አንድ ሰው ንጽህናውን ጠብቆ፣ አምሮና ተውቦ ከቤቱ ሲወጣ ውስጡ ደስተኛ ሆኖ ይውላል፤መጥፎ ሽታ የሚባል ነገር በጭራሽ አይቀርበውም ብሎ ማሰብ ግን አይቻልም። ምክንያቱም በየአካባቢውና በከተማው የሚታየው የተዝረከረከ የቆሻሻ ክምር ለአፍንጫ የሚከረፋ፣ ለዓይንም አስቀያሚ ነገር በመሆኑ ለጤና ጉዳት እንዳለው ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም ቆሻሻን ማጽዳት ተገቢ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አካባቢ ከደረቅ ቆሻሻ ስለጸዳ ብቻ ጤነኝነቱ የተሟላ ይሆናል ማለት አይደለም። የሰው ልጅ አእምሮውም ንጹህ መሆን አለበት። አእምሮው ንጹህ የሚሆነው ቅንነትና ደግነት በውስጥ ሲኖር፣ ለወገኑ፣ ለአገሩ የሚያስብ፣ የሚቆረቆርና የሚሰራ መልካም ሰው ሲኮን ነው። ይህ የሚሆነው የቂምና የጥላቻ ሰንኮፉን ከስር መሠረቱ ነቅሎ ማውጣት ሲቻል ነው።
ሌላው ሰንኮፉን ለእኔ ብቻ የሚል ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ነው፡፡ ይህ ራሱን የቻለ በሽታ በመሆኑ ከዚህ በሽታ መፈወስ የሚቻለው የሰው ልጅን ሁሉም እኩል፣ሁሉም ወገን፣ ሁሉም መልካም ነገር ማግኘት ያለበት መሆኑን በማመንና በመተግበር ነው፡፡
ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ማክበር፣ መቅረብ፣ መርዳት እና በመተባበር ከቻልን ያኔ ሙሉ ጤንነት እንዳለን ማረጋገጥ እንችላለን። ያኔ በንጹህ አእምሮ ስለ ሰላም፣ ስለ እኩልነት፣ ስለ አገር ፣ልማትና እድገት እንዘምራለን። ለዚህ ደግሞ የውጪውን ደረቅ ቆሻሻ ብቻ ሳይሆን ማጽዳት ያለብን ውስጣዊ የሆነውን የቆሸሸ አእምሮም ጭምር ነው። ዘረኝነትም ሌላው ቆሻሻ ነገር ነው፡፡
ዛሬ በመላው ሀገራችን በተለይም በአዲስ አበባ “ዘረኝነትን እንጠየፍ ከተማችንን እናጽዳ” በሚል መሪ ቃል የጽዳት ዘመቻ መደረጉም ዘረኝነት የኢትጵያውያን ባህል፣ የኢትዮጵያ መገለጫ አለመሆኑን ለማሳየት ታስቦ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ወገኑን ገፍታሪ ሳይሆን እንግዳ ተቀባይ፤ ለቸገረው ደራሽ፤ የተራበን አጉራሽ መሆኑን ነው በአያት ቅድመ አያቶቻችን የተነገረን፡፡ ገፍታሪነት፣ አፈናቃይነት የኢትዮጵያውያን መገለጫ መታወቂያው አይደለም። ስለሆነም ይሄን የእኛን ያልሆነ የዘረኝነት ቆሻሻ እንደ ደረቅ ቆሻሻው ሁሉ ከውስጣችን አውጥተን መጣል አለብን። ለዚህ ደግሞ ጊዜው አሁን ነው።
ይህንን በማድረግ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን መመለስ ከእያንዳንዳችን ይጠ በቅብናል።
በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም እንደታዘብነው ዘረኝነት ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙ፤ አጥፊነቱ እንጂ አልሚነቱ አልታየም። ስለዚህ ይሄንን የዘረኝነት አስተሳሰብ ከሚሰበሰበው ደረቅ ቆሻሻ ጋር ልናቃጥለውና ልንቀብረው ይገባል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ተዋናዮች እያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን መሆን አለብን።
የደረቅ ቆሻሻ ጽዳት ዛሬ በዘመቻ መልክ ቢጀመርም በቀጣይነት የምንሰራው ሥራ መሆንም አለበት። ሥራው ሲሰራም አንዱ ሰሪ ሌላው ተመልካች የሚሆንበት ሳይሆን ሁሉም እንደየአቅሙ የሚሳተፍበት መሆን አለበት። ሁሉም በባለቤትነት መንፈስ የሚሰራው ሥራ ሲሆን ነው ውጤታማ የሚሆነው። ስለዚህ ሁሉም ሊሳተፍ ይገባል። ቂምና ጥላቻን፣ ስግብግብነትና ዘረኝነትንም ቀጣይነት ባለው ሥራ ከአእምሯችን ልናጸዳቸው ይገባል፡፡ በምትካቸው ቅንነት፣ ደግነት፣ ወገን አክባሪነት፣ ሰላም ወዳድነት…በመሳሰሉ ሰናይ አስተሳሰብና ተግባራት ልንተካቸው ይገባል፡፡
ቀደም ሲል የነበሩት “ያልተማሩ ያልሰለጠኑ” ወላጆቻችን በወረርሽኝ ሲታመሱ የወሰዱት አንዱ እርምጃ የአካባቢያቸውን ቆሻሻ በዘመቻ መልክ ሰብስበው ማቃጠል ነበር። ይሄ ልማድ ሆኖ እስካሁን ድረስ ኅዳር 12 ቀን ሁሉም ሰው ግቢውንና አካባቢውን አጽደቶ ያቃጥላል።
አካባቢን ማጽዳት በሽታንም ማራቅ መሆኑንም ሳንዘነጋ ጽዳት የሥልጣኔ መገለጫ አንዱ መንገድ መሆኑን በመረዳት ጭምር ሁላችንም አካባቢያችንን ያለ ወረት ማጽዳት አለብን። እነዚሁ ወላጆቻችን በሰዎች መካከል ቂምና ጥላቻን ሲያጋጥም በሀገር ባህል መሠረት በውይይት በመፍታት መጥፎ አስተሳሰብን ከአእምሮ እንዲወጣ በማድረግ ለሰላም ሰርተዋል፡፡ ዛሬም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መወያየት፣ መደማመጥና መከባበር ያስፈልገናል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በስልክ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ለዜጎች እንዳስለላፈው አካባቢያችንን ከቆሻሻ፣ ውስጣችንን ከቂምና ጥላቻ እናጽዳ፡፡ይህ ማድረግ ስንችል ብቻ እኛም ጤና ሀገራችን ሰላም ትሆናለች፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011