አሶሳ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 102 ባለሀብቶች ለሰብል ልማት የወሰዱት መሬት ተቀምቶ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን የክልሉ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ማበረታታት ዳይሬክቶሬት አስታወቀ። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ማበረታታት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ክብረወሰን መኩሪያ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ጥራጥሬ፣ የአገዳ ሰብል፣ ጥጥ እና ሌሎችም የሰብል ዓይነቶች ለማልማት ሰፋፊ የእርሻ መሬት የወሰዱ ከ667 በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶች አፈጻጸም ግምገማ ውጤታማ ደረጃ ላይ ነው ለማለት አያስደፍርም።
በሥራ ላይ ከነበሩት መካከል 102 የሚሆኑ ባለሀብቶች መሬት የተቀማ ሲሆን፣ ሌሎቹ ማስተካከያ እንዲያደርጉ በማስጠንቀቂያ ታልፈዋል ብለዋል። በወሰዱት የሰብል ምርት ላይ ከሰል በማክሰል ለገበያ ሲያውሉ የነበሩ 30 ያህል ባለሀብቶችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እርምጃ መወሰዱን ገልጿል። ለአዲስ ባለሀብቶች አዲስ የእርሻ መሬት መስጠት ማቆሙንና አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ባለሀብቶች የተወሰደውን መሬት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች እያስተላለፈ መሆኑንም ጠቁሟል።
ወጣቱ ከክልሉ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት ውሳኔ ማስተላለፉንና በዚሁ መሠረትም ከ2010 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በተያዘው በጀት ዓመት በየወረዳቸው በአንድ ማህበር አምስት ሆነው በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ 169 ወጣቶች የእርሻ መሬት የማስተላለፍ ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል። ከእነዚህ ውስጥም ለ27 ያህል የማስተላለፍ ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።
ለኢንቨስትመንቱ ዝቅተኛ አፈጻጸም ምክንያት በእውቀት ላይ በተመሰረተ ሳይሆን በአጋጣሚ በተገኘ ሀብት ወደ ሥራው መግባት፣ በቴክኖሎጂ ሳይሆን በዘልማድ በሰው ኃይል መጠቀም፣ ባልተፈቀደላቸው ዘርፍ ላይ መሰማራትና ሌሎችም ምክንያቶች መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
በሥራው ላይ የተሰማሩት 9 ከሚሆኑ ፕሮጀክቶች በስተቀር 99 በመቶ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከዘጠኙ ፕሮጀክቶች የሕንድና የሳውዲ አረቢያ ዜግነት ያላቸው ባለሀብቶች የሚገኙበት ሲሆን፣ እነርሱም ቢሆኑ ይህ ነው የሚባል ያስመዘገቡት ውጤት አለመኖሩን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣ ከውጭ ባለሀብቶች የሕንድ ዜግነት ያላቸው «ጃትሮፋ» የተባለውን ቅጠል በማምረት ላይ የተሰማሩ እንደነበሩና ሆኖም ግን ውጤታማ አለመሆናቸውን አመልክተዋል።
ለኢንቨስትመንቱ መዳከም መንግሥትም መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማት አለማሟላቱ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።ክልሉ ባለፈው ዓመት በጀመረው የባለሀብቶች የአፈጻጸም ግምገማ ክፍተት ያለባቸውን ለይቶ የሚሰሩትን በማጠናከር፣ የማይሰሩትን ደግሞ መሬታቸውን በመረከብ የክትትልና ድጋፍ ሥራውን እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።
በሥራ ላይ ያሉት ባለሀብቶች ውጤታማ ባለመሆናቸው ለአዲስ ባለሀብቶች የእርሻ መሬት የማዘጋጀት ሥራ ቆሟል ብለዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ለባለሀብቱ ሲሰጥ የነበረው የእርሻ መሬት ከደን እና ከአርሶአደር እርሻ መሬት ይዞታ ውጪ መሆኑ ተረጋግጦ እና ባለሀብቶቹም በወሰዱት መሬት ዙሪያ የዛፍ ችግኝ በመትከል አካባቢን እንዲጠብቁ ውል ገብተው እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የገቡትንም ውል ሳይፈጽሙ ከሰል አክስሎ በመሸጥ ላይ መሰማራታቸው ተደርሶበት 30 የሚሆኑ ባለሀብቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
ለችግሩ መፈጠርም በባለሀብቶች መሬት በስብሰው የወደቁ እንጨቶች ከሰል ሆነው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በሚል የወጣው መመሪያ መንገድ በመከፈቱ ነው ብለዋል።
መመሪያው ባለሀብቱ የእርሻ ሥራውን ከማረስ ይልቅ ፊቱን ወደ ከሰል ማክሰል እንዲያዞር አድርጓል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከሰተውን የደን ውድመት ክልሉ ደርሶበት እርምጃ ወስዷል።ካለፈው አራት ወር ወዲህም መመሪያው መሰረዙንም አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2011
ለምለም መንግሥቱ