በ1963 ዓ.ም መጀመሪያዎቹ ወራት የታተሙትን ጋዜጦች ለዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን መርጠናቸዋል። በወቅቱ በጋዜጣው ታትመው ለንባብ ከበቁ ዘገባዎች መካከል በሁመራ የሰሊጥ አዝመራ ከመሰብሰብ ጋር የተያያዘ አንድ ዜና ይገኝበታል። ይህ ዘገባ በቅርቡ የአማራ ክልል ሰሊጥ ለመሰብሰብ አንድ ሚሊየን ሰዎችን እንደሚቀጥር ካወጣው ኩነት ጋር ተመሳሳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በዚያን ወቅት ከተዘገቡ አደጋ እና ወንጀል ነክ ዜናዎችን መርጠን እንደሚከተለው ለትውስታ አቅርበናቸዋል።
የሰሊጥ አዝመራ ስለደረሰ 100‚000 የቀን ሠራተኛ በሰቲት ሁመራ ይፈለጋሉ
ጐንደር፤(ኢ-ዜ-አ) የሰቲት ሑመራ እርሻ ልማት የሰሊጥ አዝመራ በመድረሱ ከ100 ሺህ በላይ የቀን ሙያተኞች እንደሚያስፈልገው ትናንት አስታወቀ።
የሰሊጥ መከር ስብሰባ ሥራ መስከረም 20 ቀን 63 ዓ-ም – የሚጀመር ሲሆን፤ በተከታታይም የማሽላ ቆረጣና የጥጥ ለቀማ እንደሚቀጥል ተገልጧል።
የሰቲት ሑመራ እርሻ ልማት የሙያተኛውን የዕለት ምግብ እየቻለ ለጠንካራ ሠራተኛ በቀን ከ6 ብር በላይ አበል እንደሚከፍል ታውቋል። ከዚህም ሌላ በቀን ሠራተኝነት ከየሥፍራው ለሚመጡበት ሠራተኞች የማጓጓዣ እርዳታ የሚደረግላቸው ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ በበጌምድርና ስሜን፤ እንዲሁም ከኤርትራ ጠቅላይ ግዛቶች ከአሥመራ ተነስተው በከረንና በአቆርዳት ለሚመጡት የትራንስፖርት አገልግሎት ተዘጋጅቶላቸዋል።
በዚህ ዓመት በሰቲት ሑመራ የእርሻ ልማት በተለይም የሰሊጥ አዝመራ በሚያስደስት ሁኔታ ላይ ይገኛል። ሰሊጥ እንደሌላው ሰብል ደርቆ ስለማይቆይ በወቅቱ መሰብበሰብ ያለበት መሆኑ ተገልጧል።
ገበሬው የደከመበት አዝመራ በሠራተኞች እጦትና በአንዳንድ ድርጅቶች አለመሟላት ባክኖ እንዳይቀር የሥራ ፍላጐት ያላቸው የቀን ሙያተኞች ወደ ተጠቀሰው ቦታ እንዲሄዱ ክቡር ቢትወደድ አዲሱ መኮንን የወገራ አውራጃ ገዥ በገበሬዎቹ ስም ጠይቀዋል።
(መስከረም 17 ቀን 1963 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
የከርከሮ ሥጋ በልተው 2 ሰዎች ሲሞቱ 42 ታመሙ
ጅማ፤ (ኢ-ዜ-አ) በሊሙ ኮሳ ወረዳ በቦተር በቱ ቀበሌ ኗሪ የሆኑት፤ 44 ሰዎች የከርከሮ ሥጋ በልተው የሞትና የጤና መታወክ ሕመም የደረሰባቸው መሆኑን የሊሙ ኮሳ ወረዳ ተጠባባቂ ገዢ አቶ አስቻለው ከበደ ገለጡ።
ከርከሮውን ባለፈው ሳምንት ውስጥ በፍሎቨር ጠብመንጃ ገድሎ ለሰዎቹ ያከፋፈለው ተፈራ ጐሹ የተባለው ሰው መሆኑ ታውቋል።
የከርከሮውን ሥጋ ከበሉት ሰዎች መካከል፤ ካሣ ጥላሁንና ነጋሽ ወሰና የተባሉ ሰዎች ሲሞቱ፤ ሌሎች ፵፪ ሰዎች ደግሞ በጽኑ መታመማቸው ተረጋግጧል።
ይኸው አደጋ በሰዎቹ ላይ መድረሱ እንደተሰማ፤ የሊሙ ኮሳ ክሊኒክ ጤና መኰንን አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ ወደ ሥፍራው የተላከ መሆኑንና የወረዳው ፖሊስ አዛዥም የአደጋውን ሁኔታ እንዲያጣራ መታዘዙን የወረዳው ተጠባባቂ ገዥ በተጨማሪ አረጋግጠዋል።
(መስከረም 9 ቀን 1963 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ሁለት ሰዎች እንጨት ሲፈልጡ ገደል ገብተው ሞቱ
አሰላ፤ (ኢ-ዜ-አ) በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በጢቾ አውራጃ የአሚኛ ወረዳ ቀርሳ በተባለው ቀበሌ ኗሪ የነበሩ ሁለት ሰዎች ባለፈው ሳምንት የቆሙበት መሬት ተደርምሶ ገደል በመጣል ገደላቸው።
ተፈራ ዘለቀና ወንድሙ አያኔ በተባሉት ሰዎች ላይ ይኸው አደጋ የደረሰው ርቀቱ ፪፻ ሜትር ከሆነ ገደል አፋፍ ላይ ቆመው በመተጋገዝ እንጨት በሚፈልጡበት ጊዜ መሆኑ ታውቋል።
የሰዎቹ አስከሬን በአካባቢው ሕዝብ ርዳታ ወጥቶ ተቀብሯል። ከዚህም ሌላ በዚሁ ጠቅላይ ግዛት በጢቾ አውራጃ በሮቢ ወረዳ ኗሪ የሆነው ሼህ አማል ኢስካ የቀጭኖን ወንዝ ሲሻገር በደራሽ ወሀ ተወስዶ ሞቷል።
ሼህ አማል በወሀ ሙላቱ ተወስዶ የሞተው፤ በአንዲት አህያ ጫት ጭኖ ለመሻገር ሙከራ ባደረገበት ወቅት፤ ድንገተኛ የወሀ ሙላት ስለደረሰበት መሆኑ ታውቋል።
የፉሩሽካ ሌባ 2 ዓመት እሥራት ተፈረደበት
ደሴ፤ (ኢ-ዜ-አ) አሥር ጊዜ በስርቆት ወንጀል ተከሶ የተቀጣው መኰንን ዓሊ፤ ለ፲፩ ጊዜ ሲሰርቅ ተይዞ፤ በ፪ ዓመት እሥራት እንዲቀጣ ተፈረደበት።
ተከሳሹ ለ፲፩ ጊዜ ሰርቆ የተያዘው በደሴ ከተማ ባለፈው ጥር ወር ፷፪ ዓ /ም / ከሌሊቱ ፰ ሰዓት ነው። መኰንን በዚሁ ሌሊት የአቶ ዓመዴ የሱፍ ንብረት የሆነ ፩ ጆንያ ፉሩሽካ ሰርቆ ሲሔድ መያዙ ተረጋግጧል።
ተከሳሹ የከብቶች መኖ የሆነውን ፉሩሽካ ከቤት ሰርቆ በሚያመልጥበት ጊዜ፤ ተከታትሎ የያዘውን አደም ይመርን ክፉኛ ያቆሰለው መሆኑ በተጨማሪ ተገልጧል።
በዚህም አድራጐቱ ስለተመሰከረበት የደሴ ዙሪያ አውራጃ ፍርድ ቤት ከትናንት በስተያ በዋለው ችሎት በ፪ ዓመት እሥራት እንዲቀጣ ፈርዶበታል ሲሉ ሕግ አስከባሪው ሻምበል ባሻ ጨዋቃ መልካ ገልጠዋል።
(መስከረም 3 ቀን 1963 ከታተመው አዲስ ዘመን)
ነብር የገደለ 30 ብር ተቀጣ
አዲስ አበባ፤ (ኢ-ዜ-አ) መገርሣ ሞጅና የተባለ ሰው፤ በአዋጅ የተከለከለውን ነብር በወጥመድ ገድሎ ቆዳውን ለመሸጥ ይዞ ሲዘዋወር፤ በትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ ወታደር ዮሴፍ ጌታሁን ተይዞ ሰባተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋቱን ስላመነ፤ ፴ ሺህ ብር ተቀጥቶ ብርቱ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑን የሰባተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ገለጠ።
ከተከሳሹ እጅ የተያዘው የነብር ቆዳ ግን በውርስ ለመንግሥት ገቢ መሆኑ ታውቋል።
(መስከረም 9 ቀን 1963 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/ 2015 ዓ.ም