የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት፤ የአገሪቱ የፋይናንስ ፍሰት በአግባቡ እንዲሳለጥና እክሎች እንዳያጋጥሙት፤ ችግሮች ካጋጠሙም በፍጥነት በማረም በሕግና ደንብ የሚመራ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር ይሠራል።በዋናነት ደግሞ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይንም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ጥቅም ላይ እንዳይውል፤ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን የመከላከል፣ መቆጣጠርና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ይወጣል።
የዝግጅት ክፍላችንም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አሁናዊ ተልዕኮዎች፣ ቀጣይ ውጥኖች፣ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትና የመሳሰሉትን በተመለከተ ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሌን ጊዜወርቅ ጋር ቃለመጠይቅ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋነኛ ተግባራት ምንድን ናቸው?
አቶ ብሌን፡- የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት 490/2014 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መልሶ የተቋቋመ ተቋም ነው።ተልዕኮውም በወሳኝነት በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይንም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን የመከላከል፣ መቆጣጠርና ባለድርሻ አካላትን የማስተባበር ብሎም ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን መወጣትን ያካትታል።ወንጀሎቹ ድንበር ተሻጋሪና ዓለም አቀፍ ባህሪ ያላቸው በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋ ሥርዓት አለ።በዚህ ውስጥ የምንወጣው ሚና አለ፤ ይህን በተመለከተ አገራዊ ውክልና ወስደን እንሠራለን።
በቀጥታ ከወንጀሎች ጋር በተያዘዘ ከተለያዩ ሪፖርት አድራጊ አካላት ጋር በተለይም የፋይናንስ ተቋማትና ፋይናንስ ነክ ካልሆኑ ተቋማት ሪፖርት ማድረግ ካለባቸው አካላት እንዲሁም ከኅብረተሰቡ በምናገኛቸው መረጃዎች ላይ ተመስርተን መረጃዎችን የመተንተን ሥራዎችን እናከናውናለን።ተንትኖ የወንጀል ፍሬን የመለየት እንዲሁም በሕግ የተያዙትን ጉዳዮች ለሕግ አስከባሪ የማስተላለፍ ሚና አለው።
ይህን ስናካሂድ በመሠረቱ ‹‹መኒ ላውንደሪንግ›› ላይ ብናተኩርም ለዚህ አመንጪ የሆኑ ወንጀሎችንም ጭምር በትኩረት እናያለን።ከዚህ አንጻር አገራዊ የስጋት ተጋላጭነት ጥናት መሠረት በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ አመንጪ ተብለው የተለዩት ሙስና፣ ኮንትሮባንድ፣ ግብር ማጭበርበር፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርንና የመሳሰሉ የወንጀል እንዲሁም ሌሎች ፋይናንስ ነክ የሆኑ ማጭበርበር ተግባራትን እንደ አመንጪ ወንጀል በመውሰድ፣ ትንታኔ በማድረግና የወንጀል ፍሬዎችን በመለየት ለሕግ አስከባሪ አካላት ለተጨማሪ ምርመራና ክስ የምናስተላልፍበት ሁኔታ አለ።እነዚህ በወሳኝነት የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋነኛ ተግባራት ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይንም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎች ምን ያክል ለኢትዮጵያ ስጋት ናቸው?
አቶ ብሌን፡– እነዚህን ወንጀሎች በአግባቡ መከታተልና መቆጣጠር እስካልተቻለ ድረስ በአገር አቀፍ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሥጋት ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው።ኅብረተሰቡ ላይ በቀጥታ ጉዳት የሚያስከትሉ፣ አገር የሚጎዱ፣ በፍትሃዊነት ሠርቶ መበልፀግ ሳይሆን በሕገወጥ መንገድ መጠቀም ለሚሹ አካላት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።እንዲሁም ጤናማ ከሆነው የኢኮኖሚ ውድድር ውጪ በአቋራጭ ለመክበር ለሚፈልጉ አካላት ጥሩ ሁኔታ ይፈጥራል።
አልፎ አልፎም ለአገራት የሠላምና መረጋጋት ችግር የሚሆንበትና በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ያከማቹ አካላት ግጭትን በገንዘብ ይደግፋሉ።በአጠቃላይ የአንድን አገር ዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያዛባ፣ ሠላማዊ ኑሮና የመንግሥትን ሥርዓት የሚያውክ፣ ማህበራዊ ሕይወትን የሚያዛባና ለሌሎች ሕገ ወጥ ድርጊቶችም የሚዳርግ ነው።መንግሥት ለሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጥ የሚያደርጉና የመንግሥትን ሥርዓት የሚያዳክሙ አገርን የሚያናጉና ለሠላም እጦት መንሰዔ ሊሆኑ የሚችሉ አደጋዎች ናቸው።ስለዚህን እነዚህን በአግባቡ መቆጣጠርና መከታተል ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በተጨባጭ በአገራችን የሚታዩ በርካታ ግጭቶች፣ ኮንትሮባንድ ንግድ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር አሉ።ይህ ሁኔታ በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ትንተና እንዴት ይታያል?
አቶ ብሌን፡– ሕገ-ወጥነት ሁልጊዜም የሚኖር ነው።በአንድ አገር ወይንም ማህበረሰብ ውስጥ የሚስተዋል ሲሆን ይህን የሚመርጡ አካላት ደግሞ ሕገወጦች ናቸው።በተለይ ደግሞ በሕጋዊ ንግድ ውድድርና ባበረከቱት አስተዋፅኦ ከማደግ ይልቅ በአቋራጭ ለመክበር እንደ ትልቅ አጋጣሚ የሚጠቀሙበት አካሄድ ነው።እነዚህ አካላት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማሉ።
ከዚህ አንፃር የሕግ ክፍተቶችን የሚጠቀሙ ሲሆን፣ በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ያሉትን አካላት ጭምር በማሳሳት ይህን ተግባራቸውን ያሳካሉ።ስለዚህ እንደ እሳቤ በአቋራጭ የመክበርና ፍላጎት ነው ብሎ ቢወሰደም እነዚህ አካላት በዚህ የሚቆሙ ሳይሆን ከዚህ ያለፈ ፖለቲካዊ ፍላጎት ይኖራቸዋል።በተለይ ደግሞ አገር ከተረጋጋ እና ሠላማዊ ከሆነ የእነዚህ አካላት ምቹ ሁኔታ እየጠበቡ ስለሚሄዱ ሁሌም አገር ባልተረጋጋ ሁኔታ እንዲኖር ይሠራሉ።የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ስለሚኖራቸውና ይህን ለማሳካት ደግሞ ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ ያደርጋሉ፤ ወደሚፈልጉት ይረጫሉ።ይህ አካሄድ በአገር ውስጥ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን እስከ ውጪ ድረስ ትስስራቸውን የሚዘረጉበት አጋጣሚና አግባብ አለ።
እንደ ማሳያ ብንወስድ ውጭ አገር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦቻቸውና ለተለያየ ዓላማ ወደ አገር ውስጥ ገንዘብ ይልካሉ።ታዲያ ሕገ-ወጦች የሚያደርጉት በሕጋዊ መንገድ ወይንም በባንክ ሥርዓት መምጣት ያለበትን ወደ አገር ውስጥ መግባት ያለበትን ገንዘብ ወይንም የውጭ ምንዛሪ እዚያው ውጭ በጥቁር ገበያ ላይ ግዥ በመፈፀም ገንዘቡ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ በማድረግ በአገራቸው ላይ ትልቅ ወንጀል ይፈጽማሉ።እነዚህ ግለሰቦች በዚህ መልኩ ውጭ ያስቀሩትን ገንዘብ ለሌላ አላማ ሊያውሉት ይችላሉ።አንደኛ በሕገ ወጥ ንግድ ምርት አገር ውስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ።በተጨማሪም ደግሞ አገር ውስጥ በሕገ ወጥ ያከማቹትን ለማሸሽ ይጠቀሙበታል።
አዲስ ዘመን፡- ከፍተኛ አመራሮችና ሕገ ወጦች ወዳጅነት ፈጥረው የሚሠሩበት አጋጣሚ መኖሩን ገልፀውልኛል።ይህን ሁኔታ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በተጨባጭ ደርሶበታል?
አቶ ብሌን፡- እንግዲህ የምናደርጋቸው ኦፕሬሽናልና ስትራቴጂክ የትንተና ሥራዎች በእያንዳንዱ ኬዝ ውስጥ የሚሳተፉ አካላትና ግለሰቦችን የመለየት ሥራ አብሮ ይሠራል።በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉ አካላትና ግለሰቦችን እንደየድርሻቸው የመለየት ሥራ ይሠራል።ምክንያቱ ደግሞ የሕግ ተጠያቂነቱም እንደተሳትፎም መሆን ስላለበት ያንን ተግባር እናከናውናለን።
በዚህ ሂደት ውስጥ በግል ወይንም በንግድ ሥራ ላይ ተሠማርተው ነገር ግን ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት የሚገኝበት ሁኔታ አለ፤ እንዲሁም በመንግሥት ሥራ ላይ ሆነው ኃላፊም ይሁን ባለሙያ የዚህ ድርጊት ደጋፊ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ።በዚህ አግባብ እነዚህም አካላት አንዱ የሕግ ተጠያቂነት ሊያርፍባቸው ስለሚገባና ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ስላለባቸው ይህን የሚመለከት መንግሥት አካል በተለይም የምርመራው ሥራን ወይንም የክስ ሥራው የሚያከናውነው አካል በእነዚህ መንግሥት ኃላፊነትን በአግባቡ ባልተወጡ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ሥራዎች ይሠራሉ።
አዲስ ዘመን፡- ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎችን ወይንም ፋይናንሱን በተመለከተ ሕገ ወጦች ላይ የተወሰደ እርምጃና በቁጥር የሚገለፅ ነገር አለ?
አቶ ብሌን፡- እንደገለፅኩልህ በተቋማችን ደረጃ ኬዞችን ፕሮዲዩስ አድርጎና ተገቢውን ትንታኔ አድርጎ ወደ ምርመራ አካል የማሰራጨት ነው በዋናነት የምንሠራው።ከዚህ አንፃር ፖሊስ በተለይም ደግሞ የምርመራ ሥራውን ሲያከናውን እኛ ካገኘነው ግኝት ባሻገር ሰፊ የምርመራ ሥራ በመሥራት ተጨማሪ መረጃዎችን የማደራጀት ሥራዎችን ያከናውናል።በዚህ ሂደት ውስጥ የሚገኙ ተጨማሪ ተዋንያን እንዲሁም ጥቅም ላይ የዋለን ገንዘብ ጭምር የሚገኝበት ሁኔታ አለ።ምክንያቱ ደግሞ ፖሊስ የተለየ የምርመራ ቴክኒኮችን ስለሚጠቀም ይህንን ተከትሎ ሕጋዊ ሥርዓትን አስይዞና የሕግ ሂደቱን የመምራት ኃላፊነት ያለበት አቃቢ ሕግ ደግሞ እንዲሁ ሁኔታው ወደ ፍርድ ቤት አቅርቦ ተገቢው የሕግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይሠራል።
ስለዚህ በተጨባጭ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላት በስፋት የምርመራ ሂደት ላይ እንዳሉ አውቃለሁ።በተጨማሪም በተገቢው ፍርድ ሀብታቸው እስከ መውረስ ድረስ የደረሱ አካትም አሉ።ከዚህ በተረፈ እያንዳንዱ ጉዳይ ዝርዝርን በተመለከተ በፖሊስ፣ አቃቢ ሕግና ፍርድ ቤት ደረጃ ከተሄደ እነዚህን አሃዛዊ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በጥቁር ገበያ ላይ ዶላር መመንዘር አንዱ የወንጀል ድርጊት ነው። በዚህ ላይ ተቋማችሁ ምን እየሠራ ነው ?
አቶ ብሌን፡- እንደሚታወቀው የሕግ አስከባሪ አካላት ይህን የጥቁር ገበያን እንቅስቃሴ ለመከታተልና ለመቆጣጠር ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠሩ ነው።በቅርቡ ኅብረተሰቡ እንደሚገነዘበው በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ አካላት ላይ መወሰድ የጀመረ ጠንካራ እርምጃ አለ።ለአብነትም ማንሳት ከተፈለገ ለዚህ ጥቁር ገበያ የሚውሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የባንክ ሂሳቦች የመዝጋትና በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ አካላትን በሕግ ለመጠየቅ ምርመራዎችና ሂደቶች ቀጥለዋል።ስለዚህ እንደሕግ አስከባሪ ተቋም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤ በቀጣይም መጠናከር አለባቸው።እንደሚታወቀው ባንኮች አካባቢ ሲኬድ እጥረት ስላለባቸው ዜጎች ለሚፈልጉት ዓላማ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቸገራሉ።
አዲስ ዘመን፡- ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የማይሰጡት እጥረት ስላለባቸው ወይስ ደካማ አሠራርና ሙስና ስለተስፋፋ?
አቶ ብሌን፡- በተቋም ደረጃ ያሉ ግለሰቦች ሕገ ወጥነትን በሚያበረታታ ድርጊት ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ።እነዚህ አካላት ላይ ተገቢ የሆነ ክትትል በማድረግ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ እንደ መንግሥት ውሳኔ ተላልፏል።በተለይም በባንኮችና በፋይናንስ ተቋማት ያሉ የባንክ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመሰል ድርጊት ላይ እንደሚሳተፉ ኅብረተሰቡ የተለያዩ ጥቆማዎችንና ሃሳቦችን ይሰጣል።በዚህም ላይ ሲሳተፉ የነበሩ በርካታ ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል።ስለዚህ ሕጋዊ የባንክ ሥርዓቶችን በመጠቀም የሚፈፀሙ ሕገ ወጥነቶችን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት በመጀመሪያ ደረጃ የባንኩ ሥራ ነው።
በአዋጅ 782/2005 ላይ እንደተቀመጠው በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር የፋይናንስ ወንጀል የፋይናንስ ተቋማት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ የመከላከል ኃላፊነት ለተቋማቱ ተሰጥቷል።በዚህ መንገድ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡት ላይ እርምጃ ይወሰዳል።በዚህ ሂደት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ።በመስሪያ ቤታችንና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የተወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎች አሉ።በቀጣይነት እነዚህ ተቋማት የሕዝብ ተቋማት እንደመሆናቸው መጠን የሕገ ወጥነት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ በተቋማት ውስጥ ተጠያቂነትን ማስፈን ያስፈልጋል የሚል የመንግሥት
ውሳኔ አለ።በመሆኑም የእኛም ሆነ የሌሎች ሕግ አስከባሪ አካላት እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል።ሁኔታዎች ካልተሻሻሉ በቀጣይ የሚወሰድ እርምጃ ስለማይቀር በተለይም በተቋማት ውስጥ የተቋማትን ሕጋዊ ሥርዓት ተከትለው ሕገወጥነትን በሚያራምዱት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- በዲፕሎማት ሽፋን ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ስለመኖሩ ይነገራል።የውጭ ዜጋ ሆነው ሐሰተኛ ገንዘብ በማተም ተጠርጥረው የተያዙም አሉ።ተቋማችሁ በዚህ ረገድ ምን እየሠራ ነው፤ ይህ ወንጀል ስለመከናወኑስ የጠራ መረጃ አላችሁ?
አቶ ብሌን፡– በውጭ አገር ዲፕሎማቶች በተመለከተ በተወሰነ ደረጃ የምናገኛቸው መረጃዎች እንዳሉ አውቃለሁ።ነገር ግን በሕግ አስከባሪ ደረጃ በእነዚህ አካላት ላይ ቁጥጥር ተደርጎ የተወሰደ ጠንካራ እርምጃ የለም።
አዲስ ዘመን፡- ለምን ጠንካራ እርምጃ አልተወሰደም?
አቶ ብሌን፡- እነዚህን ተግባራት በማከናወን ሂደት በወሳኝነት ኃላፊነቱ በአካባቢው የሚገኙ የሕግ አካላት ናቸው።ስለዚህ አንድ ተቋም ሌላውን ወክሎ መረጃ መስጠት ተገቢ አይደለም።መሰል መረጃዎችን በአካባቢው ባሉ ፖሊሶችና የፖሊስ ተቋማት የሚያከናውኗቸው ክትትሎችና ምርመራዎች የሚፈፀሙ ተግባራት ናቸው።የእኛ ተቋም መረጃ ክትትል በማሰማራት የራሱን ሥራ ይሠራል።ነገር ግን ሕግ አስከባሪ ተቋማት የሚወስዷቸው እርምጃዎችና ክትትሎች አሉ።መረጃዎችንም ከእነዚህ አካላት በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በፋይናንስ ደህንነት ረገድ ኢትዮጵያ ያለችበት የጂኦ ፖለቲክስ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነት ስጋትና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች ያገናዘበ ሥራ እየተሠራ ነው ማለት አንችላለን?
አቶ ብሌን፡– ትክክል ነህ።በተለይም ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ላይ ከፍተኛ የሆኑና ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንጀሎች የሚካሄዱበት ነው።ከዚህ አንፃር የሽብርተኞች እንቅስቃሴ አለ።በዚህም ሁኔታ ለእነዚህ አካላት የሚሆን ገንዘብ እንዳይተላለፍ ጠንካራ የሆነ ፀረ ሽብር የፋይናንስ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል።ሕገ ወጥ የሰዎች እና ገንዘብ ዝውውር የሚካሄድበት ሁኔታ አለ።ሰፋፊና ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን ለማካሄድ ብዙ ተዋንያን የሚንቀሳቀሱበት ቀጣና መሆኑ ይታወቃል።ከዚህ አንጻር ሥራዎችን ቀጣናዊ በሆነ ተቋም አማካኝነት በጋራ የመሥራት እንቅስቃሴ አለ።በተለይ ከምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና አንፃር የተቋቋመ ተቋም አለ።ይህም ተቋም የምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ ፀረ-ገንዘብ ዝውውር ይሰኛል።
በዚህ ተቋም ይህ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን አገራቱ በተለይም አባል የሆኑ 18 አገራት አሉት።አገራቱ በተናጠልና በጋራ እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል በጋራ ይሠራሉ።በመደበኛ የሚገናኙበት፣ ሥራዎችን የሚገመግሙበትና የጋራ ኃላፊነት መወጣት የሚችሉበት መድረክ አለ።በዚህ መልኩ እንደ አገር በተናጠል የምናከናውነው ነገር አለ።ቀጣናዊ በሆነ መልኩ ከጎረቤት አገራት ጋርም የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ።መረጃዎችን ገደብ ሳይኖር በስፋት እንለዋወጣለን፤ ከአንዳንዶቹ፣ ጋር የሁለትዮሽ ሥምምነት ተፈራርመናል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን የማተራመስ ፍላጎትን ለማሳካት በስተጀርባ ገንዘብ ኢንቨስት ማድረግ ነው።ከዚህ አኳያ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ብሌን፡- አዎ ልክ ነው።በዋናነት ይህ ሥራ ሊገለፅ የሚችለው ከአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች አንፃር፤ በአገር ውስጥ ያሉና ሕገ ወጥ ተግባራትን ለሚያከናውኑት ድጋፍ በመስጠት ሊገለፅ ይችላል።በዚህም ሕግ አስከባሪ አካላት ጉዳዩን በትኩረት ይከታተሉታል።ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በገንዘብ ለመደገፍ የሚሠሩትን በንቃት የመከታተል ሥራ አለ።
በዚህ ረገድ እንደ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያሉ ተቋማት ይህን ድርጊት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በስፋት ይንቀሳቀሳሉ።የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ደግሞ በተለይ ሕጋዊ የፋይናንስ ሥርዓትን ሽፋን ተከትሎ ሊመጡ የሚችሉ ተጋላጭነትን እንዳይኖር ለማድረግ ተከታታይ የቁጥጥር ሥራ ይሠራል።ድንበር አካባቢ ደግሞ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽና ዜግነት መምሪያ ከመሳሰሉት ተቋማት ጋር በተቀናጀ ሁኔታ ክትትሉና ቁጥጥሩ ይሠራል።በዚህ ረገድ እንደ አገር ቅንጅታዊ አሠራር አለ፤ በጋራም አፈፃፀም ይገመገማል።ኢትዮጵያ በርቀት ያሉ ታሪካዊ ጠላቶቿን ሁኔታ መመከት ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ ያሉ ጎረቤት አገራትና የኢትዮጵያ ሠላም ይገዳቸዋል ከምንላቸው ጭምር በጋራ እንሠራለን።ድንበር በመሻገር መረጃ ማግኘትና ጉዳትን ቀድሞ መከላከል እየተቻለ ነው።በተለይ ደግሞ በዚህ ወቅት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዘመን በአደጉት አገራት ጭምር የወንጀል አድራጊዎች አቅም ከተቋማት አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል።የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከሚቃጡት ጥፋቶች አኳያ አቅሙ ምን ደረጃ ላይ ነው?
አቶ ብሌን፡– ጥሩ ጥያቄ ነው።ተቋሙ በመንግሥት ደረጃ ያለውን ሚና በመገንዘብ ድጋሜ ተጠናክሮ ማቋቋምና ማስቀጠል በመታመኑ ባለፈው ዓመት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ተቋቁሟል።ተቋሙ ተልዕኮውን የሚመጥን ቁመና እና የሰው ኃይል እንዲኖረው ለማድረግ ትልቅ ውሳኔ ተወስኗል።ይህም በቂ ባለመሆኑ ከችግሩ ውስብስብነት ጋር የሚመጥን ወንጀልን መከላከል አቅም በተለይ ደግሞ ከቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ሥራዎችን መሥራት ስለታመነበት እንደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት (ኢንሳ) ካሉ ተቋማትና ሌሎች ቴክኖሎጂ ከሚያበለፅጉ ተቋማት ጋር ችግሩን በቴክኖሎጂ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው።
የፋይናንስ ተቋማት ጋር በቀጥታ መረጃ ለማግኘት የተዘረጋ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ብሎም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ሥርዓትና ከመንግሥት ተቋማትም መረጃ የሚገኝበት ሥርዓት ሰፊ ሥራ ተሠርቷል።በአሁኑ ወቅት በተሻለ ኃላፊነት ለመወጣት እየተሠራ ሲሆን የሰው ኃይል አቅም ለመገንባት የተቋሙ ሠራተኞችን ከአገር ውጭ ዓለም አቀፍ ስልጠና እየወሰዱ ነው።ተቋሙ የሰው ኃይል ብዛትና ብቃቱም እያደገ ነው።በቀጣይ እየተጠናከረ የሚሄድ ሲሆን፤ የመንግሥትም ድጋፍ በየጊዜው እየተጠናከረ ነው። አሁን ካለው በላይ ችግሩን የሚመጥን ተቋማዊ ግንባታ ያስፈልገናል፤ በዚህም በስፋት እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሌላው የዘመኑ ፈተና ምናባዊ ገንዘብ ነው የሚል ስጋት አለ።ያደጉ አገራት ምናባዊ ገንዘብ በሚል እየገበያዩና በርካታ አገራትን እያጥለቀለቀ ነው።በዚህ ላይ ኢትዮጵያ ምን እየሠራች ነው?
አቶ ብሌን፡- በርካታ አገራት በተለይም ያደጉ አገራት ቀደም ብለው አይቀሬ የሆነውንና በእኛ አገር ቢትኮይን፤ ክርፕቶ ከረንሲ እና የተለያዩ ስያሜ የተሰጧቸው ሲሆን በሙያዊ አጠራር ደግሞ ቨርቹዋል ወይንም ምናባዊ ገንዘብ በሚል ይወሰዳል።ያደጉ አገራት በየራሳቸው ሕግና ቁጥጥር አበጅተው በሕጋዊ ፈቃድ እየሠሩ ነው።በየአገራቱም ከፋይናንስ ሥርዓታቸው ጋር አጣጥመው እየሠሩበት ሲሆን፤ በርካታ የአፍሪካ አገራት ይህን አሠራር ተግባራዊ እያደረጉ ነው።
ስለዚህ የዚህን ገንዘብ ባህሪ ያገናዘበ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል።ይህንንም በአግባቡ ተገንዝበን ወደ ሕገ ወጥነት እንዳይሄድ የሚቆጣጠር ተቋም ያስፈልጋል።በእኛም ሁኔታ እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ የፋይናንስ ሥርዓት ሕግ መሠረት የኢትዮጵያ ብቸኛው መገበያያ ገንዘብ የኢትዮጵያ ብር ብቻ ነው።ከዚህ ውጪ ያለ ማንኛውም ግብይት ሕገ ወጥ ነው።ከዚህ አንፃር ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል።በአሁኑ ወቅት በምናባዊ ገንዘብ ኢትዮጵያ ውስጥ ግብይት መፈፀም ወንጀል ነው።መሰል እንቅስቃሴዎችን ስናስተውል በብሔራዊ ባንክ በኩል ሕገ ወጥ ስለመሆኑ ለኅብረተሰቡ መረጃ የሚሰጥ ሲሆን እንደ መንግሥትም መግለጫ እየተሰጠበት ነው።
ምናባዊ ገንዘብ ግብይት በኢትዮጵያ ቢፈቀድና ባይፈቀድ ምን ጥቅምና ጉዳት አለው የሚለውን ለማወቅ የተጋላጭነት ጥናት እየተካሄደ ነው።የዓለም ባንክም በዚህ ረገድ ቴክኒካዊ ድጋፍ እየሰጠ ነው።የሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ ተቋማትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ያሉበት የጥናት ቡድን በማቋቋም ጥናቶች እየተካሄዱ ነው።በሂደት ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ ላይ በምን ዓይነት ሁኔታ እየተካሄደ ነው ጉዳቱ ምንድን ነው፤ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ የጥናቱ ውጤት ያሳያል።ከዚህም በመነሳት ተቋማዊና የሕግ ማዕቀፎች ምን መምሰል አለባቸው የሚለውንም ጭምር የጥናቱ ውጤት የሚያሳይ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ፍንጭ ተሰጥቷል።ከዚህ አኳያ የፋይናንስ ሥርዓቱ እንዳይታወክና ከታለመው ዓላማና ቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ብሌን፡– እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ከተለመደው ወጣ ያሉ የአሠራር ሥርዓቶችን ይዘው ሊመጡ ይችላሉ።የየራሳቸው ባህሪ ያላቸው ሲሆን ትስስራቸው ዓለም አቀፋዊና ቅርንጫፎቻቸው ከአገር ውጭ ሊኖሩ ይችላል።በዚህ ረገድ የእነዚህን አካላት እንቅስቃሴ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል ሁኔታ ስለመኖሩ በመንግሥት ደረጃ የሕግ ማዕቀፍ የዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው።ይህን የሚቆጣጠረውም በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የራሱን ሕጎች ያወጣል።
ከፋይናንስ ወንጀሎች አኳያ ደግሞ የእኛ ተቋም የራሱን ሕግ ማዘጋጀት ይኖርበታል።ለዚህ ደግሞ በቂ ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል።የልምድ ልውውጦችን ማካሄድ፣ ጥናቶችን ማከናወንና የመሳሰሉ ሥራዎችን ከወዲሁ ጀምረናል።የትኞቹ ባንኮች ይምጡ ምን ያህል በአገር ውስጥ ይስሩ የሚለው ነገር ከወዲሁ የሚታወቅ ባይሆንም በመንግሠት ደረጃ አስቀድሞ ተቋማዊ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል የተሄደበት ነገር እንዳለ ሆኖ፤ በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትም ዝግጅት የማድረግና ሁኔታዎችን የማጤን ጅምር መኖሩን መግለፅ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፤ ተጨማሪ ሐሳብ ካለ ዕድሉን ልስጥዎት።
አቶ ብሌን፡- እነዚህ ወንጀሎች በተወሰኑ ተቋማትና ጥንካሬና ጥረት ብቻ መከላከል አይቻልም።ከዚህ አንፃር የኅብረተሰቡ ሚና ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል።የወንጀሉ መንሰራፋት የሚጎዳው ሕዝብና አገርን ነው።ኅብረተሰቡ የሚሰጠው መረጃ አለ፤ ይህንን ማጠናከር አለበት።በተለይ በሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር፣ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ የተነሳ የኑሮ ውድነት ይስተዋላል።ይህ ኅብረተሰቡን በቀጥታ እየጎዳ ነው።በመሆኑም መሰል ድርጊት በመንግሥት ጥረት ብቻ ስለማይሸፈን ማህበረሰቡ ከጎናችን በመሆን ሥራችንን እና ጥረታችንን እንዲያግዝ ብሎም ለእነዚህ ሕገ ወጥ አካላት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር መሥራት አለበት፤ እንደ ተቋምም ጥሪያችን ማስተላለፍ እንወዳለን።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2015