በ1962 ዓ.ም የታተሙ ጋዜጦችን ለዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን መርጠናል።በኤሌክትሪክ የሚሽከረከር አውቶሞቢል ተሠራ የሚለው ዜና ብዙዎች የዘመናችን ክስተት አድርገው ቢመለከቱትም ግኝቱ የቆየ ስለመሆኑ ይህ ዘገባ ይነግረናል።የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በነበረበት ቦታ ላይ የገበያ አዳራሽ ይሠራል የሚለው ዜናም፤ መርካቶ የነበረው ሆስፒታሉ ፈርሶ ወደ ፓስተር መዘዋወሩን ያስረዳናል።ከሳምንት በፊት በወጣው ጋዜጣችን ሆስፒታሉ ከ2ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑ በማሰብ አቅርበነዋል።ሌሎች ዘገባዎችንም አካተናል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በነበረበት ቦታ ላይ የገበያ አዳራሽ ይሠራል
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት ቀድሞ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በነበረበት ቦታ ላይ የገበያ አዳራሽ ሥራ እንዳስጀመረ ገለጸ።ይህንንም መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ከበደ በይበልጥ ስለሁኔታው ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል።‹‹ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችን ሌላ የገቢ ምንጭ ስሌለው ድኩማኖችን ለመርዳት ይቸገራል።ችግሩን ለማቃለልና ሠፊ የበጐ አድራጐት ሥራ ለመፈጸም ለሱ የገቢ ምንጭ ይፈጥራል።ቤቶች እየሠራ ያከራያል፤ የእርሻ ሥራዎች ያከናውናል።ከዚህም የሚገኘውን ገቢ ለችግረኞችና ላጡ ለነጡ ሕሙማን ያከፋፍላል።ይህንንም የተቀደሰ ተግባር ለማከናወን ድርጅቱ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በነበረበት በተለይ ፩ ሚሊዮን ፭፻ሺህ ብር የሚፈጅ የገበያ አዳራሽ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡››
ከዜናው ለመረዳት እንደተቻለው በቅርቡ ሥራውን የጀመረው የገበያ አዳራሽ በሚመጣው ዓመት ተጠናቅቆ አገልግሎቱን ስለሚሰጥ ፫፻፶ሺህ ብር ያህል የዓመት ገቢ እንደሚገኝ ታውቋል።ከዚህም የሚገኘው ገቢ በቀጥታ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ አንዳንድ ላልተጠናቀቁ የሥራ ክፍሎች ማሟያ ይውላል።በአሁኑ ጊዜ የማዋለጃው ክፍልና ሌሎች ያልተሟሉ እንዳሉ ተገልጿል፡፡
አሁን በመሠራት ላይ የሚገኘው የገበያ አዳራሽ ዘመናዊ ከመሆኑም በቀር ፩፻ የንግድ ክፍሎች የመታጠቢያና የመጸዳጃ ቤቶች አሉት።ይህን አዳራሽ ለመከራየት እስካሁን ፩ሺህ፭፻ ሰዎች የተመዘገቡ መሆናቸውን አቶ አበበ ከበደ ገልጸዋል።
(ታኅሳስ 4 ቀን 1962)
በኤሌክትሪክ የሚሽከረከር አውቶሞቢል ተሠራ
የጥንቱ ጥበብ ባቀረበው በቤንዚን ናፍጣና በላምባ ሲሽከረከር በኖረው ፤ በድሮውና በዛሬው ተሽከርካሪ ምትክ የሚያገለግል፤ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሮጥ ኦቶሞቢል ተሠርቷል።ኦቶሞቢሊ እገበያ ውስጥ የሚውለውና ለሽያጭ የሚቀርበው ጊዜ የተወሰነ ባይሆንም፤ ትክክለኛውን ውጤት ለዓለም ጋዜጦች የሚያቀርበው በ፲፱፻፷፫ የኢትዮጵያዊ ዓ.ም ማብቂያ ግድም እንደሆነ ታውቋል፡፡
ይህንንም መኪና ሠርቶ ለማውጣት የወሰደው የጥናት ጊዜ፤ ከ፲ ዓመታት በላይ ፈጅቷል።መኪናውን በእሳት ኃይል ሊያንቀሳቅስ የሚችለው የባትሪው አሠራር ልዩ ዘዴ ነው።
ምንም እንኳ እስከዛሬ ድረስ በሌላ ሰው እጅ ባይታይም አንዲት አነስተኛ ካሚዎኔት ተሠርቶ ለሙከራ ያህል በሰዓት ፹ ኪሎ ሜትር እየተሽከረከረ ጥሩ ውጤት አሳይቷል፡፡
የተሞከረበት ጐዳና ርዝመት ፩፻፳ ኪሎ ሜትር እንደነበር የሚታወስ ነው።ሆኖም፤ በዚህ በረራ ላይ ባትሪው እያለቀ ጉልበት መቀነስ ስለአለበት በየጐዳናው ላይ ስምንት ጊዜ እየተሞላ የተጓዘ መሆኑን ዮዓሣ በሚል የሚታወቀው የጃፓን የመኪና ፋብሪካ አመለከተ ሲል አንድ የፈረንሳይ ዕለታዊ ጋዜጣ ገለጠ፡፡
(ጥቅምት 22 ቀን 1962 )
በየዓመቱ ፩፻፶ሺህ ቶን ዓሣ በኢንዱስትሪ ሊዘጋጅ ነው
በሦስተኛው የአምስት ዓመት ፕላን ዘመን የዓሣ ሀብት ልማት መሥሪያ ቤት በየዓመቱ ፩፻፵ሺህ ቶን ዓሣ ለማቅረብ ማቀዱን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ዓሣ ሀብት ኢኮኖሚ አቋም ተስፋ ያለው ነው።በዚህ የተነሣ በአንዳንድ ቦታ ካፒታል ያላቸው የውጭ አገር ሰዎች የንግድ ቤቶችን አቋቁመው ይገኛሉ።ከተከፈቱትም የንግድ ቤቶች መካከል ራስድኮ የሚባል ኩባንያ በኢትዮጵያና በቡልጋሪያ መንግሥት መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት ተቋቁሞ ዘመናዊ ዓሣ ማጥመጃ መርከቦችን አስመጥቶ ሥራውን ጀምሯል።ከዚህም ሌላ ሦስት የዓሣ ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመው አገልግሎታቸውን በመስጠት ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ባለፉት የልማት ዘመን በዓሣ ሀብት ልማት በኩል ለማከናወን ከታሰበው ግብ ባይደረስም፤ ከሞላ ጐደል መፈጸሙ አልቀረም።በጣም ተስማሚ በሆኑ ቦታዎች ላይ የተሻሉትን ልዩ ልዩ ዓይነት ዓሣዎች የሚያደርቅና በቆርቆሮ የሚያሽግ፤ ምርጥ ያልሆኑትንም ዓሣዎች ወደ ከብት ምግብነትና ዘይት የሚለውጥ ኢንዱስትሪ ተቋቁሟል።ለዚህም ኢንዱስትሪ የሚያገለግሉ ዓሣዎች ዓይነትና ብዛት እንደዚሁም ወደፊት በብዛት ለማርባት የሚቻልበትን በአዋሳና በላንጋኖ ሐይቆች ውስጥ ሰፊ ጥናት ለማድረግ ታስቧል።የዚህ ፕላን ከግቡ እስኪደርስ ድረስ የዓሣ ሀብት የሚሰበስብ ስድስት ሺህ ሠራተኞችና ከ፷ በላይ አነስተኛና ከፍተኛ ዓሣ አጥማጅ ጀልባዎች የሚገኙበት ኢንዱስትሪ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ፤ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ኢንዱስትሪዎች ከሚሠሩት ከዓሣ ሀብት ውጤት ውስጥ አብዛኛው ሰርዲንና ከሊል እናት ዓሣ ነባሪ ተብሎ ከሚሠራው አዝራር ቁልፍ ነው።እንደዚሁም ልዩ ልዩ ጌጣ ጌጦች ይሠራሉ።ከዓሣም ጥፍር ለሽቶ መቀመሚያ የሚያገለግል ያወጣሉ፡፡
( ኅዳር 20 ቀን 1962 )
ሁለት ራስና ሁለት አፍ ያላት ኤሊ ተገኘች
በሎስ አንጀለስ ከተማ ክልል ውስጥ ባለው የአራዊት ማርቢያ ውስጥ ሁለት አፎች ያሏት ኤሊ በጥንቃቄ በመጠበቅ ላይ መሆኗ ተነገረ፡፡
ኤሊዋ በሁለቱም አፎችዋ በአንድ ጊዜ የምትመገብ ናት፤ ለዘወትር ምግቧ የሚቀርብላት ሠላጣና ሌላ ቅጠላ ቅጠል ነው፡፡
የሎስ አንጀለስ አራዊት ሰብሳቢ ጠበብት ሲናገሩ፤ ኤሊዋ በመብል በኩል ብርቱ ናት።በልታ በቶሎ አትጠግብም፤ አንድ ጊዜ መብላት ከጀመረችም ደግሞ የቀረበላትን በሙሉ ልታግበሰብስ የምትችል ናት ብለዋል። ከዚህም በቀር ባለሁለት አፍ ኤሊ በሌላው ክፍል የሌለ መሆኑን አረጋግጠዋል።ኤሊዋ አሁንም በሙሉ ጤንነት እዚያው ሎስ አንጀለስ ትገኛለች ሲል የአዲስ ስዋር አራዊት ማርቢያ ዜና አቅራቢ አመለከተ፡፡
(ጥቅምት 15 ቀን 1962 )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 /2015