ሰባ ደረጃ ወጣ እንደተባለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር መስማትና ማየት የተሳናቸውን ታዳጊዎች ራሳቸውን እንዲችሉ የሚረዳ የሕይወት ክህሎት ሥልጠናን እንዲሁም ለአዋቂዎች የሙያ ሥልጠናን የሚሰጥ ተቋም ነው:: ሹራብና ብሩሽን የመሰሉ መገልገያዎች መሥራትን ያስተምራል:: ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ዜጎች መሥራት አይችሉም ከሚለው የተሳሳተ አመለካከትም ይታደጋል::
ወይዘሪት ሮማን መስፍን ይህንን ማህበር መስራች ናቸው:: ዋና ዳይሬክተር ሆነውም ያገለግላሉ:: እሳቸውም የመስማትና የማየት ችግር ያለባቸው ከመሆኑ አንጻር ወገኖች አደባባይ ወጥተው ድምጻቸው እንዲሰማ በየዘርፉ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑም ለማድረግ ማህበሩን ከመመስረት ጀምሮ ጠንክረው እየሠሩ ነው:: እዚህ እንዲደርስም ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል:: እኛም በዚህ ሥራቸው ያመጡትን ለውጥ በማየትና ወደፊትም የሚሠሯቸውን የሥራ እቅዶች በመገንዘብ ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ አድርገናቸዋል::
ወይዘሪት ሮማን መስፍን ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ልደታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው:: ተወልደው ባደጉበት አካባቢ በተለይም እስከ አራት ዓመት ዕድሜያቸው ድረስ በጣም ጤናማ፣ ቀልጣፋ߹ ተጫዋችና ተግባቢ ነበሩ:: ከአራት ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ግን የሕይወታቸው መስመር ተቀየረ:: ምናልባትም በጣም ከባድ የሚባል አጋጣሚ ገጠማቸው:: «…እናትና አባቴ ወደዚህች ምድር ሲያመጡኝ ሲወልዱኝ ሙሉ ጤንነት ይዤ ነው:: እስከ አራት ዓመት ተኩል ዕድሜዬ ድረስም ከእኩዮቼ ጋር የምጫወትና የምማር ነበርኩኝ:: አራት ዓመት ተኩል ሲሆነኝ ግን ያላሰብኩት ሁኔታ ተፈጠረ:: ከትምህርት ቤት ስንመጣ በጣም ብዙ በጎች አይቼ ፈራሁና በመካከላቸው ስሮጥ ወደኩ:: በወቅቱ የወደኩበት ቦታ ላይ የአጥር ሽቦ ነበር፤ ለነገሩ የበጎቹም ቀንድ ትልልቅ ነበር፤ በመካከል ዓይኔን ምን እንደወጋኝ ሳላውቅ ህመም ተሰማኝ:: ቤተሰቦቼ በአቅራቢያው ስለነበሩ ወዲያው ወደህክምና ወሰዱኝ›› በማለት ለአካል ጉዳት የዳረጋቸውን አጋጣሚ ያስታውሳሉ::
ጉዳቱን የተመለከቱት ቤተሰቦቻቸው በአፋጣኝ ወደህክምና ተቋም ወሰዷቸው፤ ዓይናቸውን ለማዳን በጣሙን ደፋ ቀና ብለዋል:: ከህክምናው ጎን ለጎን ጸበልም ሞክረዋል:: ስፔሻሊስት ሀኪም አለ በመባሉ አስመራ ድረስ ሄደዋል:: ሆኖም ያሰቡት ነገር ሊሰምርላቸው አልቻለም:: በወደቁበት ወቅት የወጋቸው ነገር በመኖሩ አንድ ዓይናቸው ጠፋ:: ይባስ ብሎ የጠፋውን ዓይን በማስወገድ ሁለተኛውን ዓይናቸውን ለማትረፍ ቤተሰቦቻቸው ጥረት ቢያደርጉም በወቅቱ የህክምና ባለሙያዎች «ሕፃን ስለሆነች ማደንዘዣ አትችልም 12 ዓመት ሲሆናት ትምጣ » በማለታቸው ሙከራው ሳይሳካ ቀረ ::
ቤተሰቡ ቢደናገጥም አባታቸው የተማሩ አክስቶቻቸው እርሳቸውን ከችግሩ ለማላቀቅ የሚፈልጉ በመሆናቸው ብዙ ተረባረቡላቸው:: ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙሪያም ሰፊ ውይይትን ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ መረጃዎችን ከየአቅጣጫው አሰባስበው ወይዘሪት ሮማንን የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ወደሰበታ መርሃ እውራን ትምህርት ቤት ወሰዷቸው:: በዚያም ትምህርት እንዲጀምሩ አደረጓቸው::
ትምህርት ቤት ገብተው እየተማሩ ሌላኛው ዓይናቸው ማየት ተሳነው:: ይህም ሆኖ ግን ሮማን ትምህርታቸውን በአግባቡ ይከታተላሉ:: የደረሰባቸው ጉዳት ዓይናቸው እንዳያይ ማድረጉን እንጂ ተጨማሪ ችግር ይዞባቸው እንደመጣ የሚያውቁት ነገር አልነበረም:: ነገር ግን የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው በርቀት ሆነው ሲጠሯቸው አይሰሙም:: ይህንን የተገነዘቡት ቤተሰቦቻቸው በባለሙያ ሊያሳዩዋቸው ወደ ጤና ተቋም ይዘዋቸው ሄዱ ውጤቱም በወደቁበት ወቅት ዓይናቸው ሲጎዳ አብሮ የተጎዳ የነርቭ ክፍል እንዳለና ጆሯቸውም እንደማይሰማ ተነገራቸው:: አሁን ወይዘሪት ሮማን ለተደራራቢ የአካል ጉዳት ተጋልጠዋል:: ከዚህ በኋላ በትምህርታቸው ለመቀጠል ከፍ ያለ የቤተሰብ እንዲሁም የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ እገዛና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል::
«…የማየት የመስማት አካል ጉዳት እንዳለብኝ ከተረጋገጠ በኋላ መምህራን በትምህርት ቤቱ የነበሩ ሞግዚቶች ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ይንከባከቡኝ ነበር:: መምህራን በትምህርት ክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት ምን ያህል እንደምከታተልና እንደምረዳ ይቆጣጠሩኛል:: ከዓይነስውራን ጋር በመሆን በጥሩ ሁኔታ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ተማርኩ» ይላሉ ሂደቱን ሲያስታውሱ::
ሰባተኛ ክፍል ሲደርሱ ግን ከዓይናማዎች ጋር ተቀላቅሎ መማር ግዴታቸው ሆነ:: ለእሳቸው በጣም ከባድ ጊዜ ነበርም:: ምክንያቱም በፊት ላይ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ 15 እስከ 20 ተማሪ ብቻ ስለሚማር መምህራን በሚረዱት መልኩ ቀርቦ ያስረዷቸዋል:: ይህ ደግሞ በቀኝ ጆሯቸው እየሰሙ የክፍል ተሳትፎ ሁሉ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል:: በግቢው ውስጥም ከልጆች ጋር እኩል ተጫውተው ተደስተው ይውሉ ነበር:: እዚህ ግን ያንን ነገር ማግኘት አቃታቸው፤ ሁሉም ነገር ለእሳቸው አዲስ ሆነ:: ከባድ ጊዜን ለማሳለፍም ተገደዱ::
«…ከዚያ ሁሉ እንክብካቤ ወጥቼ በጣም ከተመቸኝ የትምህርት አካሄድ ተለይቼ ስመጣ ሁሉ ነገር ከበደኝ :: አሁን በአንድ ክፍል ውስጥ 60 እና 70 ተማሪ ከመኖሩም በላይ ከዓይናማዎች ጋር ተቀላቅዬ እንድማር ሆንኩ:: ይህ ደግሞ በጣም ከባድ ነው፤ በጣም የሚገርመው ነገር አስተማሪው የሚያስተምረውን አንድም ቀን ሰምቼው አላውቅም:: እሱም አናግሮኝና ጠይቆኝ አያውቅም:: ስለሚያስተምረው ትምህርትም የማውቀው ነገር ባለመኖሩ በጣም አዝንና አለቅስ ነበር» በማለት ሁኔታውን ያስታውሱታል::
ወይዘሪት ሮማን ለዚህ ችግር እጅ አልሰጡም:: ይልቁንም መምህሩ ሲያስረዳ ባይሰማቸው የትምህርቱን ፍሬ ነገር ለመጨበጥ የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ:: አንዱ ዓይነስውራን የሆኑ ነገር ግን መስማት የሚችሉ ጓደኞቻቸውን መጠቀም ነው:: እንዲያግዟቸውና ከእነሱ ጋር አብረው እንዲያጠኑ በመጠየቅ ትምህርቱን በሚገባ እንዲረዱት ሆነዋል:: ከክፍል ክፍል እየተዘዋወሩ እስከ 12ተኛ ክፍል መማር ችለዋልም:: ከዚህም በላይ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እየተማሩ ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው ያመጡት ውጤት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ያስገባቸው ነበር:: ነገር ግን በመለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የገጠማቸውን ነገር ሲያስቡት «ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ምን ልሆን? ማንስ ዞር ብሎ ሊያየኝ» በማለት ውጤታቸውን ይዘው መቀመጥን መረጡ::
«…የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስጄ ያመጣሁት ውጤት በጣም ጥሩ የሚባል ነበር፤ ወደ ዩኒቨርሲቲም ሊያስገባኝ ይችላል:: ነገር ግን በመለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያላገኘሁት የመምህራን እገዛ እዛማ ስሄድ ማን ዞር ብሎ ሊያየኝ ይችላል በሚል ፈራሁ:: በመሆኑም ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባት ይልቅ አለመግባቱን መረጥኩ» ይላሉ::
መርሃ እውራን ትምህርት ቤት እያሉ ለእጅ ሥራ ትልቅ ፍቅር ነበራቸው፤ በተለይም ሹራብ ሥራን በጣም ወደውት ነበር የሚሠሩት:: እናም ከ12ተኛ ክፍል በኋላ ሹራብ እየሠሩ ለገበያ ያቀርባሉ:: ብዙ ሰዎች ያበረታቷቸውና ይደግፏቸውም ነበር::
«…እኔ ከሰው ጋር ለመግባባት አብሮ ለመኖር ከፍ ያለ ፍላጎት አለኝ፤ ራሴንም አልደብቅም፤ የሚገርምሽ ነገር ግራ ጆሮዬ ሙሉ በሙሉ አይሰማም፤ የቀኙ ጆሮዬ ትንሽ ትንሽ ይሰማልኛል፤ እናም ሰዎች መንገድ ስጓዝ በቀኝ በኩል እንዲይዙኝ አደርጋለሁ:: ይህንን የማደርገው ደግሞ ቢያዋሩኝ እንኳን ለመስማትና መልስ ለመስጠት ነው:: ሰውም በጣም ያግዘኛል፤ ከሁሉም በላይ ትልቅ ደጋፊዬ አባቴ ነበር:: ነገር ግን እሱ በሞት ተለየኝ:: ይህ ለእኔ በጣም ከባድ ሆነ» ይላሉ አሁናዊ ሁኔታቸውን ሲያስረዱ::
ይህ ዓይነቱ የመግባባት የመሥራት ፍላጎት ቢኖራቸውም ትምህርታቸውን ባለመቀጠላቸው ቤት ቁጭ ብለው እንዲውሉ አደረጋቸው፤ ኀዘኑም በዚያው መጠን ጎዳቸው:: አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ቢሰማቸውም ምን የሚለውን ነገር ግን አያውቁትም:: ኋላ ላይ በሚያውቋቸው በትልልቅ ደረጃ ላይ በሚገኙ አይነስውራን አማካይነት አይነ ስውራን ማህበር የብሬል መጽሐፍት አራሚነት (ፕሩፍሪደር) ሆነው እንዲቀጠሩ ሁኔታዎችን ተመቻቹላቸው::
ሥራውን ማግኘታቸው ከቤት እንዲወጡ ምክንያት ቢሆናቸውም ዘላቂ ደስታን ግን ሊፈጥርላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም እርሳቸው በተደራራቢ የአካል ጉዳት ውስጥ በመሆናቸው ወደከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብተው እንደ ጓደኞቻቸው ትልቅ ደረጃ ላይ አልደረሱም:: እናም ሁኔታው እጅግ ይረብሻቸው ጀመር:: በሌላ በኩል ደግሞ በቢሮም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ሲጫወቱ ባለመስማታቸው ጥሩ ስሜት አይሰማቸውም:: በዚህም ውስጣቸው እየተጎዳ በራስ መተማመናቸው እየከዳቸው ነበር:: ይህም ሆኖ ይሠራሉ::
‹‹ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው›› ይሉት ዓይነት ሆነና ወይዘሪት ሮማን በሥራቸው ላይ እያሉ የትምህርት ክፍሉን የሚቆጣጠሩ ካናዳውያን መጡ፤ ከመጡት መካከል አንደኛዋ ሮማን ሁለት ጉዳት ያለባቸው በመሆኑ በአራሚነታቸው አልተማመንም ወይ ምንጣፍ አልያም ቡርሽ ክፍል ይግቡ በማለት ሃሳብ አቀረበች:: ይህ ሀሳብም ለእርሳቸው በጣም ያስከፋና ያስለቀሳቸው ነበር:: በዕድላቸው የተማረሩበትም::
በሥራ ባልደረቦቻቸውና በቦርዱ ከፍ ያለ ክርክር ምክንያት ከቦታቸው ሳይነሱ የቀሩት እንግዳችን፤ ለችግር እጅ ሰጥተው እንደማያውቁ የሚያስረዳላቸው ብዙ ተግባራት አሉ:: ይህም ‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል›› እንደሚባለው ያልተማመኑባቸው አገራቸው ሲገቡ የተማመኑባቸው ደግሞ ሥራውን እንዲቀጥሉ ማድረጋቸው ነው:: በዚያ ላይ ወይዘሪት ሮማን ዛሬ ላሉበት ሁኔታ መንገድ የከፈተ ዕድል አጋጥሟቸዋል::
«… የአይነስውራን ብሔራዊ ማህበር ተወካይ በኡጋንዳው ዓለም አቀፍ አካል ጉዳተኞች ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ሆነ፤ በስብሰባው ላይም በቀጣይ የዓለም አቀፍ ማየትና ማስማት የተሳናቸው ፌዴሬሽን የሚቀላቀሉ ማየትና መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ከየአገራችሁ መርጣችሁ እንድትልኩ፤ ምክንያቱም ‹ናይሮቢ ላይ ሄለን ኪለር ኮንፈረንስ ይኖራል፤ እንደ አፍሪካም ፌዴሬሽን ይቋቋማል› ተብሎ መልዕከት ተላለፈ» በማለት የአዲስ የሕይወት ምዕራፍ ጅማሯቸውን ያነሳሉ::
በወቅቱ በኢትዮጵያ ደረጃ የሚታወቁት እሳቸው ብቻ ነበሩና የአይነስውራን ብሔራዊ ማህበሩ ፕሬዚዳንት ከኡጋንዳ ሲመለሱ «አንድ ስብሰባ ትጋበዣለሽና ተዘጋጂ » የሚል መልዕክት አስተላለፉላቸው:: ለጉዳዩ አዲስ የሆኑት ሮማንም ምን ላደርግ ነው የምሄደው? ሄጄስ ምንድን ነው የምናገረው? የሚለው ነገር በእጅጉ አሳሰባቸው:: እንደተባለውም አልቀረም የግብዣ ወረቀቱ ተላከ:: ሮማንም ፓስፖርት አወጡና ዝግጅት ጀመሩ:: የግብዣው ወረቀት ላይ ደግሞ የሚላከው ሰው ማየትና መስማት የተሳናቸው የአካል ጉዳተኞች ያሉበትን ሁኔታ የሚገልጽ የ15 ደቂቃ ገለጻ ማድረግ እንዳለበት ያዛል:: ይህ ሁሉ ነገር ቢያሳስባቸውም ሮማን ግን ሁኔታውን በቦታው ሄደው ለመመልከት ተነሱ::
«…በወቅቱ ናይሮቢ መሄዱ በተለይም ምንም ትኩረት ካልተሰጠው የመስማትና የማየት ችግር ወይም ተደራራቢ ጉዳት ያለባቸው ሰዎች አንጻር መልካም ቢሆንም እኔ ግን የንግግር ልምድ የሌለኝ መሆኑ ሄጄ ምንድን ነው የማደርገው የሚለው ነገር አሳሳቢ እንዲሆንበኝ አድርጎ ነበር:: ነገር ግን የ15 ደቂቃ ንግግሩን ልምድ ያላቸው የአይነስውራን ማህበር ሰዎች በአገራችን በዘርፉ ምንም እንዳልተሠራ ለወደፊቱ ለመሥራት ከታሰበ እኛም ተባባሪ እንደምንሆን የሚገልጽ ጽሑፍ አዘጋጁልኝ፤ በዚህም ነገሮች ቀለል አሉኝ » ይላሉ::
ናይሮቢ ሄደው በስብሰባው አዳራሽ ሲገቡ «ከኢትዮጵያ የመጣች እንግዳ» ተብለው የተደረገላቸው አቀባበል ሰዎች እሳቸውን ለማናገር ያሳዩት ፍላጎትን ሲመለከቱ ፍርሃታቸው ሁሉ ከእሳቸው ራቀ:: በሌላ በኩል ደግሞ ከእሳቸው የባሱ ማየት፣ መስማትና መናገር የማይችሉ በሁለት አስተርጓሚ እጃቸው እየተነካኩ የሚግባቡ ሰዎች መኖራቸውን ሲሰሙ ትልቅ ተስፋም ደስታም ተሰማቸው:: ተደራራቢ ችግሩ የእሳቸው ብቻ እንዳልሆነም ገባቸው:: በሰብሰባው ላይም ተራቸው ሲደርስ ያዘጋጁትን ገለጻ «ፕረዘንቴሽን» ይዘው መድረኩ ላይ ወጡ፤ ያለምንም ፍርሃትና መደናገጥ ያለውን ነገር ከተመደበውም ሰዓት ባጠረ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለውን ማየትና መስማት የተሳናቸው ወገኖች ችግር እንዲገነዘቡ አድርገው አቀረቡ:: ይህ ደግሞ ለእርሳቸው ትልቅ ድልም ተስፋና መነሳሳትም የፈጠረላቸው ነበር::
በሌላ በኩል የናይሮቢው ስብሰባ ላይ ለአፍሪካ ፌዴሬሽን አመራር መረጣ እንዲካሄድ ሆነ፤ በዚህም ማላዊ߹ ደቡብ አፍሪካና ኬንያን ወክለው በቦታው የተገኙ ተመረጡ:: እነዚህ ሰዎች ይመረጡ እንጂ ሁሉም ተሳታፊ ወደአገሩ ሲመለስ ማየትና መስማት የተሳናቸውን ወገኖች የሚያግዝ ማህበር እንዲያቋቁሙ የቤት ሥራ ተሠቶት ነበር:: እናም እርሳቸውም በናይሮቢው ኮንፈረንስ ላይ የተሰጣቸው የቤት ሥራ መሥራት ጀመሩ:: ከስድስት ወራት በኋላ ፊላንድ ላይ በሚካሄደው ጉባኤ የደረሱበትን ለማሳወቅም ደፋ ቀና እያሉ ቆዩ::
መድረኩ ላይ ይላሉ ወይዘሪት ሮማን «…ከአፍሪካ፣ ኡጋንዳና ኬንያ እንቅስቃሴውን ጀምረው ነበር፤ ችግሩ ያለባቸውን ሕፃናት እየሰበሰቡ ለቤተሰቦቻቸውም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እየሰጡ ሥራዎችን ቢሠሩም ድህነቱ ግን ከባድ ስለሆነ ሥራቸው ጎልቶ አልታየም:: ወደ ዓለም አቀፉ ሁኔታ ስንመጣ ግን በጣም መልካም ነገር ነው ያየሁት:: ለምሳሌ በአስተርጓሚዎች ብዛት߹ አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አንጻር ብዙ ነገሮች በመንግሥት እንደሚሸፈኑላቸው አይቻለሁ:: » ይላሉ ከስብሰባው የተረዱትን ሲያብራሩ::
«… እነዚህን ሰዎች ከየት ነው የምናሰባስባቸው የሚለው የመጀመሪያው ሥራም ጥያቄ ነበር:: ከዚያ ማህበሩን ለመመስረት ያደረግነው እኔን ጨምሮ የአይነስውራን ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት፣ አንድ ከአንገት በላይ ሀኪምና ሌሎች ሰዎች ያሉበት ስብስብ ፈጠርን:: ከዚያ ማህበሩን ለመመስረት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማመቻቸት የሌሎችን ልምድ የመቅሰም ሥራ ሠራን » ይላሉ::
ከአይነስውራንና መስማት ከተሳናቸው ትምህርት ቤት፣ ከምስራች ማዕከል፣ ከሆስፒታሎች እንዲሁም ከየአካባቢው መረጃን በማሰባሰብ መስማትና ማየት የተሳናቸው ወገኖች እንዲወጡ የማድረግ ሥራው ተጀመረ:: በዚህ ሂደትም ከላይ ከተጠቀሱት እንዲሁም ከሌሎች አካባቢዎች ጥቆማዎች ተበራከቱ:: ጎን ለጎን ደግሞ ስድስት አባላትን የያዘ የመስራቾች ኮሚቴ ተቋቋመ:: ከዚያም የመተዳደሪያ ደንቡን ከተረቀቀ በኋላ ምስረታውን እውን ለማድረግ ጉዞ ወደ ፍትህ ሚኒስቴር ሆነ::
«…በወቅቱ የማህበሩ ምስረታ ሙሉ ኃላፊነት የእኔ ሆነ፤ ውጣ ውረዱ ከባድ ነበር፤ በተለይም ተንቀሳቅሶ ጉዳይ ማስፈጸሙ እጅግ ፈተና ነበር፤ መውደቅ መነሳትም ሁሉ ነበረው፤ የምሄድባቸው ቢሮዎች አንዳንዶቹ የአይነስውራን ማህበር እንዲሁም መስማት የተሳናቸው ማህበር አለ ደግሞ መስማትና ማየት የተሳናቸው ማህበር ምን ያስፈልጋል የሚሉም ነበሩ፤ ነገር ግን ይህ መሰሉ ማህበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለ መሆኑን ማህበራቱ እንዲጽፉልኝ በማድረግ ከዓመት ልፋት በኋላ ማህበሩ ሕጋዊ ፍቃድ አገኘ» በማለት ያለፉበትን መንገድ ይናገራሉ፡፡
ማህበሩ በ1998 ዓ.ም መጨረሻ ምስረታውን እውን አደረገ:: አሁን ደግሞ ሌላ ጉዳይ አለ:: ማህበሩን በሁለት እግሩ እንዲቆም አድርጎ ተደራራቢ አካል ጉዳት ያለባቸውን ወገኖች እንዲጠቅም ማድረግ:: ለዚህ ደግሞ መሰብሰቢያ ቦታ ያስፈልጋል፤ ቢሮም መኖሩ ግድ ነው፤ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች በቶሎ ማሟላት ባለመቻሉ ስብሰባዎች በካፌዎች߹ በመስራች ማዕከል ግቢ ውስጥ እንዲካሄዱ ሆነ:: ይህ ያሳሰባቸው ወይዘሪት ሮማን በወቅቱ መሬት ሸጠው ካገኙት ገንዘብ ላይ 40ሺ ብር ለማህበሩ አስተዋጽዖ በማድረግ ቢሮ መከራየት፣ ኮምፒዩተር የተወሰኑ የቢሮ ወንበርና ጠረጴዛዎችን በማሟላት ሥራቸውን ወደማከናወኑ ገቡ:: አሁን ማህበሩ በሁለት እግሩ ሊቆም ዳር ዳር እያለ ነው:: የተለያዩ እገዛዎችም መምጣት ጀምረዋል:: ከአጋዦቹ መካከል ሆላንዶች ይጠቀሳሉ:: በዓመትም 1ሺህ ዮሮ ሊሰጡ ቃል ገብተውላቸዋል::
«…ሆላንዶች የፈቀዱልን 1 ሺህ ዮሮ የቤት ኪራዩን ይሸፈን ነበር፤ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይም የተወሰነ ድጋፍ ያደርጋል:: በጠቅላላው በሥራ አመራሩ ቦርድና በበጎ ፈቃደኞች አማካይነት ሲሠራ ቆየ፤ በኋላም ከፊላንድ ትሬሽሆልድ የተላከው «ሪኮ» የተባለ ሰው ስለማህበሩ ከተነጋገርን በኋላ እርዳታ እንደሌለን በበጎ ፈቃደኞች ሥራዎች እየተሠሩ እንዳሉ እንዲሁም የምናግዛቸው ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት እንዳላቸው ቤት ለቤት በመሄድ ካየና ገለጻውንም ከሰማ በኋላ አሶሴሽኑ የአቅም ግንባታና ሕፃናትን በማገዙ በኩል ልንደገፍ ይገባል የሚል ሪፖርት አደረገ:: በዚህም 2000 ዓ.ም ፈንድ ለቀቁልን» በማለት ድጋፉ በምን መንገድ እየተደረገላቸው እንደሄደ ያብራራሉ::
ደጋፊዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስምምነት እንዲፈርሙ ሆነ፤ ከዚያ በኋላ ቢሮ ተከራይተው እንዲከፍቱ ተወሰነ:: ለሕፃናት ሴንተርና ለጽሕፈት ቤት አገልግሎት የሚውል ሰፊ ግቢ ያለው የግለሰብ ቤት ሰባ ደረጃ አካባቢ አገኙና ሮማን ህልማቸውን ዳር አሲያዙ:: በ11ሺህ ብር የቤት ኪራይ እየከፈሉ ቢሮውን በጥሩ ሁኔታ አደራጅተው በተለይም ሕፃናት ተገቢውን እገዛ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች አስፈላጊውን ሁሉ አደረጉ:: በቤቱ ውስጥም ሕፃናት እየመጡ እንዲውሉ አዋቂዎችም የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ አመቻቹ:: የሰው ኃይል በመቅጠር ሕፃናቱ የሕይወት ክህሎት ስልጠና ማለትም የእንቅስቃሴ ችግር የአዕምሮ መድከም፤ አመጋገብ ላይና ራስን ችሎ መጸዳዳት አለመቻል ላይ በጠቅላላው ስለ አካባቢያቸው ያላቸውን ነገር መለወጥና ማሳወቅ ላይ በማተኮር ሥራውን ሠሩ::
ሕፃናቱ እንዲንቀሳቀሱ፣ ራሳቸው እንዲመገቡ፣ መጸዳዳት ሲፈልጉ እንዲያሳውቁ፣ መግባቢያ ቋንቋ እንዲያዳብሩ በማድረግ አዕምሯቸው እንዲነቃቃ የማድረግ ሥራ በጥሩ ሁኔታ መሰጠትም ጀመረ:: ይህ ሥራ ደግሞ ሕፃናቱ ላይ ብቻ ያበቃ አይደለም:: ወጣቶችና ሴቶችም የቡና ምንጣፎች፣ እስካርቭ፣ ሹራብ፣ ቀሚስ፣ ካልሲና ሌሎችንም እየሠሩ ራሳቸውን እንዲደጉሙ በማድረግ፤ አባላትና ችግሩ ያለባቸው ልጆች ያሏቸው ወላጆችም ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑም ስልጠና እንዲያገኙ አደረጉ:: በጠቅላላው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በመጠቀም እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን ጋር አብሮ በመሥራት በችግሩ ዙሪያ ጥሩ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረግም ቻሉ:: ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ይሠሩ እንጂ አብዛኛውን የሚገኘው ገንዘብ በቤት ኪራይ የሚጠፋ በመሆኑ ሥራውን ወደፊት ማራመድ ተሳነው:: ግን ሙሉ ለሙሉ በዚህ ሁኔታ አልዘለቀም:: ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ ባደረጉት ከፍ ያለ ትግል አሁን ያሉበትን በዚያው በሰባ ደረጃ አካባቢ የሚገኝ ቤት ሰጣቸው::
«…እንደጀመርን አካባቢ ለወላጆች የትራንስፖርት እየከፈልን ልጆቻቸውን ይዘው ወደማዕከል ያመጡልን ነበር፤ ነገር ግን እነሱም ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ በመሆኑ ሥራቸውን ጥለው ወዲህና ወዲያ ማለት ሳይችሉ ይቀራሉ:: በዚህ መካከል ደግሞ ልጆቹ ይጎዳሉ:: እናም አውሮፓ ህብረት የሚሠሩ ባልና ሚስቶች የድርጅቱን መቋቋም ሰምተው ሊጎበኙን መጡ:: ካዩን በኋላ ምን ዓይነት እገዛ ትፈልጋላችሁ አሉ:: እኔም እነዚህን ሕፃናት ለማመላለስና ለጉዳይ ማስፈጸሚያ አንድ መኪና አግዙን አልኳቸው:: እነሱም ሚኒባስ መኪና ገዝተው ሰጡን:: በሌላ በኩል ደግሞ ካርተር ሴንተር ሌላ አንድ መኪና ድጋፍ አደረገልን» ይላሉ::
አሁን ላይ ትሬሽሆልድ ፊላንድ መስራቹ ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ የድርጅቱ ድጋፉ ተቋርጧል:: ላለፉት አራት ዓመታትም ከተለያዩ ግለሰቦች በሚገኝ ድጋፍ እንዲሁም ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ በሚሰጠው ገንዘብ ነው እስከ አሁን እየሠራ ያለው:: ነገር ግን ወይዘሮ ሮማንና አጋሮቻቸው ተስፋ ባለመቁረጥ ሥራዎችን ወደፊት ለማስኬድ ተደብቀው ያሉና ተደራራቢ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ወደ አደባባይ እያወጡ ነው::
«…ማህበሩ የተቋቋመበት ዋና አላማ ማየትና መስማት የተሳናቸውን ወገኖች ለማብቃት ነው:: አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ ሐረር፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማና ትግራይ ላይ አባላት አሉት:: በቅርንጫፍ ደረጃም ድሬዳዋ߹ ሐረር߹ ሲዳማና ጎንደር ላይ እንቅስቃሴ አለ:: በተለይም በኮቪድ ወቅት ሁሉንም አባላት ለማገዝ ማህበሩ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችንም በየጊዜው ይሰጣል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው መደገፍ የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩ ማህበሩ ያበረታታል» በማለት ማህበሩ የመጣበትን ሂደት ይናገራሉ::
ህልም እውን ሲሆን
ሮማን ህልማቸው ብዙ ነው:: በተለይም በገጠማቸው ተደራራቢ ችግር ምክንያት የሚወዱትን ትምህርት መቀጠል አለመቻላቸው ሁሌም ያስከፋቸው ነበር:: መከፋት ብቻ ሳይሆን የመማርም እቅድ ይይዛሉ:: ግን ደግሞ እንዴት አድርጌ የሚለው ይይዛቸዋል:: ሆኖም የተመኙትን ትምህርት ለማሳካት ዕድል አላጡም:: ለዚህም ማሳያው ይህ ነው::
«…የመማር ህልሜ ከፍ ያለ ነበር:: ነገር ግን እንደልቤ መንቀሳቀስ የማልችል መሆኔ የማታ ትምህርት እንኳን መማር እንዳልችል አድርጎኛል:: አንድ ቀን ግን መካኒሳ ወዳለው መካነእየሱስ ዩኒቨርሲቲ በመሄድ መማር እንደምፈልግ ለዲኑ ነገርኳቸው:: እሳቸውም ታሪኬን ከሚዲያ አይተው ስለነበር በጣም ተደሰቱ፤ መማር እንደምችልም ነግረውኝ መዘገቡኝ፤ ከዚያ ለመምህራኑም፣ ለተማሪዎችም ስለእኔ በመናገር ትምህርት እንድጀምር ሆነ:: መምህራኑም በጣም እያገዙኝ ለሁለት ዓመት ያህል ጀንደር ዲቨሎፕመንት የሚባል ትምህርት ተምሬ ዲፕሎማ አገኘሁ:: በምርቃት ወቅትም ልዩ ሽልማት ከማግኘቴም በላይ መድረክ ላይ ወጥቼ ንግግር እንዳደርግ ተጋብዤያለሁ» ይላሉ::
‹‹ እኔ ህልሜ ብዙ ነው:: በሕይወቴ አንድ አሳክቸዋለሁ የምለው ትልቅ ነገር ማህበሩ ከግለሰብ ኪራይ ተላቆ የመንግሥት ቤት ማግኘቱን ነው:: ሌላው ደግሞ ሕፃናት ቤት ተቆልፎባቸው ከመዋል መውጣታቸው ለእኔ ትልቅ እርካታ ነው:: ምክንያቱም ቤታቸው ሲውሉ የሚያስታውሳቸው በማጣት በብስጭት እጃቸውን እየነከሱ ሲያለቅሱ ነው የሚውሉት፤ እዚህ ሲመጡ ግን የሚሰማቸው ስሜት የተለየ ነው:: ከሁሉም በላይ ደግሞ ቤታቸው በመቀመጥ ተስፋ ቢስ የሆኑ ሴቶችና ወጣቶችን ወደውጭ አውጥቼ የሚችሉትን እየሰሩ እርስ በእርስ በሚያግባባቸው ቋንቋ ሲወያዩ ማየት ለእኔ በጣም ትልቅ ነገር ነው:: ወደፊት ሥራውን ወደ ክልል አስፍተን ለመሥራት አቅደናል እግዚአብሔር ያሳካልን::›› ይላሉም ተስፋቸውን ምን ያህል እውን እያደረጉት እንደሆነ ሲገልጹ::
ተደራራቢ ጉዳት ያለባቸው ሰዎች
አሁናዊ ሁኔታ
ተደራራቢ ጉዳት ያለብን ሰዎች እንደ አገር ታይተናል የሚል ግምት የለኝም:: በጣም ጎልተው የሚታዩትና ድጋፍም የሚደረግላቸው አይነስውራንና መስማት የተሳናቸው ናቸው:: ወደእኛ ሲመጣ አካታች ይባላል ነገር ግን ምንም ነገር የለም:: በየጊዜው ስልጠና ሰልጥኑ ይባላል ነገርግን ለእኛ ስልጠና አይደለም የሚጠቅመን:: ይልቁንም እንደማንኛውም ማህበረሰብ የምንማርበት፣ የምንሠራበት፣ በቴክኖሎጂ ታግዘን ሰው የምንሆነውን ሁኔታ ነው ሊመቻችልን የሚገባው ይላሉም::
ትምህርት ሚኒስቴር እስከ አሁን ለእኛ ምን እያደረገ ነው:: የትኛውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ይሁን ሌላ ሁሉንም አካል ጉዳተኞች በእኩል ቢያዩ፤ የመማር የመሥራት ዕድሎች ቢመቻቹ መንግሥትም እንደ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ከሌላው በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጥና ሊያግዝ ይገባል:: ለምሳሌ የጆሮ ማዳመጫ (ሂሪግ ኤድ ) ይዘው የሚመጡ የውጭ ዜጎች አሉ፤ ግን መሣሪያው ሊደርሰው የሚገባው ለዚህ ማህበር ነበር፤ ነገር ግን ለግለሰብ ነው የሚሸጠው፤ በየመጋዘን እየተቀመጠ ነው የሚበላሸው፤ በመሆኑም ቴክኖሎጂው ማን ጋር ነው መድረስ ያለበት የሚለውን ለይቶ ማወቅና በአግባቡ ማዳረስ ይገባልም ሲሉ ወይዘሪት ሮማን ያስገነዝባሉ::
ሌቦች በማህበሩ ላይ
ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ሌሊት ላይ ከካርተር ሴንተር የተበረከተላቸው ላንድ ክሩዘር መኪና አራቱም ጎማዎቹ እስከ ቸርኬያቸው የተወሰዱ ሲሆን፤ ሚኒባሱም ተወስዶ በክትትል ተይዞ ወደማህበሩ ተመልሷል:: መስኮቶች ተሰባብረው ኮምፒዩተር ፎቶኮፒ ማሽኖችና ሌሎች ንብረቶችም በሌባ ሊወሰዱ ችለዋል:: ማህበሩ በሌለው አቅምም በተለይም የተሰባበሩበትን በርና መስኮቶች ለማስጠገን በርካታ ወጪንም ለማውጣት ተገዶ ነበር:: ምናልባት ሌቦች ይህንን አስነዋሪ ሥራ ሲሠሩ የአካባቢው ማህበረሰብ መተባበር ቢችል ኖሮ እኛም አንዘረፍም፣ አጥፊዎችም ይያዙ ነበር:: ነገር ግን ይህ አልሆነም:: በዚህም በጣም ኀዘን ይሰማኛል ይላሉ::
የቤተሰብ ሁኔታ
‹‹የምኖረው ከእናቴ ጋር ነበር፤ በቅርቡ ግን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፤ እናቴ ለእኔ ሁሉም ነገሬ ነበረችና ከአካል ጉዳቴ ይበልጥ የእናቴ ሞት በጣም ጎድቶኛል:: ምንም እንኳን መስማትና ማየት ለተሳነው ለእንደኔ ዓይነቱ ብቻ መኖር ከባድ ቢሆን እየኖርኩ ያለሁት ግን ብቻዬን ነው:: ወደትዳር አልገባሁም፤ መጀመሪያም አይነስውራን ማህበር ስሠራ እከፋ ፤ አለቅስ ነበር:: ደስተኛም አልነበርኩም፤ ከዚያም በኋላ አባታችን ከሞተ በኋላ እናቴን ለማገዝ ብዙ አደርግ ነበር:: በመጨረሻ ግን ማህበሩ ሲመጣ ሁሉም ነገሬ ለማህበሩ ሰጠሁና ራሴን ማዳመጥ ተውኩ:: አሁን እናቴ ስትሞት ቤተሰብ አለመመስረቴ፣ ልጅ አለመውለዴ እየተሰማኝ ነው፤ በር እንኳን ሲንኳኳ ሰምቶ የሚከፍት ልጅ ማጣቴ ያሳዝነኛል ፤ ግን ያው የቴክኖሎጂ መሣሪያን እየተጠቀሙ መኖር ይቻላል ብዬ ራሴን አሳምኛለሁ» ይላሉ::
ቀጣይ ህልም
ይህ ማህበር በዚህ መልኩ መቋቋሙና እዚህ ደረጃ መድረሱ ለእኔ ትልቅ ደስታን የሰጠኝ ነገር ነው:: መሰሎቼ እኔ የደረስኩበት ደረጃ እንዲደርሱ፤ ሁሉም ከሰው ጥገኝነት ወጥተው ራሱን እንዲችልና እንጀራ እንዲበላ ነው የምፈልገው:: በጠቅላላው ጥሩ ነገር ሠርቼ ማለፍ ምኞቴ ነው ይላሉም::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ህዳር 18 ቀን 2015 ዓ.ም