አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከገንዘብ ሚኒስቴር በጋራ በመተባበር በ13 የስኳር ፕሮጀክቶች ላይ መዋለንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚፈልጉ የግሉ ዘርፍ አካላት ግልጽና በተቀናጀ መልኩ መረጃ ማግኘት የሚያስችል መጠይቅ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ የመረጃ መጠይቁን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የመረጃ መጠይቁን ማዘጋጀት ያስፈለገው ከተለያዩ አካላት በስኳር ኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ በተበጣጠሰ መልኩ ጥያቄ በመቅረቡ ነው። በመሆኑም 13ቱን የስኳር ፕሮጀክቶች ወደ ግሉ ዘርፍ የማዞሩን ስራ በተቀናጀና ግልጽነት በተሞላበት መንገድ መምራት ያስችል ዘንድ በዚህ ዘርፍ ላይ ፍላጎት ያለው የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውንና ሃሳባቸውን የሚገልፅበት መጠይቅ ተዘጋጅቷል።
ሚኒስቴሩ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሪፎርሙን የማስተባበር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልፀው፤ የልማት ድርጅቶቹን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወደ ግሉ ዘርፍ የማዞር ስራ የሪፎርሙ አካል መሆኑን አስረድተዋል። «ይሄንን ስራ ለማከናወን ለእያንዳንዱ ዘርፍ ጥልቅ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶና ተዘርግቶ እየተመራ ነው» ብለዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ የመረጃ መጠይቅ ዋና አላማው ወደ ግል ዘርፉ የሚዞሩ የልማት ፕሮጀክቶች ሙያዊ እውቀት በተሟላበት፣ ግልጽነት በሰፈነበትና ወጥነት ባለው መልኩ እንዲመራ ለማድረግ ነው።በዚህ መሰረትም የመረጃ መጠይቁ 15 የሚደርሱ ጥያቄዎችን ያዘለ ሲሆን፤ ይሁንና ሌላ አማራጭ ካለው በመጠይቆቹ ብቻ ሳይወሰን የራሱን ሃሳብ እንዲካተትለት ማድረግ ይችላል።
በተጨማሪም የመረጃ መጠይቁ አላማው መረጃ መሰብሰብ ብቻ አለመሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀው፤ መንግስት በዘርፉ መሳተፍ የሚፈልጉት ባለሃብቶች መጠን፤ ያላቸውን ካፒታልና በየትኛው ፕሮጀክት ላይ መሳተፍ እንደሚሹ ለመረዳት እንደሚያስችለው ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም ሚያዝያ 7/2011 ዓ.ም የመረጃ መጠይቁ ታትሞ የሚወጣ ሲሆን ከዚህ ቀን ጀምሮ ማንኛውም ጥያቄ ያለውና ተጨማሪ ማብራሪያ የሚፈልግ ባለሀብት እስከ ሚያዝያ 18/2011ዓ.ም ድረስ ማቅረብ እንደሚችል አመልክተዋል።ባለሃብቶቹ በዘርፉ መሰማራት እንደሚፈልጉ የሚያሳውቁት የመጨረሻ ቀንም እስከ ግንቦት 16/2011ዓ.ም ድረስ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል። ሚኒስቴሩ ከባለሃብቱ በተሰጠው ሃሳብና አስተያየት መሰረት ላይ ተንተርሶ ፕሮጀክቶቹን የማዞሩን ስራ እንዴት መካሄድ እንዳለበት ውሳኔ ሰጥቶ ፕሮጀክቶቹን ወደ ማስተላለፉ ስራ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደሚኒስቴሩ መረጃ፤ የፊታችን ሰኞ መረጃ መጠይቁ ታትሞ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፤ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በስኳር ኮርፖሬሽንና በመንግስት ልማት ድርጅቶች ድረ ገጽ ላይ የሚለቀቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2011
ሶሎሞን በየነ