የሕይወት ስኬት እንደ ሙያ፣ እንደ ሰው ምልከታ፣ እንደ ሁኔታዎች አጋጣሚ የሚለካና የሚታይ ነው። ስኬት ለአንዳንድ ሰዎች በሙያ መደነቅና ዝነኛ ሆኖ መገኘት ሲሆን ፤ ለሌሎች ደግሞ ማወቅና ማማር ብቻ ይሆናል። ስኬትን በገንዘብ መጠን መመንደግ አድርገው የሚመለከቱም አሉ። ስለሆነም ሰዎች ለስኬት የሚሰጡት ትርጉም የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን። ይሁን እንጂ በስኬት እሳቤ የብዙ ሰዎችን ምልከታ የሚያቀራርበው ትርጉም አንድና አንድ ሲሆን፤ ይህም ደስተኛ መሆን ነው።
በሰው እይታ የሚሞላ ሀብት ንብረት ባይኖርም ደስታ ካለ ጉዞው ሁሉ ያማረ እንደሚሆን ሁላችንም እናምናለን። ምክንያቱም በደስታ ውስጥ ለሰው መትረፍ አለ። ሰውን ማትረፍ ደግሞ ስኬታማነትን በአንድ ጀንበር እንደማምጣት ነው። ለዚህ አብነት የሚሆኑን ለዛሬ ‹‹ የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ ያደረግናቸው አቶ ሀብታሙ አበራ ሁነኛ ማሳያ ናቸው።
የልጅነት ጊዜ
ትውልዳቸው አዲስ አበባ ኮልፌ አጣና ተራ ልኳንዳ አካባቢ ነው። በቦታው ላይ እንደ ሌሎች ልጆች ቦርቀው አድገዋል ማለት ባይቻልም ቤተሰባቸውን እንዲያግዙበት እድል የሰጣቸው ስፍራ ስለሆነ የትውልድ ቦታቸውን አብዝተው ይወዱታል። በተለይም እናታቸውን ከማገዝ አኳያ ስፍራው ለእርሳቸው የተለየ ነበር።
አባት ወታደር በመሆናቸው ባለታሪካችን ልጅነታቸው ላይ ሳሉ እንደወጡ አልተመለሱም። አሁን ድረስ የት እንዳሉም አያውቁም። ስለዚህም እናታቸውን የማገዙ ኃላፊነት እርሳቸው ላይ ወድቆ ነው የቆየው። በእርግጥ እናታቸውም ብርቱ ሴት ነበሩ። ለልጆቻቸው ሲሉ የማይቆፍሩት ድንጋይ የለም።
እናታቸው እነርሱን ለማሳደግ አትክልት ሸጠዋል፤ ሸቀጣ ሸቀጦችን በጉልት መልክ ነግደዋል። የእለት ጉርሳቸውን ለመሙላት ሁልጊዜም እንደተሯሯጡ ነበር። ይህ ደግሞ ለትንሹ ሀብታሙ ራስ ምታት ነበርና እርሳቸውን ለማገዝ የማያደርገው ነገር አልነበረም። እናቱን ለመደጎም ሲል ከትምህርት ቤት መልስ ደብተሩን አስቀምጦ ሸንኮራ ንግድ ይሰራ ነበር። እንደ ልጅ ከረሜላ ሳያምረው ያገኛትን ገንዘብ በሙሉ ለእናቱ ይሰጣል።
እድሜው ከፍ ሲልም ሳይክል ገዝቶ በማከራየት በሚያገኛት እናቱን ያግዝ ነበር። ይህ ደግሞ ከዛሬው ህልሙ ጋር አገናኝቶታል። ማለትም ሳይክል ከማከራየት ባለፈ ሲበላሹ የመጠገን ሥራ ይሰራ ነበርና ቴክኒሽያን የመሆን ህልሙን እውን አድርጎበታል። ሀብታሙ ልጅነቱ አባት ከጎን ከሌለ መጀመሪያ ጫናው የሚያርፈው የመጀመሪያ ልጅ ላይ እንደሚያርፍ ያየበት ጊዜ ነው። ጭንቀቱ ሁሉ እናቱ ሆነው ለዓመታት ዘልቋል።
የትናንቱ ልጅ የዛሬው ጎልማሳ አቶ ሀብታሙ ልጅነታቸውን ሲያስቡ ቀድሞ ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው የእናታቸው ልፋት ነው። የእርሳቸው እረፍት ማጣትም እንዲሁ ያስታውሱታል። ነገር ግን አይቆጩበትም። ምክንያቱም ትናንት ሥራን ባይለምዱ ኖሮ ዛሬን አያዩትም ነበር። በተለይ ደግሞ ሁልጊዜ የሚጓጉለትን የልጅነታቸውን ፍላጎት አያሳኩትም ነበር። ይህም ውትድርና ሲሆን፤ በእድገታቸው ውስጥ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ነበር። ለዚህ ደግሞ መሰረት የሆናቸው በአካባቢው ያለው የውትድርና ማሰልጠኛ ተቋም ሲሆን፤ የወታደሮቹ አቋም፣ አለባበስና ስነምግባር እርሳቸውን ሁልጊዜ ይስባቸዋል። እናም በሙያው ለመሰማራት ይጓጉ ነበር። ቤተሰብ ሳያውቅም ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የገቡትም በዚህ ምክንያት እንደነበር ያስታውሳሉ።
በፈተና የታጠረው ትምህርት
ትምህርትን አሀዱ ያሉት በዚያው በአጣና ተራ አካባቢ ነው። በቦታው ላይ ግን ብዙም አልቆዩም። ምክንያቱም ቤተሰብ ብዙ ፈተና ውስጥ ስለነበር ወደ ኬሚሴ እንዲጓዙ አድርጓቸዋል። እናም እስከ አምስተኛ ክፍልም ቢሆን እየተዟዟሩ ነው ያጠናቀቁት። ውትድርና ቤት አለመማር ቦታ የለውምና ከዚያ ቀጣዩ ትምህርት በርቀት ተምረው አጠናቀዋል። እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረው ከጨረሱ በኋላም አሰላ ቴክኒክና ሙያ በመግባት በጀነራል መካኒክ የትምህርት መስክ መመረቅ ችለዋል።
አሁን ጀነራል መካኒክ ቢሆኑም አንድ ኢንጅነር የሚሰራውን ሙሉ እውቀት ኖሯቸው እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚህም ‹‹ወረቀቱ ቢኖር በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን ጊዜ ስላልነበረኝና ልምዱን በየጊዜው በተለያየ መልኩ እያዳበርኩት ስለመጣሁ ትምህርቱን መማሩ አልቻልኩም። ብዙ የሚጨምርልኝ ነገር አለ ብዬ ለማሰብም ተቸግሬያለሁ›› ይላሉ።
እርሳቸው መማርን የሚያዩት ከወረቀት መኖር አንጻር ብቻ አይደለም። ኮሌጅ ወይም ዩኒቨርሲቲ ገብቶ መውጣቱም ሊሆን አይችልም። መማር ዋጋው ከዚያ በላይ ነው። በተግባር የሚፈተን ሥራ ሲያርፍበት ነው ባይ ናቸው። ይህንን ደግሞ አሁን ላይ እያገኙት እንደሆነ ያስባሉ። በቋሚነት ገብተው ባይማሩም በሥራቸው የሁልጊዜ ተማሪ እንደሆኑም ያምናሉ። በምክንያትነት የሚያነሱት ደግሞ በየጊዜው የሚመጣውን ቴክኖሎጂ አውቀው መንቀሳቀስ መቻላቸውን ነው። በዚያ ላይ ገና ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ተማሪዎችን ቀጥረው ሲያሰሩ ሁልጊዜ መምህራቸው ሆነው እንደቀጠሉ ነው። ስለሆነም ‹‹ትምህርትቤት ገብቶ ከመማር በላይ እየሆንኩ ስላለሁ መግባቱ አላስፈለገኝም›› ይላሉ።
እንግዳችን ትምህርት ቤት ገብተው ፤ የተለያዩ ስልጠናዎችን ሳይወስዱ በሥራቸው አጋጣሚ በርካታ ቋንቋዎችን ማወቅ ችለዋል። ለአብነት ከአገርኛው ብንነሳ ኦሮምኛ ፤ ትግሪኛ፤ ሱማልኛና አማርኛ በደንብ ከሚግባቡባቸው መካከል ናቸው። ከውጭው ደግሞ ቻይንኛና እንግሊዝኛ ጥሩ የሥራ ቋንቋቸው ሆነውላቸዋል። በተለያየ አጋጣሚ ወደተለያዩ አገሮች በመሄድም ልምዶችን መቅሰማቸው አንዱ ትምህርት እንደሆነም ይናገራሉ።
የራስ ትግልና ውጤቱ
‹‹ወታደር በመሆኔ ብዙ ነገር አግኝቻለሁ። አንዱ ከባድ ችግሮችን እንዴት ቀላል ማድረግ እንደምችል የተማርኩበት ነው። ከችግሮች እንዴት መውጣት እንደምችል አውቄበታለሁ። ፍርሃት ያደረበት፣ ግራ የተጋባ ወይም የተደናገጠ ሰው እንዳልሆንም አድርጎኛል። በጣም ጥንቁቅ እና መላ ፈጣሪ መሆንንም አስተምሮኛል። የበላይነትንና ጠንካራ ርምጃ መውሰድንም ልምድ ያደረኩበት ነው። ወሳኝነት ባህሪዬ እንዲሆንም አድርጎኛል። ሥራው ኃላፊነት የተሞላበትና አልፎ ተርፎ ውጤትን የሚያቀዳጅ ስለሆነ ድል እንዳለ እያሰብኩ እንድራመድም ያደረገኝ ነው።
የአካል ጥንካሬ እና ብቃትም ኖሮኝ ሰርቼው የማላውቀውን የጉልበት ሥራ ጭምር በውጤት እንዳከናውነው ያገዘኝ ነው። በማንኛውም መንገድ ችግር ቢገጥመኝ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ እንጂ ስነልቦናዊ ውድቀት እንዳይኖርብኝ አግዞኛል። ስለዚህም ሁልጊዜ እንኳንም ወታደር ሆንኩ እላለሁም›› ይላሉ ያሳለፉትን ጊዜ ከራስ የሥራ ፈጠራቸው ጋር አስተሳስረው ሲያስታውሱ።
እንግዳችን ሥራን ‹‹ሀሁ›› ብለው የጀመሩት ደብረዘይት ከተማ በሚገኘው ኢስት አፍሪካ በሚባል ድርጅት ውስጥ የቀን ሰራተኛ በመሆን ነው። ከውትድርናው ዓለም ወጥተው በገጠማቸው ምስቅልቅል ሕይወት የተቀላቀሉት ሥራ ነው። ስርዓቱ ሲገፋቸው ቀን ሥራ እሰራለሁ እኖራለሁ በማለት ነበርም ወደ ደብረዘይት የመጡት። ከዚያም በቻሉት ልክ በቦታው ዞር ዞር እያሉ እንዲያሰሯቸው የተለያዩ አካላትን ጠየቁ።
እንዳሰቡትም አንድና ሁለት ቦታ ላይ የቁፋሮ ሥራ ተሰጣቸው። ነገር ግን ከሳምንት በላይ በቦታው መቆየት አልቻሉም። ምክንያቱም የቀን ሥራ በባህሪው ሳይበሉ የሚሰራ አይደለም። እናም ሥራው አቃታቸውና ተባረሩ። ነገር ግን ወታደር ተስፋ መቁረጥን አያውቅምና ሌላ ሥራ ማማተራቸውን ቀጠሉ። የሞከሩትም ተሳካላቸው። ይህም ሥራ የጀመሩበት ኢስት አፍሪካ ድርጅት ውስጥ ሲሆን፤ ብቃትና ጥንካሬያቸውን ያሳዩበት ሆኗል። ይህንን ያዩ አለቆች በተለይም አቶ ቴዎድሮስ የሚባሉ ኃላፊ አስጠርተው ጠየቋቸውና የሙያ እድገት ሰጧቸው።
ከዚህ በፊት ምን ሙያ እንደነበራቸው ሲጠየቁም ኮንትሮባንድ ላይ እንደሚሰሩ ነገር ግን እንደከሰሩ ተናግረው እንደነበር የሚያስታውሱት ባለታሪካችን፤ ይህንን ያደረጉበት ምክንያት በነበረው ስርዓት በመገፋታቸው ሳቢያ ከውትድርና ስራቸው ስርዓቱን ተቃውመው ስለወጡ ታስረው እንዳይወሰዱ ወይም እንዳይገደሉ በማሰብ እንደሆነ ይናገራሉ። ውትድርናውን ትተው በመውጣታቸው ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸው መሰቃየታቸውን አይረሱትም። ይሁን እንጂ በስራቸው ስኬታማ ያደረጋቸው ወታደር በመሆናቸው እንደሆነ ያምናሉና ስቃያቸውን በደስተኝነታቸው ያጠፋፉታል።
አቶ ሀብታሙ በድርጅቱ ውስጥ ‹‹ከኬኒያ የሚመጣ ማሽን አለ እርሱን ትተክላለህ ›› የመጀመሪያ የከፍታ ሥራ ትዕዛዛቸው ነበር። እንደተባሉት አደረጉም። ረዳት ኦፕሬተር በመሆንም ማገልገል ቀጠሉም። ብዙም ሳይቆዩ ሲኒየር ኦፕሬተር ሆኑ። ከዚያም አልፈው አለ የሚባለውን ሥራ በመካኒክነት አከናወኑ። በድርጅቱ ውስጥ አንቱታን ያተረፈላቸው ተግባርም ፈጸሙ። ለዚህ ደግሞ ያበቃቸው ወታደር መሆናቸው እንደሆነ ያነሳሉ።
‹‹ወታደር በባህሪው አልችለውም የሚለው ነገር የለም። በዚህም ከቀን ሥራው ወደ መካኒክነቱ ስገባ እንደምችለው አምኜ ነው። ውጤታማም ሆኜበታለሁ›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ውጤታማነት በአንድ ጀንበር እንደማይመጣ ያምናሉ። በዚህም መጀመሪያ የሥራውን ምንነት ተረድተው ለዚያ የሚመጥነውን ተግባር መከወን ጀመሩ። ከዚያም ለመማር ዝግጁ ሆነው የተሰጣቸውን በኃላፊነት መወጣት ቀጠሉ። ይህ ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ ሰባት ዓመታትን ሲያሳልፉ በቂ እውቀትን ከመጨበጥ አልፈው ምስጉን ሰራተኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
አሁን በብዙ ልምድና ስልጠናዎች ራሳቸውን አዳብረው ወደ ራሳቸው ሥራ ዓለም ገብተዋል። እርሳቸው ቀጣሪ ጭምር በመሆንም ለሌሎች ልምዳቸውን እያጋሩም ነው። ስለዚህም ወደፊት ሊገጥሙዋቸው የሚችሉት ፈተናዎች ብዙም ሳያሳስቧቸው ያላቸውን ጊዜ በመያዝ እየተጓዙ ይገኛሉ።
ሀብታሙ ዛሬ
‹‹ሰራተኛ ሰው መቼም ቢሆን አይደክምም። የተሻለውን ሁልጊዜ ያያል። ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ሰባት ዓመት የቆዩበትን ድርጅት ሲለቁ የተሻለ ቦታ ላይ ነበሩ፤ ደመወዝ ጨምረውላቸው እንዲቆዩም ለምነዋቸው እንደነበር አይረሱትም። ሆኖም ከፊት ያለውን የተሻለ ነገር የግድ ነውና ድርጅቱን እንዲለቁት ሆኑ። ከዚያ እንደወጡ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ነው የመጡት። ቃሊቲ አካባቢ በሚገኘው ፋንሱን በሚባል የቻይና ካምፓኒ ማሽነሪ ሽያጭ ውስጥ።
ካምፓኒው ለሌላ ድርጅት አጠቃላይ ማሽነሪዎችን ሽጦት ነበርና የገዛው አካል እርሳቸውን በመካኒክነት ቀጥሮ ያሰራቸዋል። ቴክኒካል ኃላፊ በመሆንም እንዲሰሩ አድርጓቸዋል። በዚህ ሳያበቁ ሙሉ ለሙሉ ማሽነሪውን ተረክበው መስራታቸውን እንዲቀጥሉ ሆነዋል። ይህ ደግሞ የሆነው ከቻይናው ካምፓኒ ጋር ቀረቤታቸውን በማጠናከራቸው ነው። በአገር ደረጃ ውክልና በመውሰድ ሙሉ የማሽነሪ ሽያጩን እንዲያከናውኑ እድሉን ሰጥቷቸዋል። እናም አሁን ድረስ ድርጅቱን ቢለቁም ወኪልነቱ በእርሳቸው አማካኝነት የሚንቀሳቀስ ሆኗል። ተከላውንም ቢሆን ‹‹ሀዊ ኢንጂነሪንግ ፒኤልሲ›› የተሰኘ የራሳቸው የኢንጂነሪንግ ካምፓኒ ስላላቸው በእርሱ በኩል እድሉን ካገኙት ተግባሩን ይከውናሉ።
አቶ ሀብታሙ ሙያቸውን ለማሳደግ የተለያዩ አገራት በመሄድ ልምድ ቀስመዋል። አንዱ ቻይና እንደነበር ያነሳሉ። ከአንዴም ሁለትና ሦስት ጊዜ በመሄድ ማሽነሪዎችን በሚገባ የሚያውቁበትን ልምድ አካብተዋል። አሁን እንደ አገር በድርጅታቸው አማካኝነት እየተዘዋወሩ የሚሰሩትም ለዚህ ነው። ከሰሯቸው ሥራዎች መካከል ባህር ዳር ላይ ሦስት ፕሮጀክቶችን፤ ቃሊቲ ላይ አልባር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያን፤ በሐዋሳ የሚገኝ ሱፐር ኦባ የሚባል ድርጅትንና ደብረብርሃን ላይ የሰሩት የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካና የእህል ማበጠሪያ ማሽን በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
እንግዳችን ከኢንጂነሪንጉ ሥራ ባለፈም የተለያዩ ሥራዎችን ሞክረዋል። እንደውም ‹‹ያልገባሁበት የሙያ መስክ የለም›› ይላሉ። ለአብነት ከአነሱልን መካከል የከብት እርባታ አንዱ ነው። ከብቶቹ ሲሞቱባቸው ነገሩን እርግፍ ቢያደርጉትም። ከዚያ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ በማህበር የሚደራጁበትን እድል ሲሰጣቸው እርሳቸው የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት አባላትን በማሰባሰብ በስራ አስኪያጅነት ማህበሩን እየመሩ የመኪና ጋራዥ አገልግሎት መስጠት ጀምረውም ነበር። በዋናነት የቀለም ቅብና የቦዲ ሥራ ያከናውኑ ነበርም። ነገር ግን ይህም ለተወሰነ ዓመት ከሰሩ በኋላ በባህሪ መስማማት ስላልቻሉ ማህበሩ ፈረሰ።
አቶ ሀብታሙ በአንድ ጊዜ ሁለትና ሦስት ሥራን መስራት የሚወዱ በመሆናቸው ሥራቸው አልተቋረጠም። ምክንያቱም የቻይኖቹ ማሽነሪ ሽያጭ ስራ አለ። እናም አሁን ድርጅታቸው ሥራውን በዋናነት በማሽን ጥገና፤ ተከላና ሽያጭ ላይ አድርጎ ይንቀሳቀሳል። በቀጣይ ትልቅ ሕልምም አለው። ይህም ማሽነሪ ማምረት ሲሆን፤ የተወሰነ ክፍሉን በሁለት ዓመት ውስጥ ለማምረት ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂውን ሙሉ ለሙሉ ማወቃቸው እንደሚያግዛቸው ያምናሉ። በተጨማሪም አብረዋቸው የሚሰሩት ካምፓኒዎች ቴክኒካል ፓርቱን እንደሚያግዟቸው ቃል ስለገቡላቸው የእቅዳቸው ፍጻሜ ቅርብ እንደሚሆን ያስባሉ።
የውትድርና ጥሪ
አቶ ሀብታሙ ገና በ14 ዓመታቸው ነው መከላከያን ተቀላቅለው ለአገራቸው የተዋደቁት። ወደዚህ ሙያ ሲገቡ ልጅ ስለነበሩ በቅርብ የሚከታተላቸው ሰው ነበር። መጀመሪያ ሥራቸው የሆነውም ከተወሰነ ስልጠና በኋላ እግረኛ ሆኖ ማገልገል ነው። ተግባሩን በሚፈለገው ደረጃ በመከወናቸው፤ ጠንካራና ቀልጣፋ በመሆናቸው ከዚያ ባሻገር የሚል ሥራ ተሰጥቷቸዋል። ይህም ኮሚኒኬሽን ዘርፉን በተለያየ ቦታ ላይ ሆነው እንዲያገለግሉ ነው።
‹‹ኮሚኒኬሽን የሰራዊቱ የጀርባ አጥንት ነው። ሕይወታቸውም እንደሆነ የሚታሰብ ክፍል ነው።›› የሚሉት አቶ ሀብታሙ፤ እዚህ ክፍል ሲመደቡ ትልቅ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው በማሰብ በሄዱበት ሁሉ በትጋት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ከውትድርናው እስኪለዩ ድረስም ኃላፊነታቸው ከፍ እያለ ይሂድ እንጂ ከዘርፉ አልወጡም ነበር።
አቶ ሀብታሙ ውትድርናው ሲቀላቀሉ እስከ አምስተኛ ክፍል ብቻ ተምረው ነው። ነገር ግን መማር ፍላጎታቸው ነበርና የውትድርናውን ዓለም በሚገባ እንዲያውቁት ሆነው ነው የወጡት። መውሰድ ያለባቸውንም የውትድርና ስልጠና ወስደዋል። መጀመሪያ የሰለጠኑበት ቦታ ጦላይ የወትድርና ማሰልጠኛ ሲሆን፤ ጥሩ አቅም የፈጠሩበት ነው። በመቀጠልም ወደ ደብረዘይት በመሄድ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደዋል። ሦስተኛ የስልጠና ቦታቸው አዲስ አበባ ላይ ቃሊቲ አካባቢ የሚገኘው አየር መቋሚያ ምድብ ሲሆን፤ እስከ 1987 ዓ.ም መጨረሻ የቆዩበት ነው።
በውትድርና ዓለም ስልጠና ብቻ ሳይሆን ትግልም አብሮ የሚጓዝ ተግባር ነው። ስለዚህም ከስልጠናው ጎን ለጎን አገር መጠበቁና፤ ጸጥታ ማስከበሩን ሰርተውበታል። ትግራይ ክልል ሳይቀር ይህንን ተግባራቸውን ከውነዋል። ለምሳሌ፡- የሃ የምትባል ከተማ የውትድርና ሥራቸውን ከሰሩባቸው ቦታዎች መካከል ይጠቀሳል። በርሃሌ ከተማ ተዛውረው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል። ይህ ደግሞ እስከ 1989 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የዘለቀ ነው። ቀጥለው ወደ ሱማሌ ክልል ነው የሄዱት። ምክንያቱም ጊዜው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተጧጧፈበት ወቅት ነበር። እናም በቡሬ ግንባር ሆነው ውጊያው እስኪጠናቀቅ ድረስ የሻለቃ መገናኛ ኃላፊነትን በመያዝ ቆይተዋል።
ውጊያው ካለቀ በኋላ ደግሞ ወደ ድሬዳዋ ጉዟቸውን አድርገው ለተወሰነ ጊዜ አርፈዋል። ይሁን እንጂ በጊዜው ግምገማ ነበርና ውስትን የሚሰብር ነገር ገጥሟቸዋል። ከውትድርናው ዓለም እንዲለዩም ያደረጋቸው ይህ ተግባር ነበር። ግምገማው አድሎነት ብቻ ሳይሆን ማሸማቀቅ የነበረበት ነው። ዳግመኛ መከላከያ የሚባል ነገር እንዳይታሰብ የሚያደርግም ነው። ምክንያቱም ሹመቱ ወይም ምስጋናው በሥራ ሳይሆን በቅርበትና በተፈላጊነት የሚከወን ነበር። በዚህ ውስጥ ደግሞ ‹‹ለምን›› ማለትም አይቻልም። ይህ በመሆኑም የሰሩ ሰዎች ዓይንህ ለአፈር ተባሉ። እርሳቸውም አንዱ ነበሩና ይህንን እያየሁ አልቀመጥም በማለት ከመከላከያ ጠፍተው ሄዱ።
መጥፋታቸው ብዙ ነገራቸውን አደበላልቆባቸው ነበር። አንዱ ቤተሰቤን ማሰቃየቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የእርሳቸውን ሕይወት አዘቅት ውስጥ መክተቱ ነው። አንድ ቲሸርትና አንድ ሱሪ ብቻ ይዘውም እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል። ነጻ ሆነው ለመሥራትም አልችሉም፤ በሙያቸው ማገልገልም እንዲሁ። ስለዚህም እሰረዋለሁ ብለው ያላሰቡትን የቀን ስራ በመስራት ጊዜውን እንዲገፉ አስገድዷቸዋል። ከመከላከያ የወጡበት ዓመት ዋሽተው ጭምር እንዲቀጠሩ ያደረጋቸው ነው። ምክንያቱም ነገሩ ከመሞት መሰንበት ነው።
አንድ ነገር ግን ያምናሉ። መከላከያ ውስጥ በመግባታቸው ብዙ ነገር እንዳገኙ። አንዱ ወታደር ዝም ብሎ ሥራ ውስጥ አለመግባቱ ነው። ለሚሰራው ሥራ አላማ አለው፤ አቋምም ይይዛል፤ ፍርሃት የሚባልን ነገር አያስብም። ከዚያ ይልቅ ጥንቁቅነትን መመሪያው ያደርጋል። ለድርጊቱ ቀድሞ ማወቅ ያለበትን ነገር ይመረምራል። ስለዚህም ብር ሳይሆን ሕሊናውንና ክብሩን ያስቀድማል። ሁልጊዜ እዚህ ላይ እቆማለሁ ሳይሆን ታሪክ እሰራለሁ ብሎ የሚያምን ነው። ›› የሚለውን።
ወታደር ለአገሩ
ወታደርነት መነሻውም ሆነ መዳረሻው አንድ ነገር ነው። የሀገር ፍቅርና የሀገር ክብር። ሀገሩ ካለች እርሱ ቢሰዋ እንኳን ቤተሰቡ እንደሚኖር ያምናል። የሰው ልጅ ጭምር ደስተኛ ሆኖ እንደሚቀጥል ያስባል። ስለዚህም እስከ መጨረሻው የሚሳሳላትን ሕይወቱን ለውድ ሀገሩ ሉዓላዊነትና ለሕዝቡ ሰላም አሳልፎ ይሰጣል። ለእርሱ ሀገሩ የደም ቃሉ ነችና የሚሰስተው ነገር አይኖርም። በታማኝነት ማገልገሉም ነው በክፉ ሰዎች ያስበላው። የአገሩን ሰው ልክ እንደራሱ ይወደዋል፤ ያገለግለዋልም።
መልዕክት
ባለፉት አመታት በአገራችን ውስጥ እያየነው የመጣነው መከራ ከቀን ወደ ቀን እየከፋ ሲመጣ ቆይቶ አሁን የተስፋ ወጋገን መታየት ጀምሯል። የሰላም አየር በሀገራችን መንፈስ ጀምሯል። ኢትዮጵያን ተነጋገግረን ወደ ሰላም መምጣታችን ሁላችንንም ድል አድራጊዎች ያደርገናል። የማናሸንፈው ነገር የለምም። ስለሆነም ያንን አስበን እንደሕዝብ አንድነታችንን በማጠናከር አገራችንን ከአለችበት ችግር ማውጣት ይጠበቅብናል የመጀመሪያው ምክራቸው ነው። አንድ ከሆንን የሚጫነን ኃይል አይኖርም፤ ኢኮኖሚያዊ ችግር፣ ፖለቲካዊ ጫና እንዲሁም ስነልቦናዊ ውድቀት የሚባሉ ነገሮች አይነኩንም ይላሉም።
ሌላኛው መልዕክታቸው በአገራችን የነበሩ ችግሮች ወደፊት ላለው አንድነታችን ጭምር ጥላ የሚሆን ነው የሚለው ሲሆን፤ እንደ ዜጋ የፍቅር መንፈሱን፣ ልማዱንና የእለት ተእለት ተግባሩን፣ ከሃሳቡና ከስነምግባር መርሁ ጋር ለማስተካከልና ወደ ሰመረ ሕይወት ከፍ ለማድረግ ቀን በቀን በመታገል ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ። እኛ ወደ ባሰ መከራ ሳይሆን ወደተሻለው መውጣት ያለብን ሕዝቦች ነን። ቢወድቅ እንኳ ተነስቶ የሚያንሰራራ ምሉዕ፣ የስሜትና የመንፈስ ስምረት የሚያስፈልገን ነን። ስለሆነም እዚህ ላይ ከምንም በላይ መስራት ይኖርብናል ይላሉ።
አይቀሬ መዘዞችን እየጐነጐኑ ቁልቁል የሚጐትቱን፣ ወደ አይምሬ መቀመቅ ወርውሮ የሚፈጠፍጠንን አንቀበልም ማለት መጀመር ያለብን ከአሁኑ ነው የሚሉት አቶ ሀብታሙ፤ ለዚህ ደግሞ የሕይወት መንገዳችንን የሚያቃና፣ ከፍ ወዳለ ወደከበረ ሕይወት የሚመራን ሰው ያስፈልገናል። አሁን ይህ እንዳለን የሚያሳዩ በርካታ ነገሮች አሉ። ስለዚህም እርሱን መደገፍና ለተሻለች ኢትዮጵያ መትጋት ይገባናል ሌላው መልዕክታቸው ነው።
እኛ ከሚያጨልም ይልቅ የሚያፈካ፣ የተሳከረ ሳይሆን የተስተካከለ፣ የጠመመ ሳይሆን የተቃና የሚያደርገን ባህልና ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን። ሆኖም መጠቀሙ ላይ አልቻልንበትም። እናም ከክስረት ይልቅ የስኬት በረከትን ማብዛት ላይ ማተኮር ይኖርበናል። ያ ደግሞ ባህልና ታሪካችን ነውና እርሱን በሕይወት ልንኖረው ያስፈልጋል። ምክንያቱም እርሱ ከባዶ ድንዛዜ ይልቅ የሚያነቃ የሕይወት ጣዕም አለው። ከወረደ ይልቅ የከበረ መንፈስን የሚያላብስ ነው። ለድንቅ የሰው ተፈጥሮ የሚመጥን ሃሳብና ምኞትንም ይሰጠናል። ስለሆነም እርሱን ለብሰን ብርሃን ለአጡት ብርሃን እንሁናቸውም ባይ ናቸው።
ሃሳብና ተግባር፣ መንፈስና ስሜት፣ የስነ ምግባር መርህና ባሕርይ ሲጣጣም ትርጉሙ አንዱ የሕይወት ገፅታን ይሰጠናል። ይህም አገር ነው። ለዛሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን ይህ ብቻ ያስፈልገናል። ስለሆነም ከውስጥም ከውጭም ያማርን እንድንሆን እነዚህ ባህሪያትን እንላበስ። ምክንያቱም እነሱ ካሉን የሚያደበዝዝ፣ የሚያጠወልግ ፍቅር ሳይሆን በአበቦች ወደ ተንቆጠቆጠ የደስታ መስክ እንወርዳለን። አዕምሯችን በደመቀ የደስታ እርካታ ውስጥ ይወድቃል። ከመልካም ውድ ስሜት ጋር የሰመረ፣ በጐ ክቡር ፍቅርን የሚያመነጭ ሰው እንሆናለንም። እናም ይህ ይገባናልና መመሪያችን እናድርገው ማሳረጊያ መልዕክታቸው ነው። እኛም ምክሩ ያሻግረናልና እንጠቀምበት በማለት ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/ 2015 ዓ.ም