ሾላ ድልድይ አካባቢ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ ሁለተኛ ፎቅ በዛ ያሉ ሰዎች ይታያሉ። አንዳንዱ ተክዞ ሲቆም፤ ሌላው ቁጭ ብሎ ሞባይሉን ይነካካል። አንዳንዶቹ በቡድን ሆነው ያወራሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ በመስታወት የተከፈሉትን ክፍሎች እያለፉ ተቀምጠው ኮምፒውተር የሚነካኩ ሰዎችን ያነጋግራሉ። ጠያቂ የለም የፈለገ ይገባል፤ የፈለገውን ያነጋግራል፤ ከዛም ይወጣል።
ከበሩ በስተግራ ያለው ክፍል መዝገብ ቤት ሲሆን፤ በተለምዶ ‹‹ኩርቱ›› በሚባሉ ቢጫ ፌስታሎች ብዛት ያላቸው ፋይሎች ወለሉ ላይ ተበታትነው ተቀምጠዋል። ፋይሎቹ ከኢትዮጵያውያን መሬት ወዳድነት አንፃር የመሬት ጉዳይን የያዙ ናቸው ለማለት ያዳግታል። በአገልግሎት ሰጪዎቹ መቀመጫ ግራና ቀኝ ተሰትረው በግምት ሃያና ከዛ በላይ የሚሆኑ ፋይሎች በቃጫ ታስረው ተቀምጠዋል። አንዳንዱ ሠራተኛ በቀናነት ያስተናግዳል፤ ፋይሉ ሲጠፋ ይበሳጭ እና ተገልጋዩን ሳይቀር ፈልግ ብሎ ያስፈግጋል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ መሰረት ወልዴ (ስማቸው የተቀየረ) ተክዘው ከሚመለከቱት መሃል ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ መዝገብ ቤት አካባቢ ከፍተኛ ችግር በመኖሩ የሌሎቹንም ሥራ እያበላሸው ነው። ፋይሎችን ፈርሞ እና መዝግቦ በሥነሥርዓት ማስቀመጥ ቢገባም ይህ እየሆነ አይደለም። ትልልቅ ተፈላጊ ፋይሎችን እንደአልባሌ እቃ መቀበልና እንደተራ ነገር ጠረጴዛ ስር ማስቀመጥ ይስተዋላል።
ወይዘሮ መሰረት «ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሰው ለመጉዳት ቢፈልግ ወይም ሌላ ጥቅም የማግኘት ዓላማ ቢኖረው የፈለገውን ፋይል ሰርቆ መውሰድ ይችላል። ያለው ዝርክርክነት ይህን ከሚያክል አካል ፍጹም የማይጠበቅ ነው።» ይላሉ።
ወይዘሮ መሰረት እንደሚናገሩት፤ እርሳቸው ፍላጎታቸው ግንባታ ማከናወን ነው። ለግንባታው ደግሞ በአዲስ መልክ ፈቃድ ማደስ ይኖርባቸዋል። ይህን አገልግሎት ለማግኘት የክፍለ ከተማውን መሬት አስተዳደር አልፈው ወደ ከተማ አስተዳደሩ መሬት ልማት እና ማኔጅመንት ሲመጡ ማሟላት ያለባቸው ከተነገራቸው በኋላ ቅድመ ሁኔታውን አሟልተው ሲገኙ ፋይላቸው እንደተራ ነገር ጠፍቷል ተባሉ።
‹‹ግንባታውን የማከናውነው ከባንክ ብድር በመውሰድ ነው፤ የፋይሉ መጥፋት ህይወቴ ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም›› ይላሉ ወይዘሮ መሰረት። መዝገብ ቤት ያሉት ሰዎች ከተቋሙ ተገቢው ግብዓት የቀረበላቸው እንደማይመስላቸው፤ የዕውቀት እና የአቅም ችግርም አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው የጠቆሙን።
ሌላው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ተገልጋይ እንደሚናገሩት፤ ፋይሎች ተስተካክለው ባለመቀመጣቸው ፋይል ጠፍቶባቸው፤ የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም። ሠራተኞቹም ሆነ አመራሮቹ ቀና ሆነው ቢያገለግሏቸውም፤ ነገር ግን ፋይሉን ማግኘት አልተቻለም።
ግለሰቡ ድርጅት የሚያስተዳድሩ መሆኑን ጠቁመው፤ የፋይሉ መጥፋት በሠራተኞቻቸው ጉሮሮ ላይ ብቻ ሳይሆን በእርሳቸው እና በቤተሰቦቻቸው የወደፊት ህይወት ላይም የሚኖረው ጉዳት ከባድ መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹ ፋይሉ በህይወቴ ላይ ወሳኝ በመሆኑ ወደ ደጅ ወጥቼ የማገኝበትን መንገድ በማጠያየቅ ላይ ነኝ። ያገኘሁት መልስ ‹አቧራ ጠራጊዎችን ፈልግ› የሚል ነው። ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም›› ብለውናል።
ሌላዋ ተገልጋይ የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሜሮን አያሌው ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በመሬት ዘርፍ ላይ ያለው አገልግሎት አሰጣጥ አሁንም በችግር የተጨማለቀ ነው።
ኃላፊዎቹም ሆነ ባለሙያዎች መመሪያን ከማወቅ ጀምሮ በእያንዳንዳቸው ጉዳዮች ላይ የዕውቀት እና የብቃት ችግር ስላለባቸው ለመወሰን ይቸገራሉ። አንዳንዶች ደግሞ የቀናነት ችግር አለባቸው። ውሳኔ ካልሰጡ እና ተገልጋዩ በውሳኔው ካልረካ ቅሬታ ማቅረብ ቢችልም፤ የቅሬታው አቀራረብ ባለሙያውም ሆነ ኃላፊው ውሳኔ ያልሰጠበትን ምክንያት ጠቅሶ እንዲፈርሙ ይጠይቃል። ሆኖም አንዳንድ
ባለሙያዎች እና ኃላፊዎች ውሳኔ ያልሰጡበትን ምክንያት ጠቅሰው፤ ለመፈረም ፈቃደኛ የማይሆኑበት ጊዜ አለ። የመሬት አስተዳደር ላይ የባለሙያዎችም ሆነ የኃላፊዎች በየጊዜው መቀያየር ተገልጋዮችን እያንገላታ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም ሰዎች ሌሎች መንገዶችን እንዲጠቀሙ የሚገፋፋ መሆኑን ነው ያብራሩልን።
ሌሎች ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ ወይዘሮ ወይንሸት አሰፋ እና ወይዘሮ መሰለች አሰፋ እንደሚናገሩት፤ ጉዳያቸው ዓመታትን የፈጀ ነው። አሁን ላይ ውሳኔ አግኝተዋል። ሆኖም ውሳኔው ‹‹ተቋሙ አጥፍቷል። አሁን ምንም ማድረግ ስለማይቻል ለወደ ፊቱ ትምህርት ይሆናል የሚል ነው። እኛ ግለሰቦቹ በተቋም ጥፋት መቀጣት አለብን ወይ?›› ካሉ በኋላ፤ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የፍትሃዊነት ችግር መኖሩን አመላክተዋል።
በቢሮው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ ንጉሱ ተሾመ እንደሚገልፁት፤ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቢሮ ከለያቸው ችግሮች መካከል ፋይል መጥፋት አንደኛው በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ ለመሥራት ታቅዷል።
ፋይል ስካን እየተደረገ እስከማደራጀት የዘለቀ ሥራ ከክፍለ ከተማ ጀምሮ እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ በከተማ አስተዳደሩ መሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮም የሚቀጥል ይሆናል። የተገልጋዮቹ አቤቱታም ተገቢነት አለው። ያም ሆኖ ግን ፋይሉ የጠፋበት ሠራተኛ ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ አለ።
በባለሙያዎች እና በአመራሮች አቅም እና የዕውቀት ችግር ላይ ለቀረበው አቤቱታም አመራሮች አንዳንዶቹ አዲስ በመሆናቸው ጉዳዩን በዝርዝር አይተው በአግባቡ ለመወሰን ጊዜ የሚወስድባቸው ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ። በተገልጋዮች በኩልም ከበፊት ጀምሮ በተደጋጋሚ አይቻልም የሚል ምላሽ የተሰጣቸው እና ፋይላቸው የተዘጋ ሰዎች ሳይቀሩ በተደጋጋሚ የሚመጡበት ሁኔታ በመኖሩ እና የእነርሱ ጉዳይ እስከሚታይ ጊዜ እንደሚፈጅም ይገልፃሉ።
አቶ ንጉሡ አንዳንዶቹ ተገቢ ጥያቄ ያላቸውም ረዥም ጊዜ የሚፈጅበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ ሆኖም በርካታ ምላሾች እየተሰጡ ውሳኔዎችም እየተላለፉ መሆኑም መዘንጋት እንደሌለበትም ነው የተናገሩት።
በተቋሙ በኩል ከህግ ውጪ የሚሠራ እና የተፈጠረ ስህተት ካለ ግን ተቋሙ ትምህርት ይወስዳል የሚል ምላሽ ብቻ በቂ አለመሆኑን በመግለፅ፤ ይህ ምላሽ የተሰጣቸው ተገልጋዮች ጠይቀው፤ ስህተቱን የፈጠረው አካል ባለሙያም ሆነ አመራር መጠየቅ እንዳለበትም አመልክተዋል። በቅሬታ አሰጣጥ በኩል ውሳኔ ሳይሰጥ ቅሬታው ላይ አልፈርምም፤ ውሳኔውን ያልሰጠሁበትን ምክንያትም አልገልፅም የሚል አካል ካለ ወደ በላይ አመራር መጠየቅ የሚቻል መሆኑንም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በምህረት ሞገስ