በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1960 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የወጡትን ጋዜጦች ቃኝተናል። በዘመኑ የወጡ የውጭ ዜናዎችንም አካተናል፡፡ በነዚህም ወንጀል ነክ ዜናዎች፤ አደጋዎች ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች እንዲሁም የትራፊክ ቁጥጥሮች ላይ ያተኮሩትን መርጠናል፡፡
፷ ብርጭቆ ውሀ ጠጥታ ሞተች
ከፓሪስ፤ አንዲት ፈረንሳዊት አስተማሪ ስድሳ ብርጭቆ ውሀ ጠጥታ ራሷን በራሷ መግደሏን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አስታወቀ፡፡
፴፰ ዓመት የሆናት ወይዘሮ ስድሳውን ብርጭቆ ውሀ የጠጣችው አከታትላ ነው፡፡ ስድሳኛውን ብርጭቆ ስትጨርስ በመዝለፍለፏ ምክንያት ወደ ሆስፒታል ተወስዳ ነበር፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሞታለች።
የሞተችውም ውሀው እስከ ሳንባዋ ድረስ በመሙላቱ ነው፡፡ የአሟሟቷን ሁኔታ የመረጠችው ራሷ ስትሆን፤ ይህን ዓይነቱ ራስን መግደል የተለመደው በመካከለኛው መቶ ዓመት ነበር፡፡
ርሷም በፈረንሳይ የአትላንቲክ ውቅያኖስ ወደብ አካባቢ በሚገኘው የዕረፍት ጊዜያት ማሳለፊያ ቀበሌ ትዝናና እንደነበርና በዚያም ጊዜ ከማንም ጋር እንዳልተነጋገረች አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገለጠ፡፡
(መስከረም 3 ቀን 1960 ከታተመው አዲስ ዘመን )
በጃንሆይ የሚመራለናይጄሪያ ሁከት አስታራቂ ኰሚቴ ተቋቋመ
ከኪንሻ (ኤ-ኤፍ-ፒ)፤ የናይጄሪያን የፌዴራል መንግሥትንና ተገንጥላ ነፃነቷን ያወጀችውን ቢያፍራን ለማስታረቅ፤ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ሥር አንድ አስታራቂ ኮሚቴ መቋቋሙን ለመሪዎቹ ቅርብ የሆኑ የወሬ ምንጮች አስታወቁ፡፡
በኰሚቴው ውስጥ ዛምቢያ፤ ጋናና ላይቤርያም እንደሚገኙበት ተገልጧል፡፡ በኪንሻሳ ውስጥ የተሰበሰቡ መሪዎች፤ የናይጄሪያ የፌዴራል መንግሥት ከቢያፍራ ጋር ጦርነቱን ለማቆም ስምምነት እንዲያደርግ ለመገፋፋት ተስማምተዋል፡፡ ነገር ግን ከናይጄሪያ መሪ ከሜጀር ጄኔራል ያኩቡ ጎዎን ጋር ለመነጋገር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል አገሮች የመልዕክተኞች ጓድ ይልኩ፤ ወይም አይልኩ እንደሆነ አልታወቀም፡፡
ይህ ውሳኔ መደረጉ የተገለጠው፤ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ዑታንት በጉባኤው ላይ ለመገኘት ኪንሻሳ በገቡበት ወቅት ነው፡፡ ቀደም ብሎ የቻድ ፕሬዚዳንት ፍራንሲስ ቶምቦልቧይ በአደረጉት ንግግር ፤ ድርጅቱ የቆመበትን ዓላማ ለማሟላት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ከማሳሰባቸውም በላይ፤ ከዚህ ቀደም አባል መንግሥታት ጠብ ሲያደርጉ ጠቡን ለማስቀረት አጥጋቢ እርምጃ እንዲወሰድ ከማሳሰባቸውም በላይ፤ ከዚህ ቀደም አባል መንግሥታት ጠብ ሲያደርጉ ጠቡን ለማስቀረት አጥጋቢ እርምጃ አለመወሰዱን አስገንዝበዋል፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል አገሮች፤ ለአፍሪካ ሕዝብ ጥቅም ሲሉ የበለጠ ታታሪነት እንዲኖራቸው ቶምቦልቧይ አሳስበዋል፡፡
(መስከረም 4 ቀን 1960 ከታተመው አዲስ ዘመን )
የትራንስፖር ሕግ የተላለፉ ፰ ሺ ብር ተቀጡ
በደብረ ዘይት፤ በአምቦ፤ በጎጃም፤ በወሊሶና በሾላ በነኚህ አምስቱ ዋና ዋና በሮች የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ ትራኮች የትራንስፖርት ሕግ የተላለፉትን በመከታተልና ከፍርድ ቤት አቅርበው በመክሰስ፤ ከነሐሴ ፩ እስከ ፴ ቀን ፶፱ ዓ/ም በ፩ ወር ውስጥ በጠቅላላው ፰ ሺ ፫፻፸፭ ብር የተቀጡ መሆናቸውን ከሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ ጽ/ቤት የማስታወቂያና ሕዝብ ግንኙነት ክፍል የተገኘው ዜና ገለጠ፡፡
(መስከረም 6 ቀን 1960 ከታተመው አዲስ ዘመን )
ዝንጀሮዎች ሰው ገደሉ
ጐፋ (ኢ-ወ-ም) በገሙ ጐፋ ጠቅላይ ግዛት በጐፋ አውራጃ በጐፋ ወረዳ ኮስቲ በተባለው ቀበሌ ሺበሺ ሌንሣ የተባለው የ፲፪ ዕድሜ ያለው ታዳጊ ልጅ የበቆሎ ሰብል ሲጠብቅ ዝንጀሮዎች በቆሎውን ለመብላት መጥተው ሊያባርራቸው ቢሞክር ተሰብስበው በመያዝ እየጎተቱ የገደሉት መሆኑን የአውራጃው ፖሊስ አዛዥ በጽሑፍ መግለጣቸውን ዋናው ጸሐፊ አቶ ታደሰ ለገሠ አስታወቁ፡
(መስከረም 9 ቀን 1960 ከታተመው አዲስ ዘመን)
ጅብ ሰው ዋጠ
ፍቼ/ኢ-ዜ-አ/ በሰላሌ አውራጃ በግራር ጃርሶ ወረዳ ጥቅምት ፳፯ ቀን ቀትር ላይ አንድ ጅብ ከጫካ ወጥቶ መኖሪያ ቤት ከገባ በኋላ አንድ የአራት ዓመት ልጅ ውጧል፡፡ የልጅቱን እናት ሰውነቷን ነካክሶ ጎድቷታል፡፡
ጅቡንም ያሳድዱ የነበሩት ሁለት ሰዎች፤ ጅቡ ከገባበት ከአቶ ደበሌ ውርጋ ቤት ደርሰው በጥይት ገደሉት፡፡ ከዚያም የጅቡ ሆድ ተሰንጥቆ የልጅቱ አካላት ወጣ፡፡
እመት ድባቤ ገብሩ የተባለችው ሴት በጅቡ የተነካከሰችው በብርቱ በመሆኑ ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ተወስዳለች።
ለማኙ ታሰረ
ድሬዳዋ(ኢ-ዜ-አ) ጌታቸው ኃይሉ የሚባለው ሰው ሙሉ ጤንነት እያለው በሽተኛ ነኝ እያለ በመሬት ላይ እየተንፏቀቀ ሲለምን ተገኝቶ ድሬዳዋ ፫ኛ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ የፈጸመው ወንጀል በማስረጃ ስለተረጋገጠበት በስድስት ወር እሥራት እንዲቀጣ ተፈረደበት፡፡
ጌታቸው ኃይሉ ስሙን በመለወጥ ጀማል ኢሳ በመባል እየተጠራ ጤናማ ሆኖ ሠርቶ መኖሩን ጠልቶ በየሆቴል ቤት እየተዘዋወረ በመለመኑ ሰውን ያስቸግር እንደነበር ሕግ አስከባሪው የ፶ አለቃ ከበደ ካብትህ ይመር ገለጡ፡፡
(ጥቅምት 4 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ብር ለልማት
አሰላ፤ የአርሲ ጠቅላይ ግዛት የጢቾ አውራጃ ሕዝብ ፲፭ ሺ ብር በማዋጣት በሞተር ኃይል የሚሠራ የኤሌክትክ መብራት ለማቋቋም ተስማማ፡፡
ኅዳር ፮ ቀን በአውራጃው ገዥ ቀኛዝማች ይኩኖ አምላክ ኃይለማርያም አማካይነት ሕዝቡ በግዛቱ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ አድርጎ ለልማት ሥራ ፴፩ ሺህ ፩፻፷፭ ብር ያዋጣ መሆኑን አቶ ፈቃደ ወንድሙ ገለጡ፡፡
( ታኅሳስ 2 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/ 2015 ዓ.ም