በተማርኩበት አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ በአንድ ወቅት ይህን ተመለከትኩ። ቁጥራቸው የበዙ ተማሪዎች የጋራ መመገቢያ አዳራሽ ውስጥ በመመገብ ላይ ናቸው። ተመግበው ከጨረሱ በኋላም የተመገቡበትን ሰሀን ወደ ቦታው መመለስ የመመገቢያ አዳራሹ ሕግ ሲሆን እነርሱም ይህን ያውቁታል፤ ያደርጉታልም። በዚህ ውስጥ ግን ለዛሬው ትዝብቴ የመነሻ ሀሳብ የሆነኝን ነገር ተመለከትኩ። አንድ ማየት የተሳነው ተማሪ የተመገበበትን ሰሀን ይዞ ሲነሳ ከመሄዱ በፊት የተቀመጠበትን ወንበር እንደነበረው አድርጎ ለመመለስ በእጁ እየዳሰሰ ወደ ምግብ ጠረጴዛው ሲያስጠጋ ተመለከትኩ።
በአንፃሩ ደግሞ ሌሎች ተማሪዎች ወደ ነበረበት ቦታ ከመመለስ ይልቅ የአዳራሹን መተላለፊያ በሚዘጋ መልኩ አዘበራርቀውት ሲወጡ አስተዋልኩኝ። ስንቶቻችን እንሆን የምናደርገውን ነገር በሌሎች ለመመስገንና ዕይታ ውስጥ ለመግባት ብለን ሳይሆን መደረግ ስላለበት፣ ኃላፊነታችን ስለሆነና አምነንበት የምናደርገው? ምንም እንኳን በምንሰራበት ቦታ፣ በምንኖርበት አካባቢ፣ በቤታችን ውስጥ፣ ብሎም በሀገር ደረጃ ትክክል ወይም ስህተት፤ መደረግ ያለበትና መደረግ የሌለበት ተብለው የተቀመጡ ሕጎች ቢኖሩም ሰዎች ግን በአብዛኛው ከኃላፊነታቸው ይልቅ ለመብታቸው ብቻ ትኩረት ይሰጣሉ።
ብዙዎች የመስሪያ ቤታቸውን ወይም የቢሯቸውን ህግ የሚያከብሩት ቢጥሱት ስለሚቀጡበት እንጂ ስለሚያምኑበት አይደለም። ለአብነት በአንድ የትራ ፊክ መብራት በሚገኝበት ቦታ ላይ አንድ ሹፌር የትራፊክ ፖሊስ በቦታው አለመኖሩን ተከትሎ የቀይ መብራቱን ጥሶ ሊያልፍ ይችላል፣ በርግጥም በተለያዩ ቦታዎች የሰዓቱን መምሸት ተከትሎ ይህን የሚያደርጉ ሰዎች አሉ ፣ በአንፃሩ ደግሞ በመንገዱ ላይ የትራፊክ ፖሊስ ተመልክቶ ቢቆም አልያም የትራፊክ ፖሊስ በሚመለከትበት ወቅት ፍጥነቱን ለመቆጣጠር ሲሞክር ይታያል።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሕፃናት በሚገኙበት የመኖሪያ አካባቢ እንኳን እግረኛን በሚያሸማቅቅ መልኩ ሲያሽከረክሩ እንመለከታለን። የፍጥነት ወሰንን ጠብቆ ማሽከርከር ያለውን ጠቀሜታ አንድ ለአቅመ ማሽከርከር የደረሰ ሰው አያውቅም ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ነገሩ ወዲህ ነው፤ ጉዳዩ ከሕጉ ሳይሆን ከአስፈፃሚው ነበር። አሽከርካሪው ያከበረው ሕጉን ሳይሆን ህግ አስከባሪውን። ብዙውን ጊዜ በሕብረተሰባችን ውስጥ የሚስተዋለውም ይኸው ነው። የምንፈራው ህግን ሳይሆን ቅጣትን ነው። የምናከብረውም ህጉን ሳይሆን አስፈፃሚውን ነው። ይህ ደግሞ በተለያየ ጊዜ ለሚደነገጉ ሕጎች ያለንን የተሳሳተ ግንዛቤ ያመላክታል።
የተለያዩ የሕግ ዓይነቶች አሉ። አንደኛው ዓይነት ሕግ በወረቀት ላይ ተጽፎ የሚገኝ ሲሆን ሁሉም ሰራተኛ ወይም ተገልጋይ የሚያውቀው ነው። ምናልባትም አንድ ተቋሙ ሲቋቋም እንደመተዳደሪያ ደንብ ሆኖ የሚያገለግል ሊሆን ይችላል።
አንዳንዶቹ ሕጎች ደግሞ ከአስፈፃሚዎች ዘንድ የሚወጡ ትንንሽ ነገር ግን ትልቅ ትርጉም እየተሰጣቸው የሚተገበሩት መመሪያዎች ናቸው። እናም እንዲህ ዓይነቶቹ ሕጎች ሠራተኛ የሚያከብራቸውና የአንድ ተቋም የሥራ ኃላፊ የሚደነግጋቸው ሕጎች ወይንም በተለምዶ አገላለፅ “አሠራሮች” ሲሆኑ በብዙዎቹ ዘንድ የመከበር ዕድላቸው የሰፋ ነው። ምክንያቱም አንዳንዶች የሥራቸው ቀጣይነት በሥራ ኃላፊያቸው መልካም ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ስለሚመስላቸው ነው።
ይሁን እንጂ ሁሉም ዓይነት ሕጎች በስፋት ሲጣሱ ይስተዋላል። አንድ ሰው ሕግ ለመጣስ የተለያየ ምክንያት ሊኖረው ይችላል። ሕጉን አለማወቅ፣ ቸልተኝነት አልያም ደግሞ ማንአለብኝነት ሊሆን ይችላል። አንዳንዶቹ ሕጎች ደግሞ ሰዎች ከሕግ አስፈጻሚዎች ጋር በመላመዳቸውና በመዛመዳቸው የተነሳ የሚጥሱ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች ቅርበታቸውና ዕምነታቸው በህጉ ሳይሆን በአስፈፃሚው ላይ እየሆነ በመምጣቱ ነው።
በተለያየ መንገድ ለሚከሰቱ የሕግ ጥሰቶች ሌላው እንደምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችለው ከሕብረተሰቡ የግል ሕይወት ወይንም ከቤተሰብ አስተዳደር የሚጀምር ነው። አንድ የቤተሰብ መሪ ኃላፊነቱን በሚገባ ካልተወጣ በተቋም ወይንም በሀገር ደረጃ ኃላፊነት ቢሰጠውም ያው ነው። ምክንያቱም ልጆች እያንዳንዱን ነገር ከወላጆቻቸው አልያም በቅርባቸው ካለ ሰው እንደሚማሩት ወላጆች ለልጆቻቸው ምሳሌ መሆን ይገባቸዋል። አለበለዚያ አንድ የሚያጨስ አባት ልጁን እንዴት ስለሱስ መጥፎነት ሊነግረው ይችላል? የማያነብ መምህርስ ተማሪዎቹን ምን ብሎ ስለንባብ ጥቅም ሊያስረዳቸው ይቻላል?
በመሆኑም ዛሬ ላይ በየቦታው የምንመ ለከታቸው የሕግ ጥሰቶች ወይንም በየጊዜው እየተስፋፉ የመጡት የሕገ-ወጥነት ተግባሮች ከትንንሽ እንቢተኝነት የሚመነጩ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ መዘዙ በአንድ ተቋም ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ህግን አለማክበር ለብዙዎች ራሳቸውን ብቻ የሚጎዳ መስሎ ይታያቸዋል። ነገር ግን በምን አገባኝ አስተሳሰብ የምናደርጋት እያንዳንዷ ድርጊት ትልቅ ችግር እንደምትፈጥር ማሰብ ተገቢ ነው። ኃላፊነት መውሰድን መለማመድም ልናዳብረው የሚገባ ባህል ነው።
ከዚህ አኳያ በተለያየ መንገድና አጋጣሚም ሰዎች እንዲህ ሲሉ ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል “መብቴ ነው”። ይች ብዙዎች ማግኘት የሚፈልጉትን አገልግሎት ሳያገኙ ሲቀሩ የሚጠቀሟት ቃል ነች። ብዙዎች ስለመብታቸው እንጂ ስለ ግዴታቸው ብዙም ትኩረት ሲሰጡ አይታይም። ይሁን እንጂ ይህ ሊታረም የሚገባው የተሳሳተ አመለካከት ነው።
ምክንያቱም መብት ሊከበር የሚችለው ግዴታን መወጣት ሲቻል ብቻ ነው። ከሌሎች የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት የሚቻለው ቅድሚያ የራስን ኃላፊነት መወጣት ሲቻል ነው። እናም እንዲህ ዓይነቱ ኃላፊነትን ሳይወጡ መብትን ብቻ የመጠየቅ እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ለራስም ለሌላውም በአጠቃላይ በግልም በሕብረተሰብም፣ በሕዝብና በሀገር ደረጃም ፋይዳ የሌለው ይልቁንም ጉዳቱና ጥፋቱ የሚያመዝን ነውና ሊታረምና ሊስተካከል ይገባዋል እንላለን።
ሰሚራ በርሄ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015