አዲስ አበባ፡- የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤቶች እና ኮንስትራክሽን ፅህፈት ቤት፣ የመሬት ልማት ማኔጅመንት እንዲሁም የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት በጋራ ለዘጠኝ ሺ የቀበሌ ቤቶች ካርታ ማዘጋጀታቸውን የአራዳ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር አስታወቀ።
በክፍለ ከተማው የተቀናጀ የመሬት መረጃ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ፈይሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደናገሩት፤ የክፍለ ከተማው ቤቶች እና ኮንስትራክሽን ፅህፈት ቤት እንዲሁም የክፍለ ከተማው የመሬት ልማት ማኔጅመንት የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት በጋራ ለቀበሌ ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ።
እንደ አቶ ከፍያለው ገለፃ፤ የወረዳው ቤቶች እና ኮንስትራክሽን መረጃዎችን ያደራጃል፤ የኔ የሚላቸውን ቤቶች ፋይል ፈጥሮ ለይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ይልካል።
በመረጃው መሰረት ለአሰራር እንዲመች ከሁለቱ ፅህፈት ቤቶችና ከይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ተውጣጥቶ የተዋቀረው የባለሙያዎች ቡድን መረጃውን መሰረት አድርጎ ልኬት ያካሂዳል፤ መረጃው ተደራጅቶ ወደ ህትመት ይገባል። በመጨረሻም ካርታው ለሚገባው አካል ይሰጣል። ይህን መሰረት በማድረግ ከመብት ፈጠራው ቀጥሎ በይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ይመዘገባል ብለዋል።
የይዞታ አስተዳደሩ ከልኬት እና ከካርታ ሥራ ውጪ ከባለቤትነት ጋር ተያይዞ ያለውን ክርክርና ዝውውርን የተመለከቱ ሌሎች ጉዳዮችን እንደማያይ የተናገሩት አቶ ከፍያለው፤ እነዚህ ጉዳዮች የሚጠሩትና ፋይሎቹ የሚደራጁት በወረዳ ደረጃ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አቶ ከፍያለው ወረዳው ቤቱን ማን እንደሚኖርበት አጣርቶ መረጃ አደራጅቶ ለክፍለ ከተማው ይልካል፤ የክፍለ ከተማው ባለሙያዎች ቦታው ድረስ በአካል በመሄድ ከማረጋገጥ ባሻገር ልኬት በማካሄድ ካርታ እንዲታተም ያደረጋል ብለዋል።
አቶ ከፍያለው ለቀበሌ ቤቶች ካርታ መሰራቱ በከተማ ውስጥ ያሉ የቀበሌ ቤቶች ይዞታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሲሆን፤ በቀበሌ ቤቶች አካባቢ የሚስተዋለውን ቤቶቹን በማይገባ መልኩ ከአንዱ ወደ ሌላው የማዘዋወር ሁኔታን እንደሚከላከልና ለሚታወቅ አካል በተገቢው መልኩ ለማስተላለፍ እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ከሚፈጥረው መብት ባሻገር የመሬት ምዝገባ ተቋምም እነዚህን ይዞታዎች እንደሚመዘግብ አስታውሰው፤ ይህ በአገር አቀፍ ደረጃ እያንዳንዷን ቁራሽ መሬት ለማወቅም የሚደረገውን እንቅስቃሴም ያግዛል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በምህረት ሞገስ