አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ ካሉ 10ሺ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል ስምንት ሺ ያህሉ ደረጃውን የጠበቀ ፍሳሽ ባለመልቀቃቸው በአካባቢውና በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የአካባቢ፤ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ። የአካባቢው ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸው እውነት ነው፤ አሁን ግን የእርምት እርምጃ እየወሰድን ነው ሲል የጥቁር አባይ ጫማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ገለጸ።
በኮሚሽኑ የልማት ተቋማት የአካባቢ ሕግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ አባተ ጌትነት በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኢንዱስትሪዎች ፍሳሽ ደረጃውን ጠብቆ የማይለቀቀው በየደረጃው የማጣሪያ ቴክኖሎጂ እንዲኖር ባለመደረጉ ነው። የአስፈጻሚው አካል ክትትል የላላ መሆን፣ የእርምት እርምጃ አለመውሰድ፤ በግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ላይ ብቻ መተኮር ይበልጥ ችግሩን አግዝፎታል።
በተለይም የአስፈጻሚ አካላት ጣልቃገብነት፣ መንግሥት የውጪ ምንዛሬ የሚያገኘው ከእኔ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ከለላ ሆኗቸዋል። በመሆኑም በአገር ደረጃ ካሉት አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት የፍሳሽ ማጣሪያውን በአግባቡ ተጠቅመው ደረጃውን የጠበቀ ፍሳሽ ወደ አካባቢ እየለቀቁ አይደለም።
«ብዙዎቹ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሰነድ የላቸውም።» ያሉት አቶ አባተ ለዚህም ወደተግባሩ እንዲገቡ የሚ ያስችላቸው የአምስት ዓመት የእፎይታ ጊዜ ቢሰጣቸውም አብዛኞቹ በእቅዱ መሠረት እንዳልሰሩ ተናግረዋል። ለአብነት በ2010ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በ11 ከተሞች ላይ በተደረገ ቆጠራ ከ2ሺ150 ፋብሪካዎች 1ሺ780፤ በአማራ ክልል በ3 ከተሞች በተደረገ ቆጠራ ከ211 ፋብሪካዎች 180 የአካባቢ አያያዝ እቅድ እንደሌላቸው ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መንጠቅ፤ መዝጋትና ቦታ ማዘዋወር እንዲሁም ሌሎች አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወሰደ በመሆኑ
ብዙዎቹ ለውጥ እያመጡ ነው የሚሉት አቶ አባተ፤ በያዝነው ዓመት የኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ሆነ የሌሎች የመንግሥት ተቋማት ጣልቃ ገብነት በመቆሙ ወደመስመር የሚገቡ ፋብሪካዎች መበራከታቸውን አስታውቀዋል። በቀጣይም በተከታታይ የቁጥጥርና የክትትል እርምጃ ሥራው ካልቀጠለ ወደነበሩበት መመለ ሳቸው እንደማይቀር ገልጸዋል።
በቅርቡ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከሞጆ ከተማ በናሙና ከተወሰዱ 14 የቆዳ ፋብሪካዎች ውስጥ ሦስቱ ብቻ መካከለኛ ላይ ሲገኙ ሌሎቹ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ ወንዞችን በመበከል በውኃ አካላትም ሆነ በአካባቢ ነዋሪዎች ላይ የሚያደርሰው አደጋ ከፍተኛ እንዲሆን ዕድል ሰጥቶቷል ብለዋል።
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ መለሰ ወንድማገኘሁ በበኩላቸው፤ በደብረብርሃን ከተማ አምስት ፋብሪካዎች በነዋሪውና በአካባቢው በተለይም በሕፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን አንስተዋል። በከፍተኛ መጠን
አደጋ እያደረሱ ያሉት የቢራ፣ የአረቄ፣ የቆዳ እና የባህርዛፍ መጭመቂያ ፋብሪካዎች መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።
የጥቁር አባይ ጫማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደብረብርሃን ቆዳ ፋብሪካ የምርት ሥራአስኪያጅ አቶ ኤርምያስ ወሰኑ የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ችግሩ መኖሩን አምነው ይህም የሆነው ሁሉም የአካባቢው ቆሻሻ፣በከተማው ያለው የፋብሪካ ተረፈ ምርት እነርሱ ደረቅ ቆሻሻቸውን በሚደፉበት አካባቢ የሚደፋ በመሆኑ ችግሩ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ደረቅ ቆሻሻን ለማስወገድ የሚያስችል ቦታ እንዲሰጣቸው ከሦስት ዓመት በላይ ቢጠይቁም በወቅቱ ምላሽ አለማግኘታቸው የአካባቢው ማህበረሰብ በችግር ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል ብለዋል።
እንደ አቶ ኤርምያስ ገለጻ፤ ፍሳሹ ከወንዞች ጋር ተቀላቅሎ ማህበረሰቡ እንዳይጎዳ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ሦስተኛ ደረጃ የማጣሪያ ቴክኖሎጂ ግንባታ እየተካሄደ ነው። ለጊዜው ከተማ አስተዳደሩ ሽታው እስኪጠፋ መዘጋት አለበት ባለው መሠረትም ደረቅ ቆሻሻ የሚያመርተውን የምርት ክፍል መዝጋታቸውን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው