ከስምንት አስርት ዓመታት በላይ ከዘለቀው አንጋፋው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጉዞና ትዝታዎች መካከል ጥቂቱን በወፍ በረር ቅኝት መራርጠን እንደተለመደው በዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን አቅርበንላችኋል። ከመራረጥናቸው የጋዜጣው ቀደምት ዘገባዎች አብዛኞቹ ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከታቸው አስደናቂና ግርምትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ናቸው።
በዚህኛው ዘመን ከዩኒቨርሲቲ ተቋማት 238ሺህ ተማሪዎች መመረቃቸውን የሚገልጽ ዜና ብንሰማ ምናልባት ቁጥሩ ብዙም አነሰ እንላለን እንጂ አይገርመን ይሆናል። ስልሳ ዓመታትን መለስ ብለን የነበረውን ዘመን ስናስታውስ ግን 238 ሰዎች ማንበብና መጻፍ መቻላቸው 1950ዎቹ መጀመሪያ ትልቅ ዜና ሆኖ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ ተቀምጦ እናገኘዋለን። “የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰን እንዳንሰጥ ቃል ኪዳን ገብተናል” ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ለጋዜጠኞች ከሰጡት መግለጫ፣ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ነርስ ምን አለች፣ የአምቦ ውሃ ወደውጭ መላክ ስለመጀመር እና የኢትዮጵያን አውሮፕላን የመጥለፍ ሙከራ ስላደረጉት ወንበዴዎች የወጡ አስገራሚ ዜናዎችንም አካተን እንደሚከተለው ለትውስታ አቅርበናል።
238 ሰዎች በሦስት ወር ማንበብና መጻፍ ቻሉ
በአድአ ወረዳ ዕድገት ሚኒስቴር አማካይነት ለ3ወር የማንበብና የመጻፍ ችሎታ የሚያስገኝ ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ 238 ጎልማሶች ሚያዝያ 18 ቀን ባለፈው እሑድ ከሕዝባዊ ዕድገት ሚኒስቴር ከክቡር አቶ ጌታሁን ተሰማ እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።
ማክሰኞ ሚያዝያ 4 ቀን 1951 ዓ.ም
የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰን እንዳንሰጥ ቃል ኪዳን ገብተናል
ግርማዊ ጃንሆይ ለጋዜጠኞች ጥያቄ የሰጡት መልስ
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የካቲት 16 ቀን ትናንት የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞችን በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው በማነጋገር በኢትዮጵያና በሱማሌ መካከል ስላለው የወሰን ግጭት ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጋዜጠኞቹ ስለጉዳዩ ከግርማዊነታቸው የተሰጠውን ማብራሪያ ካዳመጡ በኋላ፣ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን አቅርበው ነበር። ከጥያቄዎቹም መካከል አንደኛው የሱማሌ ሪፐብሊክ መንግሥት ታላቋ ሱማሌ በሚል መንፈስ የተከተለውን ዓላማ የማይለውጥ ቢሆን፣ በኢትዮጵያና በሱማሊያ መካከል ያለው ሁኔታ ምን ውጤት ያስከትላል የሚለው ነበር።
ለዚህ ጥያቄ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የሰጡት መልስ “ኢትዮጵያ ከራሷ መሬት አንዲትም ስንዝር ብትሆን ቆርሳ አትሰጥም። የሱማሊያ መንግሥት ባለሥልጣኖች ከኢትዮጵያ ጋር በሰላም ተጎራብቶ የመኖር ፍላጎት ቢኖራቸውም የባህላዊ ቅርስ የንግድ፣ የግጦሽና የውሃ ግንኙነቶች ለማድረግ ይቻላል። ከዚህ የተለየ የምናደርገው ቸርነት ግን የለም። የኢትዮጵያን ዘውድ ስንደፋ በምንም አይነት ሁኔታ ከአገሪቱ መሬት ቆርሰን ለሌላ እንዳንሰጥ የሚያስገድደን ቃል ኪዳን በሕገ መንግሥታችን ላይ ሰፍሯል” የሚል ነው።
ማክሰኞ የካቲት 17 ቀን 1956
የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ነርስ
“ነርስነት ለምልክት፣ ለደመወዝና ለሌላ ነገር የተሰጠ ስያሜ አይደለም። ሰው ሳያማርጡ በሽተኞችን በቅን መንፈስ ማገልገልና ታዛዥ መሆን ግን የነርስ ተቀዳሚ ሥራ ነው” አሉ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ነርስ ሲስተር ምሕረት ጳውሎስ።
የካቲት 26 1956 ዓ.ም
የአምቦ ውሃ ውጭ አገር ሊላክ ነው
በቀን 116ሺህ ውሃ እያዘጋጀ የሚያቀርብ በአምቦ (ሐረር ሕይወት) እንዲቋቋም ስለታዘዘ በኢትዮጵያ ቴክኒክ ድርጅትና በኢጣሊያን ስታይም ኩባንያ ጋር የካቲት 27 ቀን ፩፱፻፶፯ ዓ.ም አንድነት ተፈርሟል።
ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የመንግሥት ንብረት ስም አቶ ሀብተ አብ ባይሩ በረዳት ሚኒስትርነት ማዕረግ የቴክኒክ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ በኢጣሊያ አጥኝነት ስራ አስፈጻሚ ኩባንያ በኩል ወኪሉ ሚስተር ማንካ ናቸው።
ሐሙስ የካቲት 28 ቀን 1957 ዓ.ም
የኢትዮጵያን አኤሮፕላን ለማስገደድ የሞከሩት 2 ወንበዴዎች ተገደሉ
አዲስ አበባ፣ (ኢ-ዜ-አ) ከትናንት በስቲያ ማታ ከማድሪድ ወደ አቴን ሲበር ሳለ አቅጣጫውን እንዲለውጥ ለማስገደድ የሞከሩት ሁለት ወንበዴዎች በውስጡ በሚገኙ የአየር ኢንስፔክተሮች የተገደሉበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 707 ጀት አኤሮፕላን ትናንት ከእኩለ ቀን በፊት ከአቴን አዲስ አበባ ገባ።
በዚሁ ኤሮፕላን ከፍ ያለ የጀግንነት ሥራ የሠሩት የአየር መንገዱ ኢንስፔክተሮች፣ የኤሮፕላኑ ሠራተኞችንና የ2ቱን ወንበዴዎች አስክሬን ይዞ አዲስ አበባ ገብቷል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
ታህሣሥ 5 ቀን 1962 ዓ.ም