አዲስ አበባ፡- የህሙማን መርጃና እንክብካቤ ማእከል ለማቋቋም ይረዳው ዘንድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድጋፍን እንዲቸረው «የፓርኪንሰን ፔሸንት ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ» ጠየቀ።
የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ክብራ ከበደ በኢትዮጵያ ለ9ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ19ኛ ግዜ የተከበረውን የዓለም የፓርኪንሰን ቀን አስመልክቶ ትናንት በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለፁት እስካሁን ድረስ ለፓርኪንሰን ህመምተኞች የተለያዩ ድጋፎች ሲደረጉ ቢቆዩም አሁንም ለታማሚዎች ተጨማሪ ድጋፎች ያስፈልጋል።
እንደ ስራ አስኪያጇ ገለፃ በአሁኑ ወቅት ለታማሚዎች ከሚያስፈልጉ ድጋፎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ህሙማኑን የመርጃና መንከባከቢያ ማእከል ማቋቋም በመሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብሎም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።
ማእከሉን ለማቋቋም የድጋፍ ጥሪ ያስፈለገበት ዋነኛ አላማም በተለይ አስታማሚና የሚያስጠጓቸው ያጡ የፓርኪንሰን ታማሚዎችን በጋራ በማሰባሰብ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግና ከዚሁ ጎን ለጎንም የህክምናና የመድሃኒት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው ብለዋል።
የፓርኪንሰን ህመምን በሚመለከት በክልሎች ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጇ፤ በዚህ ምክንያት በርካታ የፓርኪንሰን ታማሚዎች በር ተዘግቶባቸውና ከማህበረሰቡ ተገልለው እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
ታማሚዎቹ ህመሙን በመረዳት የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች መኖራቸውን አውቀው እንዲጠቀሙ ለማድረግ የቅርንጫፍ ቢሮዎች በተወሰኑ የክልል ከተ ሞች መክፈት እንደሚያስፈልግና ይህንንም ለማድረግ ከመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያስፈለግ ስራ አስኪያጇ አመልክተዋል።
ፓርኪንሰን ዶፓሚነ በተሰኘ ንጥረ ነገር እጥረት የሚከሰትና እየባሰ የሚሄድ የአንጎል (ነርቭ) ህመም ሲሆን በአብዛኛ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ያጠቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በአስናቀ ፀጋዬ