አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ ያለው የፍትሕ ሥርዓት በተለይም የፍርድ ቤቶች ማስረጃ አቀባበል በሰው ምስክር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ በመሆኑ ፍርድን እያዘገየ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ገለጹ።
በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የይቅርታ ቦርድ አቃቤ ሕግ ሀብታሙ ጋረደው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፍርድ ቤት ማስረጃ በሰው ምስክር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሆኗል። ለዚህ ዋነኛ ችግሩ የተበታተነ የማስረጃ ሕግ በመኖሩ ነው። በተለይ ፍትሐብሔር እና ወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች ውስጥ ያሉትን የማስረጃ አካሄዶች ለመከተል ሲባል በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል። በመሆኑም ወጥ የሆነ የማስረጃ ሕግ ያስፈልጋል።
እንደ አቃቤ ሕግ ሀብታሙ ገለጻ፤ፖሊስ የወንጀል ጥቆማ ሲያገኝ ክስ የሚመሰርተው የሰው ማስረጃ መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ነው። የሰው ማስረጃ ላይ አይቻለሁ ወይም አላየሁም የሚለው ቃል ብቻ ጥቅም ላይ ማዋል ኋላ ቀር አካሄድ ነው። ይልቁንም የተለያዩ እና ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ማስረጃዎችን በፍትሕ ሥርዓቱ ስለመጠቀም ማሰብ ይገባል።
በሰለጠነው ዓለም የቪዲዮ ወይም የ«ሲሲቲቪ ካሜራዎች» ምስል ለፍርድ ቤት በማስረጃነት ጥቅም ላይ ይውላሉ። በኢትዮጵያ ግን ምስሎቹ ስለመቀናበራቸው እና ትክክለኛ ስለመሆናቸው መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ባለመደረጉ በቂ የቪዲዮ ማስረጃዎች ውድቅ መደረጋቸው ፍርዱን ከማጓተቱ በተጨማሪ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
የቀድሞ አቃቤ ሕግ የነበሩት ጠበቃ ቃለክርስቶስ ጌትነት በበኩላቸው፤ በሀገራቸን ወጥ የማስረጃ ሕግ አለመኖሩ በፍርድ ቤትም ሆነ በተለያዩ የፍትሕ ተቋማት የሰው ማስረጃ ላይ መንጠልጠልን አስከትሏል። በኢትዮጵያ የሰው ምስክርነት ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስቻለው በፍትሕ ተቋማት የቴክኖሎጂ አቅርቦት ደካማ በመሆኑ ነው። እንደ ጠበቃ ቃለክርስቶስ ማብራሪያ ከሆነ፤ አንድ ፍርድ ቤት የቀረበለትን ቪዲዮ ተመልክቶ ለመወሰን በቅድሚያ ስለመረጃው ትክክለኛነት ማጣራት ይገባል።
መረጃውን ለማጣራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ ደግሞ እንዳንሳሳት በሚል የምስል ማስረጃዎችን ውድቅ ይደረጋሉ። በመሆኑም የፍትህ መዛባት እየደረሰ ነው። ነገር ግን የምስል፣ የዘረመል እና የተለያዩ ቴክኖሎጂ ቀመስ ማስረጃዎችን መመርመር ቢቻል የክርክር ጊዜን መቆጠብ ይቻላል። በተለይ በሰው ምስክር ላይ የተደገፉ የቃል ክርክሮች ተጽፈው እና ለዳኞች ቀርበው ጥናት እስኪደረግባቸው የሚወስዱት ጊዜ ረጅም ይሆናል። ነገር ግን በቴክኖሎጂ የቀረቡ ማስረጃዎችን በማቅረብ ማሳጠር ይቻል እንደነበር ተናግረዋል።
በጥብቅና ሙያ የተሰማሩት አቶ ሰለሞን አለሙ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የሰሚ ሰሚ ማስረጃ እና ከፍተኛ ማስረጃ እንዴት መመዘን አለበት? የሚለው በፍትሐብሔር ማስረጃ ምዘና እና በወንጀል ማስረጃ ምዘና ላይ አካሄዱ የተለያየ ነው። አንድ ወጥ የሆነ የማስረጃ ሕግ ቢዘጋጅ የተከራካሪዎች መረጃ ተሟልቶ እንዲቀርብና ፍርድ ቤቱም ማስረጃዎችን በአግባቡ መርምሮ ለመጠቀም ይረዳዋል። በመሆኑም የማስረጃ ምዘና እና አቀራረብ እንዲሁም የማስረጃ ዓይነቶችን በዝርዝር የያዘ ወጥ ሕግ በማዘጋጀት በዋናነት የሰው ምስክርነት ላይ የተሞረኮዘውን የሕግ አካሄድ ማዘመን እንደሚቻል ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2011
ጌትነት ተስፋማርያም