ነቀምት፡- 25ኛው መላ የኦሮሚያ ስፖርት ሻምፒዮና ከሚያዝያ 6 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ 15 ቀናት በነቀምት ከተማ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ክልል ስፖርት ከሚሽን አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ናስር ሁሴን ዛሬ በነቀምት ከተማ በሰጡት መግላጫ እንዳስታወቁት፤ ከ20 የተለያዩ የክልሉ ዞኖች የተወጣጡ ከ4ሺህ በላይ ስፖርተኞች በ20 የስፖርት አይነቶች የሚሳተፉበት 25ኛው መላ የኦሮሚያ ስፖርት ሻምፒዮና ከሚያዝያ 6 ጀምሮ ባሉት 15 ቀናት በነቀምት ከተማ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡
ከሚሽነሩ ውድድሩን ለማስኬድ በአካባቢው ያለውን ጸጥታና የአቅርቦት ሁኔታን በሚመለከት በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን፤ በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ ሠላማዊ ሁኔታ መኖሩንና ውድድሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስም ስፖርተኞች ምንም እክል ሳይገጥማቸው ቆይታ እንዲያደርጉ ከጸጥና ሌሎች አካት ጋር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
አቶ ናስር እንዳሉት፤ የውድድሩ ዓላማ ክልሉ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያለበትን ደረጃ የሚመዝንበትና የስፖርተኞችን ብቃት በመለየት ለክለቦችና ሌሎች የስፖርት ተቋማት ለማብቃት ነው፡፡
ይህም የተለያዩ ክለቦች ውድድሩ ላይ ተገኝተው ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ስፖርተኞች ለመምረጥ ያስችላቸዋል፡፡
ስፖርተኞቹ ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በአንድ ላይ ተሰባስበው እርስ በእርስ የሚተዋወቁበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ የሚዘጋጅ ውድድር ነው፡፡ ስፖርታዊ ሁነቱ ከውድድር ባሻገር ለነቀምትና አካባቢዋ መልካም ገጽታን የሚገነባ፤ እንዲሁም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ያለውና በተለይም ስፖርት ቱሪዝምን የማስፋፋት አይነተኛ ሚና ያለው ውድድር ነው፡፡
ውድድሩ የሚጀመረው የወለጋ ስታዲየም በተመረቀበት ማግስት መሆኑን ልዩ ያደርገዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የትራክ ላይ ውድድሮችና እግር ኳስ አዲስ በተሰራው ስታዲየም ውስጥ በመሆኑ በርከታ የስፖርት ታዳሚዎች በስፍራው ተገኝተው ድጋፍ እንዲሰጡና በውድድሩ እንዲዝናኑ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ክልሉ በዚህ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ በጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀው የሴቶች ውድድር ላይ በሶስት የውድድር ዘርፎች ማለትም በኦሊምክ፣ በፓራ ኦሊምፒክና ማስማት የተሳናቸው ውድድር አሸናፊ ሲሆን፣ በመቀሌ ከተማ በተካሄደው ሶስተኛው አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ ቀዳሚ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
አዲሱ ገረመው