ጾታዊ ጥቃት ፈርጀ ብዙ ሲሆን ዓይነቱ ሴት ልጅን ወሲባዊ ወይም ጾታዊ ድርጊቶችን እንድትፈፅም ከማስገደድ ይጀምራል። ጾታዊ ወይም ወሲባዊ ምስሎችን እንድትመለከት ማስገደድ፤ የሰውነት ክፍሎቿን መነካካት፤ ድብደባ፤ ለከፋ ስድብ፤ ሌሎች ጥቃቶችን ይጨምራል።
የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን ከኅዳር 16 እስከ ታኅሳስ 1/2015 በተከበረበት ጊዜ በተለያዩ መድረኮች ያገኘናቸው ልጃገረዶችና ሴቶች በዚሁ ዙሪያ የገጠማቸውን አካፍለውን ነበር።
‹‹ለከፋ በቃላት ብቻ ሳይሆን የሴቷን የሰውነት ክፍሎች በመነካካት ጭምር የሚፈፀምበት ነው ››የምትለው ወጣት እሴተ በአታማርያም ለከፋ ከጾታዊ ጥቃቶች አንዱ ሆኖ በሕግ መቀመጡንም ታነሳለች። ብዙ ጊዜ መንገድ ላይ ሳያውቋት መቀመጫዋን በእጃቸው ቸብ ቸብ የሚያደርጉ ወንዶች እንደሚገጥሟትና በዚህም ተደባድባ እንደምታውቅ ሁሉ ትገልፃለች። ከድብድቡ በኋላ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ተንበርክኮ ይቅርታ እንዲጠይቃትና ሁለተኛ አይለምደኝም እንዲል አድርጋዋለች። ደስ የሚለው እሷ ባትምረው ፖሊስ በድርጊቱ ጥፋተኛ ብሎ ሊያስረው ነበር።
የተባበሩት መንግስታት ያወጣው ጥናት እንደሚያመላክተውም ሆነ በተለያዩ መድረኮች ያገኘናቸው ልጃገረዶችና ሴቶች እንደሚሉት ለፖሊስ መንገሩ ብቻውን መፍትሄ ያስገኛል ብለው አያስቡም። ጥቃቱን የተመለከተ ውይይት በተካሄደበት እስካይ ላይት ሆቴል ያገኘናትና የአስገድዶ መድፈር ጥቃት የደረሰባት እንዲሁም ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገችው ልዕልት ባራኪ (ስሟ የተቀየረ)የሚደርሰውን ጥቃት ለፖሊስ መንገሩ ብዙም ለውጥ እንደሌለው ታወሳለች። ፖሊስ የደረሰውን ጥሪ መሰረት አድርጎ ለሴቷ በጥቃቱ ቢደርስላትም የሕግ ሂደቱ ከፖሊስ በደረሰው መረጃ ልክ ለጥፋተኛው ምላሽ ይሰጣል ብላ አታስብም።
ምላሹን ቀልድ ነው የሚመስለው ስትል ትገልጸዋለች። ብይን ከተሰጠ በኋላ ያለውን ተፈፃሚነት አስመልክታም ‹‹ሴቷ የሚደርስባትን የስነ ልቦና ስብራት፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ታሳቢ ያደረገ አይደለም›› ትላለች። ጥቃት አድራሹ በተፈረደበት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በገንዘብ ወይም በስልጣን ኃይል ከሥር ቤት ወጥቶ ውጭ አገር ሁሉ የሚሄድበት ሁኔታ መኖሩን መታዘቧንም ታወሳለች።
ሌላዋ በፀረ ፆታዊ ጥቃት መድረክ ያገኘናት አልማዝ በላይ አስገድዶ በደፈረ ግለሰብ ላይ የሚጣለው ቅጣት በቂ እንዳልሆነ ታነሳለች። ግለሰቡ ጥቃቱን ካደረሰ በኋላ ጥፋተኛ ለማድረግ የሚኬድበትን የሕክምና ምርመራና ሌላ ሌላ ሂደት ጊዜ የሚወስድና አሰልቺ መሆኑንም ትጠቅሳለች። ነገሩን በሽምግልና በመያዝ የስነ ልቦናና በርካታ ጫናዎች ላሉባት ሴት በአካሏ ላይ የደረሰውን ጉዳት የማይመጥን ካሳ ይከፈላት የሚባልበት ሁኔታም አለ። ‹‹እኔ ተገድጄ ተደፍሬ፤ ከመደፈሬ ቀደም ብሎ ደግሞ ድብደባና የአካል ጉዳት ደርሶብኝ የአንድ ሺህ ብር ካሳ እንዲከፍለኝ ነው በሽምግልና ተወስኖልኝ የነበረው›› ብላናለችም ሥራ ፍለጋ ብላ ከገጠር በመጣችበት ወቅት የአዲስ አበባ ነዋሪ በሆነ አስቀጣሪዋ ደላላ የተደፈረችው አልማዝ።
እንዲህ ዓይነቶቹ ጥቃቶች ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ሲሆኑ በዓለማችን፤ በአህጉራችን በተለይም በአገራችን እየተባባሰ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከኮረና በኋላ በተለይ ጥቃቱ መጨመሩን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች ወጥተዋል። በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ባወጣው መረጃ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ልጃገረዶች ቁጥር ከፍ ማለቱን ያረጋግጣል።
ኮሮና በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዚያት በ13 አገራት የተደረገን አንድ ጥናት ዋቢ ያደረገው መረጃው ከሦስት ሴቶች መካከል ሁለቱ የተናገሩት በወረርሽኙ የሴቶች ጥቃት መጨመሩን ያሳያል። ሁለቱ ሴቶች በራሳቸው ወይም በቅርብ በሚያውቋት ሴት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ገልጸዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት አዲስ ትንታኔ መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሦስት ሴቶች መካከል አንዷ በሕይወቷ ውስጥ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባታል። በቅርቡ በወጣ ጥናት እንደተመለከተው የሴቶች ጥቃት ሲቃኝ ተባብሷል። በጎርጎሮሳዊያን 2013 ድርጅቱ ካጠናው ጥናት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ቁጥር ጭማሪ አሳይቷል። በቅርብ ያደረገው ጥናቱ በ2013 ካጠናው በተለየ በልጃገረዶችና በሴቶች ላይ የሚደረገው ጥቃት የሚጀምረው ገና በልጅነት መሆኑንም አካቷል።
በ2020 የተደረገው ጥናት ከጎርጎሮሳዊያን 2013 ከተደረገው የሚለየውም አሁን ላይ ጥቃቱ ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ ከለጋ የልጅነት ዕድሜ መጀመሩ ነው። እንዳከለውም ዕድሜያቸው 15 እና በላይ 736 ሚሊዮን ልጃገረዶችና ሴቶች የጥቃት ሰለባ ሆነዋል። የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት ውስጥ በተለይ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሚደርስ ሴቶች ይገኙበታል። በዚህ ዕድሜ ካሉት አራት ሴቶች መካከልም አንዷ ዕድሜዋ 20ዎቹን ሊደፍን ግማሽ እስኪቀራት በቅርብ አጋሯ ጥቃት ይደርስባት ነበር። ጥቃት ከደረሰባቸው 6 በመቶዎቹ አጋራቸው ባልሆነ ሰው ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ጥናቱ በቅርብ ባልደረባ የሚደርስ ጥቃት መኖሩንና እየተስፋፋ መምጣቱንም አመላክቷል። ጥቃቱ ወሲባዊም አካላዊም ሲሆን ይሄ ዓይነቱ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚኖሩ መሆናቸውን ደግሞ የሚናገሩት የጥናቱ ፀሐፊ ዶክተር ክላውዲያ ጋርሲያ ሞሬኖ ናቸው። ክላውዲያ በደምሳሳው በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ በወረርሽኝ መጠን የሕብረተሰብ ጤና ችግር መሆኑንም አውስተዋል። ለማሳያነት እንደጠቀሱትም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ከሚኖሩት 37 በመቶው ጥቃት ይደርስባቸዋል። ጥቃቱ በአደጉት አገሮች ከሚኖሩት ሴቶች አንፃር ሲታይ ዝቅ ያለ ነው። ለምሳሌ፦ በአውሮፓ ከ16 እስከ 24 በመቶ ዝቅ ይላል ብለዋል። በማዕከላዊ እስያ የሚኖሩ 18 በመቶ ወይም ከአምስት ሴቶች ወደ አንድ ዝቅ እንደሚልም ተመልክቷል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ስር የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች ዋና ዳይሬክተር ፉምዚሌ ምላምቦ-ንግኩካ ጾታዊ ጥቃትን “በዓለም ላይ እጅግ ተስፋፍቶ የሚገኝ፣ ቀጣይነት ያለው እና አውዳሚ ከሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች አንዱ ነው ይሉታል። ፉምዚሌ እንዳሉት ጾታዊ ጥቃት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችንና ቤተሰቦቻቸውን ይጎዳል።
‹‹ጥቃት የደረሰባቸው ልጃገረዶችና ሴቶች ጥቃቱን ደፍረው ሪፖርት አያደርጉም። ምክንያቱም በራሳችንና በቤተሰባችን ላይ መገለል ይደርስብናል ብለው ይፈራሉ። ይሄም በራሱ ጥቃቱ የሚባባስበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ይገመታል›› ያሉት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ ሰብዓዊ መብት ሪጅናል ቢሮ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሪጅናል ጾታ አማካሪ ካታሪን ዲፕሬክስ ፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀን በመዲናችን አዲስ አበባ በሚገኘው ስካይላይ ሆቴል በተከበረበት ወቅት ነው። በዚህ ሁኔታ በ2030 ለማሳካት የታሰበውን የዘላቂ ልማት ግብ ፈፅሞ ማሳካትም አይቻልም። በመሆኑም ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማስቀረት ያስፈልጋል። ጥቃቱን ለማስቀረት ደግሞ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቀናጅተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ሥራቸው ቀጣይነት ያለው ሊሆን ይገባል። ይሄ የበለጠ እርምጃም ለመውሰድና ችግሩን ለመቀነስና ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ጾታዊ ጥቃት በስብሰባው የተገኙት ብቻ የሚነጋገሩበት ሳይሆን ሁሉም የኔ ሊለውና ጥረት ሊያደርግበት የሚገባ ጉዳይ ነው። የማዕከላቸው የ16ቱን ቀን ፀረ ጾታዊ ቀን መድረክ ሲያዘጋጅ ሁለተኛው ጊዜ መሆኑን አስታውሰዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት በተለይ በግጭት ወቅት በልጃገረዶችና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ከመቼውም በላይ እየከፉ መጥተዋል። በመሆኑም ማዕከላቸው እነዚህን ጥቃቶች አንድም ለማስቆም ሁለትም አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙና በእነሱ ላይ የተጣለው ቅጣት ለሌላው መማሪያ እንዲሆን ማድረግ፤ ሶስትም በጥቃቱ የአካል ብቻ ሳይሆን የስነ ልቦናም ቅጣት ለደረሰባቸው ድጋፍ በማድረግ እየሰራ ይገኛል። በተለይ ጥቃቱ በስነ ልቦናቸው ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። ሆኖም በዚህ ላይ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል የሚል ዕምነት የላቸውም። በመሆኑም ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት መንግስትም ሆነ የሲቪል ማህበራት ትኩረታቸው ቁሳቁስ ላይ ያተኮረ የነበረ መሆኑን ያነሳሉ።
በማዕከሉ የሴሚናር አድቮካሲ ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር ወይዘሮ ቃልኪዳን ተስፋዬ ማዕከላቸው ችግሩን በቅንጅትና በዘላቂነት ለመፍታት በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገራችን በነበረ ጦርነት ጾታዊ ጥቃት ለተፈፀመባቸውና በአካልና በስነ ልቦና ለተጎዱ ሴቶች ከቁሳቁስ ባሻገር ከስነ ልቦና ጉዳት መላቀቅ የሚያስችላቸው የሕክምናና የማማከር ድጋፍ አድርጓል። ከ300 በላይ ለሆኑ በጉዳዩ ላይ ለሚሰሩ አካላትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ስልጠና ሰጥቷል። በተጨማሪም በውጭ ካሉ አጋሮቹ ጋር በመሆን አሁንም በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሴቶች ጥምረትን አቋቁሟል። ሥራውን ለማስፋት ይረዳው ዘንድ ጭምርም የአካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጥምረትን በማቋቋምም ላይ ይገኛል። በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት በየዓመቱ ለ16 ቀናት በጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን የመከላከል ዘመቻ በብርቱ ይሳተፋል፡፡
ከኅዳር 16 እስከ ታኅሳስ 1/2015 ሲካሄድ የነበረው የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀን ዜጎች በሴቶች ላይ የሚደርሱትን ጾታዊ ጥቃቶች እንዲገነዘቡና ተግባራዊ ምላሽም እንዲሰጡ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ሴቶች በተለይም የጥቃት ሰለባ የሆኑ ልጃገረዶችና ሴቶች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙበት ነው፡፡ ድምፅ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ለመቀየር ያስችላል ያሉት ደግሞ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ታየ ናቸው፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ እንዲህ ዓይነቶቹ መድረኮች ግንዛቤ ለማስጨበጥም ዓይነተኛ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብርቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ያሻል፡፡ ሴቶች በጥቃት ላይ ያላቸውን ስጋትም ይቀንሳል፡፡ ጥቃቱን ለማስቆም የወንዶች ተሳትፎ፤ ቤተሰብ፤ የዕምነት ተቋማት፤ በየትምህርት ተቋማት የሚገኙ የልጃገረዶች፤ ክበባት ድርሻቸው የጎላ ሊሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡ እኛም በዚህ መልኩ በጋራ በመንቀሳቀስ የሴቶች ስጋት የሆነውን ጾታዊ ጥቃት እናስወግድ መልዕክታችን ነው፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 /2015