የዛሬ ሁለት አመት በዛሬው ቀን፤ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም። ይህ ቀን የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ኢትዮጵያን የገዛው አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያን፣ በተለይም የትግራይን፣ ሕዝብ ከጠላት በሚጠብቀውና ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ውለታ ባኖረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ታሪክ ይቅር የማይለውን ዋነኛ ክህደት የፈጸመበት ነው። በዚህ የክህደት ተግባር በርካታ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአሸባሪው ሕወሓት ተጨፍጭፈዋል፤ በርካታ የሚሆኑት ደግሞ በጠላት ላይ ጭምር ሊፈጸም ይችላል ተብሎ የማይታሰብ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት በዚህ ከሀዲ ቡድን ላይ ባካሄደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ከሀዲ ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያሰለፈው ሰብዓዊና ቁሳዊ አቅም በጥቂት ቀናት ውስጥ ተሰባብሮ መላ ትግራይን በመቆጣጠር የሀገርን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ቢቻልም፣ ቡድኑ ያ ሁሉ ቅጣት ደርሶበትም ከጥፋቱ ሊማር አልቻለም።
መንግሥት በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ማስወጣቱን ተከትሎ አሸባሪ ቡድኑ አጋጣሚውን ለጥፋት ተግባር በማዋል ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላትነቱን በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ባካሄደው ወረራ ደግሞታል። በዚህም ወረራም በሰሜን እዝ ላይ ክህደት በመፈጸም የሀገር ባለውለታዎቹን የቁርጥ ቀን ልጆች እንደጨፈጨፈው ሁሉ በአማራና አፋር ክልልም ንጹኃንን በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፍጭፏል፤ አያሌ ሰዎችን ከቀዬቸው አፈናቅሏል፤ ታጣቂዎቹ ያደረሱት ዘግናኝ አስገድዶ መድፈርና የስነ ልቦና ቀውስም ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። የህዝቡን ሀብትና ንብረት ዘርፏል፤ አውድሟል። በቅርቡም ሌላ ሶስተኛ ዙር ጦርነት ቢከፍትም፣ በጥምር ጦር በሚገባ እየተመከተ ይገኛል።
የፀጥታ መደፍረስ፣ ዘረፋና ውድመት
በሕግ ማስከበርና በህልውና ዘመቻዎቹ ወቅት አሸባሪው ሕወሓት የመከላከያ ሰራዊቱን ጥቃት መቋቋም ሲያቅተው በብዙ ገንዘብና እውቀት የተገነቡ የኢንቨስትመንትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ተቋማትንም አውድሟል። ቡድኑ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ክህደት ከፈጸመ አንስቶ የአማራና አፋር ክልሎችን በወረረበት ወቅት ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት ከፈጸመባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የኢንቨስትመት ዘርፉ ነው። ቡድኑ በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የፈፀመው አሳፋሪ ዝርፊያና ውድመት፣ የሕወሓት ወዳጅ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የአንዳንድ ምእራባውያን ሀገሮች መንግሥታትና ተቋማት ጫና የኢንቨስትመንት ተቋማት ጉዳት እንዲደርስባቸውና ዘርፉ እንዲቀዛቀዝ አስገድደዋል።
በዚህ በተጠናና በባለሙያ በተደገፈ ዘረፋና ውድመት ሀገርና ባለሀብቶች እንደ አይናቸው ብሌን የሚመለከቷቸው፣ በእጅጉ ተስፋ የተሰነቀባቸው፣ የብዙ ሺዎች እንጀራ የሚጋገርባቸውና እጣ ፈንታቸው የተሳሰረባቸው የመንግስትና የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተቋማት ተዘርፈዋል፤ እንዲወድሙ ተደርገዋል።
የቡድኑ የዘረፋና የውድመት ድርጊት ሆን ተብሎ የታቀደበትና ሕዝብን ለመጉዳት ያለመ እንደሆነ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። በጦርነቱ ላይ ተሳታፊ ያልሆኑ እናቶችና ህፃናት አገልግሎት የሚያገኙባቸውን የውሃ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማትን ማውደም ሕዝብን የመጉዳት ዓላማ እንጂ ሌላ ምን ሊባል አይችልም፤ ሌሎች አሰቃቂና አሳፋሪ ድርጊቶቹን ለመዘርዘር ጊዜና ቦታም አይበቃም።
የአማራ ክልል መንግሥት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው፤ ሕወሓት ከሰኔ 2013 እስከ ታኅሳስ 2014 ዓ.ም በክልሉ 292 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት አውድሟል። ቡድኑ ከአንድ ዓመት በላይ በወረራ ይዟቸው በነበሩት እንዲሁም ለሦስተኛ ጊዜ ወረራ በፈፀመባቸው የክልሉ አካባቢዎች የፈፀመው ውድመት ሲታሰብ በክልሉ ያደረሰው ዘረፋና ውድመት መጠን ከተጠቀሰው የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ዝርፊያና ውድመት ከተፈፀመባቸው ተቋማት መካከል የማምረቻ ድርጅቶች ተጠቃሽ ናቸው። ለአብነት ያህል በደሴና በኮምቦልቻ ከተሞች በርካታ ፋብሪካዎች ዘረፋና ውድመት የተፈፀመባቸው ሲሆን፣ በእነዚህ ፋብሪካዎች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ለኢኮኖሚያዊና ለስነ ልቦና ችግር መዳረጋቸውን እንዲሁም አስር ፋብሪካዎች ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይም ቡድኑ በርካታ የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች በሚገኙበት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፈፀመው ዘረፋና ውድመት ትልቅ አቅም ባላቸው የፓርኩ ኩባንያዎች ላይ ካስከተለው ኪሳራ በተጨማሪ በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይም ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ይፋ ባደረገው መረጃ፣ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች፣ የማምረቻ ቦታዎች፣ የኬሚካል ማጣሪያ እና ሌሎች በፓርኩ ውስጥ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ክፍሎች በሙሉ ዝርፊያና ውድመት ደርሶባቸዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ተሽከርካሪዎችም በአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች ተወስደዋል። የፓርኩ የቢሮ እቃዎችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተሞች፣ የአምራች ኩባንያዎች ቢሮዎችና ቁሳቁስ፣ ለውጭ ገበያ የተዘጋጁ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች ተዘርፈዋል። በተጨማሪም የምርት ማከማቻ መጋዘኖች ውስጥ የነበሩ ለምርት የተዘጋጁ ጥሬ እቃዎች፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም አምቡላንስ እና የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎች በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁስ ዝርፊያና ውድመት ደርሶባቸዋል።
በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ የደረሰው ጉዳት በሁለት መንገድ የሚገለጽ እንደሆነ ያመላከተው የኮርፖሬሽኑ መረጃ፣ የመጀመሪያው ዝርፊያ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውድመት ነው። ከዝርፊያው አንጻር ድርጅቶቹ ያመረቷቸውና ወደ ውጭ ሊላኩ የነበሩ ምርቶች ተዘርፈዋል፤ የኩባንያዎቹን ምርቶች ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ሙሉ በሙሉ ተወስደዋል፤ በድርጅቶቹ ቢሮዎች ውስጥ የነበሩ መገልገያዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተዘርፈዋል። በተለይ ደግሞ በቀላሉ ሊተኩ የማይችሉ መሳሪያዎችና የምርት ሥርዓቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
በፓርኩ ውስጥ በሚሰሩ ድርጀቶች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የቢሮ እንዲሁም የአገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች ውድመትና ስርቆት ተፈፅሞባቸዋል። የኢንዱስትሪያል ፓርኩ ማጣሪያዎች ተነቅለው ተወስደዋል። ሊወሰዱ ያልቻሉት ደግሞ እንዲወድሙና እንዲቃጠሉ ተደርገዋል። የደኅንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችም ጭምር ወድመዋል። የኤሌክትሪክ እና ሌሎች ገመዶች አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገው ተቆራርጠዋል። ለፓርኩ ተጨማሪ ግንባታ ለማድረግ እንደ መጋዘን ሲያገለግሉ የነበሩ ሦስት ኮንቴይነሮች ተጭነው ተወስደዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት እንዳስታወቀው፣ በክልሉ የነበረው የተሻለ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ክፉኛ ተጎድቷል። አሸባሪው ሕወሓት በክልሉ ላይ ወረራ በፈፀሙት ወቅት በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ ባለሀብቶች ዘረፋና ውድመት የደረሰባቸው በመሆኑ አካባቢውን ለቀው እስከ መውጣት ደርሰዋል። ውድመት ባልደረሰባቸው ቦታዎችም የስነ-ልቦና ችግሮችን አስከትሏል።
በሕወሓት ጥቃትና ወረራ ምክንያት የተከሰተው የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በሚከናወኑባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች አፈፃፀም ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች እንደሚሳዩት፣ የፀጥታ መደፍረሱ በፓርኮቹ ውስጥ የነበሩ ትልልቅ አምራች ድርጅቶችን ትልቅ ጫና ውስጥ አስገብቷቸዋል። አለመረጋጋቱን ተከትሎ የመጣው የውጭ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘመቻና ጫና አምራች ድርጅቶች ተረጋግተው እንዳይሰሩና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ተፅዕኖ አሳድሯል። በተጨማሪም ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ስለነበር አምራቾች በጫና ውስጥ ሆነው ለመስራት ተገድደውም ነበር።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩና ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያዎች የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በረጅም ጊዜ የግዥ ውል ለገዢዎች ስለሚያቀርቡ ምርቶቻቸውን በሌሎች ሀገራት ወደሚገኙ ቅርንጫፍ ማምረቻዎች እንዲያዞሩ ጫናዎች ነበሩባቸው፤ ግዢዎችም ይሰርዙባቸው ነበር።
ሕወሓት በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት በተቋማቱ ውድመት ብቻ የሚለካና የሚገለፅ አይደለም። የተቋማቱ መውደምና መዘረፍ የችግሩ አንዱ መገለጫ ከመሆኑ ባሻገር ውድመቱንና ዝርፊያውን ተከትለው የተከሰቱት ውጤቶች በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ላይ ተራዛሚና አሉታዊ ተፅዕኖዎችን የሚያስከትሉ ናቸው። በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ካስከተላቸው ችግሮች መካከል የሰራተኞች ከስራ መፈናቀል፣ የምርት አገልግሎትና አቅርቦት መቋረጥ፣ የምርት ሽያጭ ገቢ መቀነስ፣ የስነ ልቦና ጫናዎችና ሌሎች ቀጥተኛ ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪ ዘረፋውና ውድመቱ ካስከተላቸው ቀጥተኛና ፈጣን ውጤቶች ባሻገር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ እንቅፋት ሆኗል።
ቡድኑ በህልውና ዘመቻው ድል መደረጉን ተከትሎ የወጡ ሌሎች መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ አሸባሪ ሕወሓት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ ብቻ አይደለም ዘረፋና ውድመት ያደረሰው። በተለይ ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ውጭ በሚገኙ ሌሎች ኢንዱስትሪዎችና ሆቴሎች ላይም ጭምር ነው። በዚህም በርካታ የኢንቨስትመንት ተቋማት ምርቶቻቸውን ግብአቶቻቸውን፣ ተሸከርካሪዎቻቸውን በቡድኑ ተዘርፈዋል፤ ቡድኑ የዘረፈውን እየዘረፈ የተቀሩትን ደግሞ አውድሟል፤ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ተቋማት ጭምር የዚህ ግፍ ሰለባ ተደርገዋል።
የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ተቋማት ጫና
አሸባሪው ሕወሓት ብቻውን የሚንቀሳቀስ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ ሆኖም ነው የሚሰራው። በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ ማካሄድ ከተጀመረ አንስቶም ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘዋሪ የሆኑት እነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች ስለህግ ማስከበር ዘመቻው፣ ስለሰብዓዊ አቅርቦቱና ስለመሳሰሉት የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ፣ ፍጹም ለአሸባሪ ቡድኑ የወገነ፣ ፀረ-ኢትዮጵያ ይዘት የነበረው ነው። ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ (እንዲኖረው) ከማድረጉ ባሻገር የኢትዮጵያ ጠላቶች ‹‹ኢትዮጵያን ለመበታተን ከዚህ የተሻለ ጊዜ/ እድል አናገኝም›› ብለው ታጥቀው እንዲነሱና በረጅም ጊዜ ታሪኳ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን፤ ከኃይል ይልቅ ንግግርን ለማስቀደም እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ትብብርንና ወንድማማችነትን የሚያሰፍኑ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲመሰረቱና እንዲጠነክሩ ባላት ቁርጠኛ አቋም የምትታወቀው ኢትዮጵያ ስሟ እንዲጠለሽ በር ከፍቷል።
የቀድሞ ወዳጃቸውን የከሃዲውን የሕወሓትን የቁልቁለት ጉዞ አምኖ መቀበል ያቃታቸው አንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ ጋዜጠኞች፣ ተንታኝ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተብዬዎች በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት አፍራሽ ዘመቻ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። ‹‹ውሻ በበላበት ይጮሃል›› እንዲሉ ሕወ.ሓ.ት የኢትዮጵያ አድራጊ ፈጣሪ በሆነበት ወቅት የኢትዮጵያን ሐብት እንዳሻቸው እንዲዘርፉት የፈቀደላቸውና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘረፈው ገንዘብ እየመዥረጠ ያጎረሳቸው መንግሥታት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች [ውለታቸውን ለመመለስ አልያም ወዳጃቸውን ከሞት አስነስተው በድጋሚ ኢትዮጵያን ለመዝረፍ በማሰብ] ሐሰተኛና የጥላቻ መረጃዎችን፣ ወገንተኛ መግለጫዎችን እንዲሁም አሳፋሪ የክህደት ሪፖርቶችን ሲያወጡና ሲያሰራጩ እንደነበር ይታወሳል።
ሕወሓት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ባሉ አጋሮቹ በኩል አገሪቱ ልትበታተን እንደሆነና የፌዴራሉ መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀ አስመስሎ በርካታ የውሸት መረጃዎች እንዲሰራጩ አድርጓል። እነዚህን መረጃዎች ያዳመጡና የተመለከቱ ብዙ የውጭ አገራት ሰዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ መረጃዎቹን እንደወረዱ በመቀበል ከእውነት የራቀ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ተስተውለዋል። ቡድኑ ስለሕግ ማስከበር እርምጃው የተዛባ መረጃ ሲያስተላልፍና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ሲፈጥርም ነበር። እነዚህ ሁሉ የሐሰት ውንጀላዎች በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ አሳርፈዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በ2014 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ከጦርነቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ የኢንቨስትመንት ዘርፉ ተግዳሮቶች መካከል እንደሚጠቀሱ አመልክቷል። በ2014 በጀት አመት ከሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ቢቻልም ማሳካት የተቻለው የዕቅዱን 64 ነጥብ አራት በመቶ ብቻ ነው። በሀገሪቱ በነበረው አለመረጋጋትና የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በአፈፃፀሙ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።
የሕወሓት የክህደት ተግባር ኢትዮጵያ አሜሪካ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት ከሰጠችው ነፃ የንግድ እድል /አጎዋ/ ተጠቃሚነት እንድትታገድ አድርጓታል። ባለፈው ዓመት የአሜሪካ መንግሥት ባሳደረው ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት ነው ኢትዮጵያ ከዚህ ነፃ የንግድ እድል ተጠቃሚነቷ የታገደችው። ከ2014 በጀት አመት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ሆኖ የተጠቀሰውም ይኸው የኢትዮጵያ ከ‹‹አጎዋ›› ተጠቃሚነቷ የመታገዷ ጉዳይ ነው።
ኮሽታ የሚያስበረግገው ኢንቨስትመንት በአጠቃላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በተለይ በአሸባሪው ሕወሓት የክህደት ተግባር በአያሌው ተጎድቷል። ቡድኑ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዳከም አጥብቆ የሚሰራ እንደመሆኑ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው በታመነባቸው በእነዚህ ኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ አቅዶና በቂ ዝግጅት አድርጎ ያደረሳቸው ጥፋቶች ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው። ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ሁሉ መነሻቸው አሸባሪው ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያን፣ በተለይም የትግራይን፣ ሕዝብ ከጠላት ሲጠብቅና ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ውለታ ሲውል በነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው እጅግ አስነዋሪና አሳፋሪ የክህደት ጥቃት ነው! ይህ ግፍ በኢትዮጵያውያን ላይ መጥፎ ጠባሳ አሳርፎ አልፏል፤ የግፉ ሰለባዎች ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ግን ሁሌም ይታወሳሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም