በ1952 ከወጡት የአዲስ ዘመን ጋዜጦች በማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ዜናዎችን መርጠናል። የግዮን መዋኛ ገንዳ መመረቅ ዜና ስናየው በዘመናችን ለሸገር ልጆች መዋኛ መዝናኛ ለምን የላቸውም እንላለን። በፍቼ ከተማ ቀን ቀን የኑግ ዘይት እያመረቱ የነበሩ ባለሀብቶች ሌሊት ለከተማው ነዋሪ ኤሌክትሪክ ብርሃን ያዳርሱ ነበር። ሌሎችም ዜናዎች አሉ እነሆ
በሁለት ቀን ሦስት ልጆች
በወለጋ ጠቅላይ ግዛት በጉድሩ አውራጃ በጐበያ ም/ወረዳ ግዛት በግራዝማች አመኑ መልከኝት ውስጥ የምትገኝ የአቶ ደሬሳ ወዬሳ ባለቤት የሆነች እመት አሠጋሽ ምስክር የተባለች በወላድነቷ የታወቀች ሴት መስከረም ፲፫ ቀን ፶፪ ዓ ም አንድ ወንድ ልጅ ከወለደች በኋላ እንደገና በሦስተኛው ቀን ማለት መስከረም ፲፭ ቀን ፶፪ ዓ ም አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅ ወልዳች ። በጠቅላላው ሦስት ልጆች በመውለዷ ሀገሯን የምታኮራ መሆኑ ቢታወቅም ፤ ለጊዜው የሚደርስባትን የዕለት ሁኔታ ሁላችንም ልናውቅላትና ልናዝንላት ይገባናል። ይህንንም ሁኔታ ለማወቅ የቻልነው የክፍሉ ወረዳ ዋና ጸሐፊ አቶ ጳውሎስ ለአውራጃው ገዥ ለተከበሩ ደጃዝማች ተስፋዬ ወልዴ በቁጥር ፩፻፴፩/፴፮ መስከረም ፳፯ ቀን ፶፪ ዓ ም ሲጽፉ ባደረጉልን ግልባጭ ስለሆነ፤ የነገሩ እርግጠኝነት የሚታመን ነው።
የሕፃናቱ ማደግ ያለማደግ የሚታወቀው የፈጠራቸው ብቻ መሆኑን ከተገነዘብን በኋላ፤ ፅንሳቸው ወይም ዘራቸው እንዴት ነው? የማለት ሀሳብ ይታገለን ይሆናል።
የወለጋ ጠቅላይ ግዛት አዣንስ ኃይለመስቀል ወልደየስ
(በኅዳር 29 ቀን 19 52
ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የአዲሱ የውሀ መዋኛ መመረቅ
መስከረም ፳፱ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ. ም ከዕኩለ ቀን በላይ በ፱ ሰዓት በግዮን ሆቴል ቅጽር ግቢ ውስጥ አዲስ የተሠራ የውሀ መዋኛ ሥፍራ በልዑል ሣህለ ሥላሴ ኃይለሥላሴ የገሙ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ተመርቆ ተከፍቷል።
በአመራረቁ ሥነ ሥርዓት ላይ ንጉሣውያን ቤተ ሰብ፤ ክቡራን ሚኒስትሮችና መኳንንት፤ እንዲሁም የውጭ ሀገር መንግሥታት እንደራሴዎች ተገኝተው ነበር።
የአዲሱ መዋኛ አካባቢ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና በልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት ባላቸው ጌጣ ጌጦች አምሮና አሸብርቆ ከመገኘቱም በላይ፤ በብዙ መቶ የሚቆጠር ሕዝብ ወደ በዓሉ ሥፍራ ሔዶ የአመራረቁን ሥነ ሥርዓት ተመልክቷል።
ልክ ፱ ሰዓት ሲሆን፤ ልዑል ሣህለ ሥላሴ ደርሰው በተዘጋጀላቸው ሥፍራ ላይ እንደተቀመጡ ስድስት ዋናተኞች ከአምስት ሜትር ርቀት ላይ እየዘለሉ ወደ ተከተረው ውሀ በመጥለቅ፤ የአጠላለቅ ዋና አሳዩ።
(ጥቅምት1 ቀን 1952
ከወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለኛ አውሎ ነፋስ
በኅዳር ፲፯ ቀንና ፲፰ ቀን በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በአሰላ ከተማ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ስለተነሳ የብዙ ቤት ቆርቆሮዎችን በሙሉ ሳይሆን በከፊል እያነሳ አውልብልቧቸዋል። እንደዚሁም ብዙ ሊባል አይቻልም እንጂ አነስተኛ ዛፎችንም ጥሏል።
በሌላ በኩል ምንም ጉዳት ያደረገው ነገር የለም።
• • •
ዝናብ
ኅዳር ፳፩ ቀን ፶፪ ዓ ም ጀምሮ በአሰላ አካባቢ ከፍ ያለ ዝናብ ስለዘነበ በመሰብሰብ ላይ ለሚገኘው አዝመራ ሳያሰጋ አይቀርም በማለት ገበሬዎች የስጋት መንፈስ አድሮባቸዋል።
አንዳንዶቹም ጨረቃዋ ጠፍ በመሆንዋ ጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ብዙ አይዘንምም በማለት ቀድሞ ምልክት ሲናገሩ አንዳንዶች ደግሞ ለማናቸውም ሰብልን ቶሎ ቶሎ መሰብሰብ አይከፋም ሲሉ ይሰማሉ።
የአሩሲ ጠቅላይ ግዛት አዣንስ
ተፈራ አሸናፊ።
የኤሌክትሪክ ብርሃን መስፋፋት
የፍቼ ከተማ ብዙውን ጊዜ የኤሌክትሪክ ብርሃን እንዳልነበረው የታወቀ ሲሆን ከሐምሌ ፲፱፻፶፪ ዓ. ም ወዲህ በፍቼ ከተማ የሚገኙት ያኑሪስ ወንድማማቾች ነጋዴዎች ባለ ፳፬ የፈረስ ጉልበት ሞተር አቋቁመው በሥራ ሰዓት የኑግ ዘይት ሲያወጣ የምሽቱን ጊዜ ግን ለከተማው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን በመስጠት የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን በብዙ እንደጠቀመ አንዘነጋውም።
ነገር ግን የሞተሩ ኃይል ከተማውን በሙሉ በኤሌክትሪክ ብርሃን ለማገልገል ስላልቻለ እነዚሁ ወንድማማቾች በከተማው መካከል የነበረውን ሞተር አንስተው ከከተማው መግቢያ በር ላይ ፲፭ ሜትር በ ፲፭ በሠሩት መጋዘን ውስጥ ባለ ፹ ፈረስ ጉልበት የዘይት ማውጫ ሞተር አቋቁመው የኑጉ ዘይት በትሩ መልክና መአዛ እየወጣ ገበያውን ከማስፋፋቱም በላይ ፳፬ ሰዓት ሙሉ ባለማቋረጥ የኤሌክትሪክ ብርሃኑን የሚሰጥ ሆኗል። ካሁኑ በፊት የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላገኙትም ቦታዎች ሁሉ እንዲታደላቸው ምሶሶውን በማቆምና ሽቦውን በመዘርጋት ሥራ ላይ ስላሉ ከፍተኛ ብርሃን ያለውን ኤሌክትሪክ የፍቼ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ በሙሉ ለማግኘት ችሏል።
የመርሐ ቤቴና የሰላሌ አውራጃ አዣንስ ላዕከ ደስታ
(ኅዳር 4 ቀን 19 52 ዓ.ም
ከታተመው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/ 2015 ዓ.ም