አዲስ አበባ፡- ከባለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ቡና በዝቅተኛ ዋጋ ውስጥ ሲወድቅ ዘንድሮ የመጀመሪያው መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሳኒ ረዲ፤ ቡና ከባለፉት 15 ዓመታት ወዲህ በዝቀተኛ ዋጋ ለገበያ ሲቀርብ ዘንድሮ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸዋል። ለዋጋው መውረድ በርካታ ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል ያሉት አቶ ሳኒ ከዋና ዋናዎቹ መካከል ትልልቆቹ የዓለም ቡና ገዢ ኩባንያዎች ትርፋማነታቸውን ለማስጠበቅ መዋሃዳቸውና በዚህ ምክንያት ደግሞ ገበያውን በጋራ የመወሰን አቅማቸው በመጨመሩ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ቡና አምራች አገሮች ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ገልፀዋል።
እንደ አቶ ሳኒ ገለጻ፤ ሌላው ዘንድሮ የብራዚልና ኮሎምቢያ ቡና ችግር ይገጥመዋል የሚል ትንበያ ስለነበር ገዢ አገሮች ከፍተኛ የሆነ የቡና ምርት ይዘዋል፤ ሆኖም ምንም ችግር ሳይገጥም በርከት ያለ ቡና ኢትዮጵያን ጨምሮ በሁሉም ቡና አምራቾች ዘንድ ተመርቷል፤ እነዚህ ሁኔታዎች የቡና ግብይቱን እንደጎዱት ገልጸዋል።
ቡና በብዛት ተመርቷል፣ ተዘጋጅቷል ግን ወደ ውጭ አገር እየተላከ አይደለም ያሉት አቶ ሳኒ፤ ‹‹አዳዲስ ገበያዎችን መፈለግ አለብን ብለን ሌሎች የገበያ ዕድሎችን የመፈለግ ስራን ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀናጅተን በመስራት ላይ ነን።›› ብለዋል። ይህም ቢሆን ግን ቡና በአስራ አምስት ዓመት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው እየወረደ መምጣቱን ጠቁመዋል።
«ዋጋ ተቀባይ እንጂ ዋጋ ተደራድረን የምንወስን አይደለንም» የሚሉት አቶ ሳኒ፤ ይህን ለማሻሻል ባለፈው ዓመት ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የተጀመረ ስራ መኖሩን አስታውሰው፤ ሥራውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አቶ ሳኒ ተናግረዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ችግሩን የሚከታተል ስትራቴጂ እየተቀረፀ ነው። በዋናነትም ቡናን በጥሬው ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ መላክ ጎን ለጎንም አዳዲስ የገበያ አማራጮችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንዲሁም የስብሰባና የቱሪዝም ማዕከል ናት። እድሉን ለቡና ገበያ መጠቀም ያስፈልጋል፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የግል ዘርፉ የነቃ ተሳትፎ ማድረግና አጋጣሚውን መጠቀም ከማስፈለጉም በላይ መንግስት ብድር የማቅረብ ገበያን የማስተሳሰር ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
የቡና የውጭ ንግድ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን የ 7 ሺ 628 ነጥብ 8 ቶን እንዲሁም በገቢ የ 61 ነጥብ 34 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፖርት ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በእፀገነት አክሊሉ