
አዲስ አበባ፡- በአንድ ጊዜ ከ20 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን ሊያስጠቅም የሚችል ዋይፋይ ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን የአብረሆት ቤተ-መጽሐፍት አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የአብረሆት ቤተ-መጽሐፍት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ውባየሁ ማሞ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በቤተ-መጽሐፍቱ በአንድ ጊዜ ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን ሊያስጠቅም የሚችል ዋይፋይ ሊዘርጋ ነው፡፡
ከዋይፋይ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ከቤተ-መፅሐፍቱ ተገልጋዮች የሚነሱ ቅሬታዎች እንዳሉ የገለጹት ኢንጂነር ውባየሁ ፣ በቤተ-መጽሐፍቱ ችግሩ መኖሩን አመላክተዋል፡፡
ይህንንና መሰል ችግሮችን በመሠረታዊነት ለመፍታት ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በጋራ በመሆን የዋይፋይ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የዋይፋይ መሰረት ልማት ማስፋፊያ እና ዝርጋታ ስራው እስኪያልቅ ድረስ ተገልጋዮች በትዕግስት እንዲጠባበቁም ኢንጅነሩ አሳስበዋል።
አብረሆት ቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ ዓመት ከሁለት ወር እንደሞላው ያወሱት ኢንጅነሩ፣ ቤተ-መጽሐፍቱ በቀን ከ43 ሺ በላይ ተጠቃሚዎችን የማስተናገድ አቅም ያለውና አሁን ላይ በቀን ከ 7000 በላይ ተጠቃሚዎችን እያገለገለ ነው ብለዋል፡፡
ቤተ-መጽሐፍቱ ከማንበቢያነት ባሻገር በውስጡ የአንፊ ቲያትር፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የልጆች መዋያና እናቶች ልጆቻቸውን የሚመግቡበት ክፍልን በውስጡ ያካተተ ቤተ መጽሐፍት እንደሆነም አመላክተዋል።
አብረሆት ቤተ-መጽሐፍት ኢንተርናሽናል ቤተ-መጽሐፍቶች ሊያሟላቸው ከሚገቡ ነገሮች ውስጥ የአባልነት ፕሮግራም ነው ያሉት ኢንጅነሩ፣ የአባልነት ፕሮግራም የተጀመረበት በሁለት ምክንያቶች ነው ያሉ ሲሆን አንዱና ዋነኛው ማህበረሰቡ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቶት እንዲገለገልበትና በሌላ በኩል ማህበረሰቡ የማንበብ ባህሉን እንዲያጎለብት የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የቤተ-መጽሐፍቱ አባል መሆን ሲቻል የተለያዩ ጠቀሜታዎች ይኖራሉ ያሉት ኢንጅነር ውባየሁ፣ ከጥቅሞቹ ውስጥ አንዱ ማንኛውንም መፅሐፍት ቤቱ ወስዶ ማንበብ ያስችላል ብለዋል።
በሌላ በኩልም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ጋዜጦችን እና የህትመት ውጤቶችን ለግሷል፣ እነኝህን ቤተ-መጽሐፍት አባሎቹ በኦንላይን በየትኛውም ቦታ እንዲጠቀም ያስችላል ብለዋል።
ለ10 ሴቶችና ለሁለት ወንዶች የውጭ የትምህርት ዕድልን ለአባላቱ የሚሰጥ ፕሮግራም ቤተ-መጽሐፍቱ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
ቤተ-መጽሐፍቱ ሰፊ ስለሆነ ከአራት ሚሊየን በላይ መጽሐፍት ያስፈልጉታል፣ መጽሐፍቱን ክልሎችንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ኢንጅነሩ፣ ይህ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቤተ-መጽሐፍቱ የድንገተኛ ጊዜ ጥሪ ማሳወቂያ የተገጠመለት ነው፡፡ በመሆኑም የቤተ-መፅሐፍቱ ተገልጋዮች የአጠቃቀም ህጎችን ሲጥሱ የተገጠመለት የሴንሰር ማሽን የድንገተኛ ጊዜ ጥሪ እንደሚያሰማና በዚህ ምክንያት ተገልጋዮች ይረበሻሉ፡፡ ተገልጋዮቹ የተቀመጡ ህጎችን በማክበር መገልገል እንደሚገባቸው ኢንጂነሩ ገልፀዋል።
ማህበረሰቡ ቤተ-መጽሐፍቱ የህዝብ መሆኑን በመረዳት የባለቤትነት ስሜት ተሰምቶት እንዲገለገልና የአባልነት ምዝገባ ፕሮግራም እድሉን እንዲጠቀሙበት ኢንጂነሩ ለተጠቃሚዎች ሁሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አማን ረሽድ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18 ቀን2015 ዓም