ስለ ዓሊ ቢራ የሙዚቃ ችሎታና ተወዳጅነት ከኦሮምኛ ተናጋሪዎች ያላነሰ የአማርኛና የሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪዎች ሲያወሩ እንሰማለን። የሙዚቃ ጣዕም የሚያውቁ ሰዎች እንዲህ ናቸው። ውስጣቸው በሙዚቃ ሀሴት የሚያደርገው በግጥሞቹ ሳይሆን በዜማውና ቃናው ነው። ለሙዚቃ ግጥም ሁለተኛ ጉዳይ ነው። ‹‹ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ›› የተባለውም ለዚህ ነው፡፡
ሙዚቃን ለመልዕክት የምንጠቀመው ከሙዚቃ ራቅ ያልን ሰዎች ነን። እንዲህ አይነት ሰዎች ምናልባትም ትኩረት የሚያደርጉት ግጥሙ ላይ ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው ዘፈኖችን ለፍቅረኛ ስሜትን ለመግለጽ ወይም የፖለቲካ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የምንጠቀማቸው፡፡
ለሙዚቃ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ግን መጀመሪያ የሚያጣጥሙት ዜማ እና በውስጡ ያሉ ለእኛ የማይገቡን ሌሎች መለኪያዎቹን ነው።
የሙዚቃ ነገር ረቂቅ ነው። ‹‹ምኑን ወደዳችሁት?›› ብንባል መለኪያው ላይገባን ቢችልም፤ የግጥሞቹን ትርጉም በማናውቀው ቋንቋ የተዘፈኑ ዘፈኖችን እያጣጣምን እንሰማለን።
ይህን ለማለት የፈለኩበት ምክንያት የዓሊ ቢራ ዘፈኖች የዘፈነባቸውን ቋንቋዎች የማያውቁ ሰዎች እንኳን ተመስጠው ሲሰሙት ስለማይ ነው። ‹‹ሰው ከሞተ በኋላ ነው የሚመሰገን›› የሚል ብሂል ቢኖረንም ዓሊ ቢራ ግን በሕይወት እያለ ብዙ ተመስግኗል። ብዙ አድናቂዎች የእሱን ሙዚቃዎች ሰምተው እንደማይጠግቡ በሕይወት እያለ ነው ሲያወሩ የሰማነው፡፡
ለመሆኑ ዓሊ ቢራን እንዲህ ተወዳጅ ያደረገው ምንድነው?
ይህን ጥያቄ መመለስ የሚችለው የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሐት ነው። ጅማ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ቅዳሜ ታኅሳስ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ‹‹ዝክረ ዓሊ›› በሚል የዓሊ ቢራን የሙዚቃ ሕይወት የሚዘክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በመድረኩ ላይ በርካታ ዝግጅቶች ቀርበዋል። ሌሎችን ለሌላ ቀን እንተዋቸውና ለዛሬው የሰርፀ ፍሬስብሐትን ማብራሪያ እናካፍላችሁ።
‹‹ዓሊ ብዙ ሰው ነው›› ይላል ሰርፀ። በፎክሎር ዓይን ቢታይ ብዙ የባህል ተመራማሪዎች መድረክ አዘጋጅተው ሊወያዩበትና ሊመክሩበት የሚችል ነው። የቋንቋ ሰዎችና የፍልስፍና ሰዎች አገላለጹና ፍልስፍናው ላይ መድረክ አዘጋጅተው ሊወያዩ ይችላሉ። የሙዚቃ ሰዎች ስለድምጹ (ቮካል)፣ አሬንጅመንት ሰፊ ውይይት ሊያደርጉበት ይችላሉ። በሁሉም ዘርፎች ለህትመት የሚሆኑ የጥናት ውጤቶችን ሊያቀርቡ ይችላሉ።
እንደ ሰርፀ ገለጻ፤ ዓሊ ዲስኮግራፊ(discography) ሊዘጋጅለት ይገባል። ዲስኮግራፊ ማለት የአርቲስቱን ሥራዎች ዝርዝር ከነ ሙሉ መረጃቸው በፈርጅ በፈርጅ የሚያስቀመጥ ሰነድ ማለት ነው።
ወደ ዓሊ የሙዚቃ ሕይወት ቅኝት ሲገባ ‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች የሁለገብነት ምዕራፍ በዓሊ መሀመድ ቢራ ፈር ቀዳጅነት›› በሚል ርዕስ ነው። ‹‹ሙዚቃ የምክንያታዊነትንና የቋንቋን ድንበር ትጥሳለች›› የሚባለው ‹‹ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ›› የሚለውን የተለመደ አባባል ለመግለጽ ነው።
እንደ ሰርፀ ማብራሪያ፤ እነዚህ አባባሎች የዓለምን የሙዚቃ ባለሙያዎች ሲያከራክሩ የቆዩ ናቸው። የፍልስፍና እና የሙዚቃን ግንኙነት የወዳጅነትና የፀብ ሲያደርጉት ቆይተዋል።
ሙዚቃ የምክንያታዊነትን ድልድይ ከጣሰች በቀጥታ ከፍልስፍናዊና ከሃይማኖታዊ ሞራል አስተምህሮ ጋር ትጣላለች። የቋንቋን ድንበር ከጣሰች ደግሞ የገጣሚውን ቦታ አጠያያቂ ታደርጋለች ወይም ዋጋ ታሳጣለች። በዜማ ብቻ ትልቅ ሀሳብ መገለጹ ነው ማለት ነው።
ከዚህ ሁሉ ጥሰት ከወጣች ግን ሙዚቃ በጂኦግራፊና በባህል ዓውድ ውስጥ ብቻ የመደመጥ ዕድሏን ወደተሻለ ደረጃ ታሳድጋለች። ገጣሚውን፣ ፈላስፋውንና የባህል ሞራል ጠባቂውን ከጣሰች በኋላ ደግሞ የዓለም ቋንቋ ትሆናለች።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከጥንት ሲያያዝ በመጣ ባህሪው፤ ሀሳብ ተሸካሚነቱ፣ የግጥም ምሉዕነቱ ያመዝናል። አንድ ኢትዮጵያዊ ሙዚቃ ወይም ዘፈን አዳመጥኩ ሲል በአብዛኛው ግጥም አዳመጥኩ ማለቱ ነው። የዜማው፣ የሙዚቃው ፎርም እና ሌሎች ጓዞች የመጀመሪያ ትኩረቱ አይደሉም። ኢትዮጵያዊ አድማጭ ከቃል ወደ ድምጽ የሚሸጋገር የሙዚቃ ትኩረቱ በይበልጥ ያመዝናል።
ወደ ምዕራቡ ዓለም ከሄድን ግን የሙዚቃ አድማጭ ከሙዚቃ ሀሳብ ጋር የሚገናኘው የሙዚቃውን ፎርም፣ ቅማሬውን፣ እና የድምጽ መዋቅሩን በትኩረት በማዳመጥ ይሆናል። የቃል ዋጋ ቀጥሎ የሚመጣ ቁም ነገር ነው። መጀመሪያ ሙዚቃው ነው የሚነካን።
በዚህ መሰረት የምዕራባውያን ሙዚቃ የማድመጥ ባህል ከድምጽ ወደ ቃል ሲሆን የኢትዮጵያ ግን ከቃል ወደ ድምጽ ነው። ይህን ልዩነት የሚሰብሩ ሰዎች ግን አሉ። እነዚህም ከቃል ወደ ድምጽ እና ከድምጽ ወደ ቃል የሚሄደውን ጉዞ አደናጋሪ አድርገው ሙሉ በሙሉ የሙዚቃቸው ምርኮኛ የሚያደርጉን ድምጻውያን አሉ። እነዚህ ድምጻውያን ፍጹም የቃል ዋጋን ሳናስተውል፣ ቋንቋ ሳይገድበን፣ ትርጉም ሳያስፈልገን የምናዳምጣቸው ናቸው። እነዚህ ድምጻውያን ለተፈጠሩበት የሙዚቃ ዓለም ሁለገብ (universal) የሚባሉ ናቸው።
እነዚህ ድምጻውያን የሚጠቀሙትን የሙዚቃ ፎርም በዓለም ላይ ያለ ሙዚቃ የሚወድ ሰው ሁሉ ሊያዳምጠው የሚችል ጣፋጭ ቃና ይሰጡታል። ያ ቃና ነው ተደማጭነታቸውን የሚያሳድገው፡፡
ከአፍሪካ ውስጥ እንኳን ማሪያ ማኬባን መጥቀስ እንችላለን። የዙሉ ጎሳ ጨዋታዎችን ነው የምትጫወተው፤ ግን ‹‹አፍሪካ›› የሚል ከፍታ ነው የተሰጣት። ማሪያ ማኬባ ይህን ያህል የተወደደችው ቋንቋውን በማስተርጎም አይደለም። ስሜታችንን መቆጣጠር የቻለ ድምጽ እና አዘፋፈን ስላላት ነው።
እንደ ሰርፀ ገለጻ፤ በዚህ ልኬት ነው ዓሊ መሀመድ ቢራን የምናስቀምጠው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በታላቅነቱ ያከበረበት ምክንያት በዚህ የሙዚቃ ስሌት ነው። አንድ የዓሊ ቢራ አድናቂ ‹‹ለምን እንወደደው ቢጠየቅ እኔ ያልኩትን ላይል ይችላል›› ብሏል ሰርፀ። ይህ የብዙዎቻችን ችግር ነው። አንድን በጣም የምንወደውን ዘፋኝ ምኑን እንደወደድነው ብንጠየቅ ምናልባትም ከግጥሙ ውጭ ሌላው ላይገባን ይችላል፤ ግን ሰፍ ብለን ነው የምንሰማው።
‹‹ዓሊ ወርቃማ ድምፅ ያለው ነው›› ይላል ሰርፀ ማብራሪያውን ሲቀጥል። በተለይም በወፍራም ድምጾች የሰራቸው ሙዚቃዎች ወደ ‹‹ቤዝ ሬንጅ›› ወርዶ የሰራቸው ናቸው። ወደ ‹‹ሃይ ሬንጅ›› የሚወጡ ሙዚቃዎቹ አሁን ላሉ የዘመኑ ድምጻውያን ዛሬ ድረስ የቮካል ፈተና የሆኑ ናቸው።
ዓሊ ከሌሎች የኦሮምኛ ድምጻውያን በተለየ የሁለገብነት ተቀባይነት ሊያገኝ የቻለበት ሁለት ምክንያቶችን ያብራራል ሰርፀ። የመጀመሪያው፤ ዓሊ የሚጫወትባቸው የሙዚቃ ስልቶች በሌሎች አገሮች ባህሎች ወይም ለኢትዮጵያዊ አድማጭ አዋሳኝ ከሆኑ የምሥራቁ ኢትዮጵያ ባህሎች የፈለቁ መሆናቸው ነው።
ሁለተኛው ምክንያት፤ የዓሊ እግጅ የተሟላ ሙዚቃዊ ስብዕና ነው። የሙዚቃ ስብዕናው ግልጽና ያልተወሳሰበ ነው። ድምጽ አወጣጡ በጣም ቀላል ነው፤ ቀላል በሆነ አቀማመጥ ነው የሚያስቀምጣቸው። ወጣ ገባ እና ጥምዝምዝ አይበዛባቸውም። ብዙ ሰው ‹‹ቀላል›› ሲባል ተራ ወይም ዝቅተኛ ማለት ይመስለዋል። በሙዚቃ ውስጥ በጣም ከባዱ ሥራ ቀላል ነገር ማስቀመጥ ነው። ሰዎች እየሰሩ ሲሄዱ በረጅም ጊዜ ሊያገኙት የሚችሉት መታደል ነው። ዓሊ ምክንያታዊ ኖት ነው የሚያወጣው። ድምጽ አማረልኝ ብሎ ምክንያታዊ ያልሆኑ ኖቶችን አይነካካም። ይህን ያመጣለት የጥበብ ዕውቀቱ ነው፡፡
ለብዙዎች የዓሊ የሙዚቃ ስልት በኦሮምኛ ውስጥ ብቻ ያለ ሊመስላቸው ይችላል። የሙዚቃዎቹን ባህላዊ ቅርጽ ካየነው ግን በበርካታ ባህሎች ውስጥ የሚገኝ የሙዚቃ ስሪት ነው ያለው። ይህን ብዝሃ መልክ ደግሞ ያገኘው ብዝሃ ባህል ባለበት ምሥራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ማደጉ ነው። ለሙዚቃ በተሰጠው ተሰጥዖ ላይ ይህ የምሥራቅ ኢትዮጵያ አስተዳደጉ ሲጨመርበት የሙዚቃ ሕይወቱን ከፍ አደረገው።
የምሥራቅ ኢትዮጵያ (ሐረሪ) ባህል መገለጫው በርካታ ነው። ለባህሉ ይህን አይነት መልክ መያዝ ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ጋር ቀደም ሲል የነበረው የንግድ፣ የባህልና የሃይማኖት ግንኙነት ነው። ስለዚህ በተለመደው የሰሜን ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አይነት ሙዚቃዎች የምንረዳው አይደለም። ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚቀዳ ቅርጽ አለው።
ዓሊ በኦሮምኛ ብቻ ሳይሆን በሶማሊኛ፣ በሱዳንኛ፣ በሐረሪኛ የሚጫወታቸውን ዜማዎች በሐርሞኒክ ማይነር ሙዚቃዊ ስልት የተከተሉ ናቸው። አንዳንድ የኦሮምኛ ሙዚቃዎቹ በሌሎች የኦሮሞ አካባቢዎች (በወለጋ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሰላሌ) ከምንሰማቸው ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። የተለዩ የሚሆኑበት ምክንያትም በምሥራቅ ኢትዮጵያ በማደጉ ነው፡፡
ሰርፀ እንደሚለው፤ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ እንደ ዘመናዊ የሙዚቃ ተቋማቱ ዘመን ተሻጋሪ ያደረጉት ግለሰብ ሙዚቀኞች ናቸው። ከተቋማቱም በላይ የሙዚቀኞች ታሪክ ዘመን ተሻግሮ እንደ ዓሊ ከ50 ዓመት በላይ በስኬት የተጓዙ ይሆናሉ። ከ1950ዎቹ በፊት እንደ ዓሊ የሁለገብነትን ተሰጥዖ የተጎናፀፈ ሙዚቀኛ ብዙም አልነበረም። ድምጻዊ ከሆነ ድምጻዊ ነው፤ ምናልባት ዜማ ሊጨምር ይችላል። የመሳሪያ ተጫዋች ከሆነ የመሳሪያ ተጫዋች ነው። ዓሊ ግን በሁሉም የተሳካለት ሰው ነው።
ዓሊ የገባበትን የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን ጨምሮ በሌሎች የጥበብ ተቋማት ውስጥ በድምጻዊነት የተቀጠሩትን ታላላቅ ድምጻውያን በሙዚቃ የተሟሉ ለማድረግ ሲባል የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎችን እንዲማሩ አስገዳጅ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው ነበር። ለምሳሌ ጥላሁን ገሠሠ የሙዚቃ መሳሪያ እንዲማር ደብዳቤ ተጽፎበት ነበር። እሱም የሰጠው መልስ ‹‹እኔ ድምጼ ይበቃኛል›› የሚል ነው።
ሁለገብ ተሰጥዖ ያላቸው በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው። እንደ ዓሊ ቢራ፣ ጌታቸው ካሳ፣ ግርማ በየነ፣ አለማየሁ እሸቴ ያሉት ናቸው የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት የሚችሉ። እነዚህ ሙሉ የሙዚቃ ሰው ሊባሉ ይችላሉ።
እንዲያውም ዓሊ ቢራ ዛሬ በድምጻዊነት ከመታወቁ በፊት በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሶማሊኛ ፕሮግራም ስቱዲዮ መጥተው ይቀረጹ የነበሩ የሶማሊኛ ድምጻውያንን በጊታርና ሌሎች መሳሪያዎች በማጀብ ትልቅ አስተዋፅዖ ነበረው። ይሄ ብዙ ያልተነገረለት ታሪኩ ነው። በኢትዮጵያ ሬዲዮ የተቀዱ የመጀመሪያ የሶማሊኛ ሙዚቃዎች ዓሊ ቢራ በጊታር እያጀባቸው የተሰሩ ናቸው።
የዓሊ የሙዚቃ ተፈጥሮ በዜማና ግጥም ደራሲነት፣ በድምጻዊነት፣ በሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት፣ በሙዚቃ አቀናባሪነት አካቶ በመያዝ የክዋኔ ተሰጥዖንም አጎናጽፎታል። ዓሊን ‹‹ፕሮዲዩሰር›› ማለትም ይቻላል። በተለይም ከኢትዮጵያ ውጭ ሆኖ የሰራቸው ሥራዎች ሙሉ የስቱዲዮ ጣጣቸው የራሱ ነው።
ሰርፀ እንደሚለው፤ የዓሊ የሙዚቃ ሕይወት ሲጠቃለል፤ ከሙዚቃ ሕይወት ውጭ ሌላ ማንነት የሌለው ነው። ከሙዚቃ ሥራ ለመውጣት ሞክሮ አያውቅም፤ እስከ ሕይወት ፍጻሜው ድረስ ከማይክ ጋር ነበር። ሲመቸው ሳይሆን ሳይመቸውም ሙዚቃ ሲጫወት የኖረ ሰው ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓም