ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች። ከ3 ሚሊዮን ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው “የሉሲ” ወይም ድንቅነሽ አፅም መገኛ። የአረቢካ ቡና ዝርያ፣ የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ጥቁር አባይም፣ የኤርታአሌ የእሳተ ገሞራ ሀይቅና የዓለማችን እጅግ ረባዳና ሞቃት ስፍራ ዳሎል በኢትዮጵያ ይገኛሉ። ምን ይሄ ብቻ! ኢትዮጵያ የንግስት ሳባ አገር ነች፣ በርካታ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆችና ፍል ውኃዎች፣ እንዲሁም የዱር እንስሳት ፓርኮችና ጥብቅ ቦታዎች ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፤ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ለመሆን በቅታለች። ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የበለፀገች፤ የቱሪስት መስህብ ያላት ብትሆንም ቱሪዝሙ በተለይ ዜጎች የራሳቸውን አገር እና ሃብት የመጎብኘትና የማወቅ ባህል በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያ ዶክተር ተስፋዬ ዘለቀም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጡት። እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሃብት ካላቸው አገራት በቀዳሚነት የምትመደብ ነች። በተለይ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሃብት ያላት አገር ነች። ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ያለው ማንኛውም ነገር የቱሪዝም እምቅ ሃብት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ የሆኑ ሃብቶች እንዳሉ ይታወቃል። ከእኛ የሚጠበቀው ትልቁ ሥራ እነዚህን እምቅ ሃብቶች ወደ ቱሪዝም ምርትና አገልግሎት ቀይሮ ለዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ማበርከት ነው። መንግሥትም ሆነ በቱሪዝም ዙሪያ የሚሰሩ የግል ዘርፉ አንቀሳቃሾች ይህን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል። የትምህርት ተቋማትም ይህንን ያገናዘበ ስርዓተ ትምህርት ቀርፀው ብቁ የሰው ሃብት ማፍራት ይኖርባቸዋል። ከምንም ነገር በላይ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተቻቸው እንደ መስቀል፣ ጥምቀት፣ ኢሬቻ፣ እና ሌሎችም የተፈጥሮና የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነን። በመንግስት እየተሰሩ ሜጋ የቱሪዝም ፕሮጀክቶችም ተጨማሪ የቱሪዝም ሃብቶች መሆናቸውን ገልፀው ፀጋውን ወደ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመቀየር መስሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
ይህንን የተረዳው መንግሥትም በተጠናና በፖሊሲ በተደገፈ መልኩ ከዓመት በፊት ቱሪዝምን ከቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ አንዱ አድርጎ ማካተቱን ይፋ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እና መሰረተ ልማቶችን እየገነባ ይገኛል። በዋናነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበላይ ጠባቂነትና ጥንስስ ሀሳብ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ግዙፍ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ይገኛሉ። በተጨማሪ የቱሪዝም ምርትን በማሳደግ፣ ገበያና የማስተዋወቅ ስራውም በእውቀትና በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማድረግ ስትራቴጂ ተነድፎ በሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን መንግሥት ይፋ አድርጓል።
ከቀናት በፊት ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ማብራሪያ ለመስጠት ብቅ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ዘርፉን ለማሳደግና አገሪቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን ከፍ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉትን ሥራዎች አንስተው ነበር። በተጨማሪ ዘርፉ እየገጠመው ያለውን ፈተናና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችንም እንደሚከተለው አስቀምጠዋል።
ቱሪዝም አእማድ ዘርፍ
በምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የቱሪዝም ዘርፍ የብልፅግና አእማድ ከሆኑ ዘርፎች ውስጥ አንዱ መሆኑን አንስተዋል።ይህ የሆነበት ምክንያት ሲያስረዱም በማለት ገለፃ አድርገዋል። የአገልግሎት ዘርፉ በጣም እያደገና እየሰፋ የሚሄድ መሆኑን አረጋግጠው፤ ኢትዮጵያ የቱሪዝም እምቅ አቅም በጣም በስፋት ያላት እንደሆነች ተናግረዋል። በዚህ ላይ በትኩረት መሥራት ከተቻለ ያለጥርጥር ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ነው ከገለፃቸው መረዳት የሚቻለው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በርካታ ሃብቶች መኖራቸውንም አንስተው ይህንን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ በመግለፅ ሃብቱን ዜጎችን እና አገርን ሊጠቅም በሚችል መልኩ መለወጥ እንደሚገባ ገለፃ አድርገዋል። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ኢትዮጵያ አንደኛ ባህል፣ ሁለተኛ ታሪክ፣ ሶስተኛ ታይተው የማይጠገቡ ቦታዎች አሏት።
አሁን ምን እየተሰራ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ከቅርብ ግዜ ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። ከግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶችና የመዳረሻ ልማቶች በተጨማሪ ቅርሶችን መጠገንና መንከባከብ ላይም ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል። በምሳሌነትም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን አንስተዋል።
“ላልይበላ እጅግ አስደማሚ የሆነ ሥራ ነው።መጠነኛ ችግር ገጥሞታል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ሆነን ለመጠገን ብዙ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።የነበረው ቅርስ ሳይፈርስ መቆየት እንዳለበትም ይናገራሉ።በተመሳሳይ አክሱም ከጣሊያን መንግሥት ጋር በትብብር ለመጠገን ጥናት ከተጀመረ በኋላ የሰላም ችግር መፈጠሩንና መጓተት እንዳጋጠመው ነው የሚገልፁት። ሰላም ሲመጣ የጥገና ሥራው የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።ሌላው ደግሞ ብሄራዊ ቤተመንግሥት በከፊል ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር (ፕሬዚዳንት ማክሮን አግዘው) በከፊል ደግሞ አንድነት ፓርክ ከተከፈተ ጀምሮ በርከት ያለ ሃብት እያስገባ በመሆኑ በዚያ 300 ሚሊዮን ብር ተመድቦ በታችኛው ቤተመንግሥት ላይ ኢንቨስት እየተደረገ ነው።ራሱ ገቢውን ችሎ ፅዳቱን ጠብቆ 300 ሚሊዮን ብር ደግሞ ታችኛው ቤተመንግሥት ኢንቨስት አድርጎ በጣም ዘመናዊ የመኪና ኤግዚቢሽን እየሠራ ነው።ይህ ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻና የገቢ ምንጭ የሚሆን ነው ብለዋል።
አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በመንግሥት ቁርጠኝነት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል። በቅርቡም “ዩኒቲ የመኪና ኤግዚቢሽን” እንደሚሠራ ይፋ አድርገዋል።የፈረንሳይ መንግሥት ባደረገው ትብብርና እገዛ መነሻም ቤተመንግሥቱ በጣም በፍጥነት እየታደሰ መሆኑን ገልፀዋል።ሥራው ተገባዶም በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ነው ቃል የገቡት፡፡
“ታችኛው ቤተመንግሥት በከፊል ወርቁም፣ መፅሃፉም፣ ታሪኩም፣ መኪናውም ለቱሪስት መስህብ ሆኖ በምናስበው ደረጃ ከወጣ እጅግ አስደማሚ ቦታ ነው” የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ይህን የሚያክል ነገር አላት ወይ? ብለው ሰዎች እንዲጠይቁ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።ነገር ግን ቱሪዝም የነበረውን በማዘመንና በመጠገን ብቻ የሚሆን ነገር የለም በማለትም አዳዲስ ግንባታ እና የመዳረሻ ስፍራዎችን ማልማት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት ተነሳሽነት ከሚሰሩ አዳዲስ የቱሪዝም ሥራዎች መካከል ጎርጎራን በምሳሌነት አንስተው እጅግ ግዙፍ እጅግ በጣም ውብ ሥራ መሆኑን መስክረዋል። ጎርጎራ ብቻ ግን ብቻውን አለመሆኑን በመግለፅም ከጎርጎራ ሰላሳ ደቂቃ ባህር ላይ መሄድ ቢቻል ዳጋ ላይ በብዙ አለማት ልናያቸው የማንችላቸውን ታሪኮች ማግኘት እንደምንችል እነዚህም የቱሪዝም እሴቶች መሆናቸውን መስክረዋል።የአፄ ፋሲልና የአፄ ሲሲኒዮስ አስክሬን መቃብር እስካሁን ድረስ ልክ እንደ ሰው ከእነ ስማቸው ከነዘመናቸው መቀመጡንም ነው የተናገሩት።ይህን በየትኛውም ዓለም ላይ የሚገኝ ኪንግደም ሊያሳየን አይችልም ይላሉ።
“የትም ብትዞሩ እንዲህ አይነት እውቀት በቀላሉ ሊገኝ አይችልም” የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እዳጋ እስጢፋኖስ ሲኬድ በጣም በርካታ ታሪኮችን ቱሪስቱ ማግኘት እንደሚችል ያስረዳሉ።ሰው ጎርጎራ ሲሄድ ታሪክ ይማራል፤ እጅግ የሚያምር ሃይቅ ያያል፣ በውሃ ላይም የሚያዝናኑ ድርጊቶች ላይ ይሳተፋል፣ ባማረ ቦታ ማረፍ ይችላል በማለትም ከዚያም ራቅ ብሎ ባህርዳር፣ ጎንደር የመሄድና የመጎብኘት እድል አለው ይላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ሁሉ ሃብት ወደ ቱሪዝም መዳረሻነት መቀየር አንደሚያስፈልግ መንግሥት ተረድቶ በርካታ ሥራዎችን እየሠራና ፕሮጀክቶቹን ይፋ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ይህንን ሁሉ ማያያዝ ሲቻል ቱሪስት ተስቦ ወደ ቦታው እንደሚሄድ እንዲሁም በቀላሉ በርካታ ጎብኚዎችን መሳብ እንደሚቻል አንስተው ይህ እውን የሚሆነው ግን “ዳጋ ላይ እንዲህ አይነት ታሪክ አለ” ስላልነው ሳይሆን ማረፊያ ማዘጋጀትና መዳረሻዎችን ምቹ አድርጎ በማልማት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
“ትራንስፖርት ከሌለ ወደ መዳረሻዎች ጎብኚዎች አይሄዱም።ግንባታ ያስፈልጋል።ለእርሱም እየገነባን ነው” የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች እያለቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ጊዜው ሲደርስ እየተመረቁ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆኑም ነው የተናገሩት።ከግንባታ እና ጥገና ውጭ ግን የቱሪዝም አገልግሎት ዘርፉ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በተገቢው ማወቅ፣ ማልማት እንዲሁም ማስተዋወቅ ሲቻል ሁሉን አቀፍ የቱሪዝም እድገት ማምጣት እንደሚቻል ነው ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ማብራሪያቸውን የሰጡት።
እንደ መውጫ
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚ ከሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ አገሮች መካከል እንድትመደብ መንግሥት እየሠራ መሆኑን ይገልፃል። ለተፈፃሚነቱም የተለያዩ ህጎችን በማርቀቅና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ይፋ እያደረገ ይገኛል። ሜጋ የቱሪዝም ፕሮጀክቶችን የመገንባት ሂደቶችም እየታዩ ነው። ስር ነቀል የአደረጃጀት ለውጥ ማድረግም አንዱ ነው። እምቅ የቱሪዝም ሃብቶችን በገበያ ልማትና ፕሮሞሽን በማገዝ የጎብኚዎች መዳረሻ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ ዋንኛ ሥራው መሆኑም ይታወቃል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዘርፉ ሌላኛው የመንግሥት ዋንኛ ግብ አካታች ቱሪዝምን መገንባት ነው። ቱሪዝም ለጎብኚዎች የመስህብ ስፍራዎችን ማስቃኘት ብቻ ሳይሆን አገር ከዚያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል ነው። በጥቅሉ የአገር ኢኮኖሚ ያድጋል እንበል እንጂ እያንዳንዱ ዜጋ የድምር ውጤቱ ተቋዳሽ መሆኑ የማይቀር ነው። በቅንጅትና ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ የሚገነባው የቱሪዝም ዘርፍ ደግሞ በጥቅሉ ኢትዮጵያን በውብ መዳረሻነትና የላቀ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያደርስ ነው። ይህ ሲሆን ሁሉን አቀፍ (አካታች) የቱሪዝም እድገት ተገንብቷል ማለት እንችላለን። ይህንን መነሻ በማድረግም መንግሥት፣ ዜጎችና ዘርፉ የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ለተፈፃሚነቱ በጋራ ሊሰሩ ይገባል እንላለን። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/ 2015 ዓ.ም