አካል ጉዳተኞች በህብረተሰቡ ዘንድ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በማህበራዊ እና በሌሎችም አስተዋጽኦ እያበረከቱ ቢገኙም ካለባቸው አካላዊ እክል የተነሳ ያሉባቸው ችግሮች አሁንም አልተቀረፉም፡፡ ለዚህም በዋነኛነት እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው በህብረተሰቡ ዘንድ ስለአካል ጉዳተኞች ያለው የተሳሳተ አመለካከት ነው።
በተጨማሪም፣ በብዙ የስራ መስኮች ምቹ ሁኔታ ስላልተፈጠረላቸው አካል ጉዳተኛነት የመገለል እጣ ያጋጥማቸዋል። ይህ ችግር ከሚታይባቸው መስኮች አንዱ የፋሽን ሙያው ነው። ብዙ ጊዜ አካል ጉዳተኞች ተሰማርተውበት የማይታይ ዘርፍ ቢኖር ፋሽን በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በተለይም በኢትዮጵያ በርካቶች ስለ ፋሽንና ውበት ሲያስቡ አካል ጉዳተኞችን ማሰብ እንደሚከብዳቸው መካድ አይቻልም።
በኢትዮጵያ ፋሽንና ፋሽን ነክ የሆኑ ኢንደስትሪዎች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ ናቸው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር ሁኔታም የለም። በእርግጥ ፋሽኑ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ማኅበራዊ ክንውኖችም እውን አካል ጉዳተኞችን ያማክላሉ? የሚለው ጉዳይ ያጠያይቃል፡፡
ከፋሽን ትርዒቶች ጀምሮ ፋሽን የሚባሉ እንደ አልባሳትና ሌሎችም ሲዘጋጁና ለገበያ ሲቀርቡ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው አይደለም፡፡ የልብስ ዲዛይን፣ የሞዴሊንግና ሌሎችም የፋሽን ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን የዘነጉ መሆናቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።
ዘርፉ አካል ጉዳተኞችን ከማግለሉ ባሻገር አብዛኛው ማኅበረሰብ ውስጥ ውብ ወይም ቆንጆ የሚባል ሰው የሚገለጽበት መንገድ በራሱ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ‹‹ቀጠን ረዘም ያለች ሴት ወይም ደንደን ያለ ወንድ›› የሚለው ተለምዷዊ የተዛባ የውበት አገላለጽ ቁንጅናን በአንዳች መንገድ ብቻ የሚገድብ ሲሆን፣ የሰው ልጆች ባጠቃላይ እንደየአፈጣጠራቸው ውብ መሆናቸውን የዘነጋም ነው፡፡
በሌሎች ዓለማት በዊልቸር ወይም በክራንች ድጋፍ የሚሄዱ ሞዴሎችን መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ መስማት የተሳናቸው፣ ዓይነ ሥውራንና ሌሎችም አካል ጉዳተኞች የፋሽኑን ዘርፍ በስፋት ሲቀላቀሉ ይስተዋላል። ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ አልባሳት የሚያዘጋጁ ዲዛይነሮችም እየተበራከቱ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ኒውዮርክ ታይምስ በፋሽን ኤንድ ስታይል አምዱ ‹‹በአንድ ወቅት ፋሽን ገንዘብ ያላቸው፣ ተክለ ቁመናቸው ‹‹ያማረ›› የሚባሉ ሰዎች ብቻ እንደሆነ ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን ግን ፋሽን የሁሉም መሆኑን የማሳየት አብዮቱ ተጧጡፏል፤›› በማለት ስለጉዳዩ ሰፋ ያለ ዘገባ አስነብቧል። ዘገባው በዋነኛነት ያተኮረውም ለአካል ጉዳተኞች ተብለው ዲዛይን በሚደረጉ አልባሳትና በአካል ጉዳተኛ ሞዴሎች ዙሪያ ነበር፡፡
አንድ ብራዚላዊ ዲዛይነር ለአካል ጉዳተኞች ያዘጋጃቸው ልብሶችን ሲያስተዋውቅ፣ አካል ጉዳተኞች ምቹ ልብስ ለማግኘት ስለሚያዩት ውጣ ውረድ ገልጾ ነበር፡፡ አልባሳቱ በአካል ጉዳተኛ ሞዴሎች ተለብሰው እንዲታዩ አድርጎም ነበር፡፡ በዓለም ዕውቅናን እያተረፉ ከመጡ አካል ጉዳተኛ ሞዴሎች አንዷ ካናዳዊቷ ዊኒ ሀርሎ በቆዳ ሕመም ትሰቃያለች፡፡ በልጅነቷ በቆዳዋ ሁኔታ ምክንያት የዕድሜ እኩዮቿ ‹‹የሜዳ አህያ›› እያሉ ይቀልዱባት ነበር፡፡ ዛሬ የፋሽን ዘርፉን አካሄድ በተለየ ሁኔታ እየቀየሩ ካሉ ወጣት ሞዴሎች አንዷ ዊኒ ሀርሎ መሆኗ ይታወቃል።
በኢትዮጵያም አንዳንድ አካል ጉዳተኞች ዊኒ ሀርሎን ተከትለው በዘርፉ ብቅ ለማለት የሞከሩበት ጊዜ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ነገር ግን ብዙም ጎልተው ሳይወጡ ውጥናቸውም ረጅም ተጉዞ ተጽእኖ ሲያሳድር አይስተዋልም። አሁንም ቢሆን ውበት የሚተረጎምበትን መንገድ የሚቀይሩ፣ በሁሉም ሰው ውበት እንዳለ የሚያሳዩ አካል ጉዳተኛ ሞዴሎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ይታመናል። መሠረታዊ ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ ስለ ፋሽን ማሰባቸው ከባድ ቢሆንም የሚደግፋቸው አካል ሊኖር እንደሚገባ ግልጽ ነው።
በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ልብስ በማምረትም ይሁን በዲዛይንና ሞዴሊንግ አካል ጉዳተኞችን የማሳተፍ እንቅስቃሴው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ባለሙያዎች እምነት አላቸው።
ለዚህ ደግሞ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ የፋሽን ትርዒት መዘጋጀቱ አንድ ዕርምጃ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የፋሽን ዲዛይነሮች ማኅበር ከዓመታት በፊት የጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በዚህም ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን ልብስ በብዛት አዘጋጅቶ ለገበያ የማቅረብ እድል ይፈጠራል። አካል ጉዳተኞች ገበያ ሲወጡ ምቹ ብስ እንዲያገኙ ከትርዒቶች በኋላም ሌሎች ልብሶች ዲዛይን ሲደረጉ አካታች እንዲሆኑ ያግዛል። አልባሳት ዲዛይን ሲደረጉ የተጠቃሚውን ምቾችና አቅም ያገናዘቡ መሆናቸው ቅድሚያ ይሰጠዋልና አካታችነቱ እንዲቀጥልም እድል ይሰጣል። ዲዛይነሮቹ ለትርዒቱ አልባሳት ሲያዘጋጁ አካል ጉዳተኞች ምን እንደሚያስፈልጋቸው በመጠየቅና እርስ በርስ በመወያየትም ተሞክሮውን ማስፋት እንደሚችሉ የዘርፉ ባለሙያዎች እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም