አዲስ አበባ፤ በሶስት የመንግስት ተቋማት እና ፕሮጀክቶች ላይ የተፈጸመ ከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 59 የቀድሞ የስራ ሃላፊዎች እና ግብረ አበሮቻቸውን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ገለጸ፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተቋማቸውን ወቅታዊ የስራ ሁኔታና በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እየዋሉ ስለሚገኙ አካላት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ከባድ የሙስና ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል በሚል የተጠረጠሩት ተቋማት የመንግስት ግዢ ንብረት አስተዳደር እና ማስወገድ አገልግሎት፣ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እና የመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲ ናቸው፡፡
የመንግስት ግዢ ንብረት አስተዳደር እና ማስወገድ አገልግሎት የ400 ሺ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ዓለም አቀፍ ጨረተ ግዢ ጋር ተያይዞ የተፈጸመ ነው፡፡ በጥቅምና በመመሳጠር በመንግስት ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ መጠርጠራቸው ተጠቁሟል፡፡
በጨረታው ዝቅተኛ ዋጋ 96 ሚሊዩን 400ሺ ዶላር ጨረታ ያሸነፈ አቅራቢ እያለ በከፍተኛ ዋጋ በማቅረብ 19 ሚሊዩን ዶላር አላግባብ እንዲከፈል ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡
የዚሁ ተቋም ተጠርጣሪዎች በከፍተኛ ዋጋ ስንዴ ያቀረበው ድርጅት ስንዴውን በበህር ለማጓጓዝ የኢትዩጵያን መርከብ መጠቀም ያለበት መሆኑን እያወቁ በዝምታ በማለፋቸው መንግስት ከመርከብ ኪራይ ያገኝ የነበረውን አራት ሚሊዩን 700 ሺ ዶላር በማሳጣት በድምሩ 23 ሚሊዩን 798 ሺ 376 ዶላር ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ መጠርጠራቸውን አቶ ብርሀኑ አመልክተዋል፡፡
የዳቦ ዱቄት እጥረት ተከስቶ በመንግስትና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ መጠርጠራቸውንም አክለዋል፡፡ ከኮምፒዩተር፣ የክሬንና የተሸከርካሪ ግዢዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሰቶችም እየተጣሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ተቋም ተፈጽሟል ያሉት ደግሞ ቦርዱ ዕቅድ ሳይኖረውና ሳያስፈቅዱ የብረት ክምችትን ታሳቢ ባለማድረግ ስለተፈጸመው የብረት ግዢ ነው፡፡ ተርጣሪዎቹ በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ላይ ተመድበው በመስራት ላይ እያሉ በጥቅም በመመሳጠር ከ58 ሚሊዩን ብር በላይ ያላግባብ የግንባታ ብረት ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱ መጠርጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለኮርፖሬሽኑ መካከለኛ ክሊኒክ የማያስፈልጉ መሳሪያዎች ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ ከአራት ሚሊዩን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ እንደተጠረጠሩ ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜዎች ጥራት የሌላቸው የተሸከርካሪ ጎማዎች እንዲገዙ በማድረግ በመንግስትና በህዝብ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ መጠርጠራቸውንም አክለዋል፡፡
እንደ ዐቃቤ ህጉ አቶ ብርሀኑ ገለጻ በመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲ ውስጥ ተፈጽሟል በሚል የተጠረጠረው የሙስና ወንጀልን ሲገልጹም፤ በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ደረጃዎች ተመድበው እየሰሩ በነበረበት ጊዜ የግዥ መመሪያን በመተላለፍ ከአንድ አቅራቢ 79 ሚሊየን 994 ሺ ብርና 479 ዶላር ያላቸው የመድሃኒት ግዢ እንዲፈጸም በማድረጋቸው መጠርጠራቸውንም አብራርተዋል፡፡
በዝቅተኛ ዋጋ ካሸነፈ አቅራቢ ሊገዛ ይገባ የነበረውን መድሃኒትና የህክምና መገልገያ ዕቃ የግዢ መመሪያው ከሚፈቅደው ውጪ እንዲፈጸም በማድረግም የ92 ሚሊየን ብር ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ መንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ መጠርጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
ህግ ከሚፈቅደው ውጭ የመድሃኒት መጋዘን ግንባታ አገልግሎት በተጨማሪ በማስፋፊያ ሰበብ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ በመክፈል በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል የቀረበን ጥቆማ መሰረት በማድረግም ማጣራት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
በቀጣይ የሚጣሩ ስራዎች አሉ ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም በውጪ ሀገር ካሉ አለም አቀፍ የሽብር ቡድን ጋር ተቀናጅተው ሲሰሩ ነበሩ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ማጣራት እየጠደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የሽብር ጥቃት የሚፈፀምበትን ቦታ በመምረጥ፣ ፎቶ በማንሳትና የሽብር ጥቃቱ የሚፈፀምበትን ስልት በመቀየስ የተለያይ መታወቂያዎች የውጪ ሀገር ፓስፖርትና ሌሎች ለሽብር ጥቃት የሚውሉ ነገሮችን በማዘጋጅት ጥቃቱን ለመፈፀም ሲሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ አመልክተዋል።
ወንጀሉ አለም አቀፍ ይዘት ስላለውና ግንኙነቱም በአለም አቀፍ ደረጃ በሽብር ከተመደቡ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ያለው በመሆኑ ተጨማሪ ምርምራ ተደርጎ ሲጠናቀቅ ሙሉ መግለጭ ይሰጣል ብለዋል። ብዙ ህዝብ የሚሰበሰብባቸው የስብሰባ አዳራሾችና ማእከሎችን ታርጌት አድርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ ጉዳቱ ቢፈጸም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ብለዋል።
ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል፤ የቀድሞ የመንግስት ግዢ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር፣ የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ የኢትዩጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበረና የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ፣ የመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበረና ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም በተቋማቱ መካከለኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎች በተጨማሪም በጥቅም የተሳሰሩ ሌሎች ግብረ አበሮች ይገኙበታል፡፡
በዘላለም ግዛው