በትራፊክ አደጋ በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ1.3 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያም በቀን 13 ሰዎች በዓመት ደግሞ 4680 ያህል ዜጎች ሕይወታቸውን በዚሁ አደጋ ምክንያት እንደሚያጡ የቅርብ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
በኢትዮጵያ ይህን አስከፊ አደጋ ለመቀነስ የመንገድ ትራፊክ የተለያዩ የአሰራር ስርአቶችን ዘርግቶ ወደ ስራ ሲገባ ቢስተዋልም፤ አደጋውን ቀንሶታል ብሎ ደፍሮ ለመናገር አይቻልም።ካለፈው ሰኔ ወር በፊት በነበሩ ስድስት ወራት የትራፊክ አደጋ በኢትዮጵያ ከ5 እስከ 7 በመቶ ያህል መጨመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከህግ አስከባሪውና አሽከርካሪው በተጨማሪ እግረኞች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው የዘርፍ ባለሙያዎች በተለያየ አጋጣሚ ሲገልፁ ይሰማል።ያም ሆኖ በኢትዮጵያ ለትራፊክ አደጋ መንስኤ ከ85 በመቶ በላይ ምክንያት የሆኑት አሽከርካሪዎች ናቸው። አሽከርካሪዎች ሲባል ደግሞ በብቃትና በጥሩ ስነምግባር ህግ አክብረው የሚያሽከረክሩትን አይደለም። የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት ብቃቱ ሳይኖራቸው ህጋዊም ይሁን ፎርጅድ መንጃ ፍቃድ ይዘው የሚያሽከረክሩትን ነው። ፎርጅዱ መንጃ ፍቃድ በአንድ ስሙ ህገ ወጥ ነው። ትዝብቴን እንዳካፍል ያነሳሳኝ ትክክለኛውን መንጃ ፍቃድ ብቃቱ ሳይኖራቸው በህጋዊ መንገድ አውጥተው የሚያሽከረክሩትን የተመለከተው ጉዳይ ነው።
የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ጉዳይ ብዙ ጊዜ አከራካሪ ነው። የአሽከርካሪዎችን ብቃት መዝነው መንጃ
ፍቃድ የሚሰጡት ሰዎች ለዚህ ችግር ዋነኞቹ ተጠያቂዎች ናቸው። ይህን በድፍረት እንድናገር ያደረገኝን ትዝብት ላካፍል።
ከሳምንታት በፊት እንደሰው መንጃ ፍቃድ ለማውጣት የንድፈ ሃሳብ ትምህርቱንና የተግባር ልምምዱን ጨርሼ ቃሊቲ ለተግባር ፈተና በተቀጠርኩበት ማለዳ ተገኘሁ። እንደኔው ለተግባር ፈተና ማልደው በስፍራው የተገኙ(በብዛት ወጣቶች ናቸው)፣ ፈታኞችና አስተማሪዎች መካከል ያለው ወከባ አይጣል ነው። የመጀመሪያዎቹ ተፈታኞች ጨርሰው ለተከታዩ ተፈታኝ እስኪያስረክቡ ዘለግ ያለ ወረፋ መጠበቅ ግድ ነው። ተራው እስኪደርሳቸው ድረስ ወረፋ እንዲጠብቁ በተዘጋጀው ቦታ ላይ በርከት ብለው የተቀመጡ ሰዎችን ተቀላቀልኩ። ሁሉም ተፈታኝ ማለት ይቻላል ከጎኑ ከተቀመጠው ጋር የሚያወጋው በተመሳሳይ የመንጃ ፍቃድ ፈተና ጉዳይ ላይ ነው።
አጠገቤ የተቀመጡ ሁለት ወጣቶች የሚያወጉትን ጉዳይ ግን ጆሮ ልነፍገው አልቻልኩም። ወጣቶቹ የሚያወጉት ጉዳይ ሲጠቃለል ‹‹ማንኛውም ተፈታኝ የቱንም ያህል ብቃት ቢኖረው ለፈታኞች በስውር ገንዘብ እስካልሰጠ ድረስ በትንሽ ስህተት ፈተናውን ይወድቃል›› የሚል ነው። በአንጻሩ አንድ ተፈታኝ ለማሽከርከር የሚያበቃ ብቃት ባይኖረውም የተጠየቀውን ገንዘብ እስከከፈለ ድረስ መንጃ ፈቃዱን የማግኘት ጉዳይ አያሳስበውም።
ይህን ጉዳይ ቃሊቲ በቆየሁበት ግማሽ ቀን እንደ ጋዜጠኛ ሳይሆን እንደ ተፈታኝ ከተለያዩ ሰዎች ለማጣራት ባደረኩት ጥረትም እውነት መሆኑን ከተጨማሪ መረጃዎች ጋር ለማረጋገጥ ከባድ አልነበረም። አንድ ተፈታኝ መንጃ ፍቃዱን ለማግኘት በቅድሚያ ከተግባር አስተማሪው ጋር ይደራደራል። ጥሩ ተደራዳሪ ከሆነ ከሶስት ሺ እስከ ሶስት ሺ አምስት መቶ ብር ከፍሎ ለማሽከርከር ብቁ ባይሆንም መንጃ ፍቃዱን በእጁ ያስገባል። ከዚህ በላይ እንደየሁኔታው ከፍ ያለ ገንዘብ የሚከፍልም አለ። የተግባር አስተማሪውም ገንዘቡን ይዞ ለራሱ የሚገባውን ካስቀረ በኋላ ለፈታኞች ቀደም ብሎ የሚፈተነውን ሰው በማሳወቅ ያስረክባል። በቁጥር በርከት ያሉት ፈታኞችም ገንዘቡን ተከፋፍለው ተፈታኙን ያሳልፉታል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለማሽከርከር ብቁ ያልሆኑት ብቻ ሳይሆኑ ብቃቱ እያላቸው በተገቢው መንገድ ተፈትነው ማለፍ የሚችሉም ገና ለገና በጥቃቅን ነገር እወድቃለሁ በሚል ስጋት ክፍያውን ይፈጽማሉ። ሌሎች ደግሞ ፈተናውን ድንገት ወድቄ ለሌላ ፈተና ከማባክነው ጊዜ ይልቅ ገንዘቤን ይጭነቀው ብለው ይከፍላሉ።
በእርግጥ እዚህ ጋር ጥቂት ቢሆኑም የተጠየቁትን ገንዘብ አንከፍልም ብለው በተገቢው መንገድ ተፈትነው የሚገጥማቸውን ነገር የሚጋፈጡም አሉ። ፈታኞችም እንዲህ አይነቶቹን ሰዎች መጋፈጥ አይችሉም። ምክንያቱም የፈተናው ሂደት ሙሉ በሙሉ በካሜራ እይታ ውስጥ በመሆኑ ፈተናውን በብቃት ተወጥተው ቢወድቁ ማስመርመር የሚችሉበት እድል አለ። ነገር ግን ፈተና በራሱ ተፈታኝ ላይ የመደናገጥ ስሜት የመፍጠር ባህሪ ስላለው ብቃቱ ያላቸው ሰዎችም ስሜታዊ (ነርቨስ) መሆናቸው አይቀርም። ፈታኞችም ይህን ስለሚያውቁ ይመስለኛል በተፈታኞች ላይ የሚፈጥሩት ወከባና ማጣደፍ ሆን ብለው የሚፈጽሙት ነው። በዚህም ተረጋግቶ ማድረግ ያለበትን ነገር ሳያደርግ ቀርቶ የሚወድቅ ተፈታኝ ጥቂት አይደለም።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ተደጋግሞ እንደሚነገረው ለአገራችን የትራፊክ አደጋ መባባስ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ ጉዳይ ነው። ፈታኞች ለትንሽ የገንዘብ ጥቅም ብለው ምንም የማሽከርከር ብቃት ለሌላቸው ሰዎች በሚያድሉት መንጃ ፍቃድ የስንቱ ሕይወት ተቀጥፎ ይሆናል፣ የስንቱስ ንብረት ወድሞ ይሆናል?። ኪስ በማይሞላ ገንዘብ የበርካቶች ሕይወት ተመሰቃቅሏል፣ በርካቶች ቤተሰብ አልባ ሆነዋል። የዚህ መዘዝ በግለሰብና በቤተሰብ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ማህበራዊ ጉዳቱ ይበልጥ የጎላ ነው። ብቃት ሳይኖራቸው ህጋዊ መንጃ ፍቃድ ይዘው እያሽከረከሩ አደጋ በሚያደርሱ ሰዎች ምክንያት አገርን መለወጥ የሚችሉ በርካቶች በአጭሩ ሊቀጩ ይችላሉ፣ ተቀጭተዋልም።
መንግስት ለዚህ አንገብጋቢ ችግር መፍትሄ ለማበጀት በየጊዜው ጥረት ቢያደርግም ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶታል ለማለት አያስደፍርም። የዚህን ችግር አሳሳቢነት ይበልጥ አጉልቶ በማውጣት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ብቃት ሳይኖራቸው ህጋዊ መንጃ ፍቃድ ይዘው የሚያሽከረክሩ ሰዎች በሚያደርሷቸው አደጋዎች ዙሪያ ጥናቶች በስፋት መሰራት አለባቸው። መንጃ ፍቃድ ሰጠን ብለው “ሕይወት መቅጠፊያ ፍቃድን” በሶስት ሺ ብር የሚሰጡ ሰዎችም ህሊና ካላቸው በጥናቶቹ ውጤቶች ትንሽ ደንገጥ ብለው የሚሰሩትን ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸው ይሆናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም