ደረቅ ቆሻሻ የከተማዋ አንዱ ችግር ከሆነ ብዙ ዓመታት ተቆጥሯል። ዘመናዊነት የሚጎድለው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ የማህበረሰቡ ቀዳሚ ችግር ሆኖ አሁንም የመፍትሄ ያለህ እያስባለ ይገኛል። በአንድ ወቅት በዘመቻ የሚደረግ ጽዳት ችግሩን ሊያቃልለውም አልቻለም። አሁንም በየመንገዱ፣ በየወንዞች አጠገብና በቱቦዎች የሚታየው የቆሻሻ ክምር ኅብረተሰቡን ለተለያየ ችግር እየዳረገ መሆኑን የከተማዋ አንዳንድ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
አቶ ታፈሰ መንገሻ ይባላሉ። የአዲስ አበባ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው። በመገናኛ አካ ባቢ ትራንስፖርት በመጠበቅ ላይ እንዳሉ አግ ኝተናቸው ስለ ጉዳዩ አነሳንባቸው። ሃሳባቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ ከመሆን በዘለለ በንግግራቸው የቁጭት ስሜት ይነበብ ነበር። እንደእርሳቸው እይታ ከየቤቱ የሚወጣው ቆሻሻ፣ ወደዋና ማስወገጃው እስኪደርስ ድረስ የሚቆይበት ስፍራ የአፍሪካ መዲና ለምትባለው ከተማ አጸያፊ መሆኑን ይናገራሉ።
በጊዜያዊ የቆሻሻ ማሳረፊያ ቦታዎች ተብለው
በተለዩ አካባቢዎች የሚከመር ቆሻሻ ሥርዓት መያዝ እንዳለበት ያምናሉ። ይህን ጉዳይ መፍትሄ የሚያበጅ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት መፈጠር እንዳለበት ይናገራሉ። ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በየአካባቢው ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በአስተያየት መልክ ሃሳባቸውን ቢሰነዝሩም ጆሮ የሰጣቸው እንደሌለ ነው የሚያስረዱት።
«የቆሻሻ አሰባሰብና አወጋገድ ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚደረጉ ሙከራዎች መበረታታት አለባቸው» የሚሉት አቶ ታፈሰ ኅብረተሰቡም ሆነ የቆሻሻ አወጋገዱን በበላይነት የሚመሩት አካላት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የፅዳት ችግር በቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ አሠራር ማቃለል አለመቻሉን ያነሳሉ። ሁሉም በጋራ ተረባርቦ ለዘመናት ፈተና የሆነውን ችግር መፍትሄ መስጠት ይገባል ብለዋል።
ወይዘሮ ትዕግስት ኃይሉን ፒያሳ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ ነው ያገኘናት። አስተያየት እንድትሰጠን ፍቃደኝነቷን ስንጠይቃት «ሰሞኑን ስለ ፅዳት እየተወራ ስለሆነ ብቻ ነው እየዞራችሁ አስተያየት የምትሰበስቡት» በማለት በምፀት ሸንቆጥ ካደረገችን በኋላ አስተያየቷን እንደማትነፍገን ገልጻልን ሃሳቧን እንዲህ አካፈለችን።
እንደርሷ እሳቤ የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ አገልግሎት ክፍያ ከውኃ ጋር አብሮ እንዲከፈል ሥርዓት ቢዘረጋም፣ በየሠፈሩ ሙሉ ለሙሉ ደረቅ ቆሻሻ ተጓጉዟል የሚል እምነት የላትም። መንግሥት ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ቢዘረጋም በቴክኖሎጂ ታግዞ ቆሻሻን ያለ ችግር መሰብሰብ እና ማስወገድ አልቻለም ትላለች።
ለዚህም እንደ ማስረጃ የምትጠቅሰው በየመንገዱ እና በየሰፈሩ ተከምረው ለጤና ችግር የሆኑ ቆሻሻዎችን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ግን ከየመኖሪያ ቤት እና ንግድ ተቋማቱ ከሚወጣው ቆሻሻ በላይ ዝም ብሎ በየመንገዱ የሚጣለው ቆሻሻ የከተማዋን ፅዳት መበከሉን ይጠቅሳሉ።
በመርካቶ አካባቢ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት ዮሐንስ ኃይሉ አንዳንድ አገሮች ቆሻሻን ጥቅም ላይ አውለው እየተጠቀሙ መሆናቸውን ይገልፃል። ይህ ጠንካራ የሥራ ባህልና ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ አለመኖሩ ያስ ቆጨዋል።
የቆሻሻ ክምር ሀብት ከመሆን ይልቅ፣ ተደርምሶ ለሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል። ይህን እውነት ተቀብለን ከሌሎች አገራት ትምህርት መውሰድ አለብን፡፡ ይህ ከሆነ አዲስ አበባን ከማፅዳት አልፈን በዘርፉ ጠንካራ ኢኮኖሚ መፍጠር እንችላለን፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ዋና መዲና አዲስ አበባ ብቻ ከሚሰበሰበው ቆሻሻ በዓይነት የሚለየውም 30 በመቶ ያህሉ ብቻ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉን ወደ ጥቅም መለወጥ አልተቻለም፡፡ ከመንግሥት በኩልም ዘመናዊ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን ወደ ሥራ የማስገባት እና መልሶ የመጠቀም ሥራውን የሚያቀላጥፉ ፕሮጀክትን በሙሉ ኃይል ወደ ሥራ የማስገባት ክፍተት እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር