– የልቦና መዋቅር ግንባታም ያስፈልጋል
ዲስ አበባ፡- ለመንግስት ተቋማትን ጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት የሰው ሃብት ልማት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ።ለመንግስት ሰራተኞች የልቦና መዋቅር ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራም ባለሙያዎችና ፖሊሲ አውጪዎች ጠየቁ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በየሩብ ዓመቱ የሚዘጋጀው ‹‹የአዲስ ወግ›› የውይይት መድረክ አካል የሆነው ‹‹አዲስ ወግ- አንድ ጉዳይ›› የውይይት መድረክ በዘርፉ ባለልምድና እውቀት ብሎም በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች በተመረጡና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንትና ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የግል አማካሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተሳትፈዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ተቋማትን በመገንባት ሂደት በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና መልካም እድሎች ዙሪያ ሰጥተው የተወያዩ ሲሆን፤ተቋማትን ጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት የሰው ሃብት ልማት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።የሰው ሃብት ልማት ስራ የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ስራዎችን ይፈልጋል ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች፤ ስራው በአፋጣኝ ቢጀመር በሂደት ፍሬ እያፈራ ይሄዳል ብለዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ መንግስት ለሰው ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል።የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መቋቋም መንግስት በትኩረት እየሰራ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
በትምህርት፣ በአገልግሎት አቅርቦት፣ በፖለቲካ ምህዳርና በፍትህ ዘርፎች ባለፉት ጊዜያት የነበሩትን ክፍተቶች ለማስተካከል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በነዚህ ዘርፎች ተጨባጭ ስኬት ለማስመዝገብ ለቀጣይ 15 ዓመታት የሚያገለግል ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ በዛብህ ማብራሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ከፖለቲካ ወገንተኝነት ይልቅ ችሎታን መሰረት ያደረጉ ሹመቶች እንደ ጥሩ እርምጃ መታየት አለበት።
የተቋማትን ሁኔታ በማየት አንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲዋሃዱ መደረጉና ሌሎቹ እንዲለያዩ መደረጉም መንግስት ጠንካራና ውጤታማ ተቋማትን ለመገንባት ያለው ቁርጠኝነት ማሳያ ነው። ወቅታዊና አዳዲስ ፍላጎቶችን በማገናዘብ ተቋማት ሊሻሻሉና ሊቀየሩ እንደሚችሉ የተናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሶስት አስርት ዓመታት ያገለገሉት ዶክተር ራስወርቅ አድማሴ በበኩላቸው፤በአሁኑ ወቅት ሀገሪቷ እያጋጠማት ላሉ ችግሮች በፊት የነበረውን ባህል መውቀስ አላዋቂነት ነው ብለዋል።ተቋማትን በአንድ ሌሊት መገንባት እንደማይቻል በመጠቆም አሁን ያለው ትውልድ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ የስራ ባህል መፍጠር አለበት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዷ የሆኑት ህይወት አለማየሁ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት ምንም አይነት አቋራጭም አማራጭም የለም።መልካም የልቦና መዋቅር ያለው ግለሰብ የለውጥ ሀዋሪያ ሊሆን ይችላል።ለውጡ ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ግን አካታች መሆን አለበት። በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገሉት ፕሮፌር ዳንኤል ቅጣው፤የሰው ሃብት ልማት ላይ ትኩረት በማድረጋቸው አንዳንድ ሀገራት ይህ ነው የሚባል የተፈጥሮ ሀብት ሳይኖራቸው የዓለም ቁንጮ ለመሆን መብቃታቸውን ተናግረዋል።
እኛ ትልቅ ሀገር ሆነን ለምን ከትናንሽ ሀገራት እርዳታ እንቀበላለን? ፤ያለፉት ትውልዶች ላሊበላን የመሳሰሉ ቅርስ መገንባት ሲችሉ አሁን ያለው ትውልድ ግን ቅርሱን በሀገር በቀል እውቀት መጠገን እንኳን ለምን አቃተው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለተሳታፊዎች ያነሱት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ ጥያቄዎቹን ለመመለስ የአስተሳሰብ ችግሮችን መቅረፍና የተግባቦት ክፍተቶችን መድፈንና ያስፈልጋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2011
መላኩ ኤሮሴ