ብዙዎቻችን ‹‹ ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች›› የሚለውን አባባል ከእናቶቻችን ማንነት ጋር ማያያዛችን የተለመደ ነው። የአብዛኞቻችን ምክያታችንም ተመሳሳይ ይመስለኛል። እናት ለቤተሰቧ ስትል የማትከፍለው ነገር እንደሌለ ለማሳየት አባባሉ ተስማሚ ነው።
አዎ እናት ስለቤተሰቧ ብዙ ትሆናለች ።አንዱና ዋንኛው ዝቅ ብላ ሰርታ ልጆቿን ከፍ ማድረጓ ነው። ሌላው ደግሞ ምንም ሳያምራት ልጆቿ የፈለጉት ነገር እንዲሟላላቸው ታደርጋለች። ሕይወቷን፣ ልጅነቷን፣ ደስታዋን ሁሉ ለእነርሱ ትሰጣለች። የእርሷ የሆነ ነገር ሁሉ የእነርሱ ብቻ እንደሆነ ታስባለች ። ‹‹ከእኔ ልጆቼ ይቅደሙ›› ማለት መለያዋ ነው።
እናት የጓዳ መብራት ብቻ አይደለችም። የተራራ ላይ ብርሀን ጭምር ናት የምንለው ለዚህ ነው። ልጆቿን በባህሪና በተስተካከለ መንገድ እየመራች ከፍታውን ታሳያለች። እንዲሆኑላት የምትሻውን ብቻ ሳይሆን እንዲሆኑ የሚፈልጉትን ለመምራት እንደሻማ ቀልጣ ያሰቡትን ታደርጋለች። በቃ ስለእሷ ለመናገር በቃላት መወሰን አይቻልም። እርሷ ስትታሰብ እርግዝና እና ሕፃናትን ተንከባክቦ ማሳደግ ትንሹ ሥራ ይሆናል ። ከዚያ ሻገር የሚለውና ብዙ ፈታኝ ነገሮች ያሉበት ሥራ ነው ለእነርሱ ብርታትና መሻገሪያቸው። በዚያ ውስጥ ሆነው የልጆቻቸውን ነገ አሻግረው ያያሉ፤ በዚያ መከራ ውስጥ ሆነው ተስፋ የሚያደርጉትን ያረጋግጣሉ። ምክንያቱም ያንን እንደሚያሳኩት አምነው ይጓዛሉና ።
ስለ እናትነት ስናነሳ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አርግዞ መውለድ ብቻ እንዳልሆነም ብዙዎቻችን የምንስማማበት ጉዳይ ነው። ምክያቱም የእናትነት ቦታ ተጨማሪነት አለበት። ሳይወልዱ የእናትን ኃላፊነት መሸከም፤ ከእናት አልፎ አባትም መሆን፤ ያልወለዱትም ማሳደግና መሰል ነገሮችን አክሎና የእኔ ነው ብሎ መስራትን ይጨምራል።
አንዳንዴ እናትነት ዘመድ ወይም የሥጋ ግንኙነት የማይተካው ሲሆንም ይታያል። ይህ ደግሞ እናትነት ከሴትም በላይ ተጨማሪ ተፈጥሯዊ ስጦታ እንደሆነ ይነግረናል።
ወደ ሥራው አለም ስንገባም ይህንኑ ነው የምናረጋግጠው። እናትነት ለማንኛውም ተልዕኮ በቂነት እንደሆነ። ጾታ፤ እድሜ የማይገድበው ትህትና። ለዚህም በማሳያነት የምናነሳው እያንዳንዱ ቀን ለልጆቼ በሚል የተከፋፈለና ያለ እረፍት የሚለፋበት መሆኑን ነው። እናት ዘወትር በቀኗ ውስጥ የምታደርገውን ነገሮች እንዳለ ለልጆቿ ለውጥ የሚውል መሆኑ። ከቤት ህይወት ብንነሳ እንኳን ልጆቿን አጥባ ማሳመር መነሻዋ ነው።
ሲርባቸው መመገብ፣ ሲደክማቸው ማስተኛት፣ የተዘበራረቀውን ማስተካከል፣ የቆሸሹትን ልብሶች ማጠብ፣ የከፋቸውን ልጆች ማጽናናት ፤ ባዶ የሆነውን መሶብ መሙላት፣ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል ። ይህን ሀላፊነት ስትጨርስ ደግሞ ከውጭ የሚጠብቃትን ሥራ ትቀጥላለች።
ሁሉንም ቤተሰብ በቤት ውስጥ ደስተኛ የምታደርገው ከቤት አልፋ ውጪም ላይ ሰርታ በምታመጣው ገንዘብ እንደሆነ ይታወቃል። እናም ልክ እንደወንዱ እኩል ለፍታ ቤቷን ሙሉ ለማድረግ የቤቱን ሥራ አጠናቃ ትወጣለች። ትንሽ ከትልቅ የሚባለውን ሁሉ ትሰራለች። ዋና አላማዋ ልጆቿን የሚደጉምላት ገቢ ማግኘቷ ላይ ነው።
የውጩን ልፋት ፤ የቤቱን ችግር ለመፍታት ታትራ ትሰራለች። ቤቷ ስትገባ ፈገግታ የሚሞላትም ይህ ነገሯ ሲሳካላት ነው። በዚያው ልክ ቤቱ ሳይሞላላት ሲቀር ደግሞ የምታለቅስና ምን ላጉርሳቸው እያለች የምትጨነቅም እናት ትኖራለች ።
ሥራ ማግኘቱ፤ የኑሮ ውድነቱ፤ የቤት ኪራዩና መሰል ጉዳዮች ከራሳቸው አልፎ ቤተሰባቸውን የፈተነባቸው እናቶች ቁጥር ቀላል አይደለም። ከእነዚህ መካከል ለዛሬ ልናነሳቸው የወደድናቸው መጋቢ እናቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። እናቶቹ ሥራ አላቸው ቢባልም የሚያገኙት ገቢ ግን ኑሯቸውን የሚደጉምና ከፍ ሊያደርጋቸው የሚችል እንዳልሆነ በአንደበታቸው ይናገራሉ።
መንግስት በፈጠረው የተማሪዎች ምገባ ሥራ ላይ በመሰማራታቸው በመጠኑ ችግሮቻቸው እንደተቀረፈ ግን አይሸሽጉም ። ከራሳቸው ልጅ አልፈው ለሌሎች የሚደርሱ መሆናቸው ደስታን ቢፈጥርላቸውም ደስታው የሚደምቀው ግን ጎዶሏቸው ሲሞላ እንደሆነ ያነሳሉ። ለሥራው የሚመጥን ገንዘብ ማግኘት ቢታከልበት በሚል።
እነዚህ እናቶች ጉዳያቸውን መንግስት በአግባቡ ሊያይላቸው እንደሚገባ አንስተውልናል። ወይዘሮ አይናለም ጉልላት ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ብቻቸውን አምስት ልጆች አሳድገዋል። ልጆቻቸውን ለማሰደግ እሞክረዋለሁ ብለው የማያስቡትን ሥራ ጭምር ሰርተዋል። የሰው ቤት ጠርገዋል፤ ልብስ አጥበዋል፤ በአጠቃላይ የቀን ሰራተኛ ሆነዋል። ሁሌ በማህበረሰቡ ዘንድ ትንንሽ በሚባሉ ሥራዎች ለመገኘት ወደኋላ ብለው አያውቁም።በዚህም ኑሯቸውን በመለወጥ ቤት ጓዳቸውን ሞልተዋል ።
ለእናቶች የሥራ ፉክክር ይሉት ጉዳይ ቦታ የለውም። ሁልጊዜም ጥረታቸው ያለፉክክር ቤታቸውን እንዴት መሙላት እንደሚችሉ ነው። ደፋ ቀና ሲሉም ለዚህ ሁሉ ችግራቸው መፍትሄ በመስጠት ውስጥ እያለፉ ነው። ሁሉን በስርአት እየመሩ፣ የቻሉትን ያህል እየደከሙ፣ ቤቱ ሙሉ ባይሆንም ጎዶሎውን ይደፍናሉ። ቤት በብልሀት ሲገነባ የማይሞላ አይኖርምና አሁንም በዚህ የትጋት መስመር እያለፉ መሆኑን ይናገራሉ ፡ ፡
እንደርሳቸው እምነት ርቀትን ጠብቆ ፣ ፍጥነትን ገድቦ ለመብረር የድካም ዋጋ መክፈል ግድ ነው። መልካም አጋጣሚዎች የሚገኙት ደግሞ በዚህ ልክ መልፋት ሲቻል ነው ። እናቶች ከምንም በላይ ትጉህነታቸው የሚቀድም የመሆኑ ምስጢርም ሌላ ሚስጥር የለውም ።ሁሌም በትጋት ውስጥ ወርቃማ ውጤት ይገኛል ብለው ያስባሉ ።
ስለዚህም ትጋትን መመሪያቸው፤ መታወቂያቸው፣ ብርታትና ከበሬታቸው አድርገው ይጓዙበታል። በዚህ ደግሞ ያሰቡት ላይ ይደርሳሉ ።
ምንም እንኳን በአጋሮችና በዘመድ ድጋፍ ኃላፊነታቸው ቢቀልም ከእነርሱ ውጪ የሚደረግ ነገር ደስተኛ አያደርጋቸውም። በዚህም ቤታችን ያለእኛ አስተዳደር ሙሉ አይሆንም በሚል ቀን አልፎ ቀን እስኪተካ ይለፋሉ። እፎይ የሚሉትን ነገር አያስቡትም የሚል አመለካከት ያላቸው ወይዘሮ አይናለም፤ በሥራቸው ውስጥ ልጆቻቸውን እያዩ በተስፋ ፈረስ መጋለብ ነው የእርሳቸው ስኬትና የዛሬ ጉዟቸው ውጤት። እናም ለሁሉም ልጆቻቸው የሚመቹ መሆናቸውን እያረጋገጡ ይጓዛሉ።
እንደ ተፈጠሩለት አላማ አድርገው ለባላቸው ፤ ለልጆቻቸው ምቹ መሆንን ያውቁበታልና ባለቤታቸውን በሞት ቢነጠቁም ለልጆቻቸው ብለው ይኖራሉ። ዕድሜያቸውን ሙሉ መልካም ማድረግን ባህሪያቸው አድርገው ለልጆቻቸው አልፎ ተርፎ ለቤተሰብና ለጎረቤታቸው ተምሳሌት እየሆኑም ይገኛሉ። መልካምነታቸው በጊዜና ሁኔታ፣ በማግኘት በማጣት አይገደብም። ምክንያቱም ሁሉንም የሚያዩበት ዓይን የልጅነትና የእናትነት ነውና።
እናትነት ፈተናን ለልጆች ሲባል መጋፈጥ እንደሆነ ያውቃሉና የሚሰጡትን አጋጣሚዎች ሁሉ ይጠቀማሉ። አንደኛው ማሳያ ወደ ምግባ ሥራ የገቡበት አጋጣሚ ነው። ሥራውን የጀመሩት ከዛሬ ሰባትና ስምንት ዓመት በፊት ነበር። በአካባቢያቸው ‹‹ የእናት ወግ›› በተሰኘና የተመረጡ ችግረኛ እናቶችን በያዘ ስብስብ የሥራ አማራጭ የሚያገኙበት ሁኔታ ነበርና በዚያ ውስጥ ተመልምለው ትምህርትቤት ውስጥ የተወሰኑ ተማሪዎችን እንዲመግቡ ተደርገዋል። ይህ ደግሞ ቢያንስ ልጆቻቸው በልተው እንዲያድሩ አስችሏቸዋል። ከሙሉ ጊዜ የቀን ሰራተኝነትም በመጠኑ ላቋቸዋል።
አሁን ደግሞ ሁሉም ተማሪ ይመገብ ሲባል የመስራት አቅማቸው ጨምሯል። ልጆቻቸውን በቤታቸው እንደሚያጎርሱ እናቶች ሆነው ጥራት ያለው ምግብ በማዘጋጀት መመገብ ጀምረዋል ። በእርግጥ በዚህም ቢሆን ፈተናው ቀላል አልሆነላቸውም ። ለተማሪዎቹ ሲባል ሁሉንም በቤታቸው ያዘጋጃሉና ክፍያውና የሚያወጡት ወጪ እንዲሁም የልፋታቸው ነገር ተመጣጣኝ አይደለም።
ወይዘሮ አይናለም እንደሚሉት፤ እናቶች ከእነርሱ የባሱ ሰዎች ካዩ አያስችላቸውም። መስጠትን ልምድ አድርገውታል ። እጃቸውን ወደ ድሀ መዘርጋት ባህሪያቸው ነው። መልካም እናት ስጦታዋ እንካ በእንካ ነውና በአፀፋዉ የምትጠብቀዉ የለም። ‹‹አድርጌያለሁ›› የሚል አስተሳሰብም አይንጸባረቅባትም። ወረታዋን በልጆቿ ደስታ አለያም ሰርቶ በመለወጥ እንደምታገኘው ታምናለች። ይህንን ሥራዋንም በራሷ ደስታ ትመነዝረዋለች። ወይዘሮዋም ለዚህ ማሳያ እንዲህ ይላሉ። ‹‹ ብዙ ችግሮች ገጥመውኝ መፍትሄ ሲሆኑኝ አይቻለሁ። አንዱና ዛሬ ድረስ የማልረሳው ለልጆቼ የምመግበው አጥቼ የለመንኩትና አንድ እፍኝ ሩዝ ያገኘሁበት ነው››
በአሁኑ ጊዜ ሁሉም በቤቱ የኑሮ ውድነቱ በገባበት ሰዓት እንኳን ተጋርቶ መብላት በሁሉም ዘንድ አለ የሚሉት ወይዘሮ አይናለም፤ የቀን ሰራተኛ እያሉም ሆነ አሁን በምገባው ላይ ተሰማርተው ባሉበት ወቅት በምግብ ጉዳይ አይመለከተኝም የሚል እንደማይኖር ያነሳሉ ።
ቀና አድርጎ ውሃ ማጠጣት ብቻ ሳይሆን ምግብ ማብላትም በሁሉም ማህበረሰባችን ዘንድ ልምድ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮም እርካታ ነው። እናም እኛ በምገባው ዙሪያ ያልተቸገርነው ለዚህ ነው ይላሉ ። ይሁን እንጂ አሁን ላይ አንድ ነገር እንደሚያሳስባቸው አልሸሸጉንም። ይህም የሚመጣው ገንዘብ የልጆቻቸውን የትምህርት ወጪ የሚሸፍን አለመሆኑን ነው።
መንግስት የደንብ ልብስና ደብተር፣ እስኪርብቶ ፣ መሰጠቱ ትንሽ እፎይታን እንደሰጣቸው የሚያነሱት ባለታሪካችን፤ ወጪው በዚህ ብቻ የሚያበቃ ስላልሆነ እጅግ እየተፈተኑ እንደሆነ ያስረዳሉ። በተለይም ሁለተኛ ደረጃ ላይ የገባ ልጅ ስላላቸው ምገባው በዚያ አለመድረሱ፤ ተጨማሪ አጋዥ መጸሐፍትና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች ለምትማረው ልጃቸው ማስፈለጉ እርሳቸው ከሚያገኙት ገቢ ጋር አለመጣጣሙ፤ የቤት ኪራይና የማገዶ ወጪዎችም ቢሆኑ ለእርሳቸው ፈተና ናቸው። እናም ሁልጊዜ ጭንቀት ውስጥ ሲሆኑ፤ ደጋግመው
ምን ላድርግ ? እንደሚሉ ነግረውናል።
በቀደመው ኑሯቸው ቤታቸውን ሙሉ ለማድረግ የሚጥሩት ባለቤታቸው ነበሩ። እሳቸውም ቢሆኑ በቀን ሰራተኛነት በግንበኝነትና ለሳኝነት ላባቸውን ጠብ አድርገው በሚያመጡት ገንዘብ ደስተኛ ቤተሰብን ሲፈጥሩ ቆይተዋል። ሆኖም ሞት አይቀሬ ሆኖ እሰከወዲያኛው በመለየት ተሰናበታቸው ።
ከጊዜ በኋላ የአባወራውን ቦታ ተክቶ ለልጆቻቸው ደስታ መኖር የእርሳቸው ኃላፊነት ሆነ ። እናም ልጆቻቸውን ለማኖር የቻሉትን እያደረጉ ዛሬ ድረስ ዘለቁ። በዚህ አጋጣሚ ልጆች ሥራ ወዳድ ሆነው አድገዋል። ትንንሾቹ የቤት ሥራ ሲያግዙ ትልቋና ዘንድሮ 12ኛ ክፍል የተፈተነችው ልጃቸው የፋብሪካ ሥራ በመስራት ከራሷ አልፋ ቤቱን የመደጎም ተግባርን እንድታከናውን ሆናለች።
እርሷ ባትኖር ኖሮ በቤት ኪራዩ ጭማሪ ኑሮን መቋቋም እንደማይችሉ ያጫወቱን ወይዘሮ አይናለም፤ ዛሬ በትንሹም ቢሆን ‹‹እፎይ›› የማለታቸው ምስጢር ልጃቸው እንደሆነች ይናገራሉ። የራሷን የትምህርት ቤት ወጪ በራሷ ሸፍና ለእናቷ መቀነት የቡና ማለት ችላለችና ሁልጊዜ ይመርቋታል።
እንደ ወይዘሮ አይናለም ሁሉ ወይዘሮ ዘነበች ኃይሌም በብዙ ፈተናዎች ያለፉ ሴት ናቸው ። አሁንም ብዙ ችግሮቻቸው መፍትሄ እያገኙላቸው እንዳልሆነ ይናገራሉ። በተለይ የራስ ሥራ መፍጠር ላይ ብዙ ችግሮች እያጋጠሟቸው መሆኑን ያስረዳሉ። ሁልጊዜም በምገባው ላይ መስራት ለሌላው ችግረኛ ቤተሰብ ቦታ አለመልቀቅ እንደሆነ ያስባሉ። በብዙዎች ዘንድ ምገባ ላይ መስራት ትርፋማ እንደሆነ ይታሰባል። ሆኖም በተለይም እንደእነርሱ ያሉ ሴቶች በዚህ ዘርፍ ላይ ብቻ ተወስኖ መስራት ከትርፉ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም ያስረዳሉ። በምክንያትነት የሚያነሱትም ወጣት ሲኮን ብዙ መልፋትና መሥራት እንደሆነ ማመናቸው ነው።
አሁን ባለንበት ሁኔታ ‹‹አጣሁኝ ›› ማለት አይቻልም ። ነገር ግን ቋሚ ሥራ ያስፈልገናል ። ኑሮ በጣም ተወዷል። በምገባ የምንሞላው ነገር እንደ አንድ ገቢ ቢወሰድም ከዚያ ውጪ ያሉ ወጪዎች ግን የበረከቱ መሆናቸው አጣጥሞ ለመጓዝ ፈተና ሆኗል።
እንደሳቸው ዕምነት በመንግስት ብድር ተፈቅዶላቸው ሌላ ተጨማሪ ሥራ አለያም በስፋት የሚንቀሳቀስበት የሥራ መስክ ቢፈጠር የተሻለ ይሆናል። እንዲህ ማድረግ ከተቻለ ውጤታማ ለመሆን አማራጩ ይሰፋል። በተጨማሪም ለሌሎች የሥራ እድሉን ለመፍጠርም አቅም ይኖረናል ይላሉ።
ጠንካራዎቹ እናቶች ዘመኑን የሚዋጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል ። ባለፉት ችግራቸው እየሳቁ ፣በአዲሱ ኑሯቸው ደስታን ለማምጣት ሊተጉም ይገባል። ኋለኛዉ ዘመን አልፏል። ያለፈውን ችግር እያሰቡ በትዝታ እየቆዘሙ እንዲጓዙ ለራሳቸው መፈቀድ የለባቸውም ።
የቆሙበት ዘመን ሳያስፈራቸው ኑሮን ድል የሚያደርጉበት መንገድ አንዲፈጠር ከመንግስትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ ሊኖር ያስፈልገናል። ይህ ሀሳብ የሁሉም እናቶች ውስጣዊ ስሜት ነው ።
ሴቶች የሚመሩት ቤተሰብ ሲኖራቸው ቀድመው መዘጋጀትና ለወደፊቱ መደላደልን መፍጠር ግዴታቸው እንደሆነ የሚያነሱት ወይዘሮ ዘነበች፤ ከባለቤታቸው ጋር አብረው መኖር ስላልቻሉ ሦስቱንም ልጆቻቸውን ራሳቸው ለማስተዳደር ወስነው ቀን ከሌት እየለፉ ነው። ይህንን ደግሞ በተሻለ ሥራ መደገፍ ካልቻሉ ነገሮች እንደሚከብዱባቸው ያውቃሉና አሰራርን በማስተካከል መንግስት ቢያግዘን ይላሉ።
ብርቱዎቹ እናቶች የታወቁ ባለሙያም ናቸው ። በእጆቻቸው ፍሬ የማያጠግቡት የለም። የሚል እምነት ያላቸው ወይዘሮ ዘነበች፤ በሙያቸው የውስጡንም የውጪውንም አለም ያጣፍጣሉ። ያላቸውን አቅም ተጠቅመው በማስተዳደር ብቃትታቸውን ማስመስከርም ይችላሉ። የሌለውን ፈጥሮ የማቅረብና ከቤት አልፈው ለውጪ ግርማ ሞገስ ይሆናሉ። መፍትሄ አምጪም ናቸው።
እነዚህን እውነታዎች ተገንዝቦ ትኩረት ቢደረግ የሚል አስተያየት ያላቸው ወይዘሮ ከቀበሌ ብድር ይሰጣችኋል ተብለው ምገባ ላይ ስለሚሰሩ ብቻ አትችሉም መባላቸው እንዳሳዘናቸው ይገልጻሉ። የሚመለከተው አካልም ለጉዳዩ መፍትሄ ሊቸራቸው እንደሚሹም አጫውተውናል።
ወይዘሮ ዘነበች መንግስትን አመስግነው አይጠግቡም። መንግስት ምንም የስራ ዕድል በሌለበት ሁኔታ እርሳቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ በሩን ክፍት አድርጎላቸዋል። ልጆቻቸውም ቢሆኑ በትምህርትቤቱ ዕድል ተመጋቢ ስለሆኑ እፎይታን አግኝተዋል። ለዚህም ዘወትር ምስጋናን ይቸራሉ። ከዚያ ባሻገር ግን እንደ አንዲት ሴት ሥራዎቿ በሸንጎ፣ ልጆቿ በአደባባይ የሚያደንቋት መሆንን ይሻሉና ብድሩ የሚፈቀድበት አጋጣሚ ካለ ቢመቻችልኝ ይላሉ። እኛም በምገባው ዙሪያ ያሉ እናቶች ደሞዝና ችግሮቻቸው ቢፈቱላቸው በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/ 2015 ዓ.ም