አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል ለመሆን የሚያስችላትን ስምምነት አፅድቃ ሰሞኑን ለአፍሪካ ህብረት ማስረከቧን ተከትሎ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ስምምነቱ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ተስፋም፤ ስጋትም ያለው መሆኑን ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ የተፈረመው የአገሪቱን ጥቅም ከግምት ውስጥ ሳይገባና በአግባቡ ሳይጠና በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባ በምጣኔ ሃብቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል።
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵም ሆነ ሌሎች አገሮች የቀረጥ ታሪፋቸውን ዜሮ የሚያደርጉ በመሆኑ ምርቶች ያለገደብ ገብተው ገበያውን የሚያጥለቀልቁበት እድል ይፈጥራል። በተለይም ገና በማቆጥቆጥ ላይ ያሉትን የአገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶችን የገበያ እድል ይዘጋል።
ለዚህም አብነት አድርገው የሚጠቅሱት የኬንያን የኢንዱስትሪ ምርቶች ሲሆን በተለይም የፕላስቲክ ምርቶች የሚመረቱና የሚሸጡት ከኢትዮጵያ በጣም ባነሳ ዋጋ በመሆኑ በስምምነቱ መሰረት ምርቶቹ ወደ አገር ውስጥ ያለ ገደብ ከገቡ የኢንዱስትሪዎችን ገበያ በመሻማት አምራቾቹ ተስፋ ቆርጠው እንዲወጡ ያደርጋል የሚል ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል።
በሌላ በኩልም «የእኛ ኢንዱስትሪዎች፤ አርሶ አደሮች እንዲሁም ነጋዴው ይህንን መቋቋም እንደሚችሉ በውሉ ተጠንቷል የሚል እምነት የለኝም» ያሉት ዶክተር አለማየሁ ፣ ለዚህ ደግሞ በድርድሩ ላይ የተሳተፉት አካላት በዘርፉ የሰለጠኑ አለመሆናቸውን መሆኑ ሊያመጣ ከሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ይልቅ ከአገራት ለሚኖረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቅድሚያ መስጠታቸውን እንደሚያመላክት አስገንዝበዋል።
አክለውም «እንደ ናይጄሪያ ያሉ በአህጉሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ አገራት እስካሁን ያላፀደቁት ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆን ጥቅሞቻቸውን እንደሚጎዳ በመገንዘባቸው ነው» ብለው ፣ሌሎች ስምምነቱን የፈረሙት አገራት ሁኔታውን በግልፅ ሲረዱ ማፈግፈጋቸው አይቀሬ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ሲኒየር ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ደመላሽ ሃብቴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ማፅደቋ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚረዳ እንጂ ጫና የሚፈጥር አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ አቅም ተቀራራቢ በመሆኑ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከደረሰችበት የማምረት አቅም አኳያ ያን ያህል ውድድሩን መጋፈጥ እንደማያዳግታት አንስተዋል። ይልቁንም የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚያነቃቃና ሸማቹም የፈለገውን ምርት በስፋት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቀስ በቀስም በአለም አቀፍ ገበያ ሰብራ መግባት የሚያስችላትን አቅም ለማዳበር እድል እንደሚፈጥርላት ተናግረዋል። የምንከተለው ስርዓት በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የሌሎችን ምርት ብቻ በመቀበል አምራቹ ላይ ጫና የሚፈጠርበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችልም ረዳት ፕሮፌሰር ደመላሽ አስረድተዋል።
«ገና ለገና የሌሎች አገራት ምርቶች ይቆጣጠሩናል በሚል ስጋት በራችንን ዘግተን የምንቀመጥና ዘላለም ችግር እያወራን የምንኖር ከሆነ መቼም ከድህነት ልንወጣ አንችልም፤ እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ራሱ ወደ ኋላ የሚያስቀር ነው» የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ደመላሽ ፣ በመሆኑም መንግስት ስምምነቱን አፅድቆ መላኩ ተገቢና የሚያስመሰግነው መሆኑን አመልክተዋል።
በንግድ ሚኒስቴር የመልቲላተራል የንግድ ግንኙነት ድርድር ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳይ እንደተናገሩት፤ የንግድ ትስስሩ ሃሳብ ከእ.ኤ.አ 1980 ዓ.ም ጀምሮ የአፍሪካ አገራት በውይይት ያዳበሩትና በርካታ ድርድሮችን ያደረጉበት ጉዳይና በህብረቱ ደረጃ ውሳኔ የተላለፈበት ነው።በተለይም ኢትዮጵያ ፅንሰ ሀሳቡን ካፈለቁ አገራት አንዷ እንደመሆንዋ ትስስሩ ለሯሷ በሚጠቅም መልኩ እንዲተገበር ህጎችን እስከማውጣት ድረስ ተሳትፋበታለች።
«ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ስድስት የቴክኒክ ቡድኖች ተዋቅረው ለአገሪቱ አዋጭ ስለሆኑ ሰፊ ጥናት እንዲጠና ተደርጓል» የሚሉት አቶ ሙሴ፣ በተደረገው ድርድርም ኢትዮጵያ ስምምነቱን ተግባራዊ የምታደርገው በ15 ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሆነና የምታስገባቸው ምርቶች የተወሰኑና ደረጃ በደረጃ የሚያድጉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የነፃ ንግድ ቀጣና አባል መሆን የሚያመጣውን ጠቀሜታ ሲያብራሩም «እኛም ሆነ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ዘለቄታዊ እድገት ለማምጣት፥ ህዝቦቻችንን ከድህነት ለማውጣት፣ ስራ አጥነት ለመቀነስ፣ የተሻለ ዋጋ ለማግኘትና የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለመቀነስ ያስችለናል» ብለዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ የንግድ ግንኙነትና ድርድር ለመሳተፍ የሚረዳ መሆኑን አመልክተው፤ እነዚህ ድርድሮች ከንግዱ የሚገባውን ጥቅም በማግኘት ልማታቸውን በማረጋገጥና በዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት ተጠቃሚ ለመሆንም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም አስረድተዋል።
«በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ አገራት የምናስገባቸው ምርቶች 4 በመቶ በመሆኑ ስምምነቱን መተግበራችን በኢኮኖሚያችን ላይ ጫና ባያደርስም ወደፊት ግን መጠኑ ሊጨምር እና ኢንዱስትሪው ላይ ጫና ሊያሳርፍ ስለሚችል ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባ ድርድር ነው ያደረግነው።በዋናነትም የማንደራደርባቸውን ምርቶች ለይተን በስምምነቱ ውስጥ በማካተት አምራቹን ከጉዳት ለመከላከል ጥረት ተደርጓል» በማለት አብራርተዋል።
የንግድ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን ስምምነቱን 52 አገራት የፈረሙ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 22 አገራት በምክር ቤታቸው አፅድቀውታል፤ ከእነዚህ ውስጥም ለአፍሪካ ህብረት ያስረከቡት 19ኙ ብቻ ናቸው።ኤርትራ፣ ናይጄሪያና ታንዛኒያ እስካሁን ስምምነቱን ያልፈረሙ አገራት ናቸው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2011
ማህሌት አብዱል