በ1963 ዓ.ም የታተሙት የአዲስ ዘመን ጋዜጦች ለዛሬው ዓምዳችን የሰበሰብናቸው ቀደምት ዘገባዎች ትኩረት ናቸው።በዚያን ዘመን የነበሩ ኩነቶችን መለስ ብለን እንድናስታውስ ከሚያደርጉን የጋዜጣው ዘገባዎች መካከል ግርምትን የሚፈጥሩና ዛሬ ላይ ሆነን ስናያቸው ሊያዝናኑን የሚችሉም አሉ።አደጋዎች እና ወንጀል ተኮር ዜናዎችም ይገኛሉ፡፡በሮይተርስ የዜና ወኪል ተዘግቦ የነበረ ትንግርት የሚጭር አንድ ዘገባንም አካተን እንደሚከተለው መልሰን ለንባብ አቅርበናል።
በባሌ ጠቅላይ ግዛት ጅብ ሁለት ልጆች በላ
ጐባ፤ (ኢ.ዜ.አ) በባሌ ጠቅላይ ግዛት በሐፍጀር ወረዳ ኗሪ የነበሩት የ፭ና የ፫ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ፪ ህፃናቶች በጅብ መበላታቸውን የኢልከሬ አውራጃ ግዛት ዋና ጸሐፊ አቶ ግዛው ጋሻው ገለጡ፡፡
መሐመድ ሁሴን ፤አብዲና ማህሙድ በደል የተባሉት እነዚህ ሕፃናቶች ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በተለያዩ ቀናቶችና ሥፍራዎች በጅብ ተወስደው የተበሉት ሌሊት በወላጆቻቸው መኖሪያ ቤት ውስጥ ከተገኙበት ቦታ ላይ ነው፡፡
ጅቦቹ የቤቱን ግድግዳ ሰብረው ገብተው ሕፃናቶቹን ከመኝታቸው ላይ በወሰዱበት ወቅት፤ወላጆቻቸው የተቻላቸውን ያህል መከታተል አድርገው ሳይሳካላቸው በመቅረቱ ፤ሕፃናቶቹ መበላታቸው ታውቋል፡፡ከዚህም አስቀድሞ እነዚሁ ጅቦች
፤ቀንም ሆነ ማታ በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ያረባቸውን የጋማና የቀንድ ከብቶች በመብላት በጣም ያስቸገሩበትን ያህል ፤ባሁኑ ወቅት ደግሞ ከእንስሳት ሰው ወደ መብላት በማዘንበላቸው፤ በአካባቢው ከፍ ያለ ሥጋት መፍጠራቸውን አቶ ግዛው ጋሻው በተጨማሪ ገልጠዋል።የሐፍጅር ወረዳ የሚገኘው በአልከሬ አውራጃ ግዛት ነው።
( መስከረም 9 ቀን 1963 ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የሰባት ዓመት ልጅ ተቃጥላ ሞተች
ነቀምቴ፤(ኢ-ዜ-አ) ፀሐይ ጀማነህ የተባለች የ፯ ዓመት ልጅ በአለፈው ነሐሴ ፳፮ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም በእሳት ተቃጥላ መሞቷን የቄለም አውራጃ ግዛት ጽ/ቤት ገለጠ፡፡
ይህ አደጋ የደረሰው በቄለም ወለጋ አውራጃ ተጆ ወረዳ ጐፊ በተባለው ቀበሌ ነው፡፡ልጅቱ በዚህ አደጋ ተቃጥላ የሞተችው ቤቱ ውስጥ እንዳለች ቤቱ በመቃጠሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይኸው የቃጠሎ አደጋ የደረሰባት የሣር ክዳን ቤት የአቶ ይማም አንቺላ ሲሆን፤ ቤቱን ያቃጠለው ወንድምዮው አቶ ማሻ አንቺላ መሆኑንም የአውራጃው ግዛት ጽ/ቤት በተጨማሪ አስታውቋል፡፡
(መስከረም 9 ቀን 1963 ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
፯ ጊዜ ቼክ አጭበረበረ የተባለው አሜሪካዊ ወህኒ ቤት ገባ
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመዘዋወር ሰባት ሰዎችን አጭበረበረ የተባለው አሜሪካዊ ተመስክሮበት ወህኒ ገባ።
ባርት ጆሐንሰን የተባለው የ፳፰ ዓመት ሰው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በባንኮ ዲሮማ የሌለውን ገንዘብ አለኝ በማለት ቼክ መስጠቱን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያመለክታል፡፡
ተከሳሹ አጭበረበራቸው ተብሎ ከአቶ ክበበ ነፍሶ ፬፻ ብር፤ከአቶ ታኩ አበራ ፭፻፹ ብር፤ ከሸለቃ ዓለማየሁ ደስታ ፭፻ ብር፤ ከአክሱም የጉዞ ወኪል መ/ቤት ፩ ሺህ ፬፸፱ ፤እንዲሁም ከልዩ ልዩ ድርጅቶች መሆኑ ታውቋል፡፡
ኗሪነቱ በአዲስ አበባ ጐንደር ሆቴል የሆነው በርት ጆሐንሰን ወህኒ ቤት ከመግባቱ በፊት ለ፪ ሺህ ብር የሚበቃ ዋስ ቢያገኝ እንዲለቀቅ ተፈቀደለት፤ገንዘብ በማጣቱ ወህኒ ገብቷል፡፡አሜሪካዊው ጐረምሳ ኅዳር ፰ ቀን አዲስ አበባ ፍ/ቤት ፬ኛ ወንጀል ቀርቦ ምስክር መሰማት ጀምሯል፡፡ተከሳሹ የፍርዱ ሁኔታ እስኪታወቅ ወህኒ ቤት ተመልሷል።
(ኅዳር 10 ቀን 1963 ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የነብር ቆዳና የዝሆን ጥርስ ይዘው የተገኙ ተቀጡ
መቱ፤(ኢ/ዜ/አ) ስለ ዱር አራዊት ጥበቃ የወጣውን ደንብ በመተላለፍ ፪ሺህ ፭፻ ብር ግምት ያላቸው የነብር ቆዳና የዝሆን ጥርስ ይዘው የተገኙት አቶ አውጋቸው ተከተል ፴ ተቀጥተው በእጃቸው የተገኘው ንብረት በውርስ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ተወሰነ፡፡አቶ አውጋቸው፤፬ የነብር ፪ የጨኖ ቆዳዎችና ፪ የዝሆን ጥርስ ይዘው የተገኙት በቡኖ አውራጃ በበደሌ ከተማ ነው፡፡
ተከሳሹ በፈጸሙት የደንብ መተላለፍ ጥፋት አድራጐታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠ ፤፴ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ፤ገንዘቡን መክፈል ባይችሉ በ፪ ወር እሥራት እንዲቀጡ የቡኖ ወረዳ ፍርድ ቤት ቃል አቀባይ አስታውቋል፡፡
(ኅዳር 20 ቀን 1963 ከታመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ከታረደች ፍየል ሆድ ዕቃ ውስጥ ማዕድን ተገኘ
ሌጐስ፤ (ሮይተር) በናይጄሪያ ውስጥ አንድ ፍየል ከታረደች በኋላ ፤በጨጓራው ውስጥ ልዩ ልዩ የማዕድን ሀብት እንደተገኘ የደረሰን ዜና ገለጠ
በፍየሏ ጨጓራ ውስጥ የተገኘው ፤የወርቅ እንክብሎች፤ልዩ ልዩ ውድ የሆኑ የጌጣ ጌጥ መሣሪያዎች ፤ገንዘብ፤ ዶቃና ጨሌ የመሳሰሉት የአገሬው ጎሣ ጌጣ ጌጥ ናቸው፡፡
እነዚህ ጌጣ ጌጦች ሊገኙ የቻሉት በአገሩ የባህል ደንብ መሠረት አንድ ሰው ሲሞት በእሱ ቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ፍየል ይታረዳል።ይህም እንደ መሥዋዕት የሚቆጠር ሲሆን፤ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ሲገኝ ደግሞ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡ከፍየሏ ጨጓራ የተገኘው ሀብት የማን ንብረት እንደሚሆን የደረሰን ዜና አላረጋገጠም።
( ጥቅምት 22 ቀን 1963 ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 27/ 2015 ዓ.ም