አዲስ አበባ:- «ዘረኝነትን እንፀየፍ ከተማችንን እናፅዳ» በሚል መሪ ቃል የታጀበውና ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የተሳተፉበት አገር አቀፍ የፅዳት ዘመቻ በትናንትናው ዕለት ተካሄደ።
በፅዳት ዘመቻው ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ «ጥሪ በተደረገው መሠረት በመላው ኢትዮጵያ ጠዋት ጽዳት ሲደረግ ቆይቷል። አብዛኛው ቦታ ላይ ያለው እንቅስቃሴ የሠመረ ነው። የሰፈርና የአእምሮአችንን ቆሻሻ እያጸዳን በንጹሕ ልቡና እና አእምሮ ሀገራችንን እናድስ። ሀገራችንን እንገንባ። እንደ ባሕል በየ ጊዜው እንዲቀጥል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲቀጥልበት እጠይቃለሁ። ዛሬ መውጣት ያልቻላችሁ ከዚህ ትምህርት ወስዳችሁ ኃላፊነ ታችሁን እንደምትወጡና ባሕል እስኪሆን ድረስ እንደምታስቀጥሉት አምናለሁ። ወጥታችሁ ላጸዳ ችሁም ምስጋናዬን አቀርባለሁ::» የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተሳተፉበት ይህ ኢትዮጵያን የማጽዳት ዘመቻ የተለያዩ ተቋማትም የተሳተፉበት መሆኑን በጽ/ቤቱ ድረ-ገጽ የተገለፀ ሲሆን፤ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እና ሌሎችም መሳተፋቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረ-ገፅ እንዳስታወቀው፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመላው አገሪቱ «ዘረኝነትን እን ፀየፍ ከተማችንን እናፅዳ» በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን የጽዳት ዘመቻ መላው ሕዝብ እን ዲሳተፍ ጥሪ ባቀረቡት መሠረት የተከናወነ ሲሆን ኢትዮጵያዊ ማለት አእምሮን ከክፋት ሐሳብ ለማራቅ በበጎነት ዙሪያ የተሰባሰበ፤ ለትውልድ በኩራት የምትተላለፍ ጤናማ፣ ደኅንነቷ የተጠ በቀና በኢኮኖሚ የጠነከረች አገር ባለቤት፤ በወን ድማማችነትና እህትማማችነት ፍጹም መዋደድ የሚገዛ ማኅበረሰብ ማለት መሆኑም በኢትዮጵያን ማፅዳት ጎን ለጎን የተላለፈ መልዕክት መሆኑን መረ ዳት ተችሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በድረ- ገፁ እንዳስታወቀው፣ የጽዳት ዘመቻው ላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሳተፍ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት በትናንትናው ዕለት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ሦስት ሰዓት ድረስ በመላው የጽዳት ዘመቻው ተካሂዷል። በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው የፅዳት ዘመቻ አገሪቷ ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም ከተሞች፣ መንደሮች እና ሰፈሮች ያካተተ መሆኑም በድረ-ገፁ አመልክተዋል።
ከዚህ በፊት ኅዳር 30 ቀን 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስተ ዳደር ዘመን ‹‹እኔ አካባቢዬን አፀዳለሁ እናንተስ?›› በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያው የፅዳት ዘመቻ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011
ግርማ መንግሥቴ