ሕይወት በእሾህ የታጠረች እንደሆነች የገባኝ አስራ ስምንት ዓመቴን ካከበርኩ በኋላ ነበር። ከዛ በፊት የነበረው ሕይወቴ እንደ ማር የጣመ ነበር። በድሎት የተኖረ። በሕይወት እሾህ እየተወጉ እኔን የሚያሞላቅቁ ወላጆች ነበሩኝ። ከእማዬ ካመለጥኩ አባዬ ጉያ ውስጥ ነበር የማርፈው፣ ጎረቤት ሁሉ እየተቀባበለ ያሳደገኝ ነበርኩ። የሆነ ቀን ላይ ግን በሆነ በማላውቀው ምክንያት ሁሉም ነገር ተቀየረ። አባቴ እንደወጣ ቀረ። ያን ቀን እኔም እናቴም ይመለሳል ስንል ጠብቀነው ነበር አባቴ ግን አልተመለሰም። ይሄው ዛሬም ድረስ አልተመለሰም። ያን ቀን አባቴ ከእናቴ ላይ እኔን ተቀብሎ ሕጻኑን እኔን እንዲህ አለኝ ‹የኔ ሞገስ..የኔ ልዑል..ሕልሜ ከእንግዲህ አንተ ነህ..አንተን ሳፈቅር እኖራለሁ› ይሄን የነገረችኝ እናቴ ናት። ከዛ በኋላ እኔን ለእናቴ ሰጥቶ ሁለታችንንም ግንባራችንን ስሞ እንደወጣ ነግራኛለች።
ማደግ አይቀር አደኩ..ሳድግ ግን ዝም ብዬ አላደኩም። ሁለት ነገሮችን ማሳካት እንዳለብኝ እያሰብኩ ነበር። አንዱ ሕልሜ ያለ ባል የቀረችውን እናቴን እንደ ልጅና እንደ ባል ሆኜ ተንከባክቤ ማኖር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደ አባቴ ልጆቹን የሚወድ ለሚስቱ ታማኝ የሆነ ወንድ መሆን ነበር። እንዳሰብኩት ግን ሕይወት ሕልሜን እንድኖር አልፈቀደችልኝም። አይደለም ለእናቴ ልተርፍ ለራሴ የማልበቃ አድርጋ አንገላታችኝ። እናቴን ለመርዳት ስል ትምህርቴን ከአስር አቆምኩ። አቁሜ ቢሳካልኝ ጥሩ ነበር ግን እንደተመኘሁት የሆነ ምንም አልነበረም። በልጅነት ዕድሜዬ የማልችላቸውን ብዙ ሥራዎች ተዳፍሬአለሁ። እናቴን ለማኖር ስል ከዕድሜዬ ከፍ ብዬ፣ ከአቅሜ ተንጠራርቼ ስቃይ የሚፈጥሩ ሥራዎችን ሠርቻለሁ። እናቴን እንደ ልጅም እንደ ባልም ሆኜ ልንከባከባት የገባሁት ቃል ባለመፈጸሙ እከፋ ጀመር። ሕይወት አንገላታችኝ። ሕይወት ነፍስ ቢኖራት ኖሮ ገድያት እጄን ለመንግሥት የምሰጠው እኔ እሆን ነበር። ሕይወትን አቄምኩባት..ለእናቴ እንዳልበቃ ስላደረገችኝ ጥርሴን ነከስኩባት።
እኔ በማልችለውና ከአቅሜ በላይ በሆነ ሥራ ስንገላታ አንዳንድ ሰዎች በውድ መኪናቸው እናታቸውን ጎናቸው አስቀምጠው እየተሳሳቁ ሲሄዱ ሕልሜ ያ ነበር እላለሁ። አንዳንድ ሰዎች እኔ ከዕለት ጉርስ የተረፈ ሳንቲም አጥቼ ጾሜን ስውል ከእናታቸው ጋር ትልቅ ሆቴል ገብተው ሲዝናኑ ሳይ ሕልሜ ይሄ ነበር እላለው። በዙሪያዬ ሕልሜን የወሰዱብኝን ብዙ ሰዎች አያለሁ..ከእናታቸው ጋር ሽር ብትን ሲሉ። ለእናቴ አስፈላጊ ልጅ ባለመሆኔ ብዙ ጊዜ አምርሬ አልቅሼ አውቃለሁ። አንድ ጊዜ መኪና እያጠብኩ እያለ በማየው ነገር ሆድ ብሶኝ እንባዬ ፈሰሰ። መኪና የማጥብላት ሴት ወደ እኔ ተጠግታ..‹ምነው ማሙሽ ምን ሆነሀል? አለችኝ።
‹ሕልሜን ነጥቀሽኛል › አልኳት..
ደነገጠች..
‹የምን ሕልም ነው የምትለው?
‹ሕልሜ አሁን አንቺ እንደምትሆኚው መሆን ነበር። እንዳንቺና እንደ ባልሽ በአባቴ መኪና እናቴን ጎኔ አስቀምጬ ዓለምን መዞር› አልኳት።
ምን ልል እንደፈለኩ ስለገባት ተረጋጋች። በእሷ ሕይወት መቅናቴ ኩራት የሰጣት ይመስላል። በኑሮዋ ቀንቼ ለእንባ መብቃቴ ያኩራራት ይመስላል። ‹ታዲያ እኮ አንተ ገና ልጅ ነህ፣ እንደ እኔ ለመሆንም ሆነ ከኔ የተሻለ ለመሆን ብዙ ዕድሎች አሉህ› አለችኝ። አይዞህ አታልቅስ በሚመስል ፊትና ድምፅ።
ይሄን የመኪና እጥበት ሳንቲም አጠራቅሜ ነው እንዳንቺ የምሆነው ልላት ነበር። ሆድ ይፍጀው ብዬ ዝም አልኳት። ሕይወት ማዲያቷን እኛ ቤት ላይ እንዳራገፈች ማን በነገረሽ። ዓለም በእኛ ቤት ላይ እንዳጋደለች ብታውቂ..በእኔና በእናቴ ጓዳ ውስጥ ምን እንዳለ ብትሰሚ ይሄን ባላልሽ ነበር ስል በዝምታ አጉረመረምኩባት።
መኪናዋን ካጠብኩበት ነባር ክፍያ ከፍ አድርጋ ሰጥታኝ ወደ መኪናዋ ገባች። ከዓይኔ ተሰወረች። እኔም ወደ መከራዬ እሷም ወደ ድሎቷ ተመለስን።
በዚህ ሁሉ ውስጥ የእናቴ አባቴን አለመርሳት ያመኝ ነበር። እኔ ስለማላውቀው ምንም ስሜት አልነበረኝም። በእናቴ ማዘንና መሰበር ግን በየቀኑ በማላውቀው አባቴ እታመም ነበር። በዚህ ሁሉ ዘመን ውስጥ እናቴ አባቴን ያረሳችበት የፍቅርና የእምነት ኪዳን ያስደንቀኝ ነበር። እንደ እናቴ መቼም የማትረሳኝን ሚስት ለማግባት እመኝ ነበር። ወዲያው ደግሞ በዚህ ድህነትህ አይደለም ሚስት ምንም እንዳትመኝ ሲል አዕምሮዬ ያስጠነቅቀኛል። ለመኖር ስል የተሻለ ሥራ ፍለጋ ወደ ተሻለ ቦታ መሄድ እንዳለብኝ አመንኩ። ያን ቀን ማታ ወደ ቤት ስሄድ ከነሕልሜ ካልሆነ ባዶ እጄን ዳግም ወደዛ ቤት እንደማልመለስ በማመን ነበር። እናትን ጥሎ ሕልም ፍለጋ ምን ይባላል? ብሎ ለጠየቀኝ አዕምሮዬ ምንም አይባልም ግን በየቀኑ በማይገል የናፍቆትና የማጣት በሽታ እናትህ ስትንገላታ ከማየት ግን ይሻላል› አልኩት። የምሄደው እኮ ለመቅረት አይደለም..እንደዛች በሕይወቷ ቀንቼ እንዳለቀስኩላት ባለመኪና ሴት እናቴን ሰው ለማድረግ ነው ስል ለአዕምሮዬ ማሳመኛ ቃል ሰጠሁት።
ሌሊት ተኝቼ ጠዋት ነቃሁ…ወደ እናቴ መኝታ አስተዋልኩ ለብዙ ዓመት የለበሰችውን መቼም የማረሳውን ክንብንቧን ፊቷ ላይ ጣል አድርጋ ዝም ብላለች። በዚያ ሰዓት እንዳልተኛች የምናውቀው ሁለት ሰዎች ነን..እኔና ራሷ እናቴ..ምናልባት አባቴ። እናቴ ከተኛችባቸው ሌሊቶች ይልቅ አባቴን ስታስብ ያልተኛችባቸው ሌሊቶች እንደሚበረክቱ እወራረዳለሁ። አይደለም በዚያ ናፍቆቶች በሚያገረሹበት የጀምበር መወለጃ ሌሊት ቀርቶ..በደህናውም ጊዜ ብዙም አትተኛም።
እናቴን መሳም ፈልጌ ነበር፣ ላቅፋት፣ ላያት ተመኝቼ ነበር ግን ፈራሁ። ምን አስፈራኝ? ስለእሷ አይደል የምሞተው..ስለእሷ አይደል የምንገላታው? ምንም ብል ፍርሀቴን ማሸነፍ አልቻልኩም። ወደ እናቴ መራመድ አቃተኝ። አወጣጤ ለመመለስ ነው..ምናልባት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜም ይሆናል። ሕልሜን ካልደረስኩበት እንደማልመለስ ለራሴ ነግሬዋለሁ። ሕልሜን ካልደረስኩበት እናቴን እንደማላገኛት እያወኩ እንኳን ወደ እሷ ለማቅናት ድፍረት አጣሁ። ሁሉም ትቷት እንዲሄድ የተፈጠረች ነፍስ..
እንደወትሮዬ ሥራ የምሄድ መስዬ እያለቀስኩ ከቤት ወጣሁ። አባቴ ከወጣበት ቤት..በሄደበት መንገድ እናቴን ትቼ ወደማላውቀው አዲስ አበባ መጣሁ። አዲስ አበባ ያን ያክል አላስከፋችኝም..ትንሽ አንገላትታ ተቀበለችኝ። ትንሽዬ ቤት በትንሽዬ ብር ተከራይቼ ያገኘሁትን እየሠራሁ ሕልሜን ፍለጋ ጀመርኩ። ወደ እናቴ ሳልመለስ፣ ስለ እናቴ ሳልሰማ ሁለት ዓመት ኖርኩ።
እኔ የምሠራበት ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ሥራ የሚተዳደሩ ከሰባት በላይ ወጣትና ጡረታ የወጡ ሽማግሌዎች አሉ። ስወጣና ስገባ ካልሆነ በቀር በሥርዓት እንኳን ተያይተን አናውቅም። አንድ ቀን ተጨማሪ የሥራ ቱታ አስፈልጎኝ አንዱን ተረኛ ጥበቃ ሳናግረው ‹ነገ ይገባሉ ጋሽ ተፈራን አናግራቸው አለኝ›። ስማቸው ከአባቴ ስም ጋር ስለተገናኘ ብቻ ደስ አለኝ። በማግስቱ ከሥራ ስወጣ አገኘኋቸው። ሳገኛቸው ግን ድንግጥ ብዬ ነበር። የሆነ ነገራቸው እኛ ቤት የተሰቀለውን ጠዋትና ማታ እማዬ የምትወለውለውን የአባቴን ፎቶ ይመስላል። በጣም ደነገጥኩ..እናቴ ስለ አባቴ ስትነግረኝ እጁ ላይ ስሜን ተነቅሶታል ብላኝ ነበር። እና ደግሞ አይበሉባው ላይ ትልቅ ጠባሳ አለ ብላኝ ነበር። የጋሽ ተፈራን እጅ ማየት አልቻልኩም ጠባሳውን ግን አየሁት። ልወድቅ ተንገዳገድኩ..እንደምንም ራሴን አረጋግቼ ታሪካቸውን ማድመጥ እንዳለብኝ ወሰንኩ። ስናወጋ እስከ ማታ ቆየን..ያን ቀን አባትና ልጅ ሆነን ተገኘን። ያን ቀን ለሥራ ከቤት እንደወጡ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች እንደታፈኑና መጨረሻ ላይም ተከሰው በማያውቁት ወንጀል ሃያ አምስት ዓመት እንደታሰሩ አወጉኝ። ባዶ እጄን ወደ ልጄና ወደ ሚስቴ ከምሄድ ብዬ ነው እዚሁ የቀረሁት አሉኝ።
ለሕልሜ ስሮጥ ከሕልሜ የላቀ ሌላ ሕልም አገኘሁ..ብር ብዬ ወደ እናቴ መሄድ አማረኝ። ወደእናቴ ቤት ከአባቴ ጋር ስሄድ እናቴ የምትሆነውን መሆን እያሰብኩ ብዙ ተደሰትኩ። የዛን ቀን ደስታዬ በሕይወቴ ለአንድ ጊዜ ብቻ የመጣ ነበር። ይሄ ማነው ብላ ስትጠይቀኝ እኔም..በሚያለቅስና በሚስቅ ሁለት ፊት አባቴ ነው ስላት…እሷም በደስታ ስታነባ ይሄን ሁሉ አሰብኩ።
ከሦስት ቀን በኋላ ሁለታችንም አስፈቅደን ወደ ትውልድ መንደሬ አቀናን። ከሁለት ዓመት ምናምን በኋላ ከእናቴ ጋር ልገናኝ ነው። አቤት ደስታዬ..
ግን ምን ያደርጋል ቤት እናቴ አልነበረችም..መሞቷን ሰማን..በአባትና ልጅ ናፍቆት።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም