
አዲስ አበባ፦ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት የልደት ሰርተፍኬት በነፃ መሰጠት መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በከተማዋ በሚገኙ የጤና ተቋማት ከዚህ በፊት የልደት ሰርተፍኬት አይሰጥም ነበር። ይህም በሀገሪቷ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሙሉ ለሙሉ ለማወቅ አዳጋች አድርጎታል።
ከዚህም ባለፈ መንግስት በየአመቱ የሚበጅተው በጀት ከተማሪ ምገባ፣ ዩኒፎርምና ለትምህርት ቤቶች የሚያስፈልገው የመምህር ብዛት እንዳይታወቅ አድርጎታል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ምን ያህል ህፃናት እንደተወለዱ፣ ምን ያህል ዜጎች እንደተጋቡና እንደሞቱ መታወቅ አለበት ብለዋል።
ይህን ለማድረግ በከተማዋ በሚገኙ የጤና ተቋማት የልደት ሰርተፍኬት መስጠት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ በከተማዋ በሚገኙ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት የልደት ሰርተፍኬት በነፃ በመሰጠት ላይ ይገኛል። በዚህም ቴክኖሎጂን ቀዳሚ አድርገን እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በጤና ተቋማቱ ባለሙያ ተመድቦ ምዝገባ እየተከናወነ ይገኛል። የልደት የምስክር ወረቀቱ በ33 የጤና ተቋማት እየተሰጠ በመሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን አስመዝግበው በተወለዱበት ቀን ሰርተፍኬት ይዘው እየሄዱ ነው።
አገልግሎቱ በግል የጤና ተቋማት እየተሰጠ ሲሆን ከመንግስት የጤና ተቋማት ውስጥ ዘውዲቱ፣ ጋንዲ፣ ጴጥሮስና ጳውሎስን የመሳሰሉት ይገኛሉ። እነዚህም አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ውልደት የሚከሰትባቸው የጤና ተቋማት ናቸው። ይህም እንደ ሀገር የመጀመሪያው መዋቅር ነው ብለዋል።
በጤና ተቋማት የሚሰጠው ምዝገባ ነፃ ነው። አሁን በሚሻሻለው የከተማው አገልግሎት ክፍያ ደንብም የሞትና የወቅታዊ ምዝገባ ክፍያ እንዲሁም የልደት ክፍያ ነፃ ነው። ህፃናት የልደት ሰርተፍኬት አልወሰዱም ማለት በመንግስት አይታወቁም ማለት ነው። ስለዚህ ህፃናት በተወለዱበት ወቅት ተመዝግበው ሰርተፍኬት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
በጤና ተቋማቱ የሚመዘግበው ባለሙያ የሚመራበት የራሱ የሆነ መዋቅር አለው ያሉት አቶ ዮናስ፤ ተቋሙ በከተማዋ የሚወለድ ህፃን ሳይመዘገብ መቅረት የለበትም ብሎ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
በተቋሙ ለውጥ ሲመጣ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና የልማት ኤጄንሲ የሚፈልጉትን በአንድ ላይ በማሰባሰብ፣ መሰረታዊ የዘርፍ ተነሳሽነትን ለማሳደግና የአገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞን ለማሳለጥ እንዲሁም የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2015