝርያንም የመጠበቁ ተግባር እየተሰራበት መሆኑን ይናገራሉ።
የነባር ዝርያን አስፈላጊነት አበክረው የተናገሩት አቶ ከበደ በተለይ በአካባቢያቸው እጅግ ተፈላጊ የሆነ ለፓስታ ግብአት የሚሆን ነባር ዝርያ ጥቁር ስንዴ መኖሩን በማስታወስ፣ስንዴው በአንድ በጎፈቃደኛ ግለሰብ አማካኝነት ናሙናው ጣሊያን አገር ተልኮ ለፓስታ አስፈላጊ መሆኑ መረጋገጡን ያስረዳሉ።
አቶ ከበደ መንግሥት ትኩረት እየሰጠ ያለው ለተሻሻለ ዝርያ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ይህ ስንዴ በአሁኑ ጊዜ ዝርያው እየቀነሰ እንደመጣና ጥበቃ ተደርጎለት ዘሩ እንዲስፋፋ ካልተደረገ ጭርሱኑ ሊጠፋ ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ይናገራሉ።
የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ሰብሎችን ለተከታታይ ዓመታት ለማምረት አስቸጋሪ እንደሆነም በመጥቀስ፣ በበሽታ የመጠቃት እድሉ ሰፊ እንደሆነ ነው ያስረዱት። ነባር ዝርያዎች ግን ዘመናትን የመሻገር አቅም እንዳላቸው ተናግረው፣ እርሳቸውም በሶስት የመንግሥት ስርአት ውስጥ ሲያሳልፉ ነባር ዝርያዎች እንዳልጠፉና ዛሬም ድረስ መኖራቸውን ነው የገለጹት። ዝርያዎቹ ገበያ ላይም ተፈላጊ እንደሆኑ ተሞክሮአቸውን አካፍለውናል።
ነባር ዝርያ ለምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋጽኦ አያደርግም የሚለውን ሀሳብ አቶ ከበደ አይቀበሉም። ጉድለቱ ከአርሶ አደሩ አጠቃቀም ላይ መሆኑን በመግለፅም ዝርያውን ማከም ከተቻለም ምርታማ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል ይላሉ። ኋላቀር ነው እየተባለ ነባር ሀብት በምርጥ ዘር ወይንም በተሻሻለ ዝርያ እየተተካ ነው። የሚያዋጣው ነባሩንም የተሻሻለ ዝርያንም ጎን ለጎን ማስኬድ ወይንም መጠቀም ነው ሲሉ ያመለክታሉ።
አቶ ከበደ እርሳቸውን ጨምሮ ለነባር ዝርያ ተቆርቋሪ የሆኑ የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ተነሳሽነት ወስደው ለነባር ዝርያዎች ጥበቃ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውንም ገልጸውልናል። አቶ ከበደ እንደነገሩን ጥቂት አርሶ አደሮች ሆነው በአካባቢያቸው ‹‹ጨፌዶንሳና አካባቢው የነባር ዘር ተንከባካቢ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር›› የሚል ስያሜ ያለው ህጋዊ ማህበር መስርተዋል። የማከማቻ መጋዘን ገንብተው የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች በመሰብሰብ ለዝርያዎቹ ጥበቃ ማድረጋቸውን አጠናከረው ቀጥለዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ይህ ስራቸው በአንዳንዶች ትችት ገጥሞት እንደነበር አርሶ አደሩ ይናገራሉ። ውጤቱን ተመልክተው አስፈላጊነቱን እየተገነዘቡ የማህበሩ አባል ለመሆን ፍላጎት የሚያሳዩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በ72 አርሶ አደሮች የተጀመረው እንቅስቃሴ ከአንድ ሺ በላይ አባላትን በማፍራት ይበልጥ ተጠናክሯል። በአሁኑ ጊዜ አባላትን በማፍራት ችግር የለበትም። ችግሩ ከአባላት የሚሰበሰብ ነባር ዝርያ ማስቀመጫ የሚውል መጋዘን ጥበት ሆኗል።
እነ አቶ ከበደ ዝርያዎችን ጠብቆ ለማቆየት የሚያስፈልጉ አስፈላጊ ነገሮችን ከኢትዮጵያ ብዝሓ ሕይወት ኢንስቲትዩት ግንዛቤ አግኝተው ነው ወደ እንቅስቃሴ የገቡት። ከኢንስቲትዩቱ ጂን ባንክ የተወሰኑ የዝርያ ናሙናዎችንም አግኝተዋል።
ነባር ዝርያዎችን ተደራጅተው ለማባዛት ፍላጎት ያሳዩ በጉምቢቹ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ 12 ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች የማህበሩ አባል ሆነው በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜም ሴት አርሶ አደሮችን ጨምሮ ከአንድ ሺ500 በላይ አርሶ አደሮች የማህበሩ አባል ሆነዋል።
ማህበሩ ከ20 ሚሊየን በላይ ካፒታል አፍርቷል። ማህበሩ ካፒታሉን ለማሳደግ ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች አንዱ፤ አንድ ኩንታል ስንዴ በብድር ሲሰጥ፤ 20 ኪሎ ግራም ወለድ በመሰብሰብ ነው። አዲስ አባል አርሶ አደሮችን በማፍራትና ለአባላቱ ዝርያ በመስጠት እንዲስፋፋ ማድረግ ሌላው የሚጠቀምበት ዘዴ ነው።
አሁን ላይ በአካባቢያቸው ‹‹ማንጉዶ›› የተባለ የተሻሻለ ዝርያ ያለው ለፓስታና ማካሮኒ የሚውል ስንዴ ከነባር ዝርያ የተገኘ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ከበደ፣ በኦሮምኛ ስያሜ የተሰጠው የስንዴ ዘር አንጋፋ መሆኑን የሚያመለክት መሆኑንም አስረድተዋል። አቶ ከበደ መንግሥት ሊያግዛቸው እንደሚገባም ነው መልእክት ያስተላለፉት።
ነባር ዝርያ ላይም ሆነ የተሻሻለ ዝርያ ላይ በአቶ ከበደ የተነሳው ሀሳብ ተገቢነት እንዳለው የገለጹት የዘርፉ ተመራማሪና አማካሪ ዶክተር አምሳሉ አያና፤ በዚህ ወቅት ዓለምም እየተጠቀመበት ያለው በተሻሻለ ዝርያ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥም የህዝብ ብዛት እየጨመረ፣ የምርት ፍላጎትም እያደገ በመሆኑ ይህን ለማጣጣም ምርታማ መሆን ይጠበቃል ሲሉ ይገልጻሉ።
ዶክተር አምሳሉ እንደሚሉት፤ ምርታማ ለመሆን ደግሞ በዝርያ ማሻሻያ ዘዴ ወይንም ሳይንስ በመጠቀም በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ይጠበቃል። የተሻሻለ ዝርያ በአንድ ሄክታር የተሻለ ምርት ስለሚሰጥ ተገቢ ሚና ይጫወታል። በመሆኑም የተሻሻለ ዝርያ መኖሩ የግድ ነው።
አርሶ አደሩ ዘንድ ያለው እውቀትም መጠበቅ አለበት የሚለው አስተሳሰብም ተገቢነት አለው ይላሉ፤ ዶክተር አምሳሉ። በግብርናው ሥራ መሆን ያለበት ይህን ምረጡ፣ ያንን ተው ማለት ሳይሆን፣ ሁለቱን አጣጥሞ መተግበር የሚቻልበትን መንገድ መከተል፤ እንዲሁም የትኛውን ዝርያ በየትኛው ቦታ መጠቀም የሚለውን መለየት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ዶክተር አምሳሉ እንዳሉት፤ በዝርያ ማሻሻያ ወቅት ችግሮች የሚያጋጥሙት አርሶ አደሩን ሳያሳትፉ በማበልጸግ ጥቅም ላይ እንዲውል ሲደረግ ነው። በምርምር ሥራ ወቅት አርሶ አደሩን ማሳተፍ ያስፈልጋል።
በእርሳቸው ተሞክሮ የማሽላ ምርታማነትን ለመጨመር የዝርያ ማሻሻያ ለማድረግ በወሎ እና ሐረርጌ የዝርያ ማሻሻያ ምርምር ባካሄዱበት ወቅት የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ነበር ምርምር ያካሄዱት። በአርሶ አደሩ አሰራር ላይ የተወሰነ ሳይንስ በመጨመር እንጂ ሙሉ ለሙሉ የመቀየር ምርምር አልነበረም የተደረገው።
በዚህም በሁለቱ አካባቢዎች ጥሩ ዝርያ ያለው ምርት የሚሰጥ ማሽላ ማስገኘት ተችሏል። የአካባቢው አርሶ አደር የሚያመርተውን ማሽላ ስንዴ ለምኔ፣ ወተት በጉንጬ የሚል ስያሜ እንዳወጣለትም ገልጸዋል። በትግራይ አካባቢም በአካባቢው ደቆቆ ተብሎ ከሚጠራው ሰብል የሚዘጋጀው ለሽሮ ወጥ የሚውለው ዝርያም እንዲሁ በገበያ ላይ ተመራጭ ሆኗል። ዋጋው ከሌላው የሚጨምር በመሆኑ አርሶ አደሩን በገቢ ተጠቃሚ አድርጎታል። አርሶ አደሩን ያሳተፈ የምርምር ሥራ ውጤታማነቱ የጎላ እንደሆነ እነዚህ ተሞክሮዎች ማሳያዎች ናቸው።
በጤና ላይ ሊከሰት የሚችልን ስጋት ለመከላከልም ኦርጋኒክ የሆኑ ምርቶች እንዲመረቱ በምርምር ሥራው ማድረግ የሚቻልበት እድል መኖሩን የጠቆሙት ዶክተር አምሳሉ፤ የአፈር ለምነትን የሚያሻሽልና ማሳን የሚያዳብር ኮምፖስት በመጠቀምና ሰብልን አፈራርቆ በመዝራት ዘዴ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል። ዶክተር አምሳሉ ላቲን አሜሪካ ያለውን ተሞከሮ አስመልክተው እንደገለጹትም፤ በቆሎ ይዘራል፤ ከበቆሎው አጠገብም በቆሎው ላይ ሊጠመጠም የሚችል የቦለቄ አይነት ዝርያ ያለው አብሮ ይዘራል፤ ዱባ ይተከላል። የዱባው ተክል መሬቱን ይሸፍናል። ጥራጥሬዎች ናይትሮጂን የተባለውን ንጥረ ነገር አፈር ውስጥ የመጨመር ፀባይ ያላቸው በመሆኑ ሶስቱ ሰብሎች የመሬቱን ለምነት ለመጠበቅ ያግዛሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ ከተሻሻለ ዝርያ አቅርቦት ጋር ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ዶክተር አምሳሉ ላቀረብንላቸው ጥይቄ በሰጡት ምላሽ፤ የምርምር ሥራው ነባሩን ዝርያ ያገለለ አይደለም። በመንግሥት በተቋቋመ ተቋም ውስጥ ከመላ አገሪቱ የተሰበሰቡ ዝርያዎች እንዲጠበቁ እየተደረገ ነው። ተመራማሪዎችም ከዚህ ተቋም ዝርያዎችን በመውሰድ ማሻሻያ በማድረግ እንዲለቀቁ ይደረጋሉ። የተወሰኑ ዝርያዎች ከውጭ ሊቀርቡ ይችላሉ። ነገር ግን የጤፍና ቡና ዝርያዎች የኢትዮጵያ ብቻ ናቸው። የተሻሻሉ ዝርያዎች የሚወጡ እንኳን ቢሆን መነሻው ነባር ዝርያ ነው። በአርሶ አደሩ እጅ የሚገኝ ዝርያን ማሻሻል የግድ ነው።
የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው በቀላሉ ለበሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ስለሚነሳው ሀሳብም ዶክተር አምሳሉ ሲያብራሩ ‹‹እንዲህ ያለው ችግር የሚፈጠረው እያሻሻልን በሄድን ቁጥር በዘረመል የመቀራረብ ባህሪያቸው ከፍተኛ እየሆነ ይሄዳል›› ይላሉ። ይህንንም በምሳሌ ሲያብራሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ የስንዴ ዝርያዎች በጣም የተሻሻሉ በመሆናቸው በዘረመል የመመሳሰል ነገር ተፈጥሯል ሲሉ ይገልጻሉ። በዚህም በበሽታ የመጠቃታቸው ሁኔታ እየጨመረ ነው፤ ስለዚህ በሌላ ዝርያ ይተኩ የሚል ሀሳብ እየቀረበ ነው፤ ይህም የማይቀር ነው ይላሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አንዱ በበሽታ ሲጠቃ በሌላ ለመተካት ከበፊተኛው የተሻለና በሽታን መቋቋም የሚችል መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ግብአት ያስፈልጋል። ሌላ ዘረመል የሚገባ በመሆኑ ግብአት ያስፈልጋል። በመስክና በላቦራቶሪ ውስጥ የተጠበቀ ዝርያን በማዳቀል ዘዴ ነው የሚከናወነው። በማዳቀል ዘዴ ድርቅ መቋቋም መቻሉና ጥሩ የምግብ ጣዕም ያለው መሆኑ ይፈተሻል። የእጽዋት ማበልጸጊያ ቦታ በማስፋፋት ጭምር ነው ምርምሩ እንደሚከናወን አስረድተዋል።
እንደ ዶክተር አምሳሉ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ታዳጊ ተብለው ከሚጠሩ አገሮች መካከል በግብርና ምርምር ጥሩ ፕሮግራም ካላቸው ውስጥ አንዷ ሆና ትጠቀሳለች። በፌዴራልና በክልሎች ደረጃ የምርምር ተቋማት ተቋቁመው እየሰሩ ናቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎችም በምርምር ያግዛሉ። ይህ አስፈላጊና መልካም ተሞክሮ ነው።
የኢትዮጵያ የብዝሃ ሀብት ኢንስቲትዩት፣ የፌዴራልና የክልል የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ተጣምረው በመናበብ የበለጠ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ያስገነዝባሉ። ይህም አርሶ አደሩን ያሳተፈ የዝርያ ማሻሻል ስራ ለመሥራት ይረዳል። ከአርሶ አደሩ ጋር የተሰራው የዝርያ ማሻሻያም ተመዝግቦ መያዝ ይኖርበታል። በዚህ መልኩ ተመርቶና ገበያ ላይ ውሎ ተመጋቢው ዘንድ እስኪደርስ ያለው ሂደት መቀጠል ይኖርበታል። የእሴት ሰንሰለቱ ተጠናክሮ ከቀጠለ ምርት ተቀብሎ የተለያየ እሴት በመጨመር ለተጠቃሚው ለሚያቀርበው የሥራ እድል ይፈጥራል። በግብርናው ዘርፍ አገራዊ ኢኮኖሚን ማሳደግ የሚቻለው በዚህ መንገድ መንቀሳቀስ ሲቻል ነው። በአጠቃላይ ከዝርያ ጋር በተያያዘ የተጠናከረ ሥራ ይጠበቃል ሲሉ ዶክተር አምሳሉ ሀሳብ ሰጥተዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2015