ሰው ለታላቅ ዓላማና ተልዕኮ የተፈጠረ ፍጡር ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰው ይህን ታላቅ ዓላማና ተልዕኮ አውቆና ተረድቶ ዓላማውን በተግባር ይተረጉመዋል ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም የሰው ልጅ ለታላቅ ዓላማና ተልዕኮ መፈጠሩን ያወቁና ዓላማውን በተግባር የኖሩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የኖሩ/የሚኖሩ ሰዎች የሰው ልጅ ለታላቅ ዓላማና ተልዕኮ መፈጠሩ ከተገለጠላቸው ሰዎች መካከል ይመደባሉ፡፡ በአገራችንም እንዲህ ዓይነት ሰዎች አሉ።
የ‹‹አቤኔዘር ሰፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን›› (Ebenezer Supporting and Development Association – ESDA) መስራችና ስራ አስኪያጅ እንዲሁም የግሎባል ፒስ ባንክ ሃሳብ አፍላቂና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አርጋው አየለ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ከሚኖሩ፣ ከራሳቸው ደስታና ስኬት ይልቅ ለሌሎች ሕይወት መቃናት ከሚተጉ ሰዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው።
አቶ አርጋው የተወለዱት በ1965 ዓ.ም በሲዳማ ክልል ነው፡፡ በ1989 ዓ.ም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ እንግሊዝ ለመሰደድ አስበው ዩክሬን ደረሱ። ዩክሬን ከደረሱ በኋላ ነገሮች እንዳሰቡት ሁሉ ቀላል አልሆኑላቸውም፡፡ ካሰቡበት ለመድረስ እጅግ በጣም ፈታኝ በሆነና ‹‹በምድር ላይ መራራ ሕይወትን የቀመስኩበት አጋጣሚ፣ አገሬ ውስጥ ብሞት ይሻለኝ ነበር ብዬ የተፀፀትኩበት›› ብለው በሚገልፁት ጉዞ ወደ ሀንጋሪ ሄዱ፡፡
ሀንጋሪ ደርሰው የስደተኞች ማቆያ ውስጥ ገቡ፡፡ በስደተኞች ማቆያ ጣቢያው ውስጥ የነበሩት የተለያዩ አገራት ዜጎች መራራ የሕይወት ውጣ ውረዶችን ያሳለፉ ነበሩ፡፡ በጣቢያው ውስጥ ለስደተኞች ልዩ ልዩ ድጋፎችን የሚያደርጉ ባለሙያዎች የነበሩ ሲሆን፣ አቶ አርጋው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ወጣት አሜሪካዊ ጋር መልካም ግንኙነት ፈጠሩ፤ ለትምህርቱም ልዩ ፍላጎትና ፍቅር አደረባቸው፡፡ ‹‹እንግሊዝኛ ቋንቋ በደንብ ለማወቅ ብዬ የጀመርኩት ትምህርት ወደ ውስጤ ሰርፆ ውስጤ እየተቀየረ መጣ፤ ከዚህ በኋላ በሕይወቴ ማድረግ ያለብኝ ምንድን ነው ብዬ ማሰብ ጀመርኩ›› በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ፡፡
በስደተኞች ጣቢያው የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ረዳቶቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ነግረዋቸው ባደረጉላቸው ድጋፍ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኮሌጅ ገብተው ተማሩ፡፡ መማራቸው በሕይወት ስለመኖር ምንነትና ትርጉም እንዲያውቁ አስቻላቸው፡፡
አቶ አርጋው በሕይወት የመኖርን ትርጉም ተገንዝበው ከሦስት ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ ተምረው ወደ አገራቸው የተመለሱበትን አጋጣሚ ሲገልጹት ‹‹ወደ አዕምሮዬም፣ ወደ አገሬም ተመለስኩ›› ይላሉ፡፡ በትምህርት ላይ ሳሉ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተው የነበረ ቢሆንም በዚያው መቅረት ግን አልፈለጉም፡፡ በኢትዮጵያ ችግረኞችን ሲመለከቱ የበለጠ ማዘን ጀመሩ፡፡ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት እንዳለባቸው ቢያምኑም በወቅቱ ግን ያን ለማድረግ የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። ሃሳባቸው ሁሉ የተቸገሩ ወገኖችን ስለመርዳት ሆኗልና የተቸገሩትን የሚረዳውን አበበች ጎበና የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከልን ጎበኙ፡፡
‹‹አበበች ጎበና የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከልን ስጎበኝ፣ ከዚህ በኋላ እኔም እንዲህ ዓይነት ስራ መስራት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ›› የሚሉት አቶ አርጋው፣ ይህን ሃሳባቸውን ይዘው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኮሌጅ ተመልሰው ሄዱ፡፡ የአሁኑ ጉዟቸው ግን ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሌላም መልካም ስጦታ ይዞ ጠበቃቸው። በኮሌጁ ከወደፊት የትዳር አጋራቸው ጋር ተዋወቁ፤ ትውውቃቸው ወደ ፍቅር አምርቶ በስድስተኛ ወራቸው፣ በ1997 ዓ.ም፣ ጋብቻቸውን ፈፀሙ፡፡ አሜሪካዊቷ የአቶ አርጋው ባለቤት ወይዘሮ ራሄል አየለ፣ ከ15 ዓመታቸው ጀምረው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የበጎ አድራጎት ስራዎችን መስራት ይፈልጉ ነበር፡፡
አቶ አርጋው ከባለቤታቸው ጋር ወደ አሜሪካ ሄዱ። ከአራት ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። አቶ አርጋው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው ሳይቀር ነቀፌታ ገጠመው፡፡ ‹‹እኛን መርዳት ሲገባህ እንዴት ተመልሰህ ትመጣለህ?›› የሚሉ ወቀሳዎች በረቱባቸው፡፡ ቀሪውን ዘመናቸውን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ላይ ለማሳለፍ የወሰኑት አቶ አርጋው ግን ወቀሳዎቹን ተቋቁመው ዓላማቸውን ለማሳካት ደፋ ቀና ማለታቸውን ቀጠሉ፡፡ ‹‹አቤኔዘር ሰፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን›› የተሰኘውን የበጎ አድራጎት ድርጅት በሐዋሳ ከተማ በማቋቋም የሕይወት ጥሪያቸውን ለማሳካት ፈታኙን ጉዞ ጀመሩት።
በ2000 ዓ.ም ከስምንት እስከ 17 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የነበሩ 17 የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናትን ሰብስበው በመውሰድ ቤት ተከራይተው ማኖር ጀመሩ፡፡ በ‹‹ቤተሰባዊነት›› መርህ የሚያምኑት አቶ አርጋው፣ ህፃናቱን የሚያኖሯቸው ከራሳቸውና ባለቤታቸው ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ ህፃናቱ ሱስን ጨምሮ በሌሎች አስቸጋሪ የሕይወት ገጠመኞች ውስጥ ያለፉ ስለነበሩ ሁኔታው ለእነ አቶ አርጋው እጅግ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ‹‹ህፃናቱ የኅብረተሰቡ እንክብካቤና ፍቅር የራቃቸው ስለነበሩ ከገንዘብና ከቁስ ይልቅ ለእነርሱ የበለጠ ትርጉምና ዋጋ ያለው እንክብካቤው ነው፡፡ ትምህርት ቤት ብናስገባቸውም ከትምህርት ቤት ወጥተው ሄዱ፤ እንዲነግዱ ገንዘብ ብንሰጣቸውም ያንንም ጥለው ሄዱ፡፡ ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ አዕምሯቸው ስለተጎዳ ምንም ትልቅ ነገር ብታደርግላቸው የሚተረጉሙት በተቃራኒው ነው፡፡ በመጨረሻም አንዳንድ እቃዎቻችንን ሰርቀው፣ እኛ ሳናባርራቸው ራሳቸው ጠፍተው ሄዱ›› በማለት የገጠማቸውን ፈተና ያስረዳሉ፡፡
ይህ ሁኔታ ለእነ አቶ አርጋው ትምህርት ሰጣቸው። ስለሆነም ወደ ጎዳና ያልወጡ ችግረኛ ህፃናትን ለማሳደግ ወሰኑ፡፡ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረ ወዳጃቸው ደቡብ ኦሞ አካባቢ ‹‹ሚንጊ›› ተብለው በማኅበረሰቡ የተፈረጁ ህፃናትን እንዲታደጉ ሃሳብ አቀረበላቸው፡፡ አቶ አርጋውም በፍጥነት ወደ ደቡብ ኦሞ በመሄድ ከአካባቢው የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ህፃናቱን መታደግ እንደሚችሉ ተነግሯቸው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ወደ ሐዋሳ በተመለሱበት ወቅት አሳዛኙና አስደንጋጩ ነገር ተከሰተ፡፡ ‹‹ሚንጊ›› ተብለው የተፈረጁት ህፃናት የባህል ሰለባ ሆነው ሕይወታቸው እንዲያልፍ ተደረገ፡፡
‹‹የሆነውን ስሰማ ወሽመጤ ተቆረጠ፤ ባለቤቴ ደግሞ ህፃናቱን የመታደግ ጥረታችን እንዲሳካ ጉጉት ስለነበራት በየደቂቃው እየደወለች ትጠይቀኝ ነበር›› በማለት የሚያስታውሱት አቶ አርጋው፣ ከፍተኛ በሆነ ንዴት ውስጥ ሆነው በየደረጃው ወዳሉ የአስተዳደር ኃላፊዎች ቢያመሩም ‹‹ሚንጊ የተባለውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አጥፍተናል›› ብለው እስከ ፌደራል መንግሥት ድረስ የውሸት ሪፖርት ያቀረቡት የስራ ኃላፊዎች ‹‹ለምን እንደዚህ ተደረገ?›› ለሚለው የአቶ አርጋው ጥያቄ ጆሮ አልነበራቸውም፡፡ ይባስ ብለውም አቶ አርጋውን ለማሳሰር ፖሊስ መደቡባቸው፡፡ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ‹‹አትሰሩት፣ ግን አታሰሩት›› የሚል ትዕዛዝ ስለሰጡ ለጊዜው ሳይታሰሩ ቀሩ፡፡
አቶ አርጋውና ባለቤታቸው ግን ጥረታቸውን አላቆሙም፡፡ ሌሎች በ‹‹ሚንጊ››ነት የተፈረጁ፣ ከባድ የጤና ችግር ያለባቸውን፣ ረዳት የሌላቸውንና የተጣሉ ህፃናትን እየሰበሰቡ ማሳደግ ጀመሩ፡፡ ይህ በፈተና የተሞላው ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች (ከ45 በላይ ብሄሮች) የተሰባሰቡ 130 ህፃናትን እያሳደገ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል አስሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለመሆን በቅተዋል፡፡ 120ዎቹ ደግሞ ከመዋዕለ ህፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ናቸው። በ‹‹አቤኔዘር ሰፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን›› አድጋና ተምራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን የቻለች ወጣትም አለች፡፡ በማዕከሉ ከሚያድጉ ህፃናት በተጨማሪ ማዕከሉ ድጋፍ የሚያደርግላቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም አሉ።
‹‹አቤኔዘር ሰፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን›› ህፃናትን ከማሳደግ ባሻገር ሌሎች ግብረ ሰናይ ተግባራትንም ያከናውናል፡፡ ለአብነት ያህል በጌዴኦ እና በሐዋሳ ከተማ የሰላም መደፍረስ ችግር ባጋጠመበት እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ወቅት ያደረጋቸው ድጋፎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በውጭ ከሚገኙ በጎ አድራጊዎች በሚገኝ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ድርጅቱ፣ በተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ላይም ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል፤ ለአምስት ዓመታት ከ31ሺ 700 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ምገባ አድርጓል፡፡ ድርጅቱ በክልሉ ግምገማ ከተደረገባቸው መሰል ተቋማት መካከል የተሻለ አፈፃፀም ያለው እንደሆነም ተመስክሮለታል።
አቶ አርጋው በስራቸው ስላሳኩት ነገር ሲናገሩ ‹‹በሕይወት ሊኖሩ ለማይችሉና እንዲገደሉ ለተፈረደባቸው ብዙ ህፃናት ሕይወት ሰጥተናል። መፀዳጃ ቤት ውስጥ የተጣሉና ተቀብረው የነበሩ ህፃናትን አውጥተን አሳድገናል፡፡ ይህ በጣም ያስደስተናል›› ይላሉ።
አቶ አርጋው የበጎ አድራጎት ስራቸውን መለስ ብለው ሲገመግሙት ህፃናቱን ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረጋቸውና የሁሉም ችግሮች መነሻ የሰላም እጦት እንደሆነ ተረዱ፡፡ የሰላም እጦቱ ደግሞ በግለሰብ፣ በማኅበረሰብና በአገር ደረጃ የሚገለፅ ይሆናል፡፡ ‹‹እኛ ስራ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ የችግረኞች ቁጥር ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አላስተዋልንም፡፡ ገንዘብ ማጣት ሁሉም ሰው ዘንድ የሚገኝ ችግር ላይሆን ይችላል፤ ሰላም ማጣት ግን ሁሉም ሰው ዘንድ የሚገኝ ችግር መሆኑን አስተዋልን። ስለዚህ የችግሩን ምንጭ መለየትና መሰረታዊ መንስዔው ላይ አተኩረን መስራት እንዳለብን ስለተገነዘብን ሰላምን በዘላቂነት ስለማስፈን ማሰብ ጀመርን›› በማለት ‹‹ግሎባል ፒስ ባንክ›› (Global Peace Bank) የተሰኘውን ሌላውን ተግባራቸውን እንዴት እንደጀመሩት ያስረዳሉ።
አቶ አርጋው ስለ ‹‹ግሎባል ፒስ ባንክ›› ጽንሰ ሃሳብ ሲገልፁ ‹‹ሰዎች ገንዘብ አዋጥተው የንግድ ባንኮችን ይመሰርታሉ። ትርፋማ ሆነውም ገንዘብ ይሰበስባሉ፡፡ ትርፋቸውን ለማስጠበቅም ባንኩን ይጠብቃሉ፡፡ ሰላምንም እንደዚህ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሰላም ከገንዘብ በላይ ነው፡፡ እኛ ሰላምን ጋሪ፣ ገንዘብን ፈረስ አድርገናል፡፡ ሰላም በማጣታችን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አጥተናል፡፡ ሰላም ከሌለ የገንዘብ ባንኮች ዋስትና የላቸውም፡፡ ዋስትናቸው ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ነው፡፡ ስለዚህ ሰላምን ኢንቨስት ማድረግ ይገባል፡፡ ሰላም የሚገነባው ደግሞ በሰላም ሃሳብ ነው። የሰላም ባንክ ሰላምን ሊያሰፍኑ የሚችሉ ሃሳቦች የሚሰበሰቡበት የሃሳብ ባንክ ነው፡፡ የንግድ ባንኮች ውስጥ የባለአክሲዮኖች ሀብት ገንዘብ ነው፤ የሰላም ባንክ ውስጥ ደግሞ አክሲዮኑ የሰላም ሃሳብ ነው።
ሰላም በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ብሎም በመላው ዓለም ሰፍኖ የማየት ርዕይ ያለው ባንኩ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በፌደራልና በክልል ከተሞች 13 ከፍተኛ የፖሊሲ እና 120 ማኅበረሰብ ተኮር ውይይቶችን የማዘጋጀት እንዲሁም በትምህርት ቤቶችና በመስሪያ ቤቶች የሰላም ክበባትን የማቋቋም እቅድ አለው።
የሰላም ባንክ ምስረታ ሃሳቡ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተቀባይነት አግኝቶ የእውቅና የምስክር ወረቀት አግኝቷል፤ ሃሳቡም በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ተመዝግቧል፤ ከሲዳማ ክልል መንግሥትም የድጋፍ ደብዳቤዎችን አግኝቷል፡፡ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ሃሳቡን ለማስረዳት ባደረጉት ጥረትም የጋሞ ዞን የመጀመሪያው የባንኩ ባለአክሲዮን መሆን ችሏል።
አቶ አርጋው እንደሚሉት፣ ባንኩ ‹‹ቅድሚያ ለጎረቤት›› በሚል መርህ (Neighbor First Approach) ይመራል፡፡ ጎረቤት የሚባለው በመኖሪያ ቤት አካባቢ በቅርበት ያለው ሰው ብቻ ሳይሆን በስራ ቦታና በሌሎች እለታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በቅርበት የሚገኘው ሰው ጭምር ማለት ነው፡፡ ከድርድር ይልቅ እርቅ የተሻለ ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው እርቅ ነው፤ እርቅ ደግሞ ለሰላም ዋስትና ይሆናል፡፡ የሰላም ባንክ ለሰላም ዘላቂ ዋስትና በሚሆኑ ግብዓቶች ላይ ያተኩራል።
የወደፊት እቅዳቸውን በተመለከተም ‹‹ድርጅቱ ዘላቂና ራሱን በራሱ የሚያስቀጥል እንዲሆን እንፈልጋለን›› የሚሉት አቶ አርጋው አየለ፣ ‹‹ከመንግሥት ድጋፍ ከተደረገልን፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ እገዛ የምናገኝበትን መንገድ አመቻችተን የበጎ አድራጎት ስራችንን ማጠናከር እንፈልጋለን›› በማለት ከመንግሥት ድጋፍ እንዲደረግላቸው በአፅንዖት ይጠይቃሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2015