እማ! አልኳት ወዳለችበት ራመድ ብዬ። እማ ነው የምላት..ተሳስቼ በስሟ ጠርቻት አላውቅም። እንዲህ እንደ አሁኑ እንድታስቸግረኝ ፊቷ ቆሜ አውቃለሁ።
‹ወዬ ጌታዬ! አለችኝ..ፊቷን በትንሽ ፈገግታ ሞልታ። በእሷ አፍ ጌታዬ ስባል ነፍሴ በደስታ በልቤ ውስጥ ትሟሟለች። እያየኋት ተጠጋኋት ጠዋት ስለሆነ ፊቷ ላይ የማያልቅ ውበት አለ..እኔ ብቻ የማየው፣ ለእኔ ብቻ የተሰጠ።
አጠገቧ ደርሼ ቆምኩ..እጄን ወደ ጉንጩዋ ልኬ ዳሰስኩት። በጉንጮቿ መጫወት እወዳለሁ..አጠገቤ ስትሆን ሁሌ በጉንጩዋ ነው የምጫወተው። እጆቿን ወደለበስኩት ሸሚዝና ኮት ልካ ታስተካክልልኝ ጀመር።
‹ስመጣ ምን ላምጣልሽ? አልኳት በናፈቀ ቃና ድምጼን ዝግ አድርጌ። ዓለም ላይ የማይቻል ነገር እንድትጠይቀኝ በመመኘት። ሰሞኑን ወደ ፓሪስ እበራለሁ..ከሀሳቦቼ ሁሉ ትልቁ ከጉዞዬ መልስ እሷን ማስደሰት ነው።
‹አንተ ብቻ ናልኝ..› አለችኝ አይኗን አይኔ ላይ እጆቿን ኮትና ሸሚዜ ላይ ጥላ። ብዙ ጊዜ እንድታዘኝ፣ እንድታስቸግረኝ ፊቷ ቆሜ አውቃለሁ። ብዙ ጊዜ እንድታንገላታኝ ራሴን አዘገጅቼላት አውቃለሁ ግን ለኔ ስትለፋ ነው የማገኛት። ሁሌ ሳይገባኝ እንዳገኘኋት ሳይገባኝ የኔ እንደሆነች ነው የሚሰማኝ።
ነፍሷ ትሁት ናት..በኔ መኖር የምትኖር እንዲህም ናት፡ ምንም ነገር ልጠይቃት እሺ ነው የምትለኝ። ከአፏ እንቢ የሚል ቃል ሰምቼ አላውቅም። ብዙ ጊዜ ይሄን እሺ አትለኝም ብዬ ሰግቼ ስጠይቃት እሺ ትለኛለች። ነፍሷ ነውር የላትም..ሴትነቷን አንድ ሳታስቀር ተቸግሮላት ለማያውቅ አንድ ወንድ ሰጥታለች። እኔ እኮ አልመጥናትም..እንዴት እጄ እንደገባች እሱ ይወቀው። መጀመሪያ ቀን ሳያት ከዛም እንዳናግራት የገፋፋኝ አምላክ እሷን ሰጥቶኝ ዳግም ላይዋሃደኝ ጥሎኝ የሄደ ይመስለኛል። በእሷ ሁሉን እንዳገኝ አድርጎ።
ብዙ ናት..አንሳና ጎድላ አይቻት አላውቅም። ልደርስባት ስሮጥ በእጥፍ በልጣኝ አገኛታለሁ። የነፍሷን ቦታ አልደረስኩበት። ሰው በዛ ልክ ለሌሎች ሲኖር፣ ለሌሎች ሲቆም እሷን ነው ያየሁት። እንደ ሚስትና እንደ እናት ናት..እንደ ጓደኛና እንደ እህትም።
‹እማ የሆነ ነገር ላስቸግርሽ ነበር?
‹እሺ..
‹ቀዩን ቀሚስሽን ስላልወደድኩት ቢጫውን አድርጊ›
‹እሺ..
‹ብር ጨርሻለው የሆነ ገንዘብ አስገቢልኝ..
‹እሺ..
‹ዛሬ ደክሞኛል የራት ቀጠሯችንን ሰርዤዋለሁ..
‹እሺ..
እንዲህ ናት..በእሺ ተሞልታ በእሺ የምትፈስ..የጽድቅ ውቅያኖስ። ለእኔ የሚሆን ብዙ የመቸገር ጊዜ አላት። የሆነችልኝ መሆን ከሆንኩላት መሆን ጋር ባህርና ኩሬ ነው።
ማታ በእቅፏ እሞቃለሁ..በሴትነቷ ረካለሁ..ነፍሴ መቼም የማትደግመው በረከቷ ከእሷ ሴትነት ውስጥ ነው። እንደ እሷ መሆን እፈልጋለሁ፣ እንደ እሷ መታዘዝ ያምረኛል። ልታዘዛት ፊቷ ስቆም ልትታዘዘኝ ፊቴ ስትቆም አገኛታለሁ።
መቼ ይሆን የምታስቸግረኝ እላለሁ። መቼ ይሆን የማይቻል ነገር አድርግልኝ ብላ የምታስቸግረኝ እላለሁ። ለእሷ ለመቸገር ሁልጊዜም እንደተዘጋጀሁ ነው ግን አስቸግራኝ አታውቅም። ብዙ ጊዜ እንድታስቸግረኝ፣ የማይቻለውን አድርግልኝ እንድትለኝ ፊቷ በይሁንታ ቆሜ አውቃለሁ። ግን አታስቸግረኝም..ደስታዋ ለእኔ በመቸገር ውስጥ ነው። ደስታዋ ለእኔ በመልፋት ውስጥ ነው። ደስታዋ ለእኔ ሚስት ሆኖ በመቆም ውስጥ ነው።
እግዜር እኔ እንዳመሰገንኩት በወንድ አፍ ተመስግኖ የሚያውቅ አይመስለኝም። ባየኋት ቁጥር ወደ ሰማይ አንጋጥጣለሁ። እጆቼን ዘርግቼ፣ አይኖቼን አቅንቼ፣ በጽሞናና በእንጉርጉሮ፣ በለሆሳስና በሽኩሽኩታ ጌታዬን ተመስጌን ብዬው አውቃለሁ። ማመስገኛዬ ናት..አሜን ማያዬ። በእሷ ብዙ ሳቅን ስቄአለሁ..
ትላንት ማታ አንድ ነገር እያሰብኩ ነበር እንቅልፍ የወሰደኝ። ጠዋት..በጣም ጠዋት እሷን የሰጠኝን ጌታ እያመሰገንኩ ሳትቀድመኝ ልቀድማት ከእንቅልፌ ነቅቼ ወደ ማዕድ ቤት ገባሁ..የመጀመሪያውን ቁርስ ሰርቼ ላበላት። ግን እንዳሰብኩት የሆነ ምንም የለኝም..ከእኔም በፊት፣ ከሰራተኛችንም በፊት ነቅታ ቁርስ ስትሰራልኝ አገኘኋት። ማድረግ የምችለው ሁለት ነገር ነበር ከኋላ ሄጄ እቅፍ አደረኳት።
አልቀድማትም..ደርሼባት አላውቅም ሁሌ ከኋላዋ ነኝ።
አንድ ቀን ፊቷ ቆምኩ..ፊቷ ቆሜ ጉንጮቿን አለመንካት አልችልምና ነካኋት። እሷም እኔን ብቻ በምታይበት የፍቅር አይን እያየችኝ ‹ምነው ጌታዬ? አለችኝ።
ፍቅሯ ማብቂያ የለውም ጌታዬም ትለኛለች። እሷ ፊት ሁልጊዜም አዲስ ነኝ። በሴትነቷ ሕይወቴን አጣፈጠችልኝ..። እንዲህ እንደ አሁኑ በአዲስነት ፊቷ ስቆም ‹ሴት የሕይወት ጨው ናት..በወንድነት ውስጥ ጠብ ተደርጋ የምትጥም፡› እላለሁ..በውስጤ።
‹እማ! አልኳት
‹ወዬ ጌታዬ! አለችኝ
‹ዛሬ አንቺን የማገለግልበት ቀን እንዲሆን እፈልጋለሁ..› አልኳት።
‹እሺ..› አለችኝ።
‹ከምን ልጀምር? አልኳት..ውስጤ ከምን እንደም ትጀምር ሳታውቅ ነው ላገልግልሽ ያልከው? አለኝ።
‹እቀፈኝ› አለችኝ።
አቀፍኳት..
‹ሌላስ? አልኩኝ
‹እቀፈኝ› ስትል ደገመችልኝ።
ግራ ተጋባሁ ..አቅፌያት እቀፈኝ ማለቷ
ሁለት እጆቼን ጀርባዋ ላይ አነባብሬ ወደ ደረቴ ለጠፍኳት። ደረቴን ሰርስራ ወደ ነፍሴ እንድትገባ..
‹ሌላስ? አልኩ..ምን ትለኝ ይሆን እያልኩ።
‹ሳመኝ፣ እንደምታፈቅረኝ ንገረኝ› አለችኝ።
የተባልኩትን አደረኩ…ነፍሷ ደረቴ ላይ ስትቀልጥ ታወቀኝ። በወንድነቴ ሄርታሌ ላይ ሴትነቷ ሲቀልጠ ተሰማኝ። አስራ ሁለት አመት በትዳር ስንቆይ እንደዛሬ አስደስቻት የማውቅ አይመስለኝም። ሁሌ የምስማት አልጋ ላይ ስንወጣ ነው። የሆነ ነገር ተጋባብኝ..የሞቀ ነፍስ፣ የሞቀ ሴትነት ወደ ወንድነቴ ሰረገ።
‹ሚስትህ ምን እንደሚያስደስታት ካወክና ያን ነገር ካደረክላት አገልግለሀታል ማለት ነው› አለችኝ።
ዝምታ ሰፈረብኝ..እስከ ዛሬ ምኗም ሳልሆን እንደኖርኩ ታሰበኝ።
‹ሴት ልጅ ከታቀፈችና ከተሳመች እንደምትፈቀርም ከተነገራት በቂዋ ነው። አንዳንድ ወንዶች ይሄን አያውቁም። የሴትን ነፍስ ለማስደሰት ብዙ ይለፋሉ። ብዙ ሳይለፉ በትንሽ ነገር እንደሚባርኩን የሚያውቁ ጥቂት ወንዶች ናቸው።
እስከዛሬ ባስቸገረችኝ፣ የማይቻል ነገር በጠየቀችኝ ስል ማሰቤ ተራ ሆኖ ታየኝ። በተለይ እሷ እያገለገለችኝ ያለው በትንሽና በምንም በማይተካ ነገር እንደሆነ ሳውቅ እሷን ለማስደሰት ተራራ ለመውጣት ማሰቤ ስህተት እንደሆነ ተገለጠልኝ። ተበለጥኩ..በለጠችኝ..
ደረቴ ላይ ሆና ቆየች..የምትፈልገው ደስታ፣ ያልሰጠኋት እውነት ያ እንደሆነ ገባኝ። ጀርባዋ ላይ የተጠመጠመ አንድ እጄን አንስቼ ወደ አናቷ ሰደድኩት..ወደ ጸጉሯ ስር ገብቼ ዳበስኳት። ደረቴ ላይ ያንቀላፋች እስኪመስለኝ ድረስ ትንፋሽዋን ውጣ ጸጥ አለች። አረካኋት..። በደስታ ነፍሷን ገደልኳት። ወዲያው ትኩስ ትንፋሽ ደረቴን ይፈጀኝ ገባ..ነፍስ ዘራች ስል አሰብኩ። ከእንግዲህ ተራራ ሳልወጣ እያቀፍኩና እየሳምኩ፣ እየዳበስኩና ፍቅሬን እየነገርኩ ሚስቴ ላደርጋት ለራሴ ቃል ገባሁ።
ከደረቴ ላይ ቀና ብላ አስተዋለችኝ። ቀይ ፊቷ አቅላልቷል። ያላባራ..ያልበረደ የደስታ እንፋሎት ይንቀለቀልበታል። ዝግ ብላ እንዲህ አለችኝ ‹ይሄኛውን አንተን ነው የምፈልገው..
እንደዛሬ ተዐምር ሰምቼ የማውቅ አይመስለኝም። ተጣድፌ..ተንደርድሬ ‹እሺ› አልኳት..። ተጋባችብኝ..እንደ እሷ መሆንና ማሰብ ጀመርኩ።
‹መታዘዝ ንጉስ ያደርጋል› ስትል ለሌላ የፍቅር ጨዋታ ወደ መኝታ ክፍላችን አመራን።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2015