(ክፍል 2)
በክፍል አንድ ጽሑፋችን ስለቅዱስ ያሬድ እና የቅኝት አይነቶች፣ እንዲሁም መደበኛና ኢመደኛ ሙዚቃዎችን አይተናል። እነሆ ዛሬ ደግሞ ስለባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች፣ እንዲሁም የሙዚቃን ችግሮች፣ ከሙዚቃ ባለሙያው አብርሃም ወልዴ የሰማነውን በክፍል ሁለት እናስነብባችኋለን።
የባህል ሙዚቃ አጀማመር
በኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ የተጀመረው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ1889 ዓ.ም በሸክላ ማጫዎቻ ነው። የሸክላ ማጫወቻውም ንግሥት ቪክቶሪያ ለእቴጌ ጣይቱ እና ለዳግማዊ አጼ ምኒልክ የላኩት ነው። መጀመሪያ የሰሙትም እቴጌ ጣይቱና አጼ ምኒልክ ናቸው ማለት ነው።
ይህ በሆነ በዓመቱ በ1890 ዓ.ም ሙዚቃ መቅዳት ተጀመረ። መጀመሪያ የተቀዳው (የተቀረጸው) የእቴጌ ጣይቱና የአጼ ምኒልክ ድምጽ ነው። አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ የተቀረጹት ድምጽ በእንግሊዝ የድምጽ ቅጅ ተቋም (The British Institute of Recorded sound) አሁን ድረስ ለታሪክ ተሰንዶ ተቀምጧል።
በ1901 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሸክላ ሙዚቃ የሰሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ናቸው። በዚህ የመጀመሪያው የሸክላ ሙዚቃ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ 17 ዓይነት ሙዚቃዎችን ሰርተዋል። ሙዚቃዎቹን የቀረጿቸው ጀርመኖች ናቸው። የተከፈላቸውም 17 ሺህ ፍራንክ ነበር።
እንደተጀማመረ ግን በኢትዮጵያ እንደ ሰገሌ አይነት ጦርነቶች ተጀመሩ፤ ቀጥሎም የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ተጀመረ። በእነዚህ ምክንያቶች ሙዚቃ ሳይቀረጽ ለ20 ዓመታት አካባቢ ተቋርጦ ቆይቷል። ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ የሸክላ ሙዚቃዎች ሥራ ጀምረው ብዙ ባህላዊ ሙዚቃዎች ተሰርተዋል።
የባህል ሙዚቃዎች መነሻቸው ያሬድ ነው። በኋላ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ የተለያዩ ስሜቶችን ለመግለጽ በስፋት ሥራ ላይ ውለዋል። በሀዘንም በደስታም ይጠቀሙታል።
የዘመናዊ ሙዚቃ አጀማመር
ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ያቀረቡት በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን ሩሲያውያን ናቸው። አጼ ምኒልክም ሩሲያውያን ከኢትዮጵያ ሰው ወስደው እንዲያሰለጥኑላቸው ጠየቁ።
የሰለጠኑት ሰዎች ሰልጥነው ለመጀመሪያ ጊዜ በዘመናዊ ሥርዓተ ክዋኔ የቀረበው በ1923 ዓ.ም ነው። በ1934 ዓ.ም የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የንግሥ በዓል ላይ በዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የተሰሩ ሥራዎች ቀረቡ። እነዚህ ሥራዎች በሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን እና በውጭ ሰዎች ቅልቅል የቀረቡ ናቸው።
ክቡር ዘበኛ
ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የኦርኬስትራ ሙዚቃ የተጀመረው በክቡር ዘበኛ ነው። የክቡር ዘበኛን ኦርኬስትራ ያሰለጠነውም ካፒቴን ኬቮርክ ናልባንዲያን የተባለ አርመናዊ ነው። ክቡር ዘበኛ የመጀመሪያ ኦርኬስትራ ሲሆን የምድር ጦር ኦርኬስትራን አሰልጥኗል።
የተለያዩ የንግሥ ዝግጅቶች ሲኖሩ እና ቴአትር ሲታይ ማጀቢያ የሚሆነው የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ነው። ሰዎች ሙዚቃ የሚሰሙትም በእነዚህ አጋጣሚዎች ነበር።
እንዲህ እንዲህ እያለ በ1960 ዓ.ም ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተቋቋመ። የክቡር ዘበኛ፣ የምድር ጦር፣ ፖሊስ ኦርኬስትራ፣ ማዕከላዊ ዕዝ… እየተባለ ሙዚቃ መተዋወቅ ጀመረ። ዕዞች ደግሞ የደቡብ፣ የምሥራቅ… እየተባለ ተስፋፉ።
የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ፣ ብሔራዊ ቴአትር… የመሳሰሉትም የሙዚቃ ክፍል እያዘጋጁ ማቅረብ ጀመሩ።
እንዲህ እንዲህ እያለ ሲሄድ ቆይቶ ባንዶች መጡ። ባንዶች ሲመጡ ከባህላችን ያፈነገጡ ናቸው የሚል ተቃውሞ ይገጥማቸው ነበር። አቅራቢዎችም ወጣቶች ስለነበሩ የፈረንጅ ስታይል ይቀላቅሉበት ነበር። ከመጀመሪያዎቹ የባንድ ምድቦችም ሮሃ ባንድ፣ ዋሊያስ ባንድ፣ ዳዲሞስ ባንድ፣ ኢትዮ ስታር ባንድ፣ አሞራው ባንድ ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ባንዶች ሲስፋፉ ሙዚቀኞች ዕድል ማግኘት ጀመሩ። በቤተ መንግሥት ዙሪያ ተወስኖ የነበረው የሙዚቃ ተሳትፎ ወደ ህብተረሰቡ ለመግባት ዕድል አገኘ። ባለ ተሰጥዖዎችም መቀላቀል ጀመሩ። የድሮ ዘፋኞች ከክቡር ዘበኛ፣ ከምድር ጦር፣ ከፖሊስ ኦርኬስትራና ከዕዞች የተገኙ ቢሆንም ባንዶች መመስረታቸው ግን የበለጠ ዘርፉን ለማስፋፋት፣ ነፃነትን ለመስጠት በር ከፍቷል።
የሙዚቃ ማህበራዊ ፋይዳዎች
በማህበራዊ ፋይዳው ውስጥ ሙዚቃ ‹‹እርኩስ መንፈስ›› እና ‹‹ቅዱስ መንፈስ›› ተብሎ ሊለይ ይችላል። በእርኩስ መንፈሱ በኩል፤ ቅናት፣ ሃሜት፣ ምቀኝነት፣ ውሸት፣ ጥላቻ፣ ክህደት፣ ጦረኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ሴሰኝነት… የመሳሰሉት ይተላለፉበታል። እነዚህ እርኩስ መንፈሳዊ መልዕክቶች የሚተላለፉት በግጥሙ ነው። ቅዱስ መንፈስ ያለው ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን የፀየፍና ፍቅርና ደስታን የሚፈጥር ነው።
ሙዚቃ ከሀሳብ የሚመነጭ እና ከተሰጥዖ የሚፈልቅ የጥበብ ነፀብራቅ ነው። በዚህ መንገድ የሚሰሩ ሙዚቃዎች ዘመን ተሻጋሪ ይሆናሉ። ታሪክን እየተናገሩ ይኖራሉ።
በሙዚቃ ማህበራዊ ፋይዳ ውስጥ መልዕክት ነው የሚነገር። አንድ አፍቃሪ ተፈቃሪዋ ያደረሰችበትን በደል ሊነግራት ይፈልግ ይሆናል፤ ይህ ግን እንደ ጥላቻ አይቆጠርም፤ አፍቃሪነቱን እየተናገረ ነው። በአጠቃላይ በጥበብ ውስጥ ሆኖ መልዕክትን ማድረስ ማለት ነው። ስሜትን መግለጽ ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ችግሮች
በነገራችን ላይ ይህን ነገር ከዚህ በፊትም አብርሃም ወልዴ በአንድ መድረክ ላይ ሲናገር ሰምቻለሁ። ከችግሮቹ ውስጥ በግንባር ቀደምነት የሚያነሳው ድህነትን ነው። በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቅሰው የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ነው። በእርግጥ ሁለቱም የተያያዙ ናቸው። አንድ ባለሙያ፤ መንግሥት ‹‹እንዲህ ብለህ ዝፈንልኝ›› ሲለው የሚዘፍን ለገንዘብ ብሎ ነው። በራሱ አምኖበትና በራሱ ተነሳሽነት ቢሆን ምንም ችግር አልነበረውም፤ ችግሩ ግን ያንን በማድረጉ የሆነ ነገር እንደሚያገኝ አስቦ ሲሰራው ነው።
ይህ ሲሆን ሙዚቃ ይበላሻል፤ አንድ ባለሙያ ያላሰበበትን እና ከውስጡ ፈንቅሎ ባልወጣ ስሜት የሚሰራው ሥራ ተልካሻ ነው የሚሆን። በግዴታ የተሰራ ሥራ ዘመን ተሻጋሪ ሊሆን አይችልም።
በጣም ስሜታዊ መሆንም ልክ አይደለም። ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚሳሳቱት ከመጠን ያለፈ ስሜታዊ ሲሆኑ ነው። የማሰላሰያና የማሰቢያ ጊዜ መኖር አለበት። በአጠቃላይ ሙዚቃ መሰራት ያለበት በውስጥ ስሜት ተነሳሽነት፣ ሀሳብ በማመንጨት እንጂ በግንፍል ስሜትም ወይም ደግሞ በመንግሥት ትዕዛዝ አይደለም።
ሌላው የሙዚቃ ችግር ተብሎ የተገለጸው ‹‹እውነታን መሸፈን›› የሚል ነው። አንድ ሙዚቀኛ ቢሳሳት የሰውየውን ስም ጠቅሶ የተሳሳተውን ነገር መንገር የተለመደ አይደለም። እንኳን ሥራው የሰውየ ሕይወት ራሱ ወደ ስህተት የሚሄድ ቢሆን በግልጽ ስህተቱን የሚናገር የለም። መማሪያ የማድረግ ባህል የለም።
አብርሃም እንደሚለው፤ እንኳን በአደባባይ በቃለ መጠይቅ ስማቸውን ጠቅሶ ችግራቸውን የተናገረባቸው ይቅርና፤ በግል ጠርቶ ለብቻቸው የነገራቸው ራሱ አኩርፈውታል። እንዲህ አይነት ችግሮች ካልተነገሩና ካልተቀረፉ ደግሞ ችግሩን ማስወገድ አይቻልም።
ሌላው ችግር ተብሎ የተጠቀሰው ደግሞ ሱስ ነው። ይህንንም መናገር ከብዙ ባለሙያዎች ጋር የሚያጣላ ነው። ለብዙ ህመሞች ይዳርጋል። ጎጂነቱን ተጠቃሚዎች ያውቁታል፤ ዳሩ ግን የማያውቁትና ልብ ያላሉት ነገር በሱስ ውስጥ ሲሆኑ ብዙ የሰሩ ይመስላቸዋል እንጂ አይሰሩም። በምርቃና የሚሰራ ሥራ የሚጣለው ነው የሚበልጥ። ለእነርሱ ግን የሥራዎች ሁሉ ጣሪያ መስሎ ሊታያቸው ይችላል። በተፈጥሮ መነቃቃት ነው ለሥራውም ለጤናም ዘላቂ የሚሆነው።
ሌላው ለሙዚቃ መበላሸት እንደ ምክንያት የተጠቀሰው ነገር ደግሞ፤ አንድ ዘፋኝ ሁሉንም ነገር የሚችል መስሎት ሲሰራው ነው። ግጥሙንም፣ ዜማውንም፣ ድምጹንም ራሱ ሊሰራው ይችላል። ይህ የሚሆነው የሦስቱም ተሰጥዖ ካለው ነው። ዜማ ተሰጥዖ ነው፤ ድምጽም ተሰጥዖ ነው፤ ግጥም ደግሞ ሌላ ራሱን የቻለ ተሰጥዖ ነው። አንድ ዘፋኝ ሦስቱንም ራሱ ማሟላት ግዴታ አይደለም፤ ቢቻል ጥሩ ነበር፤ ግን ደግሞ ዜማና ግጥም የራሱ ለማስመሰል መበላሸት የለበትም።
ግጥም ዕውቀት ይፈልጋል፤ ማስተዋልና ነገሮችን መረዳት ይፈልጋል። ስለዚህ ጥሩ ድምጽ ያለው ድምጻዊ ዜማና ግጥም ከሌላ ቢወስድ የተዋጣለት ሥራ ይሰራል። ዜማ የሚችል ድምጻዊ ግጥም ከሌላ ቢወስድ የተዋጣለት ይሆናል። ጥሩ ግጥም የሚጽፍ ከሆነ ለድምጻዊና ዜመኛ መስጠት ነው።
አንዳንድ ዘፋኞች የሁሉም ተሰጥዖ ያላቸው አሉ። እነርሱ በራሳቸው የሰሩት የሁሉም ተሰጥዖ ስላላቸው ነው። ለምሳሌ፤ ንዋይ ደበበ የራሱን ግጥምና ዜማ በመሥራት ተወዳጅ ሆነ። በዘመኑ በየጋዜጦችና መጽሔቶች፣ ሬዲዮ ጣቢያዎች ተደነቀ። በዚያን ጊዜ በራስ ግጥምና ዜማ ሙዚቃ መሥራት እንደ ፋሽን ተያዘ። የብቃት ማሳያ ተደረገ። ሙዚቃ ቤቶች የሚሸጥ የራሱ ግጥምና ዜማ ያለው ሙዚቀኛ ነው ማለት ጀመሩ።
በዚያን ጊዜ ዘፋኞች ከዜማና ግጥም ደራሲዎች ላይ መግዛት ጀመሩ። ለደራሲው ገንዘብ ይከፈልና ባለቤትነቱ በዘፋኙ ስም ይወጣል፤ ታሪክ እየተበላሸ ሄደ ማለት ነው።
በኋላ ደግሞ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) መጣ። ቴዲ አፍሮ የግጥም፣ ዜማ ደራሲና ድምጻዊ መሆኑ አሁንም ሌላ አብዮት ፈጠረ። ሙዚቃ የሚወደደው ዜማውም ግጥሙም የዘፋኙ ሲሆን ነው ተብሎ ታሰበ።
እውነታው ግን ይህ አልነበረም። ንዋይ ደበበ እና ቴዲ አፍሮ የተዋጣላቸው የሁሉም ተሰጥዖ ያላቸው ስለሆኑ ነው። ጥሩ የድምጽ ተሰጥዖ ስላላቸው፣ ዜማና ግጥም የመጻፍ ችሎታ ላላቸው ነው። እነዚህ ሰዎች በችሎታቸው ስላደረጉት እንጂ የግድ ሁሉም ከአንድ ሰው መሆን ስላለበት አይደለም።
ስለዚህ አንድ ባለሙያ መጀመሪያ ተሰጥዖና ችሎታውን ነው መለየት ያለበት። ድምጽ አለው? ዜማ ይደርሳል? ግጥም ይጽፋል? እነዚህን ተሰጥዖና ችሎታዎች ካሉት ራሱ መስራት ይችላል፤ ከሌሉት ግን የሚችለውን ሰርቶ የማይችለውን ከሚችሉት ቢያመጣ ለሙያውም ክብር ነው፤ ሥራውም ተወዳጅ ይሆናል። ድምጹን የሚመጥን ዜማ መኖር አለበት፣ ድምጹንና ዜማውን የሚመጥን ግጥም መኖር አለበት። እንደ ምሳሌ፤ ንዋይ ደበበ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና እሱባለው ይታየው (ትርታዬ) ተጠቅሰዋል።
እንደ ሕዝብ ደግሞ በራሳችን አገር በቀል የጥበብ ሥራዎች ልንኮራ ይገባል። ምዕራባውያን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለራሳቸው ሲናገሩ፤ በኢትዮጵያውያን በኩል ግን የራስን ማጣጣል የተለመደ እየሆነ ነው። ከበሮ፣ ማሲንቆ፣ ክራርና ዋሽንት የሚሰጡትን ጥዑመ ዜማ ከማንም ልናገኘው አንችልም። ስለዚህ እኛም የራሳችንን ማስተዋወቅ አለብን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 1/ 2015 ዓ.ም