በአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ ፖለቲካ ወይንም የሥነ መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር እሳቤዎችና ዘየዎች የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙ ስለመሆናቸው ብዙኃኑ ጠቢባን የሚስማሙበት ሃቅ ነው። ይሁን እንጂ ሌሎች የፍልስፍናና የዕውቀት ዓይነቶች፣ ጥበቦች፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀቶችና ሥራዎች ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የዚያኑ ያህል ተፈላጊና አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ከፖለቲካው ባሻገር ሳይንስና ቴክኖሎጂን ሌሎችም ዕውቀቶች ለአገር ዕድገት ያላቸውን ሚና አስመልክቶ የሃሳብ ተጋሪዬ የሆኑት ዶክተር በፍቃዱ ኃይሉ እንዲህ ይላሉ፡-
“….እንደሚታወቀው አገራችን ላለችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰብአዊ፣ የሥነ-ልቦናና የባህል ችግር፣ እንዲሁም የፖለቲካና የርዕይ ችግር የብሔረሰብ መብትን በማወቅ የሚፈታ ነገር አይደለም። የአገራችን ችግሮች ፖለቲካዊ፣ መንግሥታዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የአካባቢ መውደም ወይም መቆሸሽ ጉዳይና እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጥያቄዎች እንደመሆናቸው መጠን ጠቅላላውን፣ በዚያች ምድር የሚኖረውን ሕዝብ የሚመለከቱ ናቸው። ይህም ማለት ያሉት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት፣ በፍልስፍና፣ በሶስዮሎጂ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው።
በሌላ አነጋገር፣ በአገራችን ምድር አፍጠው አግጠው የሚታዩት ችግሮች፣ ማለትም የከተሞች በሥነ-ሥርዓት አለመገንባትና ሕዝባችንም ባልባሌ ቦታዎች እየተሰቃየ መኖር፣ የሚጠጣው፣ የሚቀቅልበትና የሚታጠብበት ንጹህ ውሃ አለማግኘት፣ አስፈላጊው ለሰውነት ገንቢ የሆኑ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በብዛትም ሆነ በጥራት አለማግኘት፣ ለማሞቂያ፣ ለመቀቀያና ለመብራት የሚያገለግል የኃይል ጉዳይ፣ የሕክምናና የትምህርት ጉዳይ፣ ለወጣቱ የሙያ ማሰልጠኛ ቦታ አለማግኘት፣ በየቦታው የሥራ መስክ የሚከፍቱ ትናንሽና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች አለመኖር… ወዘተ እነዚህ ጥያቄዎች በሙሉ ኅብረተሰብአዊ እንደመሆናቸው መጠን የብሔረሰብን መብት በማወቅ የሚፈቱ ሳይሆኑ፣ በጠለቀና ተከታታይነት ባለው የሳይንስ ምርምር ብቻ ነው። ሊያሠራ የሚችል፣ ኃይልን የሚሰበስብና በአገር ውስጥ ያለን የተፈጥሮ ሀብት በሥነሥርዓት አውጥተን በቴክኖሎጂ አማካይነት ለመለወጥና የሕዝባችንን ፍላጎቶች ለመመለስ የምንችለው አንዳች ዓይነት ርዕይ ሲኖረን ብቻ ነው። ”
ታዋቂው የኢንተርፕርነር ምሁር አሰልጣኝና ደራሲ ዶክተር ወሮታው በዛብህ በአንድ ወቅት ለተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት በተዘጋጀ መድረክ ላይ አሜሪካ የምትባለውን ኃያል አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ከፖለቲከኞች በላይ ሳይንቲስቶች፣ ምሁራንና ኢንተርፕርነሮች የነበራቸው ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። እንዲያውም ኃያሏን አሜሪካ የፈጠሯት እንደ ቬንደር ቬልት፣ ጀ.ኬ ሞርጋንና አንድሬው ካርኒጌ የመሳሰሉ በከፍተኛ ደረጃ በሥራ ፈጠራ የተካኑ ጥቂት ግለሰቦች መሆናቸውን “ሜን ሁ ቢዩልት አሜሪካ” የሚል የፊልም ሥራን በማስረጃነት በመጥቀስ በአንድ ግንባታ ሂደት ውስጥ ከፖለቲካ ውጪ የሆኑ ዕውቀቶች ያላቸውን ከፍተኛ ዋጋ አስረድተዋል።
የእኔ አመለካከትም ከዚሁ ብዙ የሚርቅ ስላልሆነ ነው ይህን ጽሑፍ የምጽፈው። ምናልባት ከዶክተር ወረታው የምለየበት ምክንያት ለአገር ግንባታ ፖለቲከኞችም ምሁራንም እኩል ሚና አላቸው ብዬ የማምን በመሆኔ ነው። ሁሉም ሰው በያለበት ሙያ ለአገሩ ትልቅ ሥራ መሥራት ይችላል ብዬ አስባለሁ። ፖለቲካንም ሳይንስንም ማናቸውም ቢሆኑ አገርን የሚጠቅሙ ነገሮችን ሁሉ እኩል መውደድ ይገባናል ብዬ አምናለሁ። እናም እኩል ትኩረት ልንሰጣቸው፣ ልናወራላቸው፣ ልንጽፍላቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ! ከፖለቲካ ውጪ ያሉ ዕውቀቶች ለአገር ዕድገት ያላቸው አስተዋፅኦ ለማይታያችሁና አገር በፖለቲካ ብቻ የምትኖር ለምትመስላችሁ ወገኖቼ «ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ በሚወጣ ኃይል ጭምር እንጂ አገር በፖለቲካ ብቻ አትኖርም» ልላችሁ እወዳለሁ።
ከዚህ አኳያ ስንመለከተው የጠፈር ምርምር ሳይንስ (Space Science) በተለይም ደግሞ በዘርፉ ምሁራን ዘንድ «የጠፈር ሳይንስ ልብ» በመባል የሚወደሰው የሳተላይት ቴክኖሎጂና ሳይንስ በማንኛውም ዘርፍ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልና በአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ ቁልፍ ሚና ሊጫወት የሚችል ተመንዝሮ የማያልቅ ፋይዳ ያለው ተግባራዊ ሳይንስ ነው። የሳተላይት ቴክኖሎጂ በአየር ትንበያ መረጃና በግብርና፣ በምህንድስና፣ በመረጃና በቴሌ ኮምዩኒከሽን፣ በከተማ ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በውትድርና ሳይንስና በአገር ደህንነት፣ በሕክምናና በጤና፣ በትምህርትና ማህበራዊ ለውጥ፣ በአየር ንብረት ብክለት ቁጥጥርና በአካባቢ ጥበቃ፣… በአጠቃላይ በሁሉም የልማት መስኮች ውስጥ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው ዕውቀቶች የሚገኙበት ከሁሉም በላይ ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው የተግባር ሳይንስ ነው። ይህም በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ ሚናን ይጫወታል።
ታዲያ ከዚህ ጋር በተያያዘ ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ወደጠፈር ያመጠቀቻት ETRSS-1 የመሬት ምልከታ ሳተላይት ተልዕኮዋን በአግባቡ መወጣት መቻሏንና ሳተላይቷ ከታቀደላት ጊዜ በላይ አገልግሎት እየሰጠች የምትገኝ መሆኗን የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከሰሞኑ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጠው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል። በኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን ኢንጅነሮች በትብብር የተፈበረከችውና ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ከቻይና ምድር ወደ ጠፈር የመጠቀችው «የምድር ምልከታ» ከሚባሉት የሳተላይት ዓይነቶች የምትመደበው ይህችው ታሪካዊት የኢትዮጵያ ሳተላይት፤ በዚህ መልኩ ተልዕኮዋን በስኬት ማከናወኗ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ ትርጉም አለው።
ምክንያቱም የሳተላይቷ ዋነኛ ተልዕኮ የአገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን የሚያግዙ መረጃዎችን መሰብሰብ ነው። በእስካሁኑ ሙከራም ያልተሳካውን ግብርናውን የማዘመንና የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ሂደት ዕውን ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ትልቅ ፋይዳ አለው። የግብርናው መዘመንና የኢኮኖሚ ሽግግሩ ዕውን መሆን በበኩሉ ዜጎችን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅና የሚፈለገውን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት የሚያስችል አቅም ይፈጥራል።
ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር ፖለቲካ እየሆነ በተቸገርንባት የድህረ 1983ቷ ኢትዮጵያችን ከፖለቲካ ውጪ ሌላ ሕይወት የሌለ እስኪመስል ድረስ በጓዳም በጎዳናም፣ በቤትም በመስሪያ ቤትም፣ በቀጥታም በሚዲያም አየሩን ሁሉ የተቆጣጠረው ፖለቲካው በመሆኑ ጉዳዩ በሚገባው ልክ ትኩረት ሳይሰጠው መቅረቱን በግሌ ታዝቤያለሁ። አዎ አሁን ላይ በእኛ አገር በዋናውም ይሁን በማህበራዊ (ፖለቲካዊ ሚዲያ ቢባል ይቀላል) ሚዲያው ሰፊውን ቦታ የያዙት ፖለቲካዊ አለያም በግዴታም ቢሆን ፖለቲካ እንዲሆኑ የተደረጉ ጉዳዮች ናቸው። የሚወራውም የሚጻፈውም ከፖለቲካዊ አንድምታው አኳያ እየታየ ሆኗል። በእርግጥ ይህ ለምን እንደሆነ “ሆነ” ከማለት ባሻገር ሁሉም ነገር ፖለቲካ እየሆነ የመጣበትንና ሁሉም ፖለቲከኛ የሆነበትን ምክንያት በዚሁ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ መጻፌን አስታውሳለሁ።
ዛሬ በድጋሜ ያነሳሁት በጉዳዩ ላይ ልጽፍበት ሳይሆን ከፖለቲካው ባሻገር ልናወራላቸውና ልንጽፍላቸው የሚገቡ ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ለማስታወስና የበኩሌን በተግባር አድርጌ ለማሳየት ነው። ያኔ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ሳተላይቷ ወደጠፈር በመጠቀችበት ወቅትም ጉዳዩ የፖለቲካውን ያህል ሽፋን እንዳላገኘ አስታውሳለሁ። ከርዕሰ ጉዳዩ ትልቅነት እና ታሪካዊነት አኳያ በቂ የሚዲያ ሽፋን አለማግኘቱና ሰፊ የመወያያ አጀንዳ አለመሆኑ በእጅጉ እንድገረም አድርጎኝ እንደነበረም አስታውለሁ። በጊዜው ትዝብቴንም በዚሁ ጋዜጣ ትዝብት አምድ ላይ ጽፌያለሁ።
ምን ያህል ፖለቲካው እንደተጫነንና ሌላ ነገር እንዳናስብ አዕምሯችንን በቁጥጥሩ ስር አውሎ በእኛ ሳይሆን በእርሱ ፍላጎት እየመራን (እየነዳን ቢባል ይቀላል) መሆኑን በመታዘቤ በጉዳዩ ላይ የራሴን ምልከታ ለማካፈል ዛሬም በድጋሜ ብዕሬን እንዳነሳ ተገድጃለሁ በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ጉዳዩ ፖለቲካ ነክ ከሆነ ትንሿን ነገር ሳይቀር እያጋነነ፣ የማይገናኘውን በግድ አገናኝቶ ፖለቲካ እያደረገ፣ እየጮኸና እያስጮኸ አገር ምድሩን ሲያዳርሰው የሚውለው «ማህበራዊ ሚዲያ» ተብየው ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት ሳተላይት ተልዕኮዋን በስኬት ስለማከናወኗ ስለሚገልጸው ዜና ያን ያህል ሲጨነቅ አለመታየቱ ነው።
በጥፋት ንግድና ሰው ማባላት የሆነ እንደሆን ናይጀሪያ ውስጥ የሆነውን ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ ለማስመሰል ዓይኑ እስኪፈዝ ድረስ «አዶቤ» ላይ አፍጥጦ የሚውለውና አገር ምድሩን በ«ፎቶ በተደገፈ ዜና» የሚያጥለቀልቀው ማህበራዊ ሚዲያ፤ የዚህ ጊዜ መናገር ተስኖት አይጥ የዋጠች ድመት ሆኖ ጥጉን ይዞ ሲቁለጨለጭ መሰንበቱ አጃኢብ የሚያስብል ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የሆነውን ሳተላይት ወደ ህዋ እንደምታመጥቅ የሚያበስረው ዜና መሰማቱን ተከትሎ በጥቂቱም ቢሆን በተሰወኑ አካላት ዘንድ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ቢነሳ እንኳን የሚነሱት ጉዳዮች በአብዛኛው ትችትን ያዘሉ መሆናቸው ደግሞ ያኔም ዛሬም የበለጠ ግርምትን ስለፈጠረብኝ «ግን ለምን?» የሚል ጥያቄን አጭሮብኛል። እናም ጉዳዩን በሚመለከት እኔም የራሴን ምልከታ እንዳቀርብ ምክንያት ሆኖኛል።
በዚህ ረገድ ሲቀርቡ ከታዘብኳቸው ዕውቀት ጎደል ትችቶች መካከል «ብዙ ችግር ባለባት አገር ውስጥ(የአገሪቱን ፖለቲካ ሁኔታ በዋነኝነት ያነሳሉ) በተጨማሪም በልቶ ማደር እንኳን አስቸጋሪ በሆነባት ድሃ አገር የህዋ ሳይንስ ያን ያህል አስፈላጊ ነገር ነውን? «ስንት መቅደም የሚገባቸው ነገሮች እያሉ በአሁኑ ሰዓት ሳተላይት ማምጠቅ ይህን ያህል ትኩረት ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነውን? ሳይንሱ ውድ ከመሆኑ የተነሳ ከሚያስወጣው ወጪ አኳያ እንደ አገር የሚያስገኘው ጥቅም፣ አጠቃላይ ፋይዳውስ ምንድነው?» የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።
ሆኖም ትችቶቹ የስፔስ ሳይንስን ሁለንተናዊ ፋይዳ ያልተገነዘቡና ዕውቀት የጎደላቸው መሆናቸውን ማስገንዘብ ይገባል። እናም እዚህ ላይ የሚቀርበው ትችት ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ከፖለቲካ በተጨማሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂም እጅግ ወሳኝ ነገር መሆኑን ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ነው። ምክንያቱም የዘርፉ ምሁራንና ባለሙያዎች እንደሚያስገነዝቡት የህዋ ሳይንስ በማንኛውም የልማት ዓይነት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልና በትልቁ ከሰው ሕይወት ጋር የተቆራኘ ሁለንተናዊ ፋይዳ ያለው ሳይንስ ነው። ሆኖም የእኛን አገር ጨምሮ በሌሎችም የሳይንሱ ፋይዳ ባልተገለጸላቸው ታዳጊ አገራት በብዙዎች ዘንድ የህዋ ሳይንስ ለድሃ አገራት አያስፈልግም የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ። በዚህ ረገድ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት እንደ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመሳሰሉ ተቋማት ለዓመታት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ማፍራት የጀመረ ይመስላል። በአመለካከት ላይ ትኩረት ተደርጎ በመሠራቱ፤ እንዲሁም መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱ ለዚህ ለውጥ እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው።
በዚህም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደጠፈር የመጠቀችው ETRSS-1 የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከመጠቀችበት ጀምሮ ተልዕኮዋን በአግባቡ ማሳካት ችላለች። የተሰጣትን የመሬት ምልከታ ሥራዎችንም በአግባቡ አከናውናለች። ለሁለት ዓመት ተኩል እንደምታገለግል ተደርጎ የታቀደ ሲሆን፤ አሁን ላይ ከታቀደላት ጊዜ በላይ ተጨማሪ አምስት ወራትን አገልግላለች። በዚህም በግብርና፣ በተፈጥሮ ሀብት መስክና ከመሬት አስተዳደር ጋር የተገናኙ ሥራዎችን ለማከናወን ውጤታማ የሆኑ መረጃዎችን መስጠቷን የስፔስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጠው መረጃ ላይ ተመላክቷል።
ከዚህ በተጨማሪም የሳተላይቷን መረጃ በመጠቀም የለሙና አሁንም ሆነ በቀጣይ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ ሞዴሎች እንዳሉም ተጠቅሷል። በግብርናው ዘርፍ የሰብል ምርታማነትን በተመለከተ ከሳተላይቷ የተገኘውን መረጃ በመጠቀም ማልማት እንደተቻለም ተገልጿል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ የደን ሽፋንና በጊዜው ውስጥ የሚኖረውን ለውጥ ለመከታተል የሚያስችል መተግበሪያም እንዲሁ ሳተላይቷ በሰጠችው መረጃ አማካኝነት ማልማት እንደተቻለም ተመላክቷል።
በየጊዜው ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር የተገናኙ መረጃዎችንም በግብዓትነት ለመጠቀም እንደተቻለ፤ በቱሪዝም ዘርፍ በተለይም በደቡብ ኦሞና በጋሞ ዞን የቱሪዝም ካርታ ለማዘጋጀትና ከዚህ ሥራ ጋር የሚገናኙ መተግበሪያዎችን የማበልጸግ ሥራዎችም በግብዓትነት ጥቅም ላይ መዋላቸውም ታውቋል። ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ ለጥጥ እርሻ አመቺና ተስማሚ የሆኑ ቦታዎችን ለመለየት የETRSS-1 ሳተላይት መረጃ በግብዓትነት ማገልገሉም በመረጃው ተጠቅሷል። በሳተላይቷ አማካኝነት ለተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ለምርምር ሥራ የሚሆኑ መረጃዎችን የመስጠት ሥራዎችም ተከናውነዋል። መረጃውን ከመጠቀም አንጻር የተፈጠረው አቅም የተሳካ እንደነበርም ተገልጿል። ከዚህም ባሻገር የተፈጠረ የቴክኒክ አቅም መኖሩም ተመላክቷል። ታዲያ ከዚህ የበለጠ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚጠቅም ሥራ በሳተላይት ሳይንስ ካልሆነ በቀር ከወዴት ይገኛል?
ስለሆነም ከዚህ ድንቅ ሳይንስ በረከት ለመካፈልና ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያበረክተውን ፈርጀ ብዙ ፋይዳ መሬት ላይ አውርዶ ለመጠቀም ሳይንሱ እንዳያድግ የዘርፉ የዘመናት ማነቆ ሆኖ የቆየውን «ምግብ ሳይጠገብ ምን የሚሉት የጠፈር ምርምር ነው» በሚል የተሳሳተ አመለካከት ሳይደናቀፉ ጅምሩን አጠናክሮ መቀጠል ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን። ለዚህም ነው ከፖለቲካ ውጪ ሌሎች የፍልስፍናና የዕውቀት ዓይነቶች፣ ጥበቦችና ሳይንሶች ለማይታያቸውና አገር በፖለቲካ ብቻ የምትኖር ለሚመስላቸው ወገኖችም «አገር በፖለቲካ ብቻ አትኖርም፤ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ በሚወጣ ኃይል ጭምር እንጂ» ልል የወደድኩት። ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/ 2015 ዓ.ም