መግቢያ፡-
የሽንት መሽኛ አካላት ተብለው የሚጠሩት ከአራቱ ክፍሎች ውስጥ የሚመደቡት፡-
1. ሁለት ኩላሊቶች
2. ከሁለት ኩላሊቶች የሚወጡ ቱቦዎች
3. የሽንት ማጠራቀሚያ የሆነው የሽንት ፊኛ
4.ከሽንት ፊኛ ጋር ተያይዞ የሚገኘው የሽንት
ማስወጫ ቱቦ ነው።
እንግዲህ የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ስንል ከላይ የተጠቀሱትን አራቱን ወይንም አንዱን ለብቻ በኢንፌክሽን ሲጠቃ ማለት ነው። በአብዛኛው የታችኛው የሽንት መሽኛ አካላት ማለትም የሽንት ማጠራቀሚያ ፊኛ እና ከሱ ጋር ተያይዞ የሚገኘው ቱቦ ለኢንፌክሽን በከፍተኛ ደረጃ ይጠቃሉ።
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን በወንዶች እና በሴቶች ያለውን ስርጭት ስንመለከት በብዛት የሚታየው በሴቶች ላይ ሲሆን፤ በወንዶች ላይ ግን በጣም አነስተኛ ነው። ኢንፌክሽኑ በወንዶች ቢከሰት እንኳን ለኢንፌክሽኑ መከሰት ሌላ ምክንያት ሆኖ ይገኛል። ለምሳሌ ያክል በተለያየ ምክንያት የሰውነት የበሽታ አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች ላይ ሊታይ ይችላል። (የስኳር ህመምተኞች ጋር፤የ HIV ታካሚዎች ጋር፤የካንሰር ህመምተኞች ጋር) ከዚህም በተጨማሪ የሽንትን አፈጣጠር ችግር ያለባቸው ሰዎች ጋር በስተመጨረሻም በተለያዩ ምክንያት የሽንት ማሸኛ ጎማ የገባላቸው ጋር ህመሙ በከፍተኛ ደረጃ ይገኛል።
የህመሙ ምልክቶች
እያንዳንዱ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ማለትም በኢንፌክሽኑ የተጠቃው አካል የራሱ የሆነ ምልክቶች የሚያሳይ ሲሆን ከዚህም በመነሳት የትኛውም አካል በኢንፌክሽኑ እንደተጠቃ ጥቆማ ሊያደርግ ይችላል ሆኖም ግን በአብዛኛው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መገለጫ ተደርገው የሚወሰዱ ምልክቶች ውስጥ እነዚህ ይገኙበታል።
* በጣም የጠነከረ ሽንት የመሽናት ፍላጎት
* ትንሽ ትንሽ መሽናት (መጠኑ የቀነሰ ሆኖ ቶሎ ቶሎ መሽናት)
* ሽንት በመሽናት ሰዓት የሚኖር የማቃጠል ስሜት
* የሽንት ቀለም መቀየር(የደፈረሰ የሚመስል)
* የሽንት ቀለም ወደቀይ ወይም ኮካ ከለር መቀየር(ይህ በሽንት ውስጥ ደም መኖሩን ያመለክታል፣
* የሽንት ጠረን መቀየር
* ከእንብርት በታች የህመም ስሜት
* ኢንፌክሽኑ እየተጠናከረ እና ወደላኛው የሽንት የቱቦ አካላት በሚሰራጭበት ጊዜ በቀኝ ወይም በግራ ወይም በሁለቱም የጎን ክፍል ከፍተኛ ህመም እና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚመጣ ማስታወክ/የማቅለሽለሽ እና ትኩሳት ይኖራል።
የህመሙ መምጫ ምክንያቶች
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በአብዛኛው የሚከሰተው በባክቴርያ ሲሆን፤ባክቴርያዎቹ ከታችኛው የሽንት ቧንቧ በመነሳት ወደላይኛው የሽንት ባንቧ አካላት ይሰራጫሉ። ለዚህ የኢንፌክሽን መምጫ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ኢ.ኮላይ ወይም ኢሰርሽያ ኮላይ (E. Coli) የተሰኘው ባክቴርያ ነው።
ይህ ባክቴርያ በሰውነታችን የሆድ ዕቃ ክፍል /በአንጀታችን ውስጥ /የሚገኝ ሲሆን በተለያየ ምክንያት ወደ ሽንት ቧንቧ በመግባት ኢንፌክሽን እንዲፈጥር ያደርጋል። ከእነዚህም ምክንያቶች ውስጥ የግል ንፅህና ይጠቀሳል። ይህም ማለት የሽንት ባንቧዎች ከሰገራ መውጫ አካባቢ ስለሚገኙ በቀላሉ ወደ ሽንት ቧንቧ የመግባት ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው።
ከላይ መግቢያው ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በሴቶች ላይ በብዛት የሚታይ ሲሆን ምክንያቱም በተፈጥሮ የሴቶች የሽንት ቧንቧ አጭር እና ከማህፀን ጋር በቅርብ ርቀት ላይ ስለሚገኝ ነው። ይህ መሆኑ ባክቴርያ በቀላሉ ወደላይኛው የሽንት መሽኛ አካላት የመሰራጨት ዕድሉን ከፍ ያደርገዋል።
የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን መዘዞች እና መከላከያ መንገዶች
የሽንት ቧንቧ በአግባቡ ከታከሙ እና አስፈላጊውን መከላከያ /ቅድመ ጥንቃቄዎችን ከተገበሩ በቀናት የሚጠፋ የህመም ዓይነት ነው። ነገር ግን ህመሙን ወይንም ቅድመ ጥንቃቄዎቹን ችላ ማለት ለከፋ የጤና ችግር እና ከህመሙ ጋር ተያይዘው የሚመጡ መዘዞች ከባድ እና ዘላቂ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። ከመዘዞቹ መካከል፡-
* ቋሚ የሆነ የኩላሊት መስነፍ/ኩላሊት በኢንፌክሽኑ የተጠቃ እንደሆነ/
* የሽንት ቱቦ መጥበብ /በብዛት በወንዶች ላይ የሚታይ ሲሆን በተደጋጋሚ በህመሙ መጠቃት ለዚህም ጎናኮካል /
* በእርግዝና ሰዓት የተከሰተ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በአግባቡ ካልታከመ እና ትኩረት ካልተሰጠው ያለጊዜ መውለድን፤የጨቅላው ክብደትን መቀነስ /
ከላይ የተጠቀሱት መዘዞች እና ብሎም ከመጀመሪያው ኢንፌክሽኑ ከመከሰቱ በፊት ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሱትን ቅድመ ጥንቃቄዎች እና የመከላከያ ዘዴዎች በመተግበር ህመሙን መከላከል ይቻላል።
* አብዝቶ ፈሳሽ መውሰድ (ውሃ)፡- ይህ የሚረዳበት መንገድ ብዙ ውሃ ስንጠጣ በብዛት እና በፍጥነት (ቶሎ ቶሎ ) ስለምንሸና ባክቴርያውን ለማስወጣት ይረዳል።
* ከግብረስጋ ግንኙነት በኋላ ውሃ መጠጣት እና መሽናት ባክቴርያውን ጠርጎ በሽንት ለማስወጣት ይረዳል።
* ሽንት ቤት ከተጠቀምን በኋላ ስንጠረግ ከፊት ወደኋላ መሆን ይኖርበታል። ይህም ከሰገራ ውስጥ የሚገኘውን ባክቴርያ ከሽንት ቧንቧ እንዲርቅ ያደርጋል።
* ሽንት ለረጅም ጊዜ አለመያዝ።
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ህክምና
አንድ ጊዜ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መኖሩ በሀኪም ከተረጋገጠ በኋላ እንደ ኢንፌክሽኑ ዓይነት እና መጠን ከሚዋጥ/አንቲባዮቲክ እስከ በደም ስር የሚሰጡ የአንቲባዮቲክ መድሐኒቶች ሊሰጥ ይችላል። ከላይ የተጠቀሱትን ህክምና ከመደረጉ በፊት የሚደረጉ ምርመራዎች ሲኖሩ በዋናነት የሽንት ምርመራ፤የደም ምርመራ፤የአልትራሳውንድ ምርመራ፤ህመሙን ለማግኘት የሚደረጉ ምርመራዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2011