የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ነገ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ከአካባቢያቸው ቆሻሻን፤ ከአዕምሯቸው ደግሞ ጥላቻን፣ ቂምንና መጥፎ ሀሳብን እንዲያጸዱ ጥሪ አቅርበዋል።ዜጎች አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ከሚያደርጉ ነገሮች በመራቅ፤ አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ከሚያደርጉ ነገሮች ጋር በመደመርና መልካም በማሰብ እሁድን እንዲጀምሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉትን መልዕክት አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ጥሪውን ተቀብለው ለጽዳት ዘመቻው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
አካባቢያቸውን ከማጽዳት ጎን ለጎን ለሀገር ነቀርሳ የሆነውን ጥላቻን፣ ቂም በቀልንና ሌሎች ክፉ ሀሳቦችን ለማራቅ በአካባቢያቸው እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ጠቁመዋል።ወደ ፊት ሊከናወኑ የታሰቡትንና መከናወን ያለባቸውን ተግባራት የዘረዘሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ እነሱም የበኩላቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ሰለሞን ገብሩ እንደተናገረው፤የማህበሩ አባል የሆኑና ያልሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች ከዚህ ቀደምም በበጎ ፈቃደኝነት በጽዳት ስራ ላይ ሲሳተፉ ነበር።የበጎ ፈቃድ ስራው ከከተማ ጽዳት ባሻገር የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ የታመሙትን በመጠየቅና ችግኝ በመትከል የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ይጨምራል።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክትም የአዲስ አበባ ወጣቶች ከዚህ ቀደም ሲያከናውኑ የነበሩትን ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያነሳሳ ነው። ወጣቶችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል የጽዳት ስራውን ለማጠናከርና የተሳታፊዎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጸው ወጣት ሰለሞን፣ አካባቢያቸውን ካጸዱ በኋላ ጽዳቱ ዳግም አካባቢውን እንዳያቆሽሽ በየደረጃው ካለው የመንግስት መዋቅር ጋር በመሆን የተከመሩ ቆሻሻዎችን የሚያነሱ አካላት እንዲዘጋጁም መነጋገራቸውን ተናግሯል።
ወጣት ሰለሞን እንዳብራራው፤ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው የመኖር ጠንካራ እሴት ቢኖራቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የሚታየው ጥላቻ፣ ጽንፈኝነት፣ አክራሪ ብሄርተኝነት በአሁኑ ወቅት ለመፈናቀል፣ ለሰው ህይወት እልፈትና ለሀገሪቱ አለመረጋጋት ምክንያት እየሆነ ነው።በየአካባቢው በጥላቻ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ ይፈጠራል ተብሎ የማይታሰቡ ክስተቶች ተፈጥረዋል።ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት የሚጎዳ ነው።ይህንን ችግር ለማስወገድ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል።
ነገ የተሻለች ሀገርን ለመፍጠር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት የአዲስ አበባ ወጣቶች ራሳቸውን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከጥላቻ፣ ከአክራሪ ብሄርተኝነትና ከሌሎች አሉታዊ ነገሮች በማራቅ ለሌሎች አርአያ ሆነው ይቀጥላሉ። የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ሀላፊው አቶ ፍቅሬ አማንም ሃሳብ አላቸው። ጥላቻና ቂምን የመሳሰሉ አሉታዊ ነገሮች በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ ላይ ከባድ ችግሮችን እያስከተሉ ነው።
በተለይም ከ56 ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተዋደው፣ ተፋቅረውና ተጋግዘው በሚኖሩባት በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሮች ታይተዋል።እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ክልል አቀፍ መድረክ ተካሂዷል።
ክልል አቀፍ መድረክን ተከትሎ በዞኖችና በወረዳዎች መድረኮች እየተካሄዱ ነው። ቂምና ጥላቻ ሰላም እንዳይረጋጋ የሚያደርግ መሆኑንና ሰላም ሲጠፋ የሚከሰቱ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፤ ቂምና ጥላቻ ተንሰራፍቶ ቀውሶች እንዳይባባሱ ህዝቡ የነበረውን መተሳሰብና አብሮነት እንዲያጠናክርና፤ ጥያቄ ያላቸው ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡ ከህዝቡ ጋራ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።
ውይይቶቹ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን የተላለፈው መልዕክትም በክልል ደረጃ የተጀመረውን ይህን ጥላቻ እና ቂም በቀል ለማስወገድና መተሳሰብና አብሮነትን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።በመሆኑም የክልሉ መንግስት ከሚካሄደው የጽዳት ስራዎች ባሻገር መጥፎ አስተሳሰብ ከአእምሮ የማጽዳት ስራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ክልሉ ከዚህ ቀደምም ጽዳት ዘመቻ በየወሩ ሲያከሂድ ቆይቷል።አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት የጽዳት ዘመቻው ተጠናክሮ ይቀጥላል።በሀገሪቱ የሚታየው ጥላቻ ቂም በቀልና ሌሎች አሉታዊ የህዝቡ ችግሮች አይደሉም።እንዚህን ስለማጥፋት በስፋት ቢወራም በመሬት ላይ የተሰረው ስራ ይህ ነው የሚባል አይደለም።በመሬት ላይ ካልተሰራ ደግሞ ጥላቻ፣ ቂምና በቀል ሊጠፋም፤ የሀገሪቱ ችግሮችም ሊቀረፉ አይችሉም። ስለሆነም ከአካባቢ ጽዳት ጎን ለጎን ሁሉም ከአዕምሮው እነዚህን ችግሮች ሊያወጣ ይገባል።
‹‹የፌዴራሊዝም ስርዓቱ፤ የብሄር ብሄረሰቦች ተከባብሮና ተቻችሎ በነጻነት የመኖር መብታቸው ከተጠበቀ መፈናቀልና የሰላም መደፍረስ ሊኖር አይችልም›› ያሉት ወይዘሮ ሊያ፤ ትግራይ ክልል ህገ መንግስቱን አክብሮና አስከብሮ የብሄር ጥቃት እንዳይፈጸም፤ መላው ብሄር ብሄረሰቦች ተከባብሮ እንዲኖሩ፤ ከዚህ ቀደም ሲሰራ የነበረውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ አጀቡሽ ተሰማ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው አካባቢያቸውን ለማጽዳት መዘጋጀታቸውን ይናገራሉ። የጽዳት ስራ የአንድ ሰሞን ፋሽን መሆን እንደሌለበት ይገልጻሉ። ያልጸዳ አዕምሮ የጸዳን አገር የማፍረስ አቅም አለው ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፤ ይህንን እውነት በመገንዘብ በተለይም ወጣቱ ከጥላቻና የቂም በቀል ጉዞ አዕምሮውን ማጽዳት አለበት ሲሉም ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የታሪክና የዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አብዱ መሃመድ አሊ፤ ከዚህ አይነት የዘመቻ ስራዎች በተጨማሪ በመደበኛ እና በኢመደበኛ መንገድ ህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በስፋት መከናወን አለበት ይላሉ።
ዶክተር አብዱ የሚዲያ ተቋማት እንደ ሚዲያ ህዝቡ ከጥላቻ፣ ከቂም በቀልና ከሌሎች መሰል ነገሮች እንዲርቅ ማስተማር አለባቸው ሲሉም አክለዋል።በተመሳሳይ ምሁራንም ህዝቡን ማስተማር፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች ደግሞ ዜጎች ከጥላቻ እንዲርቁና አዕምሯቸውን በመልካም ነገር እንዲያንጹ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት መወጣት አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2011
መላኩ ኤሮሴ