ልባሽ ጨርቆች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከከለከሉ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በሕገ-ወጥ መንገድ እንደሚገቡ አዲስ ዘይቤ በቅርቡ ያስነበበው ሰፊ ሃተታ ላይ የሰፈረው መረጃዎች ያመለክታል። ከዚህ ዘገባ መረዳት እንደሚቻለውም የልባሽ ጨርቆች ወይም በተለምዶ ሰልባጅ ተብሎ የሚጠራው የልብስ ገበያ በአገሪቱ የፋሽን ኢንዱስትሪ ላይ ፈተና እንደሆነ ነው፡፡
ዘገባው ላይ እንደተቀመጠው ያገለገሉ አልባሳት ንግድ በከፍተኛ መጠን ያደገው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው። የፋሽን ኢንዱስትሪው ፈጣን እና ተቀያየሪ የአለባበስ ዘይቤን መከተሉ ከጥቂት አገልግሎት በኋላ የማይፈለጉ አልባሳትን ቁጥር በእጅጉ ጨምሮታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የሚከማቹትን የማይፈለጉ አልባሳት ማስወገድ የመንግሥታት ፈተና እስከመሆን ደርሷል።
የቆሻሻ ክምችትን ይጨምራሉ፣ የአካባቢ ብክለትን ያባብሳሉ፣ ለምርት የወጣባቸውን ንጥረ-ነገር ያባክናሉ የሚባሉት የማይፈለጉ ልባሽ ጨርቆች አንዱ መዳረሻቸው በማደግ ላይ የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ናቸው። የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚ አሻጥረኞችም ዝቅ ባለ ዋጋ የሚቀርበውን የቻይናን ምርት ስርጭት ለማዳከም እንደመሣሪያ እየተጠቀሙበት ነው የሚሉ ተንታኞችም አሉ፡፡ እነኚህ ወገኖች የአፍሪካ አገራት በልባሽ ጨርቆች ንግድ ጉዳይ የእገዳ ሕጎች ሲያወጡ አሜሪካ እንደ አጎዋ ካሉ የንግድ ስምምነቶች የማስወጣት ውሳኔ ማሳለፏን የጉዳዩን ውስብስብነት ለማሳየት ተጠቅመውበታል።
በኢኮኖሚ ካደጉት ምዕራባውያን አገራት የሚነሱት ልባሽ ጨርቆች (ሰልባጅ) መዳረሻቸው ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ናቸው። የገቢያቸውን አብዛኛውን ድርሻ ለምግብ ወጪ የሚያውሉ ብዙ ዜጎች ላላቸው ድሃ አገራት ሰልባጅ ዋነኛ የአልባሳት አቅርቦት ምንጭ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በንግድ ሰንሰለቱ ላይ የሚገኙ እንደ ጫኝና አውራጅ፣ ቸርቻሪ፣ አጣቢ፣ ጠጋኝ ያሉ የሥራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በሂደቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የልባሽ ጨርቆች ንግድ በሚፈቅዱ አገራት የገቢ ግብር የሚሰበሰብበት ሕጋዊ የንግድ ዘርፍ ሲሆን በተለይ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት አምራች እና አስመጪዎችን አያበረታታም በሚል በሕገ-ወጥነት ተፈርጇል፡፡
ልባሽ ጨርቆች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከከለከሉ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በሕገ-ወጥ መንገድ እንደሚገቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር አስናቀ ከፋለ ከዓመት በፊት ካሰናዱት ጽሑፍ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። እገዳ ስለተጣለባቸው በስውር ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ልባሽ ጨርቆች ለሽያጭ የሚቀርቡት በግልጽ በአደባባይ ነው። ከፍ ያለ የልባሽ ጨርቆች ግብይት ከሚካሄድባቸው የአገሪቱ ከተሞች መካከል አንዷ አዳማ ናት። በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞንና በቦረናም ይህ ንግድ በስፋት ይስተዋላል፡፡
ለእርጅና ሳይደርሱ ጥቂት ጊዜ አገልግለው ለአዳማ ገበያ ከሚቀርቡ መገልገያዎች ውስጥ አልባሳት (የወንድ፣ የሴት፣ የሕፃናት)፣ ጫማዎች፣ የወንድ እና የሴት ቦርሳዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎች ይገኙበታል። ቁሳቁሶቹ አዳማ የሚደርሱት በሁለት የድንበር መተላለፊያዎች ማለትም በሶማሌላንድ ድንበር ቶጎ ውጫሌ እና በኬንያ ሞያሌ በኩል ነው።
አልባሳት የታጨቀባቸው ግዙፍ የሸራ ጥቅሎች «ቦንዳዎች» እና ጫማዎች በጭነት እንስሳት፣ በሞተር ሳይክሎች፣ በጭነት ተሽከርካሪዎች ድንበሮቹን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። በድንበር ከተሞች ለሽያጭ በጅምላና በችርቻሮ ከቀረቡ በኋላ በሦስት ዓይነት ነጋዴዎች ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ይሰራጫሉ።
የችርቻሮ ነጋዴዎች ልብሶቹን እና ጫማዎቹን በመደበኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መደበኛ ተጓዥ በመምሰል ዕቃዎቹን ለማሳለፍ የሚሞክሩበት የመጀመሪያው መንገድ ነው።
ሁለተኛው የጅምላ ነጋዴዎች በጭነት መኪናዎች ቁሳቁሶቻቸውን ጭነው በሕጋዊ ሽፋን የሚያልፉበት ነው። ለዚህኛው ዘዴ ከኬላ ጥበቃ ሠራተኞች ጋር መመሳጠር ያስፈልጋል። የገንዘብ ጥቅም ያገኙት ጥበቃዎች ያዩትን እንዳላዩ በማለፍ ነጋዴዎችን ይተባበራሉ።
የጭነት ተሽከርካሪውን ሕጋዊ ባልሆነ፣ ባልተፈቀደ መንገድ ማስጓዝ ሌላኛው አደገኛ መንገድ ነው። ከጠባቂዎች ዐይን እና ጆሮ ተሰውሮ ለማለፍ የሚደረገው ጥረት ላልታሰበ አደጋ የሚዳርግበት ጊዜ ብዙ ቢሆንም አሁንም ያንን መንገድ የሚከተሉ ደፋሮች አሉ። በዚህ መንገድ የተጓጓዘው ቁሳቁስ ኬላ ከመድረሱ አስቀድሞ ለሞተረኞች ይከፋፈላል። ከግዙፉ ጭነት ጥቂቱን የሚቆነጥረው ሞተረኛ ባልተፈቀደ አቋራጭ ኬላውን ያሻገረውን ዕቃ ከኬላው ወዲህ ማዶ ጠብቆ ለባለቤቱ ያስረክባል።
የተለያዩ የፋሽን አልባሳት መሸጫ ሱቆችም ተጫርተው ይገዙና መልሰው ለገበያ
ያቀርባቸዋል፡፡ ሱቆቹ ለችርቻሮ ገበያ የሚያቀርቧቸውን አልባሳት፣ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች እንደ ቴሌግራም ባሉ ለማኅበራዊ ትስስር ገጾች ያስተዋውቋቸዋል። ክፍያውን በባንክ በመፈጸም የመረጡት አልባሳት ወይም ጫማ በሌላ ገዢ እንዳይወሰድ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል።
የአገር ውስጥ አምራቾች በምርት ግብዓት እጥረት፣ በዘመናዊ የማምረቻ ማሽነሪዎች እና ቴክኖሎጂ ያልተደገፈ አመራረት ዘዴ ስለሚጠቀሙ በቂ ምርት አለማምረታቸው ነጋዴዎች ሕገ ወጡን መንገድ እንዲመርጡ እንዳደረጋቸው ሲናገሩ ይሰማል፡፡
የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ከአቅም በታች እያመረቱ መሆኑ ቢታመንም በዚህ ረገድ ጠንካራ ሥራ ለመሥራት ጠንካራ ፖሊሲ ያስፈልጋል የሚሉ ባለሙያዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በመሆኑም መንግሥት በበቂ ሁኔታ የተጠና እና ችግር ፈች የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የአገሪቱን ኢንዱስትሪዎች ከመሞት መታደግ እንዳለት የቴክስታይል ምህንድስና ባለሞያዎች እምነት አላቸው፡፡
ተወዳዳሪ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ እንዲፈጠር በመንግሥት በኩል የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ፣ የሎጀስቲክ ወቅታዊ መረጃን ለአምራቾች በማቅረብ በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል፣ እንዲሁም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መሰጠትም አንዱ የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኞ ኀዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም