አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የምግብና የመድ ሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ምግብን ከባዕድ ነገር በመቀላቀል ለሽያጭ በሚያቀርቡ ግለሰቦች ላይ ቁጥጥር የማካሄድ ዘመቻ መጀመሩን አስታወቀ ።
የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የቁጥጥር ዘመቻውን ማካሄድ ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት በየቦታው ምግብን ከባዕድ ነገር በመቀላቀል የሚካደውን ህገወጥ አሰራር ለመከላከል ሲባል ነው። ዘመቻው የተጀመረው ህገወጥ ተግባሩ ተዘውትረው ይከናወንባቸዋል ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ላይ ነው።
«በየጊዜው ከህብረተሰቡ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች ትኩረት በመስጠት ዘመቻውን ማካሄድ ግድ» ብሏል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ህገ ወጦችን ለህግ በማቅረብም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
በ2011ዓ.ም በተለያዩ ስፍራዎች በተደረገው ዘመቻ ለገበያ ከቀረቡና ይበልጥ ተፈላጊ በሚባሉ ምግቦች ላይ ተገቢው ቅኝትና የላብራቶሪ ምርመራ መካሄዱን ጠቅሰዋል።ናሙናቸው ከተወ ሰደው የበርበሬ እንጀራ፣ማርና ቅቤ ውስጥም የባዕድ ነገር ውህድ ተቀላቅሎ መገኘቱ እንደተረጋገጠም አስረድተዋል። እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ በተለይም ችግሩ ጎልቶ በሚስተዋልበት አዲስ አበባ ከተማ በሁለት ዙር በተካሄደው ዘመቻ 189 ተቋማት ላይ አሰሳ በማድረግ ችግሮቹን ለመለየት ተሞክሯል።
በዚህም መሰረት አብዛኞቹ የብቃት ማረጋገጫ የሌላቸውና ንጽህናቸው ባልተጠበቁ ስፍራዎች የሚገለገሉ መሆናቸው ታውቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በርካቶቹ የብቃት ማረጋገጫ እንዲያወጡ ሲደረግ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ህጋዊ እርምጃውን በመፍራት ዘርፉን ለመቀየርና ስራውን ለመተው የተገደዱ መሆናቸው ተለይቷል።
የቁጥጥር ዘመቻውን ለማካሄድ በተደረገው እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከ60 በላይ የፖሊስ አባላትና ከ30 የማያንሱ የደንብ አስከባሪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በክልሎች ደረጃም የሚገባቸው አካላት ተሳታፊ በመሆን ከፍተኛ ትብብር ሲያካሂዱ መቆየቱንም አስረድተዋል።ይህን አሳሳቢ ችግር መፍትሄ ለመስጠትና አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ የአንድ ወገን ሀላፊነት ብቻ በቂ አለመሆኑን የተናገሩት ወይዘሪት ሄራን ህገወጥነት ለመከላከል የህብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ወሳኝ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝብዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2011
መልካምስራ አፈወርቅ